Saturday, 02 December 2017 08:29

ሣኡዲ አረቢያ ህገ ወጥ ያለቻቸውን ኢትዮጵያውያን ማሰር ጀምራለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

በየቀኑ ከ1ሺ በላይ “ህገ ወጥ” ዜጎች በቁጥጥር ሥር ይውላሉ
የሣኡዲ አረቢያ መንግስት ህገ ወጥ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ማሰር የጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ከሳኡዲ መንግስት ጋር ባደረገው ምክክር ከ1300 በላይ የሚሆኑት ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ አድርጌያለሁ ብሏል፡፡
ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የመኖሪያና የሥራ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሣኡዲ አረቢያ ይኖራሉ ተብሎ የሚገመት ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በዘረጋው ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት የመመለስ ዘመቻ፣ 70 ሺህ ያህል ብቻ መመለሳቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለ ዓለማ አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን አስታውቋል፡፡
የሣኡዲ መንግስት “ከህገ ወጦች የፀዳች ሣኡዲ አረቢያ መፍጠር” በሚል በጀመረው የፀረ ህገ ወጦች ዘመቻው፣  ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በቀን በአማካይ ከ1 ሺ በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎችን በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በሣኡዲ አረቢያ በህገ ወጥ መንገድ እንደሚኖሩ ከሚነገርላቸው ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ የሶማሊያን በረሃ፣ ቀይ ባህርንና የመንን አቆራርጠው ሣኡዲ መግባት የቻሉ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  
በመላው አለም በስደት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሃገር ቤት የሚልኩ ሲሆን ይህም ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከተያዘው አጠቃላይ የ80 ቢሊዮን ብር በጀት ጋር ይተካከላል ተብሏል፡፡

Read 4597 times