Sunday, 03 December 2017 00:00

“በድንቅ አብቃይ ምድር”… ከትምሕርት ፍለጋ ሌላ

Written by  እንዳለጌታ ከበደ
Rate this item
(3 votes)

“-አብዛኛው የእኛ ሀገር ጥበብ ከመጠየቅ፣ ከመፈተሽ ይልቅ መልስ መስጠትና ማስተማር ላይ ያተኩራል፡፡ በትክክል የተጠየቀ ጥያቄ
ግማሽ መልስ እንደመስጠት መሆኑን የዘነጋ ይመስላል፡፡ ኪነቱ የሚከየነው፣ ደንብሮ የበረገገውን ለመመለስ፣ የተሸነቆረውን ለመድፈን፣
የተሰወረውን ለመግለጥ፣ የጨለመውን ለማፍካት ብቻ ሳይሆን ለመጠየቅም ጭምር ነው፡፡--”
   
    ሰሞኑን በአንድ የአገራችን ቴሌቪዥን ቻናል፣ ሕጻናት ከመሰሎቻቸው ጋር ውለውና ተጫውተው ሲመለሱ፣ ከጨዋታው ምን ትምሕርት እንዳገኙ መጠየቅ ተገቢ እንደሆነ አንድ የስነልቦና ባለሙያ ሲናገር ሰማሁ፡፡ ትንታኔው ትንሽ ጎረበጠኝ፡፡ ይሄ በየነገሩ መሃል አለቅጥ ትምሕርት ለመውሰድ የምናደርገው ጉዞ፣ መታከምና መዳከም እንዳለበት አመንኩ፡፡ አንድ ሕጻን፣ የግጥሙ ድምጸትና ዜማው እንጂ ምን ትምሕርት ለማስተላለፍ እንደተፈለገ አሳስቦኝ የማያውቀውን የልጅነት መዝሙር ማለትም፣ ”ድምቢ ለድምቢ /ድምቢ ኖራ/ ኖራ መስኮራ መስቀል ቆርኪ /ቆርኪ ሰላሌ ሰላሌምቦ/ ሌምቦ ክፍሌምቦ…”ን ከመሰሎቹ ጋር ቢጫወት፣ ወይም “በዚያ በረሃ፣ በዚያ ክረምት….” ዓይነት ጨዋታ ተጫውቶ ቢመለስ፣ ወይም በሌሎች አዝናኝ የአካልና የኅሊና ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ቢያደርግ፣ ”ምን ተማርክ፤ ከዘመርከው መዝሙር ወይም ከተጫወትከው ጨዋታ?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ አይመስለኝም፤ በቃ ጨዋታ ነው፤ ደስ ካለውና በጨዋታው ራሱንም ሆነ ሌላውን ካልጎዳ በቂ ነው፡፡ ትርጉም አልባ ግጥሞች ያሉበትን መዝሙር ቢዘምር፣ ጭቃ ጠፍጥፎ  ቤት፣ ሽቦ ቆልምሞ መኪና ቢሰራ  ሕጻኑን እስካዝናናው ድረስ በቂ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በቅርቡ ያጣነው ሰሎሞን ደሬሳ፣ ከ20 ዓመት  በፊት (እዚህ አገር በመጣ ጊዜ) በተደረገለት አንድ ቃለ መጠይቅ ላይ፣ ትምሕርት ፍለጋ ርቀን የምንሄድበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን ተናግሮ ነበር፡፡ እንደ ሰሎሞን አስተያየት፣ እኛ ኢትዮጵያውያን “የዕድሜ ልክ ተማሪዎች” መሆናችን ከሌሎች ሥልጡናን አሳንሶናል፡፡ ለዚህም ነው፣ ጉዳያችን ትምሕርት ማግኘት ላይ ብቻ በማተኮሩ ስላጣናቸው እሴቶችና ቁጭቶቹ ሲዘረዝር፣ ”ምን ተፈጠረና ነው፣ ላሊበላ ላስታ ውስጥ ብቻ ተፈጥሮ ሌላ ቦታ የቀረው? ለምንድነው ርዝራዡ ሳይደርሰን የቀረው? አክሱም ያን ያህል ተሰርቷል፤ የማያልፍ የለም፤ ከዚያ ርዝራዡ እንዴት ለትግራይ ሕዝብ አልተረፈም? እንደሚመስለኝ ቁጭ ብለን ከማየት፣ ከማተኮር፣ ከመመሰጥ አብልጠን ትምሕርት እንፈልጋለን፡፡ ሁልጊዜ ትምሕርት የምትፈልግ ከሆንክ ተማሪ ሆነህ ነው የምትቀረው፤ ዘላለም ወጣትነትን ከፈለግህ አባት ሳትሆን ታልፋለህ!” ያለው፡፡
ይህ የፍልስፍና አዋቂ፣ ኢትዮጵያውያን አንድ ነገር እንደተነጠቅን ወይም እንደጣልን የተገነዘበ፣አጥብቆም ያመነ፣ እምነቱም ሕማም የሆነበት ሰው ነው፡፡ “ማየት አልቻልንም” ባይ ነው። “ዓይናችንን አላሰራነውም” ባይ ነው፡፡ አክሱም፣ ጎንደር፣ ላሊበላ ብንሄድ የምናገኛቸውና ተመልካች የሚጎርፍላቸው አብያተ ክርስቲያናት አንዴ ከታነጹ በኋላ አለመደገማቸው፣ መሰል አለማፍራታቸው፣ ርዝራዥ አለማስቀረታቸው፣…. የአካባቢው ማኅበረሰብ በስንፍና መዋጡ፣ አጠገቡ የሚገኘውን ስልጣኔ ለመኮረጅ ኅሊናውን አለማሰራቱና ዓይኑን አለመግለጡ ወደ ኋላ እንደጎተተን ያምናል፤ ይቆጫልም፡፡ ከአንድ ነገር የሚገኘውን ጥቅም መሻት ወይም መሸመት እንጂ ውበትን ማድነቅ አልተለማመድንም፤ አልተፈታንም፤ አልተፍታታንም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል፣ በዕውቀቱ ሥዩም፣ በ”ስብስብ ግጥሞች” መጽሐፉ “በድንቅ አብቃይ ምድር” የሚለውን ግጥም ያስነበበን፡፡

