Saturday, 02 December 2017 08:36

መኢአድ ከኢህአዴግ ጋር የሚያደርገውን ድርድር በመቃወም የፓርቲው ዋና ፀሐፊ ራሳቸውን ከሃላፊነት አገለሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

በድርድሩ የተነሳ በኢዴፓ አመራሮችም መካከል ውዝግብ ተፈጥሯል

 መኢአድ ከኢህአዴግ ጋር የሚያደርገውን ድርድር ማቋረጥ አለበት የሚል አቋም የያዙት የፓርቲው ዋና ፀሐፊና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አዳነ ጥላሁን፤ ራሳቸውን ከፓርቲው የሃላፊነት ቦታዎች  ማግለላቸውን በተለይ ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡
ድርድር በሁለት ተመጣጣኝ የሃይል ሚዛን ባላቸው አካላት መካከል የሚካሄድ ነው ያሉት አቶ አዳነ፤ “አሁን የሚካሄደውና ፓርቲያቸው የሚሣተፍበት ድርድር ግን ሙሉ ለሙሉ የኢህአዴግን አጀንዳ ለማስፈጸም በገዢው ፓርቲ መልካም ፍቃድ ላይ የተመሠረተ ሂደት ነው” የሚል አቋም መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡
በዋና ፀሃፊነትና በህዝብ ግንኙነት ሲመሩት የቆዩት ፓርቲያቸው፤ኢህአዴግ ለድርድሩ አደራዳሪ አያስፈልግም የሚል አቋም በያዘበት ወቅት፣ ከድርድሩ ራሱን እንዲያገልል ለ7 ጊዜያት ያህል በሥራ አስፈፃሚው ውስጥ አጀንዳ እያስያዙ ግፊት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው እንዳልቻለ ጠቁመዋል፡፡  
“ይህ ድርድር በ289 የአገሪቱ ወረዳዎች ሠፊ ህዝባዊ መዋቅር ለዘረጋው መኢአድ አይመጥንም” ያሉት አቶ አዳነ፤በየአካባቢው ያሉ አባላትና ደጋፊዎችም በፓርቲው አቋም ግራ መጋባታቸውን ተዘዋውረው ባደረጉት ምልከታ ማረጋገጣቸውን አውስተዋል፡፡   
በድርድሩ ሂደት ኢህአዴግ የታሠሩ ፖለቲከኞችን ለመፍታት ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱንና ድርድሩ እየተካሄደ ባለበት ወቅትም ዜጎች በጥይት መሞታቸው መቀጠሉን የጠቀሱት አቶ አዳነ፤ ፓርቲያቸው ከድርድሩ ራሱን ለማግለል በቂ ምክንያቶች ቢኖሩትም በድርድሩ መግፋቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ መኢአድ በድርድሩ መሣተፉ ፓርቲው ሲመሰረት ጀምሮ ከሚያራምደው የፖለቲካ መርህና አቋም ፈፅሞ የተለየ ነው ያሉት አቶ አዳነ፤ “በአሁኑ ወቅት ፓርቲው በሚያራምደው አቋም በአብዛኛው አባላት ዘንድ እንደ ኢህአዴግ ተለጣፊ እየታየ ነው፤ ይህ ሁኔታ ለፖለቲካ አካሄዴ ምቾት አልሰጠኝም” ብለዋል፡፡
በንጉሡ፣ በኢህአዴግ ዘመን በፖለቲካ ልዩነት የእስር ቤት ደጃፎችን ደጋግመው መርገጣቸውን በመጥቀስ፤ “የኔ ትውልድ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም አስተሳሰብ ያረፈበት የሴራ ፖለቲካ አራማጅ ነው፤ አሁን ዘመኑ የሚፈልገው ደግሞ ዲሞክራሲን ነው፤በዚህ ምክንያት ለዚህ ዘመን ፖለቲካ አልመጥንም የሚል አቋም ላይ ደርሻለሁ” ብለዋል ሌላው ከፖለቲካ ገለል ለማለት የፈለጉበት ምክንያት መሆኑን በመግለፅ፡፡
ሃላፊነቴን የምለቅበት ሌላ ተጨማሪ ምክንያት አለኝ ያሉት አቶ አዳነ፤ “ይሄ ለጊዜው የድርጅቱን ህልውና አደጋ ላይ ስለሚጥል ከመገለፅ እቆጠባለሁ፣ አስፈላጊ በሆነ ሠዓት ግን ለህዝብ በዝርዝር ይፋ የማደረግ ይሆናል” ብለዋል፡፡
የፓርቲው ንብረቶች በእጃቸው ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ አዳነ፤ ይህን የመልቀቂያ መግለጫ ለአዲስ አድማስ ከሰጡበት ቀን ጀምሮ የመኢአድ አመራሮች ከሃላፊነት መልቀቃቸውን በመረዳት የፓርቲውን ንብረት እንዲረከቧቸው ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል “በድርድሩ እንቀጥል አንቀጥል” በሚል የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አመራሮች መካከልም አለመግባባት መፈጠሩ ታውቋል፡፡

Read 5586 times