Sunday, 26 November 2017 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

 “ከራሱ ጋር የተጣላ ከማንም ጋር እርቅ የለውም”
              
   በራሱ የሚቆም
“ሀ” ለ “ፐ” … ሰማዩ ቢወርድ ከመሬት፣
“ፐ” ለ “ሀ” ምድሩን - ሰማይ ቢያወጡት.
በዚህና በዚያ - ቢገለብጡት.
ልዩነት የለውም - የፊደሉ ቃና፣
ቃል ውስጥ ካልሰረፀ - ትርጉሙ እንዲቃና፡፡
ከ “አ”፣ “ዋ”፣ “ና” … በቀር - ሌላ ምንም የለም፣
“በራሱ የሚቆም” - ፊደል አልተገኘም!
በዮጋ እንቅስቃሴ በራስ መቆም (Reverse pose) ዋነኛ ነው፡፡ … ጥሩ የደም ዝውውር እንዲኖር ስለሚያደርግ ጭንቅላታችን በቂ አየር ያገኛል፡፡ … ራስ ምታታችንም ይሸሻል፡፡
ልክ እንደ ዮጋው መንፈስ “በራስ መቆም” ስንል … በራስ መተማመን መቻል፣ ጥሩምባ በተነፋ ቁጥር አለመደንገጥ፣ ከማህበርተኝነትና ከወገንተኝነት መራቅ፣ ዕውነትና ልክ ለሆነ ነገር ራሳችንን መስጠት፣ በምክንያታዊነት መቆም፣ ነፋስ የማያወዛውዘን … “እንደ ወረደ” እንደሚባለው “ሰው” መሆን ማለት ነው!!
*     *     *
 አንድ ጥንታዊ ንጉስ ነበሩ፡፡ ሀገራቸው ወደ ፊት የምትራመድበትን የስልጣኔ መንገድ አመቻችተው ማለፍ የፈለጉ፡፡ … የግዛቲቱን ወጣቶች ሰብስበው … “እንደምታዩት ዕድሜዬ እየገፋ፣ አቅሜም እየደከመ ነው፡፡ ስለዚህ ከናንተ መሃል የሚሰጠውን የቤት ስራ ከሁሉ በተሻለ ኃላፊነትና ታማኝነት የሚወጣው ልጅ ለኃላፊነት ይመረጣል፡፡ … የወደፊቱ መሪ ሆኖ ይታጫል” .. አሏቸው፡፡ … ንጉሱ የአብራካቸው ክፋይ የሆኑ ልጆች እያሏቸው ከነሱ መሃል መሪ ማጨት በመፈለጋቸው ወጣቶቹ ተገረሙ፡፡ በንጉሳቸው አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት ደስ አላቸው፡፡ …
በትንንሽ ማሰሮዎች ተዘጋጅተው የተቀመጡ የዘር ፍሬዎች ለያንዳንዱ ልጅ ታደለ፡፡ … ተንከባክቦ እንዲያሳድገውም “አደራ” ተሰጠው፡፡ … ከአንድ ዓመት በኋላም ለመገናኘት ቀጠሮ ተይዞ፣ ቀን ተቆርጦ ተሰነባበቱ፡፡ …
ዓመትም ሞላ፡፡ … ልጆቹም በቀጠሯቸው ቀን መጡ፡፡ የሚያማሩ ተክሎችን ይዘዋል፡፡ … ከንጉሱም ፊት ቀረቡ፡፡ … ከአንደ ልጅ በስተቀር፡፡ … ንጉሱ ከተቀመጡበት ተነስተው ልጆቹ ያመጡትን ቆንጆ፣ ቆንጆ ዕፅዋት አንድ በአንድ መመልከት ጀመሩ፡፡ … ይኼኔ ባዶ ማሰሮ ታቅፎ ወደ መጨረሻው ለቆመው ልጅ ጓደኞቹ … “ንጉሡ ምን ይሉት ይሆን?” በማለት ተጨነቁ፡፡ … መድረስ አይቀር .. የልጁ ተራ ደረሰ፡፡ ንጉሱ፤ ልጁንና ማሰሮውን በደንብ ተመለከቱ፡፡ … ምንም ሳይናገሩ አልፈውት ሄዱ፡፡ …ወደ ቤታቸው እንደተመለሱ ግን አስጠሩት፡፡ … ይሄኔ ልጁም፣ ጓደኞቹም በፍርሃት ተዋጡ፡፡ ልጁ እየተንቀጠቀጠ ከፊታቸው ቀረበ፡፡ … ከዙፋናቸው ብድግ ብለው ደስታ በተሞላበት ፈገግታ እቅፍ አደረጉት፡፡ .. እጁንም ይዘው ወደ ላይ ከፍ በማድረግ … “የወደፊቱ መሪ ይኼ ነው!” … አሉ፡፡ …
