Saturday, 02 December 2017 08:47

በድሃ አገራት 10 በመቶ መድሃኒቶች ጥራት የሌላቸውና ሃሰተኛ ናቸው ተባለ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 በየአመቱ እስከ 169 ሺህ ህጻናት በመሰል መድሃኒቶች ሳቢያ ይሞታሉ

   በማደግ ላይ በሚገኙ የአለማችን ድሃ አገራት ጥቅም ላይ ከሚውሉት የተለያዩ አይነት መድሃኒቶች ውስጥ 10 በመቶ ያህሉ ከሚገባው የጥራት ደረጃ በታች ወይም ለከፋ ጉዳት የሚዳርጉና የተጭበረበሩ እንደሆኑ የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባለፈው ማክሰኞ በጄኔቭ በተካሄደ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት፣ የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁና በህገወጥ መንገድ ተመርተው ጥቅም ላይ የሚውሉት መሰል አደገኛ መድሃኒቶች በአለማቀፍ ደረጃ በስፋትና በፍጥነት እየተሰራጩ ሲሆን መድሃኒቶቹ ለከፋ የጤና ጉዳት ከመዳረጋቸው ባለፈ ለሞት የሚያጋልጡ ናቸው፡፡
ከጥራት ደረጃ የሆኑና የተጭበረበሩ ሀሰተኛ ጎጂ መድሃኒቶች በብዛት በጥቅም ላይ የሚውሉት በአብዛኛው በአፍሪካ አገራት ውስጥ ቢሆንም፣ ችግሩ አለማቀፍ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ከሚገኙ መሰል ጥራታቸውን ያልጠበቁ መድሃኒቶች መካከል ለወባ ህክምና የሚውሉና አንቲባዮቲክሶች እንደሚገኙበት እንዲሁም፣ ለካንሰር ህክምና የሚውሉና የእርግዝና መከላከያ መድሃኒቶችም ከጥራት በታች አልያም በተጭበረበረ መንገድ ተሰርተው በብዛት ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
መሰል መድሃኒቶች ከማዳን ይልቅ ህመምን በማባባስ ለከፋ ስቃይ የሚዳርጉ፣ ያለ አግባብ ወጪ የሚያስወጡና የመዳን ተስፋን የሚያጨልሙ ናቸው ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ በሂደትም የትክክለኛ መድሃኒቶችን የማዳን አቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው በአለማቀፍ ደረጃ አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል፡፡
የአለማችን አገራት መንግስታት በገበያ ላይ ውለው በዜጎች ላይ እስከ ሞት የሚያደርሱ ጉዳቶችን የሚያደርሱ መሰል መድሃኒቶችን በጥብቅ ቁጥጥር እንዲያስወግዱና ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ከ48 ሺህ በላይ በሚሆኑ የተለያዩ የመድሃኒት አይነቶች ላይ የተሰሩ 100 የጥራት ደረጃ ፍተሻ ጥናቶችን በመገምገም ባገኘው ውጤት እንዳለው፣ በየአመቱ እስከ 169 ሺህ የሚደርሱ የአለማችን ህጻናት አደገኛ መድሃኒቶችን በመውሰዳቸው ሳቢያ ለኒሞኒያ በሽታ ተጋልጠው ለሞት ይዳረጋሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

Read 1918 times