Sunday, 03 December 2017 00:00

የአቶ ተካ አስፋው አስተያየቶች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከ15 ቀናት በኋላ በአፋር ክልል ዋና ከተማ  ሰመራ ላይ የፕሬዝዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫውን ያካሂዳል፡፡ በፕሬዝዳንት ምርጫው ለመወዳደር ከቀረቡት እጩዎች መካከል ከአማራ ክልል የተወከሉት አቶ ተካ አስፋው ይገኙበታል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት ሆነው ለ6 ዓመታት የሰሩ ሲሆን፤ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የዲስኘሊን ኮሚቴ አባልነት ያገለገሉት ደግሞ ከ2 ዓመታት በላይ ነው፡፡ በፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ የእድሜ ልክ የክብር አባልነት የተሰጣቸው አቶ ተካ አስፋው፤ በህግ ትምህርት የLLB ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በተለያዩ ደረጃዎች አቃቤ ህግ ሆነው በማገልገል ከፍተኛ ልምድ አካብተዋል፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር የህግ አገልግሎት ኃላፊ ሆነው  በሰሩበት ወቅት ስፖርታዊ አዋጆች፤ ደንቦችና መመርያዎችን አርቅቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርት ለሚንቀሳቀሱ ከ25 በላይ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖች የህግ አማካሪ በመሆን የሰሩ ሲሆን በተለይም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ የአትሌቲክስ ፌደሬሽንና የኦሎምፒክ ኮሚቴን መተዳደሪያ ደንቦችን አርቅቀው ስራ ላይ እንዲውሉ በማድረጋቸውና  ሌሎች ከፍተኛ አገልግሎቶችን በማበርከታቸው ልዩ ሽልማቶች እና የምስጋና ወረቀቶችን አግኝተዋል፡፡  በስፖርቱ መስክ የስፖንሰርሺፕና የማርኬቲንግ እንቅስቃሴዎችን በላቀ ደረጃ በማከናወን ከመታወቃቸውም በላይ በስፖርቱ መሰረተልማት ዙርያ በተለያዩ ክልሎች ለተገነቡ ስታድዬሞች በሰጧቸው ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፎችም የተለያዩ ዋንጫዎችና የምስክር ወረቀቶችን የተጎናፀፉም ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የወለጋ ስታድዬም ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል በሚል የምስጋና ምስክር ወረቀት እንዲሁም  በአማራ ክልል በባህርዳር እና ወልዲያ ከተሞች ለተገነቡት ስታድዬሞችም ከፍተኛ እገዛ በማበርከታቸው ዋንጫዎችና የምስክር ወረቀቶች ተሰጥተዋቸዋል፡፡ የወንድና የሴት ብሄራዊ ቡድኖች ያስመዘገቧቸውን ድሎች መነሻ በማድረግ በታሪክ ለሽልማት ገንዘብ ብቻ 16 ሚሊዮን ብር የሰጠና ለብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ መኪና የሸለመ ፌደሬሽን አቶ ተካ አስፋው በአመራር የሰሩበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ከዚህ በታች የቀረበው በፕሬዝዳንት ምርጫው መወዳደራቸውን አስመልክቶ ከስፖርት አድማስ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ነው፡፡

   ከ4 ዓመት በፊት በፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ምርጫ ላይ በእጩ ተወዳዳሪነት ቀርበው በመጨረሻው ሰዓት ራስዎን ማግለልዎ  የሚታወስ ነው፡፡ ለመሆኑ ምክንያቱ  ምን ነበር …
ምክንያቱ ባይታወቅ ደስ ይለኛል፡፡ ያለፈ ነገርን ማንሳት ምንም ስለማይጠቅም ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ምክንያት ብዬ በመናገር ጠቅላላ ጉባኤውን ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ መውሰድ ስለማልፈልግ ነው፡፡ የምርጫ መቀስቀሻ መንገድ እንዲሆንም አልሻም፡፡ ከብዙ ነገር ጋር የሚነካካ ነገር ይኖረዋል… ጠቅላላ ጉባኤው ማወቅ የሚፈልገው ስለሆነ ምክንያቱን ካወቀ ወደ ውዝግብ ሊገባ ስለሚችል ነው፡፡
በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ የእድሜ ልክ የክብር አባል እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ የክብር  አባል ሆኖ ለፕሬዝዳንት ምርጫ መወዳደርን ህጉ ይፈቅዳል?
