Saturday, 02 December 2017 09:07

የግብፅን አቋም ቸል ማለት፣ ናዳን አንጋጦ እንደመጠበቅ ነው!

Written by  ገለታ ገ/ወልድ
Rate this item
(3 votes)

 ከሳምንታት በፊት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ስለሚያንዣብበው የውስጥና የውጭ ጭጋግ፣ የግል እይታዬን በዚሁ ጋዜጣ ላይ ለመሰንዘር ሞክሬአለሁ። አሁንም ወቅታዊውን የኢትዮ-  ግብፅ የአባይ ላይ ጉምጉምታ  ተከትዬ፣  አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት ልሞክር፡፡
ምስራቅ አፍሪካዊያኑ ህዝቦች “ናይል” በሚሉት፣ በአብዛኛው የእኛ የተፈጥሮ ሀብት በሆነው  አባይ ላይ በተፋሰሱ አገራት መካከል ጠንካራ  የትብብር ማዕቀፍ ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በተለይ ለ10 ዓመታት ገደማ የዘለቀው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ስምምነት ብዙ የተደከመበት  ነበር። በቀደሙት  ሥርዓቶች  በታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይም በግብጽና አጋሮቿ በነበረው ጫና፤  በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ  በነበሩ መንግሥታት የአቅም ማነስና የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ መዳከም ምክንያት ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ህዝቦች ከውሃው ተጠቃሚ ሳይሆኑ ዘመናት አልፈዋል።
በዚህም  የፈርኦናዊያን ገዥዎች በየዘመናቸው  የተዛባውን  የውሃ አጠቃቀም  በመላው ግብጻዊያን ልብ ውስጥ ሳይቀር ሸንቅረው ሲያደናግሩት እንደኖሩ የተለያዩ  አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡  ለምሳሌ  በርካታ ግብጻዊያን አባይ ከየት እንደመጣ እንኳን መገንዘብ የጀመሩት ከኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ እንደሆነ፣ የአፍሪካን ሶሳይቲ የተሰኘው የግብጽ ተቋም ዳይሬክተር፣ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ግብፅን ለጎበኘው የአፍሪካ ጋዜጠኞች ቡድን መናገራቸዉ የሚታወስ ነው፡፡ ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ 60 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ዐረብ ነን ብሎ ያምን ነበር፤ 40 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት አቋም አልነበረውም ብለዋል።  
በወቅቱ “አባይ ሥሩ ኢትዮጵያ፣ ፍሬው ግብጽ ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ግብጽ አጠቃላይ ህይወቷ የተመሠረተው አፍሪካ ላይ መሆኑን እስከ መርሳት ደርሳ እንደነበር በግልፅ አስረድተዋል፡፡  እርግጥ የአባይ ፍሬን  ስትለቀም የኖረችው ግብጽ፣ ለዜጎቿ ጥቅም  ብቻ ቢሆንም አሁን የደረስንበት ወቅት ይህንን ሁኔታ የሚሸከም ባለመሆኑ የግንድ ሐረጓን እንዳታስታውስና ወደ አፍሪካ ለመመለስ ጥረት ማድረግ እንድትጀምር አስገዳጅም  ሁኔታ ተፈጥሯል ማለታቸው አይዘነጋም።
