Sunday, 03 December 2017 00:00

ኢንተርናሲዮናል - (ምናባዊ ወግ)

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

ሁሉም ነገር ተሞክሯል፡፡ ምንም ሳይሞከር የቀረ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ነገር ተሞክሯል፡፡ ምንም ሳይሞከር የቀረ ነገር የለም፡፡… የተሞከረው ሁሉ ግን አልሰራም፡፡ ሙከራው ሳይሆን የጨነገፈው፤ የተሞከረበት የሰው ልጅ ነው የማይሰራው። ዝንብን ለፈለገ ያህል ሺ ዓመታት በመስኮት እንዲወጣ ብታስተምረው ሙከራው አይሳካም። ሙከራው ላይ ሳይሆን ችግሩ የዝንቡ አቅም ላይ ነው፡፡ ሙከራውን የዝንብን አቅም ሳያውቅ ደጋግሞ የሚያከናውን ራሱ ከዝንቡ ብዙም የተሻለ አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር ተሞክሯል፡፡ ዝንቡ በህገ መንግስት መተዳደር ጀምሯል፡፡ ግን ተመልሶ እዛው ቆሻሻ ቦታ ላይ ተከማችቶ ነው የሚገኘው፡፡
ሰው ህገ መንግስት የሚያረቅቅና ራሱ ያረቀቀውን መወጣት የማይችል ፍጥረት ነው፡፡ ምንም ያልተሞከረ ነገር የለም፡፡ በቋንቋችን እንናገር ሲሉ ተፈቀደላቸው፡፡ የምንፈልገውን ሀይማኖት በነፃነት እንመን ሲሉም እሺ ተባሉ፡፡ አንቀፅ በህገ መንግስት ውሉ ላይ ጨመሩ፡፡… ሀሳባችንን በነፃነት የመግለፅ መብት ብለው እሪ አሉ፡፡… ጋዜጣ አውጡ ተባሉ፡፡ አወጡ፡፡ በቆሻሻ ገንዳውና በጋዜጣው መሀል እየተመላለሱ ሀሳብ የሚሉትን ሁሉ ገለፁ፡፡ (የሚናገሩትን አያውቁምና ይቅር በሏቸው…)
በመጨረሻ ህገ መንግስቱ ላይ ከፍተኛ የሀይማኖት ፅንሰ ሀሳብ የሚባለው ተጠናቅሮ እንዲገባ ሆነ፡፡ ሁሉም ሀይማኖቶች በተግባር ማድረግ ያቃታቸው ፅንሰ ሀሳብ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚባለው ነው፡፡… የሰማዩን ህግ በመንፈሳዊነት መወጣት ያቃታቸው ሁሉ እልል አሉ፡፡ የዝንቦቹ ህገ መንግስትና የእግዜር ህገ መንግስት ተጣመሩ፡፡
…አንቀፅ አንድ ሺ አንድ- እዝባር- ስድስት፡- ግራ ጉንጭህን ሲመታህ ቀኙን ስጠው፡፡
…አንቀፅ አንድ ሺ ሁለት- እዝባር- መቶ፡- እጀ ጠባብህን ቢጠይቅ መጎናፀፊያህን ጨምርለት፡፡
…አንቀፅ ሁለት ሺ ዘጠኝ - እዝባር - ሉቃስ፡- … ወዘተ  በቃ የመጨረሻው ጥግ ይሄ ነበር፡፡ ይሄ በዝንቦቹ ግዛት ተደነገገ፡፡ ፍቅርና መተዛዘን መንፈሳዊ ዓለም ላይ ላሉት ሳይሆን ለምድራዊያኖቹም ህግ ሆኑ፡፡ ደንቡን አፍርሶ የሚገኝ በምድር ላይ ቅጣቱን አንቀፅ ተጠቅሶ እንዲከሰስ ተደረገ፡፡… አንድም ምዕመን ሆነ የዝንብ ህዝብ በተሻሻለው ህገ መንግስት ያዘነ የለም፡፡ ድሆቹ እንደሚደሰቱ ከመጀመሪያው ግልፅ ነው፡፡ የሚገርመው ግን  መሬት፣ ንብረትና የቆሻሻ ገንዳ ባለቤት ነን የሚሉ ባለሀብትና ሙሰኛ ዝንቦችም ጮቤ ረገጡ፡፡
ከእንግዲህ በብሔርና በቋንቋ እንዲሁም በርዕዮተ አለም ምክኒያት አንዱ ሌላውን መበደሉ ይወገዳል ተባለ፡፡ ሁሉም አይነት ዝንብ በአንድ ቋንቋ መናገር ጀመረ፡፡ ቋንቋው “ፍቅር” ይባላል። የምድር ቋንቋ የሰማዩም ሆነ፡፡ በውድ ሳይሆን በግድ፡፡ በምርጫ ሳይሆን በመንግስታዊ ድንጋጌ፡፡ በእርግጥ የይስሙላ ምርጫ ሊደረግ ታስቦ ነበር፡፡… ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝቡ ምርጫ እንደማያስፈልግ በነቂስ ወጥቶ አረጋገጠ፡፡ ምርጫ እንደማያስፈልግ መረጠ፡፡