ከ4 ዓመት በፊት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ የእድሜ ልክ የክብር አባልነት የተሰጠንለአቶ ሳህሉ ገብረወልድ፤ የስራ አስፈፃሚ አባል ለነበሩት ወይዘሮ ጥሩወርቅ ብርሃኑ እና ለእኔ  ነበር፡፡ በስራ ዘመናችን ላበረከትናቸው አስተዋፅኦዎች እውቅና ለመስጠት  ነው፡፡ በተቀዳሚ ፕሬዝዳንትነት  ባገለገልኩበት ወቅት  የማርኬቲንግና ስፖንሰርሺፕ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኜ ፌደሬሽኑ በፋይናንስ እንዲጠናከር አድርጊያለሁ በተለይም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሰበሰብ የነበረኝ አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በመግባቱ የክብር አባልነቱ ተሰጥቶኛል፡፡ የክብር አባል ለፕሬዝዳንት ምርጫ አይወዳደርም የሚለው የትኛው የፊፋ ህግ ነው በህግ እንነጋገር ከተባለ በክብር አባልነት ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ይቻላል፡፡ ይህን የሚያግድ ምንም አይነት ህግ የለም፡፡ የክብር አባል ማለት እኮ ድምፅ አይሰጥም፡፡ አይደለም ድምፅ የማይሰጥ ይቅርና ድምፅ የሚሰጥ ማንኛውም የጠቅላላ ጉባኤ አባል ወደ ምርጫ ገብቶ መወዳደር ይችላል፡፡ የመምረጥ እና የመመረጥ መብትን ማንም ሊነፍግ አይችልም። ህገመንግስታዊ መብት ነው፡፡ በፊፋ ህግም መሰረት አንድ ሰው ለምርጫ አይወዳደርም ወይንም አይመረጥም የሚባለው  በወንጀል ተከሶ የተቀጣ ከሆነ፤ እድሜው ከ70 ዓመት በላይ ከሆነ፤ በአጉል ሱስ ውስጥ ያልገባ… በመሳሰሉ ምክንያቶች ብቻ ነው፡፡
በፕሬዝዳንት ምርጫው ለመወዳደር በመወሰን ወደ ፌደሬሽኑ ለመመለስ የፈለጉት በምን ቁጭት ተነሳስተው ነው?
የመጀመርያውና ዋንኛው ምክንያት ለስፖርቱ ያለኝ ፍቅር እና ቅርበት ነው፡፡ ይህም ስፖርት ውስጥ ለመስራት ወሳኝና አስፈላጊ ነው፡፡ ለእግር ኳሱ ያለኝ ፍቅር እና ቅርበት በሁለት መንገዶች ገልፀዋል። አንዱ እግር ኳስን ስታድዬም ገብቶ መከታተል ነው። እኔ የስታድዬም ተመልካች ደንበኛ ነኝ፡፡ ሌላው ደግሞ ስፖርቱን በተለያየ መንገድ ለመደገፍና ለማገዝ ካለኝ ፅኑ ፍላጎት ይመነጫል፡፡ መደገፍና ማገዝ ሲባል በብዙ መልኩ ሊሆን ይችላል። በገንዘብ፤ በእውቀት፤ በጉልበትና በምክር ድጋፍ መስጠት ይቻላል፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች አሟላለሁ። የስፖርት ቤተሰቡም የሚመሰክረው ነው፡፡ በሌላ በኩል በፌደሬሽኑ አመራር በነበርኩባቸው ጊዜያት ልሰራቸው አስቤ ሳልሰራቸው የቀረኋቸውና ጀምሬ ያልጨረስኳቸውን እቅዶችን ለማከናወን ስለምፈልግ ነው፡፡ ከፌደሬሽኑ ከወጣሁ በኋላ መለወጥ አለባቸው ብዬ የማምንባቸው ሁኔታዎችን ላይ ለመስራት ቁጭት አለኝ፡፡
በየትኞቹ አቅጣጫዎች ለመስራት እንደሚፈልጉ በዝርዝር ቢገልጿቸው?