መሬት ላይ ባለው እውነት መሰረት ግን አሁንም ግብፃዊያን ፖለቲከኞች፤ እንኳን ሌላውን ሀገርና ህዝብ (ያውም ጥቁር አፍሪካ)  የኑሮ መሰረታቸው አድርገው፣ ስለ ሰጥቶ መቀበል ሊያስቡ ይቅርና  እያደባ  ከሚያገረሽ “መብቴን” (በመሰረቱ የ1929 እና 1959 የቅኝ  ግዛት የተፅዕኖ ኢ-ፍትሃዊ ድልድል እንጂ   ፍትሃዊ የውሃ  ክፍፍል መብት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡)  አትንኩ ፉከራ የሚወጣ አይደለም። በኖረው ኢ-ፍትሃዊና ኢ-ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ታጥሮ ለመቀጠልም የመመኘት ልክፍት የተጠናወተው አካሄድ መንፀባረቁ አልቀረም፡፡
ግብጻዊያን የቻሉትን ያህል ፍሬ እየለቀሙ ሲመገቡና የተረፋቸውን እንዳሻቸው እያባክኑ  ሲንደላቀቁ ዘመናት ተለዋውጠዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው የተፋሰስ አገራት ደግሞ  የውሃው ዋነኛ መነሻ ሆነው ያለ ምንም ተጠቃሚነት ዘልቀዋል። ይህ አስተሳሰብም በአባይ ተፋሰስ አገራት ለዘመናት ገዢ ሃሳብ ሆኖ ዘልቋል። አወዛጋቢም ነበር፡፡
በተለይም ለአባይ ውኃ የአንበሣውን ድርሻ የያዘችው ኢትዮጵያ፣ በዚህ አባባልና ተግባር ለዘመናት ተጎጂ ሆና መኖሯ ይታወቃል። በየጊዜው በአገሪቱ የነበሩ መንግሥታትም ቢሆኑ የውስጥ መረጋጋት ስላልነበራቸውና የልማት አስተሳሰብም ስለሚጎድላቸው፣ ግብጽ ውኃውን እንዳሻት ስትጠቀምበትና ሌሎች አገራት የብድርም ሆነ ሌላ ድጋፍ አግኝተው፣ በአባይ ውኃ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ስታከላክል ኖራለች። በተቃራኒው እኛም በድርቅና በርሃብ ብቻ ሳይሆን በእርስበርስ ጦርነትና በግጭት ከሚባለው በላይ ተለብልበናል። አንድ የአካላችን ክፋይ የሆነን ህዝብና መሬትም በጊዜያዊ ፖለቲካዊ መሻትና አርቆ ያለ ማሰብ አነጣጥሎናል። አንጎበሩም እየተመላለሰ እስካሁንም ይገዳደረን ይዟል፡፡
በእርግጥ ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ካለው ሁለንተናዊ የልማት ለውጥ ጋር ተያይዞ በአባይ ውኃ ላይ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ መነሳትና መጠናከር ጀምሯል።  ሌሎቹ የተፋሰስ ሀገሮችም ወደ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም አመክንዮ መምጣታቸው  የኖረውን የግብፃዊያን የተዛባ አስተሳሰብ ቅርቃር ውስጥ እንደጨመረው ገለልተኛ ተንታኞች ደጋግመው አንስተዋል፡፡ በዚህ ጊዜም ነው ግብፅ የተፋሰሱን ሀገራት ወደ መቀራረብ ለማምጣት ስትሞክር የታየችው፡፡ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ  አል ሲሲ በአንድ ወቅት፤ “ግብጽ ከአፍሪካ ተነጥላ  የኖረችባቸው ዓመታት አግባብነት አልነበራቸውም፤ ሥር መሠረቷን አስቷታል፤ ለዚህም ቀላል የማይባል ዋጋ ከፍላለች“ ማለታቸውም መነሻውም ይሄው ነበር። ይሁንና ግን የግብፅ ፖለቲከኞች በወሬ እንጂ በገቢር ለዚህ እሳቤ ሲገዙ አለመታየታቸው፣ በየድርድር መድረኩ በሚያነሱት መንቻካ አቋም በጉልህ መንፀባረቁ አልቀረም፡፡  