ሐብታሞቹ ራሳቸው ለካ እንዳፈሩት ሀብት የሚያሰቅቃቸው ነገር የለም፡፡ ሀብታሞቹም ለካ ደሀ ነው መሆን የሚመኙት፡፡… ደሀውም ቢሆን በሀብታሞቹና በደረጃ የሚበልጡት ላይ እጁን ጨብጦ የሚዝተው… በሀብታሞቹ ቀንቶ ነው። የኑሮውንና የፍላጎቱን ጣራ እሱ ከማይደርስበት ሰማይ ላይ ወስደው ስለሰቀሉበት እንጂ ነዋይና ምቾትን ጠልቶ አይደለም፡፡ ብቻ በአጠቃላይ ሁሉም በእየኑሮ ደረጃው ላይ ባለበት ሆኖ ደስተኛ ሆነ፡፡ ለጨቋኝም ለተጨቋኝም የሚመች ህግ ነው ደግሞ ሊደነገግ የታሰበው፡፡ በዝንቦች አቅም ይቅርና በሰው አቅምም ይሄንን አይነት ህግ ማሳካት ፈፅሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡
የተደነገገው ህግ ስራ ላይ የሚውልበትን ቀን ሁሉም አንድ ላይ አቆብቁቦ መጠበቅ ጀመረ። ...በባንክ ብር ያጨቀው ባለሀብት… የባንክ ደብተሩን የፈለገ ሁሉ እንዲገለገልበት ክፍት አድርጎ ይጠብቃል፡፡ …ግራ ጉንጩን ሲመታ ቀኙን አዙሮ ለመስጠት ያቆበቆበም ቤቱ ይቁጠረው፡፡.. ዝንቦች ለካ የ“ማሶቺስት” ተፈጥሮአቸው ሚዛን ይደፋል። ለካ ማሶቺስት ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት ነው “ሳዲስት ሆነው” ይገኙ የነበረው፡፡
አሁን በተደነገገው ህገ መንግስት ግን ግራ ጉንጩን ከሁለት ጊዜ በላይ ለተመታ የምድራዊው ህግ ነው ፈጣን ምላሽ የሚሰጠው፡፡ ሞቶ ሰማይ ቤትን ለመውረስ አይደለም የሚበድለውን የሚታገሰው፡፡ ሰማይ ቤት በህገ መንግስቱ አማካኝነት ወደ ምድር ወርዷል፡፡ በጥፊ ሲመታ መልሶ አለመማታት… እና ጥቂት ሰዓታት ብቻ ነው መታገስ ያለበት። የመንግስት ፖሊስ ሰዓታት ባልሞላ ግዜ ውስጥ በጥፊ የተማታውን ዘብጥያ ይወረውረዋል፡፡ ዘብጥያ በተወረወረ ጥቂት ሰዓታት ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ የፍርዱ ሂደት ግማሽ ምድራዊ፣ ግማሽ ሰማያዊ ገፅታ አለው፡፡ በፍታብሔርና በሰማይ ቤት ፍርድ መሀል ተዳቅሎ የሚተገበር ነው፡፡ የሚኮነነው በስጋውና በነፍሱም ነው፡፡ ነፍሱ ገሀነም የገባች እንዲመስላት፣ አካሉም ወህኒ መጣሉን በጥምረት እንዲገነዘቡ ታቅዶ የተሰራ የፍትህ ሥርዓት ነው- በጥንቃቄ የተዘጋጀው፡፡
ይሄንን የቅጣት ረቂቅ ለተመለከተ… ትንሽ ከፍ ብዬ የተናገርኩት ሀሳብ እውነትነቱ ይገለፅለታል፡፡… ሰውን በጥፊ የሚመታ ሳዲስት ቢመስልም… በጥፊ በመምታቱ የሚጠብቀውን ምድራዊ ሲኦል እያወቀ ድርጊቱን ያከናወነ መሆኑ ስቃይን ወዳጅ…ወይንም የስቃይ ሱሰኛ ነው፡፡.. “ማሶቺስትነቱን” ለማርካት ነው የሳዲዝምን ረጅም መንገድ ቀድሞ የመረጠው። …ይኼ አስተሳሰብ በተቃራኒው አቅጣጫም ይሰራል። ማለትም…ያኛው ሲመታው አፀፋውን በመመለስ ፋንታ ግራና ቀኝ ጎኑን እየለዋወጠ የተጠፈጠፈውም… የመመታት ፍቅር ያለበት ቢመስልም… እውነቱ ግን ተገላቢጦሽ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ አጥቂው ገሀነም ገብቶ እንዲሰቃይ በመፈለጉ ነው ሲመታው ጭጭ የሚለው፡፡