ፌደሬሽኑ እቅድ አለው ግን ወቅቱን የጠበቀ አይደለም፡፡ ከዓለም አጠቃላይ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ፤ ዘመናዊ ስትራቴጂክ እቅድ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህን መሰረታዊ ነገር መስራት እፈልጋለሁ። ሁሉም ነገር የሚመራው በስትራቴጂክ እቅድ ጥላ ስር ነው፡፡ እቅድ የሌለው ተቋም ልጓም የሌለው ፈረስ ማለት ነው፡፡ የፌደሬሽኑ መተዳደርያ ደንብ ብዙ ጉድለቶች ስላሉበት መሻሻልም ይኖርበታል፡፡ ለውዝግብና ለአለመግባባት የሚዳርጉ የህግና የደንብ ክፍተቶች መስተካከል አለባቸው። ፊፋ መልካም አስተዳደርን መሰረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይህን አቅጣጫ የሚደግፍ መተዳደርያ ደንብ መዘጋጀት አለበት። መልካም አስተዳደር ሲባል ለስፖርት ቤተሰቡ፤ ለመንግስት እና ለባለድርሻ አካላት ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር መዘርጋት ነው፡፡ ከሙስና የፀዳ፤ አቅምና በቂ ልምድ ያለው አመራር መፍጠር፤ ለሚዲያ ወቅታዊና ተጨባጭ መረጃ መስጠት የሚችል አስተዳደር ማስፈን ነው፡፡ ለዚህም የጠቅላላ ጉባኤው አባላት እና ተሳታፊዎች ጥንቅር በጥልቀት ተፈትሾ እንዲለወጥ የማንፀባርቀው ጠንካራ አቋም አለኝ፡፡
ሌላው ፌደሬሽን ውድድርን ለባለቤቶቹ ማለትም ለክለቦች ማስረከብ አለበት ነው፡፡ ውድድር በራሱ የልማት ስራ ቢሆንም ፌደሬሽኑ ከውድድር ባሻገር ባሉ የላቁ የልማት ስራዎች እንዲንቀሳቀስ ነው የምፈልገው፡፡ ለምሳሌ በታዳጊ የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች፤ በሴቶች እግር ኳስ እና ብሄራዊ  ቡድኖችን  በተለያዩ ድጋፎች በሚያጠናክሩ ተግባራት መስራትን ነው፡፡ የፌደሬሽኑ አደረጃጀትም መስተካከል ይኖርበታል፡፡ በተለይ ፅህፈት ቤቱ በተሟላ የሙያ ብቃትና ፕሮፌሽናል አስተዳደር መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ከዞናዊ፤ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የእግር ኳስ ተቋማት ጋር በየእለቱ የነቃ ግንኙነት እያደረገ የሚሰራ ፅህፈት ቤት ማደራጀት ወሳኝ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በፊፋ እና በካፍ የአሰራር ሂደቶች እንደምታዘበው  በወር አንዴ ቢሰበሰብ በቂ ነው። ዋናው የፅህፈት ቤቱን አደረጃጀት በማጠናከር እና በብቁ ባለሙያዎች በመምራት መስራት ነው። የፌደሬሽኑን ቴክኒካል ዲፓርትመንት በትኩረት አደራጅቶ በብቁ ባለሙያዎች እንዲንቀሳቀስም እፈልጋለሁ፡፡ በሁለቱም ፆታዎች በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች የሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖችን በቅርብ ክትትል እየደገፈ የሚሰራ ቴክኒካል ዲፓርትመንት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሁለቱም ፆታዎች አሽቆልቁሎ የሚገኘው የዋና ብሄራዊ ቡድኖች ውጤት እንዲሻሻል በአጭር፤ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ እቅዶች የሚሰራበትን አቅጣጫ መዘርጋት ነው፡፡