አገሩ በሙሉ፣ የብስና ባሕሩ፣ ውኃ ሠራሽ ኾኖ
ለምን ያስቡታል? አባይን ለመስኖ
ለኛ አልተሰጠንም? ዓለምን መመልከት፣ ከጥቅሙ ነጥሎ
ውኃ ተሸምኖ፣ ባዬር ሲተጣጠፍ፣ ማዬት ዝም ብሎ
ሐሳብን ማሳረፍ፣ ከማር፣ ከሰም ስሌት
ለኛ አልተሰጠንም፣ ማዳመጥ፣ማጣጣም፣የንብን ማሕሌት
ዶሮን ከዶሮ ወጥ ነጥሎ መመኘት
ለሳት ቀለም ክንፉ፣ ለንጋት መዝሙሩ፣ ላጫጫር ምስጢሩ
ቃል መርጦ መቀኘት…

እያለ ይቀጥላል - ግጥሙ፡፡
የኪነጥበብ ዓለሙን ነጥለን እንየው፡፡ በኢትዮጵያችን ውስጥ ጥበብ ዛሬም እንደ ትናንቱ ሃይማኖታዊ፣ ምግባራዊና ተረታዊ ጥላ ክፉኛ ተጭኖታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኪነጥበቡ ሙሉ ለሙሉ አልተፈታም፤ ነጻ አልወጣም፤ በራሱ መንገድ የራሱን መንገድ አልቀየሰም፤ በቀየሰው መንገድ በልበ ሙሉነት መረማመድ አልሆነለትም፡፡ ነጻነቱ የተገደበ ይመስላል፡፡ እስረኛ ነው፡፡ ጥቂቶች ናቸው፣ ከዚህ ጎዳና አፈንግጠውና አምፀው ነባሩን መንገድ “የራስህ ጉዳይ!” ብለው  የራሳቸውን አጥርና ቅጥር ያበጁት፡፡ አብዛኛው የጥበብ ውጤት ግን የሃይማኖት ወይም የተረት ወይም የሁለቱም ጥላ ይከተለዋል፤ ጠቢቡን ያሳድደዋል፡፡ እጁን ይዞ፣ኮቴውን አስቀድሞና ድምጹን ዘለግ አድርጎ፣ ‹ና! ልንገርህ፤ ልምከርህ፤ መንገድ ላመላክትህ!› ይለዋል፡፡ ከያኒው ከሃይማኖትና ከተረት ክቡድና ንዑድ ዛፍ ስር ተነስቶ በነጻነት ጎዳና ሊመላለስ ቢወድ እንኳን፣ የኪነቱ አጣጣሚ የሆነው ምዕምን፣ በስውር ወይም በገሃድ  ሃይማኖታዊና ተረታዊ ካባ በልቦናው ደርቦ ሥራውን ሊገመግመው ቆርጦ ሲነሳ እናስተውላለን፡፡
የሰጪው ብቻ ሣይሆን የተቀባዩም የኪነጥበብና የስልጣኔ አቀባበል ደረጃ ውሱን ነው፡፡ የጠባቂና የተጠባቂ፣ የእረኛና የበግ፣ የመምሕርና የተማሪ ዓይነት ግንኙነት፡፡ ለዚህም ይሆናል፣ ሀገሪቱ ምናቧን በማሰራት በኩል ከስታ፣ ቀጭጫ፣ ከሰውነት ተራ ወጥታ የምትታየን፡፡ ሕመሟ አልታወቀላትም፤ ስላልታወቀላት በቅጡ አልታከመችውም። ማቃሰት ሆኗል ሥራዋ። ይህን ለመረዳት ደግሞ ወደማሠላሰያ ክፍላችን የሚወስደው የኅሊናችን በራችን ተቆልፏል። መቆለፉ ሳይሆን እንደተቆለፈብን አለማወቃችንና አለማየታችን ደግሞ ሌላኛው ሕመማችን