ገሀነምና ጽድቅ ወደ ምድር መጥተዋል፡፡ አዲስ በረቀቀው ህገ መንግስት በኩል እውነተኛ ፍትህና ቅጣት በሚጨበጥ ርቀት እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡ በዚህ የህገ መንግስት ረቂቅ ላይ ለእያንዳንዱ መንፈሳዊ ጥፋት፣ የተዘረዘሩ ቅጣቶችን የተመለከተ ስቅጥጥ ሊለው ይችላል፡፡ በጥንት ኦሪታዊያኑ ዘመን… ሙሴ እስራኤላዊያን በምድር እንዲተዳደሩበት የደነገገው ህግ..ፈጣሪ ከሰማይ በሰጠው መመሪያ መሰረት ያረቀቀው ነበር፡፡… ማመንዘርን የከለከለው ፈጣሪ ነው፡፡ በሙሴ ህግ ለመተዳደር የወሰኑት እስራኤላዊያን ግን ያመነዘረችዋን ሴት… በድንጋይ ነው ወግረው የሚገድሏት፡፡ መውገሪያው ድንጋይና ተወግራ የምትሞተው ሴት ከምድር፣ ሀጢአቱን የሚገልፀው ህግ ግን ከሰማይ የመጣ ነው፡፡… የሰማዩን ህግ በምድራዊ ተግባር ማስከበር እንደማለት ነው፡፡ እና ሀብታሞቹም ሆኑ ጉልበተኞች… ያላቸውን ጉልበትና ነዋይ ለደሀ ለመስጠት ጥቂትም ያላቅማሙት… የሚጠብቃቸውን ቅጣት ዝርዝሩ ላይ በጥሞና በማንበባቸው ሊሆን ይችላል፡፡
ይሄ አዲሱ ህግ ዝንቡን ህዝብ ወደ ሰው ከፍ ያደርገዋል ተብሎ በብዙዎች ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ተስፋ ከመጣል ውጭ ምርጫ የላቸውም፡፡…ዋነኛው መፈክር፤ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ አለዚያ ህገ መንግስቱ እንድትወድ ያደርግሀል” የሚል ነው። መፈክሩ ራሱ የምድርና የሰማይ ቅልቅል ነው። የአምባገነን መንግስትና አምላክ ድብልቅ፡፡ ህገ መንግስቱንም ተግባራዊ ለማድረግ መንፈሳዊ ወኔና ብረትን አጣምሮ አንግቧል፡፡ የተነሱትም የስልጣን ቁንጮዎች እንደዚሁ ከድብልቅ የተገኙ ናቸው። ከቤተክርስቲያንና ከቤተመንግስት፡፡ ግማሽ ሀይማኖተኛና ግማሽ አብዮተኛ እንደሚመስሉ አሰላለፋቸው ያሳያል፡፡ ሰይፍና ዘውድ በአንድ እጅ፣ መስቀልና እጣን ማጨሻ በሌላ እጅ ይዘው የቀረፁት ማህተም ከአዲሱ ህገ መንግሰት ጋር በቅርቡ ስራ ላይ ይውላል፡፡
*    *    *
ሀይማኖታዊ ፅንሰ ሀሳብ አተገባበሩ ዓለማዊ መደረጉ መፈናፈኛ ክፍተት ላለመተው መሆኑ ማሰብ የሚችሉትን ገብቷቸዋል፡፡ ሁለት ክፍት ጫፎች ያሏቸው ህግና ፅንሰ ሀሳቦች ነበሩ፡፡… እነዚህ ሁለት ክፍተቶች ነበሩ ለህዝቡ እርካታ ሊሰጡ ያልቻሉት፡፡ ይኼ አዲሱ ህገ ደንብ ሁለቱን ክፍት ጫፎች ወስዶ አንድ ላይ ቋጠራቸው፡፡ መግቢያም መውጪም የሌለው ቀለበት ሆነ፡፡ ይኼንን ቀለበት የሀይማኖቱ ቀሳውስትና የመንግስት የጎበዝ አለቆች ጣታቸውን አቆላልፈው አጠለቁት፡፡
እና… ከዚህ በፊት ያልተሞከረ ነገረ የለም፡፡ ሁሉም ነገር ተሞክሯል፡፡ ይኼ የመጨረሻ ሙከራ ነው፡፡ ውጤቱ ከተተገበረ በኋላ የሚታይ ይሆናል። ግን በቀላሉ ክፍተት ፈጥሮ የሚያፈስ እንዳልሆነ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