የዳኝነት አካሉም በኮሚቴ የሚመራበት አሰራር መቀየር ያለበት ነው፡፡ በፊፋ እና በካፍ ያለውን ተመክሮ ወደ ፌደሬሽኑ ማምጣት ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በዲያሬክተር ደረጃ የተዋቀረና የሚመራ ራሱን የቻለ የዳኝነት ዲፓርትመንት መመስረት አለበት፡፡ ይህ ዲፓርትመንት የዳኞችን ስልጠና የሚያመቻችና ዳኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙበት ደረጃና ተሳትፎ ከፍ እንዲል የሚሰራበት ይሆናል፡፡
በመጨረሻም በዋናነት ትኩረት የምሰጠው  የፌደሬሽኑን የፋይናንስ አቅም በሚያጠናክር አቅጣጫ ለመስራት ነው፡፡ ከላይ የዘረዘርኳቸውን የለውጥ ስራዎች ለማከናወን በቂ የፋይናንስ አቅም መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የፌደሬሽኑን የማኬቲንግና የስፖንሰርሺፕ ዲፓርትመንት በባለሙያ አጠናክሮ በማደራጀት የማይነጥፍ የገቢ ምንጭ የሚፈጠርበትን አሰራር መቀየስ ያስፈልጋል። ለምሳሌ በቴሌቭዥን የስርጭት መብት መስራት፤ ብሄራዊ ቡድኖችን በስፖንሰርሺፕ መደገፍ፤ ዘመናዊ የማስታወቂያ ስራዎችን ማከናወን ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ አስቀድሞ የፌደሬሽኑ አመራር በነበርንበት ወቅት የጀመርነውና ገቢ ይገኝበታል በሚል የፌደሬሽኑን ጂ ፕላስ 7 ህንፃ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠን የተነሳንበትን እቅድ ለመቀጠል እና ለመጨረስ ነው፡፡ በህንፃው ግንባታ ይዘነው በነበረ እቅድ የመጨረሻዎቹን ሁለት ፎቆች የመኝታና ማረፊያ አገልግሎት እንዲሰጡ፤ ሌሎች ፎቆች ላይ የፌደሬሽኑን ፅህፈት ቤት በፕሮፌሽናል ባለሙያ አደራጅቶ መጠቀም፤ ከታች ለቢሮ፤ ለሱቅ፤ ለሰርግና ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚሆኑ አደራሾችን አዘጋጅቶ በኪራይ ገቢ ለማግኘት ነው፡፡
ሌላው ከሚዲያ ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ማሻሻል ነው፡፡ ፌደሬሽኑ ሚዲያን የሚያከብር እንጅ የሚፈራ መሆን የለበትም፡፡ እውነተኛ እና ትክክለኛ ስራዎችን እየሰራን፤ ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው አሰራር እየተንቀሳቀስን ፤መረጃን በወቅቱ እየሰጠን ተዓማኒነትን ለመፍጠር ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው ብሄራዊ ቡድናችን ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ ሚዲያው ለብሄራዊ ቡድን ድምቀት እንዲሰጥና ዓለም አቀፍ ልምዱን እንዲያጎለብት በተነሳንበት ዓላማ ባለሃብቶችን አስተባብረን የጉዞ እድሎችን ፈጥረናል፡፡ ይህን አይነት ተግባር ለመቀጠልም እናስባለን፡፡ ሚዲያው በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እየተጓዘ ሰፊ ልምድ የሚያገኝበትን እድሎች እንፈጥራለን፡፡ በውድድሮች ብቻ ሳይሆን የሙያ ደረጃ በሚያሳድጉ ዓለምአቀፍ ስልጠናዎች ከአገር ውጭም በአገር ውስጥ እንዲሳተፉ ማመቻቸት እንፈልጋለን፡፡
እግር ኳስን በሚመሩና በሚያስተዳድሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ተፅእኖ ፈጣሪነት የተዳከመ ይመስልዎታል… ቢመረጡስ ምን መፍትሄ ያገኙለታል?