በመሰረቱ በኖረው ኢ-ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም መሰረት፤ ግብጽ የአባይን ውኃ መጠቀም ብቻ ሳይሆን እያባከነችውም እንደቆየች  አገሪቱን የጎበኙ ሁሉ የሚታዘቡት ነገር ነው። የአባይ ውኃ በአስዋን ግድብ ብቻ ለአገሪቱ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በእርግጥ ከአገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ የሚምዘገዘገው የአባይ ውኃ ለግብጽ ህይወቷ  ነው። አባይ ለግብጽ አማራጭ  እንዳልሆነም ተደጋግሞ የተባለ ነው። ብቸኛ የህይወታቸው መሠረትም  ነው። ይህንን መካድ አይቻልም። ነገር ግን ይህ ቅቡል እውነታ ቢኖርም የውሃ ሃብቱ ሌሎችንም (ያውም አመንጭዎቹን) በፍትሃዊነት ከመጥቀም አያግደውም ፣ሊያግደውም አይችልም፡፡
ዛሬም ቢሆን አነጋጋሪው ነገር ግን ግብጽ ውኃውን በብቸኝነት እየተጠቀመች ብቻ ሳይሆን እያባከነችም ለመቀጠል ያላት የከረረ አቋም፣ እየተመላላሰም ቢሆን የመምጣቱ  ጉዳይ ነው።  እስካሁንም ድረስ ግብጽ ከሌሎች አገራት ጋር ተባብራና ተጋግዛ፣ ለመሥራት ቁርጠኝነት አይታይባትም። ለዚህም ዋናው አስረጅ፣ የአባይ  ተፋሰስ የስምምነት ማዕቀፍም ሆነ የምሥራቅ አፍሪካ የአባይ ተፋሰስ ትብብር ላይ ለመፈረም ፈቃደኛ አለመሆኗ ብቻ ሳይሆን በእኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የያገባኛል መንፈስ ያለበት እንደራደር ስሌት ውስጥ መቆየቷ ነው። እሱ  ብቻ ሳይሆን በተፈቀደላት ድርድር ውስጥም በመግባት  ወደ ማለቁ የደረሰን ግድብ ለማስቆም የመዳዳት አቋም ማራመዷ ነው፡፡
ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ብቻ ሳይሆኑ የመላው ዓለም የውሃ ሃብት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሞጋጆች የተስማሙበት አንድ እውነት ግን በአየሩ ላይ  አርብቧል፡፡ የአባይንም ሆነ የሌሎች ሀገራት  አቋራጭ (ድንበር ተሻጋሪ) ወንዞችን  የውሃ  አጠቃቀም፣ ከግለኝነት ይልቅ በጋራና በሰጥቶ መቀበል መርህ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንፃር  በኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ግዛትን አቋርጦ፣ ለም አፈሯን እየጠራረገ የሚከንፈው የአባይ ወንዝ፣ በግብጽ ተረጋግቶና የተለያዩ ጠቀሜታዎችን እየሰጠ መፍሰሱ ባይቀርም  በኢትዮጵያም ትልቅ ጥቅም እንዲሰጥ የተደረገው ጥበበኛ ውሳኔ፣ ትክክልና ቅቡልነት ያለው ነው። ያውም ወንዙ ከደለልና ከሃይለኛ ጎርፍ ተጠብቆ፣ በሱዳን በኩል ወደ ግብፅ ሲሻገር ለቀጠናው ደግሞ ከ6ሺ 700 ሜጋዋት በላይ ሃይል ይመነጭበታል፡፡ በሰው ሰራሹ  ግዙፍ ሃይቅ መሰራትም  የአሳ ምርቱና ቱሪዝሙም ይጧጧፍበታል፡፡ ይህን ቃል ገቢር የማድረግ ጉዳይ ደግሞ የእኛ ትውልድ ትልቁ የቤት ስራ ሆኗል፡፡ መሆንም አለበት፡፡
በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት እንደታየው፤ የግብጽ መንግሥት በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን በኩል የሚደረግ የሦስትዮሽ ውይይት እንዲጀመር ብሎም፣ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳለው ደጋግሞ  ገልፆአል። በየመድረኩም ከሊቅ እስከ ደቂቅ የኢትዮጵያን ልማት አንቃወምም ማለታቸውም ይደመጣል። ይህ ከሆነ ግብጽን እያሳሰበ ያለው ነገር ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ስለ ምንድነው በቅርቡ እስከ 17 ዙር ድረስ ከሀገር ሀገር እየተቀያየረ በሚካሄደው  