Sunday, 03 December 2017 00:00

ህዝቡ ዝምታው ሊያስከብረው እንጂ ሊያስንቀው አይገባም!

Written by  ከይልቃል እውነቱ
Rate this item
(2 votes)


    “…እግር ኳሱ አሁን ያለበት ደረጃ አሳፋሪ ነው። አገራችን ካለችበት ዕድገት አኳያ ለህዝባችንም፣ ለመንግሥትም የማይመጥን ነው፡፡ ስለዚህ የደቡብ ክልል አንተ ወደ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብትገባም ይህን መጥፎ ታሪክ ትለውጣለህ፡፡ ለአመራርነቱ በተሟላ ብቃት ትመጥናለህ ብሏል፡፡ እኔም በዚህ ሁኔታ ስለማምንበት ነው….”
ከላይ የቀረበው ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ህዳር 16 ቀን 2010 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ “ስፖርት አድማስ” ላይ የሰጡት አስተያየት ነው፡፡ የአምዱ አዘጋጅ ግሩም ሠይፉ “የቅርጫት ኳሱን ራዕይ ለማን ተውት?” በማለት… ለዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ጥያቄ በማቅረብ፣ “ፈረሱም ሜዳውም ይኸው” ብሎ ለቋል፡፡
ለመሆኑ እግር ኳሱ ለህዝብም፣ ለመንግሥትም የማይመጥን አሳፋሪ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው? ከመስከረም ወር 2010 ዓ.ም ወዲህ በተቆጠሩት ወራት ነው? ወይስ ዶ/ር አሸብር በፌዴሬሽኑ አዛዥ ናዛዥ ፕሬዚዳንት የነበሩባቸውን ስድስት ዓመታትም ይጨምራል?... ይህን ለይተው እንዲነግሩን የሚኮረኩር ጥያቄ አልተጠየቁም፡፡
ዶ/ር አሸብር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ፡፡ ኮሚቴው በቅርበት ከሚከታተላቸው፣ ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን በመፈተሽ ጠንካራው ጎን እንዲጎለብት፣ ደካማው እንዲታረም የኮሚቴው አቅም በሚፈቅደው መጠን እገዛ ከሚያደርግላቸው ዘርፎች አንዱ ስፖርት እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ በዚያ የሥራ ዘመናቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ፤ ለህዝብም፣ ለመንግሥትም ከማይመጥን አሳፋሪ ደረጃ ላይ መድረሱን አያውቁም ነበር? ካወቁ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከመቃብር አፋፍ እስኪደርስ ለምን ጠበቁ? የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቆይታቸው ሲያበቃ ዳግም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በመሆን ስፖርቱን ለመታደግ አስበው ይሆን?
ይህንንም ሊጠየቁ ይገባ ነበር? “ኢትዮጵያን በቅርጫት ኳስ ዓለም ካርታ ላይ አሰፍራታለሁ…” በሚል ቃል፣ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንን ወደ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መዳረሻ መሰላል አደረጉት። ያሉት ተሳካ፣ መሰላሉን ሰብረው፣ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተግባራዊ አደርጋቸዋለሁ በማለት የደረደሯቸውን ዕቅዶች ሳይተገብሩ፣ ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያሸጋግራቸውን ድልድይ ዘረጉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝንዳትነታቸው፣ በፌዴሬሽን ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውን የውድድር ስፖርቶች በሙሉ በቅርብ የመከታተልና የማገዝ ዕድል እያላቸው በውዝግብ ወደ ለቀቁት ቤት ለመመለስ ለምን ፈለጉ? በርካታ ለጋዜጠኛው ትዝ ያላሉትን ጥያቄዎች ማቅረብ ይቻል ነበር፡፡
ያ ባለመሆኑ ዶ/ር አሸብር፤ የዲዮጋን መንፈስ በዘመናት ብዛት ባልጠፋ ፋኖስ ብርሃን፤ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈልጎ ያገኛቸው ብቸኛ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን፣ ለስፖርቱ ተቆርቋሪነታቸውንና ከከፍታማ ማማ ለመስቀል ዝግጁ መሆናቸውን በ “ስፖርት አድማስ” ገልጸዋል፡፡
“የሚሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ” እንደተባለው፣ የስፖርቱ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በምርጫ ሳጥን ድምፅ የመስጠት ዕድልና ታማኝ ቆጣሪ ቢያገኝ፣ የሚወስነውን ባለመገንዘብ ተገቢ ጥንቃቄ ባለመደረጉ ዶ/ሩ “ስፖርት አድማስ”ን ለምረጡኝ ቅስቀሳ ተጠቅመውበታል፡፡
የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ጋዜጠኛውን አይወቅስም። በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ለሚጫወቱ ግጥም እየደረደረ፣ ጉሮሮው እስኪዘጋ የሚጮህ ጋዜጠኛ ባፈራች አገር፣ “ድሀ ቤት ጎመን ሲቀቀል ሲጨፈር ይታደራል” እንደተባለው፣ ከአሥራ ስድስት ሀገራት ቡድኖች የመጨረሻውን ደረጃ ያለ ተቀናቃኝ አስመዝግቦ፣ ከደቡብ አፍሪካ ለተመለሰ ቡድን ሽልማትና ሸላሚ በማዘጋጀት፣ ከሽልማቱ የተቋደሱ የፌዴሬሽን ባለሥልጣናትን “አበጃችሁ” በማለት ነጋሪት የጎሰሙ ባልታጡበት ሀገር፤ ዶ/ር አሸብርን እንደሚፈልጉት ማስተናገዱ ላያስደንቅ ይችላል፡፡
እውነቱ ግን ከዚህ ይለያል፡፡ የስፖርቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ሊከበር ይገባል። የሚያውቀው የለም፡፡ “ማወቅ እናውቃለን…” በማለት ነው ዝምታ የመረጠው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን አሥራ ሁለተኛ ተሰላፊ በመሆን ፀሐይና ዝናብ የሚፈራረቅበት፣ ባልተዘጋጀ ቡድን ሽንፈት፣ ቆሽቱ ደብኖና አልቅሶ፣ ወደ ቤቱ ፊቱን የሚያዞር ሕዝብ፤ ድምጹን ባይነጠቅ ፌዴሬሽኑን የማስተዳደር ዕድል አግኝተው ለስፖርቱ ያልሠሩ የሚባሉበት ምክንያት “የበላን ያብላላዋል፣ የለበሰን ይበርደዋል” እንደተባለው መሆኑን በመገንዘብ በቃችሁ ይላቸው ነበር፡፡ ግን ስላልታደለ የዳር ተመልካች ሆኗል፡፡ ጦርነቱና ፍልሚያው ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት ያለመሆኑን እያወቀ ዝም ብሏል፡፡ ዝምታውም ሊያስከብረው እንጂ ሊያስንቀው አይገባም፡፡

Read 1939 times