አየህ ወዳጄ፡- ንጉሡ ለልጆቹ ያደሏቸው የዘር ፍሬዎች ተቀቅለው የመከኑ ነበሩ፡፡ … ልጆቹና ቤተሰቦቻቸው ግን ተመሳሳይ ፍሬዎችን ዘርተው አፀደቁ፡፡ … ተንከባክበው አሳድገውም ይዘው መጡ። ልጁ ግን የወሰደው ፍሬ፣ ከዛሬ ነገ “ይበቅልልኛል” እያለ በጉጉት ቢጠባበቅም ሊሆንለት አልቻለም። … ቢቸግረው እናቱን አማከረ፡፡ … የሱ ጥፋት እንዳልሆነ አረጋገጠችለት፡፡
ዛሬ የመጣው ማሰሮውን ለመመለስ ነበር። … በመምጣቱ ግን ሳይፀፀት አልቀረም፡ … ምክንያቱም የጓደኞቹን ተክሎች ሲመለከት የሱ እንደዛ ባለመሆኑ ቅር ብሎታል፡፡፡ … የንጉሡን ፊት ላለማየት በጓደኞቹ የተከለለው ለዚህ ነበር፡፡ “ይቺ ፅዋ ከኔ ትለፍ” .. ዓይነት!!
ወዳጄ፤ ክርስቶስ “ይቺ ፅዋ ከኔ ትለፍ” … ባለበት ጊዜ አልፋው ቢሆን ኖሮ የዓለማችን ታሪክ ሌላ ይሆን ነበር፡፡ … ነገር ግን መሆን የሌለበት ነገር መሆን አልነበረበትምና አልሆነም፡፡ … መሆን የነበረበት ደግሞ ሆነ!! … እያመመው፣ እየተቸገረ መራራዋን ፅዋ ተጋተ!! … ፍዳውን በፅናት ጨረሰ!! … መከራውን ችሎ “ዕውነትን” አዳናት!!
ወዳጄ ልቤ፡- ዕውነትን ገድሎ ራስን ከማዳን፣ ተቸግሮ ዕውነትን ነፃ ማውጣት ዘለዓለማዊነት ነው!! … ሶቅራጥስ፣  ብሩኖና ሌሎች ብዙ ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት ስልጣኔያችንን አትርፈዋል!! አየህ ወዳጄ፤ በህይወት መንገድ ላይ ልንጋፈጣቸው ግድ የሚሆኑብን ብዙ ነገሮች ያጋጥሙናል፡፡ … ከዕውነትና ከውሸት፣ ከመታመንና ካለመታመን … መምረጥና የመሳሰሉት ጉዳዮች መጀመሪያ በአንድ ዓቢይ ጥያቄ ይጠቃለላሉ። “መኖር ወይ አለመኖር “… በሚባለው። … ቀጥሎ ደግሞ መሰረታዊና ወሳኝ የሚሆነው … “መሆን ያለበት ምንድን ነው? … ዕውነቱ የትኛው ነው?” የሚለው ጥያቄ ይከተላል።…
ወዳጄ፤ ትክክለኛውን መልስ መምረጥ ያንተና ያንተ ብቻ ፈንታ ነው፡፡ … ውስጥህን ካደመጥከው ይነግርሃል፡፡ …ከዋሸኸው ግን ህሊናህ ላይ ፈርደሃል። ህሊናህ ደግሞ እውነትህ ነው፣ እውነት ደግሞ አንተ ማለት ነህ፡፡ … ሌሎች ባያውቁብህም ውስጥን ትጎዳዋለህ፡፡ ...ጉዳትህ ደግሞ ዕድሜህን ይበላዋል፡፡ … አንድ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት፡-
አንድ ወደ ጦር ሜዳ የሚዘምት ወታደር “አሸንፋለሁ” … “ልሞት ግን እችላለሁ” ብሎ ይነሳል። … መሸነፍን ወይም መማረክን እንደ አማራጭ አያስብም፡፡ … እንዲያ ካሰበ መጀመሪያውኑም ወታደር አልነበረም፡፡ … ውትድርናን ለመኖሪያነት… ለመጠቀም ከሆነ የተቀጠረው ራሱንም አገሩንም አታሏል፡፡ … በሁለቱም ጎን ስለት አለ፡፡ … እንዴት ሆኖ ይተኛል? … እንዴትስ ይገላበጣል? … ሽንፈትና ምርኮኝነት ከአቅም በላይ በሆነ ድንገተኛ አጋጣሚ ካልተፈጠረ በስተቀር … እንደ ምርጫ ኩነኔ ነው!!