ምክክርስ ስምምነት ላይ ያልተደረሰው? እንደገና ወደ ኋላ እየተመለሱ የውሃ ጥቅማችን ቅንጣት ያህል ሊነካ አይችልም የሚለውን ቀረርቶስ ምን አመጣው? ብሎ መፈተሽ አስፈላጊና ግድ ነው፡፡   በዚህ ፀሃፊ እምነት፤ ኢትዮጵያ ግድቡን አጠናቃ ሃይል ከማመንጨት የሚያግዳት እንደሌለ  ቢታወቅም በውስጣችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ  አለመረጋጋት ችግር ደጋግሞ ሲፈጠር ወይም በፋሽስት ጣሊያን በተሰራልን የከረረ ብሄርተኝነት ስንባላ፣ ሀገራችን በኖረው ስሌት ወደ ኋላ ትመለሳለች፤ ትዳከማለች የሚል ሂሳብ አላቸው። ሌላው ነገር  ግብጽን እያሳሰባት ያለው  የግድቡ መፋጠን ብቻ ሳይሆን  በአፍሪካ  ያላትን ሁለንተናዊ የበላይነት  በኢትዮጵያ መነጠቋ ነው።
ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ሊገነባ የሚችለውን ትልቁን ፕሮጀክት በራሷ አቅም መገንባት ከቻለችና አሁን ባለው ፍጥነት ካደገች፣ ሸለቆዋን እያቆራረጠና ለም አፈሯን እየወሰደ የሚመጣውን የአባይን ውኃ በየአካባቢው እየገደበች፣ ለእርሻ ልማትም ሆነ ለመለስተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመጠቀም የሚያግዳት ነገር የለም ከሚል የተሳሳተና የራስ ወዳድነት ድምዳሜ በመድረሷ ነው። ከዚህ የተነሳ ከአባይ ተፋሰስ አገራትም ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ልዩነቶችን በመፍጠር ነገሮች በውይይት እንዳይቋጩ የተለያዩ ጥረቶችን ከማድረግ አለመቆጠቧን የገፋችበት እየመሰለች መጥታለች።
ለዚህ አባባል ጥሩ ማሳያ የሚሆነውም ሶስቱ ሀገራት ባይግባቡም በድርድር ላይ እያሉ፣ ወደፊታችንም በመሪ ደረጃ ካይሮ ላይ ተስፋ ሰጭና፣ መደማመጥ የተላበሰ ስምምነት ይደረጋል በሚባልበት ወሳኝ ወቅት ላይ ፕሬዚደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ያደረጉት ገፍታሪ ንግግር ነው፡፡ “የናይል ውሃ ለግብጻዊያን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወንድሞቻችንን ልማት የማልማት ፍላጎታቸውን ባንከለክልም በተፈጥሮአዊ ስጦታችን ናይል ውሃ ላይ ጠብታ ቅናሽ እንዲፈጠር አንፈቅድም፡፡”  የሚል ስሜት ያለው ንግግር ነው፡፡
በተቃራኒው ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤት አገራትም ሆነ ከሌሎች የዓለማችን አገራት ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይታወቃል። በተለይ የድንበር ወሰን ካላቸው እንደ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያና ኤርትራ የመሳሰሉ አገራት ጋር በሠላም የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ላይ የተመሰረተ  የግንኙነት ስትራቴጂ ትከተላለች። አገሪቱ  ተግባራዊ  ባደረገችው  የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምክንያት ከሁሉም አጎራባች አገራት (ከኤርትራ በስተቀር) ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱም የዚሁ ውጤት ነው።
