Print this page
Sunday, 03 December 2017 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(9 votes)

ሰውየው ሞቶ… ገነት ከመድረሱ ራበው፡፡… የጣፋጭ ምግብ ሽታ ደግሞ አንጀቱን አላወሰው፡፡ አጠገቡ ወደ ነበረው ፃዲቅ ጠጋ ብሎ፡-
“በጣም የምወደው ምግብ ይሸተኛል”…አለው፡፡
ፃድቁም… “እዚህ ምግብ አይሰራም”… ሲል መለሰለት፡፡
“ኧረ በጣም ነው የሚሸተኝ”
“እኔን ምንም አይሸተኝም፡፡…ምናልባት ከሌላ ቦታ ነፋስ ያመጣው…ሊሆን ይችላል”
“ከሌላ ማለት?...ከየት ሊሆን ይችላል”
“ከገሃነም..”
“የት…ጋ... ቅርብ ነው?”
“ብዙ አይርቅም…ትንሽ ወረድ ብሎ ነው”
“ሄዶ ማየት ይቻላል?”
“እንዳንተው ፈቃድ ነው”
ሰውየው በሩን አስከፍቶ ወጥቶ ሄዶ፡፡ ወደ ገሃነም እየቀረበ በሄደም ጊዜ ሽታው ይበልጥ አስጎመጀው… ጓጓ፡፡ በሩን ሁለት ሶስቴ እንዳንኳኳ ተከፈተለትና ገባ፡፡ ወደ ውስጥ እንደ ዘለቀ ሽታው እልም አለበት፡፡ ግራ ተጋባ፡፡ ሳጥናኤል ራቅ ብሎ፣ ፊቱን አዙሮ ቆሟል፡፡ ሰውየው ሰላምታ ካቀረበለት በሁዋላ፡-
“የሚበላ ፈልጌ ነበር” …አለው፡፡
አጅሬም “የሚበላ ነገር?... ምግብ ማለትህ ነው?”
“አዎ”
“ምግብ…የሚለውን ቃል ራሱ ከሰማሁ ሚሊዮን ዓመት ይሆነኛል”
“እንዴት ሊሆን ይችላል?...አሁን በሩን በማንኳኳበት ጊዜ እንኳን ሽታው ለጉድ ነበር”
ሳጥናኤልም ሲያስመስል… “አዲስ ነህ መሰለኝ… ከየት ነው የመጣኸው?” …በማለት ጠየቀው፡፡
“ከገነት” … አለ ሰውየው ፈጠን ብሎ፡፡
አጅሬም…እየሳቀ…. “እ…እሱማ እንዳንተ አይነቶቹን፣ ያለ ቦታቸው የገቡትን እያታለልን የምናመጣበት ዘዴ ነው፡፡” …አለው ይባላል፡፡
ወዳጄ፤ ከልክ ያለፈ ሆዳምነት ከገነት እንኳ ያፈናቅላል፡፡ “ሆድ ሲሰፋ ጭንቅላት ይጠባል፡፡… እንደ ቪኖ ፋሽኮ፡፡” ይባል የለ!!
እንግሊዛዊው ፈላስፋና የሶሺዮ ፖለቲካል ሳይንቲስት ጆን ስቴዋርት ሚል ከአጠገበ አሳማ ምስኪን ደሃ ይሻላል፡፡ የዛኑ ያህል ሆዳም ሰው ከመሆንም እንደ ሶቅራጥስ መሆን ትልቅነት ነው፡፡… ይለናል፡፡
ወዳጄ፤ ከምንም ነገር በላይ “መኖር” ሊቀድም ይችላል፡፡ “Life before philosophy” … እንደሚባለው፡፡ ነገር ግን መኖር ማለት ሌሎችን አለማኖር…የሌሎችን የመኖር መብት መርገጥና ማስረገጥ አይደለም፡፡ “ጎመን በጤና” የሚሏት ነገር እኮ የዋዛ አይደለችም፡፡ ጠቢባኑ “Better bread with water than pie with trouble” የሚሉት ነገር ልከኛ ትርጉም ትመስላለች፡፡
ጆን ስቴዋርት ሚል ብዙ ከሚጠቀስባቸው ሃሳቦቹ ዋና ዋና ከሚባሉት ውስጥ፡- “አንድ ሰው ማንንም እስካልጎዳ ድረስ በመሰለው መንገድ ቢኖር ማንም ጣልቃ ሊገባበት አይገባም፡፡ One has the right not to be interfered with… as long as he does not harm others”… የሚል ይገኝበታል።… ይህ መሰረታዊ ከሚባሉት የሰው ልጆች መብት አንደኛው የሆነውን የግል እንቅስቃሴ (Privacy) እንዲጠበቅ ያቀረበው የሲቪል ሊበርቲ ማስከበርያ ሃሳብ ነው፡፡ በዚህም የስልጣኔአችን ባለውለታ መሆኑ ይነገራል፡፡
ወዳጄ፤ ሰዎች ስለ ግል ኑሯቸውም ሆነ ስላገራቸው የሚጨነቁበት ብዙ ምክንያቶች አሏቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን በማይመለከታቸው ወይም በማያገባቸው የሌሎች ሰዎች ጉዳዮች እየገቡ ጊዜያቸውን ያባክናሉ፡፡ በሃሳብ ላይ ሃሳብ ይጨምራሉ፡፡ በነሱ ቋንቋ’ ኔትዎርካቸውን ያጨናንቃሉ፡፡ እንደዚሁም በወዲያኛው በኩል ያለውን ነገር (the other side of the story) ባለመረዳት አርቆ አስተዋይነትና ኢ-ፍትሃዊነት የጎደለው ድምዳሜ በሌሎች ላይ ይጭናሉ፡፡