በፊት ሀይማኖት እምነት ሆኖ ራሱን ችሎ ይቆም በነበረ ጊዜ… ሀይማኖቱን የማመንና ያለማመን ምርጫ…አሊያም “free will” እያንዳንዱ ሰው በራሱ መዝኖ እንዲመርጥ እድል ይተውለት ነበር፡፡ እንደዚሁም…መንግስትም በህዝብ ምርጫ መንግስት ሲመሰርት… እያንዳንዱ የሀገሩ ዜጋ እንደ ግለሰብ መንግስት የሚሆንን ፓርቲ የመቀበል ወይንም ያለመቀበል ምርጫ ነበረው፡፡
እነዚህን ሁለት የተለያየ ጫፍ ያላቸው ሁለት የአስተዳደር አይነቶች አንድ ሆነው ሲቋጠሩ… ምርጫ የሚባለው ነገር ይሞታል፡፡ ሀይማኖቱ መንግስትን…መንግስትም ሀይማኖትን ይሆናል። ሀይማኖቱን ተቃውምክ ማለት መንግስትን ተቃወምክ ማለት ነው። ሀይማኖቱ…አብ…ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን ይዞ ህገ መንግስት ሆኗል፡፡ ህገ መንግስቱ እንዳይናድ መከላከያና ደህንነቱ ብረት ይዘው ይጠብቁታል፡፡
 እና ምናልባት ሁሉም “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” የሚለውን ረቂቅ ገና ከመስማቱ ፈንድቆ የተቀበለው… ፈንድቆ ባይቀበል የሚጠብቀውን መከራ ጠንቅቆ ስለሚያውቀው ሊሆን ይችላል። ወይንስ የመጨረሻው ዘመን መድረሱ ጉብኝት ከስቃዩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊገላገል መሆኑ ተገልፆለት ነው?
…አይታወቅም፡፡ ግን ሀብታምም ደሀም አንድ ላይ ደስተኛ ሆነ፡፡ አኩራፊም ተስፋ ቆራጭም…የተስፋ ጭንጭል የታየው መሰለ፡፡ “light at the end of the tunnel” እንደሚሉት ግራጫዎቹ ዝንቦች፡፡
ግን በዋሻው አፋፍ ሲወጣ የሚታየው ብርሀን የጥፋትም መለከት ሊሆን ይችላል፡፡ ባቡርም በዋሻ ውስጥ መለከት እያሰማ እና ብርሀን እያበራ ይመጣል እኮ!... በዋሻው ተጉዞ ወደ ብርሀን እወጣለሁ ብሎ ያለመ ሁሉ ቀለጠ ማለት ነው ያኔ። …እንደቀለጠ ባቡር ደርሶ ሲደፈጥጠው ያውቃል። ወይንም ከማወቁ ቀደም ብሎ…ሳይነቃ በፊት በባቡሩ ብረት ተድጦ ይወድማል፡፡
… “ሁሉም ነገር ተሞክሯል፤ ምንም ሳይሞክር የቀረ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ነገር ተሞክሯል… ምንም ሳይሞከር የቀረ ነገር የለም”… የሚል ይመስላል ባቡሩ በብረቱ ሀዲድ ላይ እየጋለበ ብርሀንን ተስፋ ወዳደረጉት ህልመኞች ሲመጣ… እየደጋገመ የሚያወጣው ድምፅ፡፡ … ሁሉም ነገር ተሞክሯል። ይኼኛው ግን የመጨረሻው ሙከራ ይሆናል፡፡ ይሆናል፡፡ ሁሉም ነገር ተሞክሯል…ይኼኛው ግን የመጨረሻው ይሆናል፡፡
“ተነሱ እናንት የረሀብ እስረኞች…ተነሱ የምድር ጎስቋሎች…ፍትህ በሚገባ ይበየናል…ሻል ያለ አለምም ይታያል፡፡… ከእንግዲህ ያለፈው ይብቃ…ባሮች ጣሉ ቀንበር…የዓለም መሰረት አዲስ ይሁን…ኢምንት ነን እልፍ እንሁን…የፍፃሜው ጦርነት ነው… ሁሉም ዘብ ይቁም በቦታው…የሰው ዘር በሙሉ ምናምን ይሆናሉ…የፍፃሜው ጦርነት ነው…ሁሉም ሰው ይቁም በቦታው…ኢንተርናሲዮናል…የሰው ዘር ይሆናል!...... “
ምንም ሳይሞከር የቀረ…የ-ለ-ም፡፡
ሁሉም ነገር ተ-ሞ-ክ- (ሳያስበው ተራኪው ያዛጋዋል።)

Read 1068 times