 ከይድነቃቸው ተሰማ በኋላ ኢትዮጵያ በካፍ ውስጥ ቁልፍ ሚና ሊሰጣት አልቻለም፡፡ እግር ኳስን በሚመሩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የኢትዮጵያ ተፅዕኖና የኃላፊነት ድርሻ መዳከሙ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ይህ የሃላፊነት ቦታ ያጣነው ያለምክንያት አይደለም፤ በየአራት ዓመቱ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ አመራር እርስበርሳችን እየተጓተተን እየተጠላለፍን ስለምንወርድ ነው፡፡ በሁለት የስራ ዘመን ፌደሬሽኑን የሚያገለግል ስራ አስፈፃሚ እኮ የለንም፡፡ ወደ ፌደሬሽኑ አመራርነት የሚመጣ የሚጨነቀው የጨዋታ ኮሚሽነር ሆኖ በመመደብና የተለያየ ኮሚቴ ውስጥ በመግባት የውጭ ጉዞዎችን እያደረጉ አበል ለማግኘት ብቻ ነው፡፡ በፌደሬሽን አመራር ላይ ከዚህ በፊት የሚቀመጡ ሁሉ ጥቅም የሚያሳድዱ ናቸው፡፡ በካፍ የአስተዳደር እንቅስቃሴዎች የጎላ ሚና በመጫወትና አስተዋፅኦ በማበርከት ለተሻለ የሃላፊነት ድርሻ ለመብቃት እና ኢትዮጵያ የሚኖራትና ተሰሚነት ለማሳደግ የሚደረግ ጥረት የለም፡፡ ለምንድነው በጨዋታ ኮሚሽነርነት በሚገኙ እድሎች ባለሙያዎች እንዲጠቀሙ የማይደረገው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ዳኞች የሉንም? እኔ አሁን በጨዋታ ኮሚሽነርነት ልመደብ ብዬ አልሯሯጥም፡፡ በመጀመርያ በኮሚሽነርነት ተመድቦ ለመስራት የቴክኒክ እውቀት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የባለሙያዎችን እድል መሻማት አልፈልግም፡፡ ለእግር ኳሱ ያገለገሉ፤ የሰሩ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ዳኞች ለምን በእድሉ አይጠቀሙበትም፡፡ ኢትዮጵያ በአህጉራዊው እግር ኳስ የሚኖራትን ተፅእኖ ማሳደግ የሚቻለው  የውጭ ጉዞ እድሎችን በመቁጠር እና አበልን በማስላት በሚንቀሳቀስ አመራር አይደለም፡፡  ተገቢውን እድል ለባለሙያዎች በመስጠት መስራት ያስፈልጋል፡፡ በካፍ ስራ አስፈፃሚ ውስጥ ሊገባ የሚችል አመራር ሳይኖረን መቅረቱ የሚያሳዝን ነው፡፡ በካፍ ደረጃ ተሰሚነቱን እያጣን የመጣነው ጥቅም ብቻ የምናሳድድ በመሆናችን፤ የመስራት አቅሙና ብቃቱ ያለው አመራር ባለማቅረባችን ነው፡፡ በእውቀት እና ጤናማ በሆነ ግንኙነት ከካፍ ጋር ተቀራርበን ባለመስራታችን፤ በአገራችን እግር ኳስ አድናቆት ሊያገኝ እና ትኩረት በመሳብ ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆን እድገት እና ውጤት ለማስመዝገብ ባለመቻላችን ነው፡፡ የብሄራዊ በድኖች ደረጃ በማሽቆልቆሉ፤ የእግር ኳስ ክለቦቻችን በአፍሪካ ውድድሮች ውጤታማ ባለመሆናቸውና በኢኮኖሚ አቅም ያሉበት ደረጃ ያን ያህል ጎልቶ የወጣ ባለመሆኑ ትኩረት  አሳጥቶተናል፡፡ ስለዚህም በካፍ አስተዳደር ውስጥ የሚገባ አመራር ለማግኘት ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ በካፍ የዲስፕሊን ኮሚቴ አባልነት ለሁለት ዓመታት ባገለገልኩበት ወቅት ያገኘሁት ልምድ ይህን መጥፎ ታሪክ ለመቀየር እንደምችል የተገነዘብኩበት ነው፡፡ የፊፋ እና የካፍ ህጎችና ደንቦች በጥልቀት የማውቃቸው እና የምረዳቸው ናቸው፡፡
ፌደሬሽኑን በተቀዳሚ ፕሬዝዳንትነት ለ6 ዓመታት ሲያገለግሉ ለምን በሚፈልጓቸው የለውጥ አቅጣጫዎች ላይ አልሰሩም?