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ያሉ አገራትን ጭምር ተጠቃሚ ማድረግ አስችሏል። የቀጠናው አገራት በኢትዮጵያ ላይ አመኔታ ማሳደርም  ችለዋል። ለዚህ አንዱ ማሣያ ደግሞ ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በተለይ በደቡብ ሱዳንም ሆነ በሱዳን መንግሥት አመኔታን አግኝታ፣ በሁለቱ አገራት አጨቃጫቂ  የጋራ ድንበሮች ሠላም አስከባሪ እንድታሰማራ በሁለት ጎረቤት አገራት እስከመመረጥ መድረሷ፣ የአገሪቱ ፖሊሲና የህዝቦቿ ታማኝነት ምን ያህል የተጠናከረ መሆኑን ያመላክታል። ከዚህም ሌላ  ኢትዮጵያ በምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሠረት፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማስጠበቅ፣ አገራዊ ህልውናን ማረጋገጥና በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሳትገባ  ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ተባብራ መሥራቷ  ነው። ፖሊሲው ለሁሉም አገራት የሚሰራ በመሆኑ ግብጽ ላይ የተለየ አቋም ሊኖር አይችልም። በእነሱ በኩል ያለው አካሄድ ግን በተቃራኒው መሆኑን ደጋግመን አይተናል፡፡ የኢፌዲሪ መንግስት ደጋግሞ እንደከሰሰው፤ ባለፈዉ ዓመት በአማራና በኦሮሚያ ክልል በተካሄዱ ግጭቶች፣ የግብፃዊያኑ እጆች ነበሩበት፡፡ በኤርትራ፣ በሶማሊያም ሆነ በደቡብ ሱዳን የውስጥ እና የውጭ ችግሮችም ኮቴያቸው የለም ማለት አዳጋች ነው፡፡
በመሰረቱ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከቀጠናው አገራት ጋር ሰፊ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ከምትጠቀምባቸው ዘርፎች አንዱ ለጎረቤት አገራት ኃይልን በተመጣጣኝ ዋጋ  ማቅረብ  ነው። እስከ አሁንም ሃይል ካገኙ ጎረቤት ሀገሮች ሌላ አገራቱ በኢትዮጵያ እየተገነቡ ካሉ ትላልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ በሰፊው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ እያመቻቸች  ትገኛለች። በዚህ መልክ ግብጽም ተጠቃሚ መሆኗ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህን ቀጠናዊ ፋይዳ ወደ ጎን ብሎ፣ ብቻዬን ልብላዉ  ወደሚል የስግብግብነት መንገድ ውስጥ መግባት ግን ያለ ጥርጥር መበላትን ያስከትላል፡፡ ዓለም አቀፋዊ ነውርም ነው!
ግብጽ የራሷን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ አሟልታ ለሌሎች አገሮች በመሸጥ ላይ ትገኛለች። ሱዳን፣ ሊቢያና ቻድ፤ ግብጽ የኤሌክትሪክ ኃይል የምትሸጥላቸው አገራት ናቸው። አሁንም በቀጣይ ሰፊ ኃይልን በማመንጨት፣ ገበያዋን ማስፋፋት እንደምትሻ በየእቅዷ ሰነዶች ተጠቅሶ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ በተለያየ መልክ ለማደናቀፍ ከመጣር ወደ ኋላ እንደማትል ይታወቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር በተለመደው የሥነ-ልቦና ጦርነትና በውስጥ ድክመት ውስጥ ገብቶ የማዳከም ስልትን ይተዉታል ብሎ መዘናጋት፣ ናዳን አንጋጦ ከመጠበቅ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ ነቃ፣ ጠንቀቅ፤ በውስጥ ብሄራዊ መግባባትና መስማማትን ማስቀደምና ጅምሩን የህዳሴ ሩጫ ማፍጠን ያስፈልጋል፤ ይገባልም፡፡

Read 2430 times