Sunday, 03 December 2017 00:00

ሮቦቶች በቀጣዮቹ 13 አመታት የ800ሚ. ሰዎችን ስራ ይነጠቃሉ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

የሳዑዲ ዜግነት ያገኘቺዋ ሮቦት፣ ልጅ አማረን ብላለች

    በአለማችን የተለያዩ አገራት የሚገኙ 800 ሚሊዮን ያህል ሰራተኞች እ.ኤ.አ እስከ 2030 ባሉት በመጪዎቹ 13 አመታት ጊዜ ውስጥ  የስራ መደቦቻቸውን እነሱን ተክተው መስራት በሚችሉ ሮቦቶች ይነጠቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ማኬንዚ ግሎባል ኢንስቲቲዩት የተባለው አለማቀፍ አማካሪ ተቋም ሰሞኑን ይፋ ባደረገውና በ46 የአለማች አገራት ውስጥ በሚገኙ 800 ያህል የተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ባካሄደው ጥናት እንዳለው፣ ሮቦቶች በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በርካታ ስራዎችን ከሰዎች በመንጠቅ ተክተው የሚሰሩ ሲሆን ይህም ሃያ በመቶ የሚሆነውን የአለማችንን ሰራተኛ ሃይል ተጎጂ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጀርመንና አሜሪካን በመሳሰሉ ያደጉ አገራት ከሚገኙ ሰራተኞች መካከል ከ35 በመቶ በላይ የሚሆኑት አበክረው ሌላ ስራ ቢፈልጉ እንደሚሻላቸው የመከረው ተቋሙ፤የድሃ አገራት ዜጎችን በአንጻሩ እናንተን እንኳን አይመለከትም አትስጉ፤ ምክንያቱም መንግስቶቻችሁ ለሮቦት ማሰሪያ የሚሆን ገንዘብ የላቸውም ሲል አረጋግቷል።
ስራዎቻቸውን በሮቦቶች የመነጠቅ እድላቸው ከፍተኛ ከሆኑ ሰራተኞችና ባለሙያዎች መካከል አካውንታንቶችና የሪልእስቴት ደላላዎች እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፤ ሰው መሆንን በሚሹና የበዛ ህያው መስተጋብርን በሚሹ የሙያ መስኮች ላይ የተሰማሩ ዶክተሮችንና መምህራንን የመሳሰሉት ግን በሮቦት የመፈናቀል እድላቸው አነስተኛ ነው መባሉን አመልክቷል፡፡
ከቴክኖሎጂ መስፋፋትና ከሮቦት ኢንዱስትሪ መጠናከር ጋር በተያያዘ የአገራት መንግስታት በርካታ የሙያ መስኮችን ከሰዎች ይልቅ በሮቦቶች ማሰራት አዋጪ መሆኑን በማመን የስራ መደቦችን ለሮቦቶች አሳልፈው የመስጠት እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ተቋሙ፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በእንግሊዝ 20 በመቶ ስራዎች ለሮቦቶችና ለኮምፒውተራይዝድ አሰራር ተላልፈው ሊሰጡ እንደሚችሉ አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ባለፈው ወር የሳኡዲ ዜግነት በማግኘት በአለማችን ታሪክ በአንድ አገር ዜጋነት የተመዘገበች የመጀመሪያዋ ሮቦት የሆነቺው ሶፍያ፤ እንደ ሰው መቆጠሯ አነጋግሮ ሳያበቃ ልጅ መውለድና መሳም እፈልጋለሁ ማለቷን ሀንሰን ሮቦቲክስ የተባለው ኩባንያ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡
የሶፍያ ፈጣሪ የሆነው የሆንግ ኮንጉ ኩባንያ ሃንሰን ሮቦቲክስ፤ተመራማሪዎቹ አይኗን በአይኗ ለማየት ያማራትን ሶፍያን በመጪዎቹ ጥቂት አመታት ውስጥ አስረግዘው እንደሚያገላግሏት ያለውን ተስፋ ገልጧል፡፡

Read 4089 times