ያኔ የነበረው የጋራ አመራር ነው፡፡ ከእኔ በላይ ፕሬዝዳንቱ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ነበሩ፡፡ ከበታች ደግሞ የስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ አባላት ናቸው። በዚህ አይነት አስተዳደርውስጥ የምችለውን ለማድረግ፤ የምፈልገውን ለመስራት ጥርያለሁ። አንዳንድ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን የቻልኩ ቢሆንም የአቅም ውስንነት ስለነበር እንደተፈለገው ለመስራት አላስቻለንም፡፡  በአራት ዓመታት ውስጥ ስርነቀል ለውጥ መፍጠርን አዳጋች ያደረጉ ፈተናዎች ስለነበሩ ብዙ ለውጥ ሳናስመዘግብ ቀርተን ይሆናል፡፡ አስቀድሞ ከነበሩ የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች የተሻለ መስራታችንን ግን በልበሙሉነት የምናገረው ነው፡፡  በውድድር ደረጃ ትልቁ ውጤታችን ብሀሄራዊ ቡድንን ከ31 ዓመታት በኋላ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፋችን ነው፡፡ በቻን ውድድር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ መሳተፍ ችለናል፡፡ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የደርሶ መልስ ማጣርያ ከበቁ 10 የአፍሪካ ቡድኖች ተርታም ለመግባት ችለናል፡፡ በታዳጊዎች ደረጃ ውድድሮችን በመጀመርና የሴቶች እግር ኳስን በማጠናከርም ጉልህ ሚና ለመጫወት ችለናል፡፡
በአጠቃላይ አሁንም በፕሬዝዳንት ምርጫው ለመወዳደር ስገባ በአንድ የስራ ዘመን ማለትም በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለውጥ ለመፍጠር እና እድገት ለማስመዝገብ ይቻላል በሚል ስሜት አይደለም፡፡ በተቀዳሚ የምክትል ፕሬዝዳንትነት የነበሩኝን መልካም ተመክሮዎች እና ልምዶችን ተጠቅሜ የጀመርኳቸውን ነገሮች ለመጨረስ እንጅ ሃ ብዬ የምጀምርው ነገር የለም፡፡
ባለፉት ሳምንታት በተደረጉት ጉባዔዎች ላይ አባላት  በአወዛጋቢ አጀንዳዎች ለመወጠራቸው ዋንኛ መንስኤዎች ምንድናቸው?
ለውዝግቦቹ ምክንያት የሆኑ ሶስት መሰረታዊ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የመጀመርያው በመድረክ ላይ የነበረው አመራር በትክክል የሚሰራ አልነበረም፡፡ ስራ አስፈፃሚው  ጉባዔውን ሊመራ ይቅርና በመካከል የነበረውን ልዩነት መፍትሄ ሊያገኝበት በሚችልበት ሁኔታ አልነበረም። በመድረክ ላይ እርስ በእርስ በመወነጃጀል፤ ማይክ በመቀማማት እና በመጎነታተል የተከፋፈሉ ነበሩ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የህግ ክፍተቶች እንዳሉ ሆነው የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ህግን መሰረት አድርጎ አስተያየት የመስጠትና የመወያየት ችግር ነበረባቸው፡፡ የፊፋ እና የካፍ ህጎችን በትክክልል አንብቦ፤ተርጉሞና ተገንዝቦ ወደ ጉባዔው ዝግጁ ሆኖ አለመግባት የተለመደ ሆኗል፡፡ በአብዛኛው የጉባኤ አባላት የሚሰጡ አስተያየቶች ያወዛግቡ የነበሩት የህግን እውቀት መሰረት ያላዳረጉ በመሆናቸው ነው፡፡ ሶስተኛው የውዝግብ ምክንያት በክልላዊ ስሜት የመጓተት ሁኔታ የፈጠረው  ነው፡፡ አገራዊ ስሜት የማይንፀባረቅበት፤ ስለ ኳስ ትኩረት የማይሰጥ ጉባኤ ሆኖ ነበር፡፡ የአገሪቱን እግር ኳስ የወደፊት እጣፋንታ የሚወስን ጉባኤ መሆኑ ቀርቶ ብግለሰብ ጉዳይ በቡድን እየተደራጀ የሚነታረክና አለመደማመጥ የሰፈነበት ጉባኤ የነበረውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
በምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአሰያየም ሂደት ላይ
በእኔ በኩል በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው የምርጫ አስፈፃሚው ኮሚቴን ለመሰየም አስፋላጊው ምርጫ ደንብን ተከትሎ ተካሂዷል በሚል አልመሰክርም፡፡ የኮሚቴው አባላት የተሰየሙት በውክልና እና ክልላዊ ተዋፅኦ እንጅ በምርጫ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ደንቡን ተከትሎ በትክክለኛ አሰራር ድምፅ እየተሰጠ ምርጫው አለመካሄዱ ብቻ አይደለም ችግሩ። የምርጫ አስፈፃሚው ኮሚቴ በገለልተኝነት ለመስራት እንደማይችል ያደረገ ውሳኔ ነው፡፡ በኮሚቴው አባልነት እንዲሰሩ የተሰየሙት አባላት በቀጥታ ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለተወዳዳሪ እጩዎች ድጋፍ የሰጡ በመሆናቸው በገለልተኛነት ምርጫውን ለማስፈፀም የሚቸገሩ ይሆናሉ፡፡በህጋዊ አካሄድ መስፈርቱን የሚያሟላ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለመመስረት በመጀመርያ ከጥቆማ ተነስቶ ከዚያም የጉባዔው አባላት በሚሰጡት ድምፅ መሰረት መወሰን ቢኖርበትም በክልላዊ ውክልና  ህግ መጣሱን አምርሬ የምተቸው ነው፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች የጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊ መሆንዎን በመግለፅ ወደ አመራሩ ቢመጡ አድልዎ ሊፈፅሙ ይችላሉ በሚል ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል… በዚህ ሁኔታ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ምንድነው?