አንድ የፕሮቴስታንት ወይም ሌላ እምነት ተከታይ ግን እምነቱን ወደ ካቶሊክ፣ ቡድሂዝም ወይም እስልምና ቢቀይር የሚከለክለው ነገር የለም። ... ጉሩ ራማ ክሪሽና “…ክርስቲያንም፣ ሙስሊምም፣ ሂንዱም ሆኜ አየሁት፡፡ ሁሉም ወደ አንድ ግብ የሚመሩ ግን የተለያዩ መንገዶች ናቸው።…” (Although the paths are different … the goal is one ande same” … እንዳለው፡፡
ወዳጄ፤ “የገነት በር አንድ ነው” … ቢባልም ወደዛ ይመራሉ የሚባሉት የእምነት መንገዶች አሁን፣ አሁን ብዙ ሺ ሆነዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ጥርጣሬ ፈጥሯል፡፡ ... በነገራችን ላይ እንደ ረኔ ዴስካትረስና ዳቪድ ሁመ ዓይነት ፈላስፎች፣ ማንኛውም ነገር ለመኖሩ በማስረጃ እስካልተረጋገጠ ድረስ ጥርጣሬ ተገቢ ነው በማለት በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ስኬፕቲሲዝም (Skepticism) ወይም ሲስተማቲክ ዳውት (systematic dout) … የሚባሉትን ፍልስፍናዊ ዘይቤ የአስተሳሰባቸው አንኳር አድርገውታል፡፡
ለነገሩ ብዙ ሊቃውንት የሚስማሙበት “ገነት” ያለችው እዚሁ ቅርብ ነው፡፡ … እያንዳንዳችን ልብ ውስጥ!! … እዚችኛዋ ገነት ውስጥ ለመግባት መንገዱ ጠባብና አንድ ብቻ ነው፡፡ እሱም “ለራሳችን መታመን ነው” … ይላሉ፡፡
ወዳጄ፤ ከቶውንስ ለራሱ ያልታመነ እንዴት ለሌላው ሊታመን ይችላል? … ራሱን የሚያከብርና የማያፈቅርስ ሌላውን ያከበረና ያፈቀረ መስሎ ቢታይ ውሸቱን ይመስለኛል፡፡ “…ከራሱ ጋር የተጣላም ከማንም ጋር ዕርቅ የለውም” … (He who is not in good terms with hismself … is always at war with the rest of the world) … ይላልና!!
ወዳጄ፤ ለራስ መታመን የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ነው፡፡ ይህንን ፀጋ በሌሎች ሰዎች ቡራኬ የምንቀባው አይደለም፡፡ .. በያንዳንዳችን ውስጥ የተቀበረ፣ በተግባራችን የምንፈለቅቀው ዕሴት እንጂ!! “… ከውስጣችን የሚፈልቀውን ማንነት እንዴት ከሌሎች እንጠብቃለን? … (becoming human emerges out of oneself … how could it emerges out of others?”) በማለት ታላቂ ኮንፊዩሸስ ይጠይቀናል፡፡
መልሱ፡- የራሳችንን ዋጋ ማወቅና በራሳችን መቆም መቻል ነው፡፡ … ይህንን ክብር ለጥቅም አሳልፈን ከሰጠነው፣ በገዛ ፈቃዳችን የነፍሳችንን ብርሃን ማብሪያና ማጥፊያ በሌሎች አስነጥቀናል፣ ወደ ጋሪ ፈረስነት ተቀይረናል፣ በፈቀድነው ሳይሆን በተመረጠልን መንገድ ለመሄድ ተስማምተናል ማለት ነው፡፡ ሊቃውንት “He who surrenders his value is at the mercy of others will” የሚሉን ይህንኑ ነው!!
ወደ ታሪካችን ስንመለስ፣ ልጃችን ለራሱ ታማኝ ሆነ፡፡ … በራሱ ቆመ!! .. በሌሎቹ ዓይን ግን ዝቅ ብሎ ነበር፡፡ ልዑልነትን በህልሙም በውኑም አስቦ አያውቅም፡፡ … ግን ሆነ!! ዕውነት ወለደው! … ከፍ ከፍም አደረገው! … ከፀሐይ እንደሚበራ ኮከብ ቦግ አለ!!
The story is adopted from Great Islamic Teaching ግጥሙም ከፀሐፊው ስብስቦች የተመረጠ ነው

Read 1287 times