ፕራግማቲስቶች እና በዘወርዋራ የሚዛመዷቸው ኩዌንሲ ኮንሺያ ሊስቶች (Consequence lists) …አንድን ነገር ወይም አንድን ሃሳብ መነሻውን ብቻ እንደ ምክንያት በመውሰድ ድምዳሜ ላይ በማዘንበል ስህተት እንዳንሰራ አጥብቀው ይመክሩናል፡፡  
ወዳጄ፤…አንድ “ወፈፌ” ነበር አሉ፡፡ ሌሎች ሰዎች በየሄደበት እንደ ጥላ እየተከተሉ መከራውን የሚያሳዩት፡፡… “በራሱ ዓለም” እንዳይኖር እየጎነተሉ ፉታ የሚነሱት፡፡… አንድ ቀን እንደለመዱት በቆመበት ከበው ሲዘባበቱ፣ የወደቀ ከሰል ሰባሪ አነሳና ተደግፎ ከነበረው የስልክ እንጨት ላይ ተንጠላጥሎ ወጣ፡፡…ጫፉ ላይ የሆነ ነገር ፅፎ ወረደ፡፡ አውደልዳዮቹ ፖሉ ላይ ተሸቀዳድመው ለመውጣትና የፃፈውን ለማየት ሲራኮቱ አብዛኞቹ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ አንዱ የበረታ ዘለቀና የተፃፈውን ሲያነብ… “Top of the Pole”… የሚል ነበር፡፡
አየህ ወዳጄ፤ በማያስፈልግ ጉዳይ ራስን መጥመድና ጊዜን ማባከን ድንቁርናን መግለፅና ሌላውን ሰላም መንሳት ብቻ ሳይሆን “የአተርፍ ባይ አጉዳይ” መዘዝም ሊያተርፍ ይችላል፡፡ አንዳንድ ዐዋቂዎች፤ ገሃነም ማለት ሌሎች ሰዎች ማለት ነው። “…Hell means other people” የሚሉት በቂ ምክንያት ስላላቸው እንደሆነ፣ ከላይኛው ቀልድ መገመት አያስቸግርም፡፡
በነገራችን ላይ “ወፈፌ”፣ “ዕብድ” የምንላቸው ሁሉ ዓመፀኞችና ህመምተኞች ናቸው ማለት ስህተት ይመስለኛል፡፡ “በዕብደታቸው ውስጥ ትልቅ ችሎታና ዕውቀት የሚታይባቸው ብዙ ናቸው” በማለት የሚመሰክሩ ሞልተዋል፡፡ ሩሶ፣ ሎርድ ባይረንና አልፈሪን እንደ ምሳሌ በመውሰድ “ዕውቀትና ዕብደት ጎረቤት ናቸው… Madness and genius are neighbours”… ይላሉ፡፡
ወዳጄ፤ አንዳንድ ሰዎች አርቆ አሳቢነታቸው ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አልጣጣም እያለ ሲያስቸግራቸው የሃሳብ ውዝግብና ውጥንቅጥነት በውስጣቸው እየተመላለሰ፣ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሊያጨቃጭቅ ይችላል፡፡
“ሰው ባወቀና በነቃ ጊዜ መከራው ይበዛል፡፡ “The one who is gifted with genius suffers most” የሚለን ታላቁ ፈላስፋ ሾፐን ሃወር ነው፡፡ አሜሪካዊው ፀሃፊ ጀምስ ሚሽነርም… “መጽሃፍትን በመረመርክ ቁጥር ብዙ ነገሮችን ታውቃለህ…እናም ህይወት ምን እንደሆነች ይገባሃል፡፡ ያ.. ደግሞ ወደማታሸንፈው ጦርነት ውስጥ ይከትሃል፡፡
“…The more you read the more you know…the more you know the more you understand life… the more you understand life it puts you in a war that you can not win”… በማለት የሊቁን ሃሳብ ይጋራዋል፡፡
ወዳጄ ልቤ፤ ከዋክብቶቹን እያዩ ሲራመዱ ዕንቅፋት የሰበራቸው፤ ሩቅ እያሰቡ ባጭር የተቀጩትን፤ በርተውልን የቀለጡትን እንደ “ወፈፌ” የቆጠርናቸውን ያገራችንን ሊቆች ደግሞ አንድ ቀን እናስታውሳቸዋለን!!
   ሠላም

Read 2653 times