የጊዮርጊስ ደጋፊ ስለመሆኔ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ልክደውም አልችልም፡፡ የሚደበቅ ነገር አይደለም፡፡ አሁን በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ለመሆን በእጩነት የሚወዳደሩ ብዙዎቹ የሚደግፉት ክለብ አላቸው፡፡ የምንም ክለብ ደጋፊ አይደለሁም ቢሉ ማንም አያምናቸውም፡፡ ለስፖርቱ  ፍቅሩ ከጅምሩ ሊገኝ የሚችለው በድጋፍ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እኔ ከውጭ ክለቦች የምደግፈፍው ክለብም አለኝ፡፡ በተለይ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሊቨርፑል ደጋፊ ሆኜ መከታተተል የጀመርኩት በእነኢያን ረሽና ጆን ባርነስ ዘመን ነው። በአጠቃላይ የጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊ መሆኔን ህዝብ ያውቀዋል፡፡  ወደ አመራር ስመጣ ግን በምደግፈው ክለብ መመዘኛ መሆን የለበትም፡፡ ትክክለኛው መመዘኛ በተሰጠው ሃላፊነት ሁሉንም ክለብ በእኩልነት ተመልክቶ ሚዛናዊ አመራር ሊሰጥ ይችላል የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ የወሰደው እኮ እኛ በፌደሬሽኑ አመራር በነበርንበት ወቅት ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለጨዋታ ያልተመዘገበ ተጨዋች ከቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ በማሰለፉ 3 ነጥብ እንዲቀነስበት ያሳለፍነው ታሪካዊ ውሳኔ የሊጉ ሻምፒዮን አድርጎታል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና የፕሪሚዬር ሊጉ ሻምፒዮን ከሆነ በኋላ በስፖንሰርሺፕ ስም ከ60ሺ ዶላር በላይ በግለሰቦች ሊመዘበር የነበረትን አጋጣሚ በልዩ ክትትል በማጋለጥ አትርፊየዋለሁ፡፡ ከ4 ዓመት በፊት በፕሬዝዳንትነት ምርጫው የምወዳደርበትን ሁኔታ ራሴን ባገለልኩበት ውሳኔ በለወጥኩበት ወቅት በጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ አዘዘ የመሰከሩት ነው፡፡ ስለዚህም ማንኛውም አመራር መለካት ያለበት በሚሰጠው ፍትሃዊ ውሳኔ፤ ሁሉንም በእኩልነት በሚመለከትበት አመራር ነው። በምርጫውየሚወዳደሩ ሁሉም የማንም ክለብ ደጋፊ አይደለንም ቢሉ ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ስፖርት ውስጥ የለሁበትም እንደማለት ነው፡፡
ከሰመራው ጉባኤ በፊት የመጨረሻ መልዕክትዎ ምን ሊሆን ይችላል?
በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ላይ ከ22 በላይ እጩ ተወዳዳሪዎች ለውድድር መቅረባቸው የምርጫ ምህዳሩን አስፍቶታል፡፡ ጠንካራ አመራር ሊሰጡ የሚችሉ ግለሰቦችን ለመምረጥ የሚጠቅም ይሆናል፡፡ የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ጎራ በመከፋፈል የሚያደርጉትን ገመድ ጉተታ ትተው፤ በምርጫ ስራ ሊሰሩ የሚችሉ ግለሰቦቹን ወደ አመራርነቱ እንዲመጡ በሚወስኑበት ደረጃ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ በሰመራው ጉባኤ ጠንካራ፤ እውቀቱና አቅሙ ያላቸው ሰዎች ወደ ሃላፊነት እንደሚመጡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስለዚህም የምንሰጠው ድምፅ ስፖርቱን ሊያድን ወይም ሊገድል እንደሚችል በማወቅ በውሳኔያችን 10 ጊዜ ማሰብ ይኖርበናል፡፡

Read 2428 times