Saturday, 02 December 2017 08:35

በኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ተቋርጦ ሰነበተ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(22 votes)

”የጸጥታ ሃይሎችና የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና” በምክንያትነት ተጠቅሰዋል

የዓመቱ ሦስተኛው ወር ህዳር ቢገባደድም በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች አሁንም መደበኛ ትምህርት በወጉ አልተጀመረም። በሃረማያ፣ ጅማ፣ አምቦና አርሲ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን የዩኒቨርሲቲ መውጫ መመዘኛ ፈተና በመቃወምና “የፀጥታ ሃይሎች ግቢያችንን ለቀው ይውጡ” በሚል ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው መሰንበታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ከባለፈው ማክሰኞ ህዳር 19 ጀምሮ “በግቢው የሚገኙ የፀጥታ ሃይሎች ይውጡ” በሚል ተቃውሞ፣ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንደወጡ ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን በጅማና በአምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውንና ከ2011 ጀምሮ የሚመረቁ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መውጫ መመዘኛ ፈተና ይሠጣቸዋል የሚለውን አዲስ መመሪያ በመቃወም ትምህርት ማቋረጣቸው ታውቋል፡፡
የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ ባለፈው ረቡዕ “የመከላከያ ሠራዊት ከግቢው ይውጣልን” እንዲሁም “በድንበራችን አካባቢ የተፈጠረው ግጭት በአስቸኳይ ይቁም” በሚል ተቃውሞ ትምህርት ማቋረጣቸውን  ምንጮች ጠቁመዋል፡፡  
በጅማና በአምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች ተቃውሞና ትምህርት ማቋረጥ ዋነኛው ምክንያት የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ያወጣውና ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ የሚተገበረው የዩኒቨርሲቲ መውጫ መመዘኛ ፈተና መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች፤ “መመሪያው ይጎዳናል” በሚል ትምህርት አቋርጠው መሰንበታቸውንና በመጨረሻም ግቢውን ለቀው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡  
“የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናውን ማለፍ ያልቻለ ተማሪ በድግሪ ሳይሆን በአድቫንስድ ዲፕሎማ ነው የሚመረቀው ተብለናል” የሚሉት ተማሪዎቹ፤ ”ይህ የኛንና የቤተሰቦቻችንን ልፋት መና የሚያስቀር ነው” በሚል እንደሚቃወሙት  ይናገራሉ፡፡
 በሌላ በኩል በወለጋ ደምቢ ዶሎ፣ የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ላለፉት 15 ቀናት ሙሉ ለሙሉ የተቋረጠ ሲሆን ለመቋረጡም ምክንያቱ “መከላከያ ሠራዊት ከከተማው ይውጣልን” የሚል መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በቅርቡ ከመንግስት የሃላፊነት ቦታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ ሰሞኑን በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ቀርበው፣ በክልሉ ትምህርት እያቋረጡ ያሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ምክርና መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወቃል፡፡   

Read 6695 times