ሆኗል። ጥቂቶች ናቸው መቆለፉን ያወቁ፤ ያዩ! ከእነዚህ መካከልም ጥቂቶች ከውስጥ ሆነው ይህም “አለ ለካ” ብለው የጨለመውን ክፍል ውበትና ቅርጽ እያደነቁ ነው፤ ጥቂቶች ደግሞ ከተቆለፈበት ክፍል እንዴት መውጣት እንዳለባቸው እያሰላሰሉ፣ ደግሞም ለመውጣት እየሞከሩ፣ አንዳንዶቹም እስር ቤቱን አምልጠው እየወጡ ነው፡፡
በርግጥም የሀገራችን ኪነጥበብ አማጺ ያንሰዋል። ከተለመደው መንገድ የሚያፈነግጡ ከያንን ብዙ የሉንም፡፡ ለማፈንገጥ ወይም እምብዛም ባልተሄደበት መንገድ ለመሔድ የአማጺነት መንፈስ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ አማጺ ከያኒ ግቡ ተደራሲውን ማስተማርና ማንቃት ላይሆን ይችላል፡፡ ከማስተማር ይልቅ ውበት - በቅርጽ መዝናናት፣ በሃሳብ መጽናናትና በስሜት መጫወት - ግድ ይለው ይሆናል፡፡ ውበት ደግሞ ሰውም ይስራው ፈጣሪ ምትሃታዊ ሃይል አለው- እንደ መስክ አበባ መንፈስን ያለመልማል፤ የኪነቱ አጣጣሚ አዲስ ዓይን እንዲኖረው ያደርገዋል፤ ውበት ለማጣጣም በመቻሉም የአዋቂነትና የዕድለኝነት መንፈስ ይሰማዋል፤ በዚህም የተነሳ የኪነቱ ቤተኛ ለራሱ ያለው ከበሬታ እንዲያድግ ያስችለዋል - በአብዛኛው። ይህ ማለት ግን ይህ ዋና ግቡ ትምሕርት መስጠት ያልሆነው የኪነት ሥራ ለአንዳንዶች አይኮመጥጣቸውም፤ አይሰነፍጣቸውም ማለት አይደለም፡፡
እኔ እንደተረዳሁት፤ አብዛኛው የእኛ ሀገር ጥበብ ከመጠየቅ፣ ከመፈተሽ ይልቅ መልስ መስጠትና ማስተማር ላይ ያተኩራል፡፡ በትክክል የተጠየቀ ጥያቄ ግማሽ መልስ እንደመስጠት መሆኑን የዘነጋ ይመስላል፡፡ ኪነቱ የሚከየነው፣ ደንብሮ የበረገገውን ለመመለስ፣ የተሸነቆረውን ለመድፈን፣ የተሰወረውን ለመግለጥ፣ የጨለመውን ለማፍካት ብቻ ሳይሆን ለመጠየቅም ጭምር ነው። መጠየቅ አዕምሮን ጅምናስቲክ ያሰራል፤ ”የት ነው ያለሁት?” ያስብላል፤ ከራስ ጋር ያጨዋውታል፤ ራስን ለአስቸኳይ ስብሰባ ያስጠራል፡፡ አለበለዚያ ቀደም ሲል ስለው እንደቆየሁት መታከት ነው፡፡ የአንድን ዘፈን አዝማች መልስ መላልሶ  እንደመደጋገም ነው። ሁሉም አስተማሪ ከሆነ ማን አዲስ ዓይን ሊሰራልን ነው? ሁሉም ነባሩን አጽንቶ ለማቆየት ተጋድሎውን የሚፈጽም ከሆነ ማን የራሱን ዘመን ሐውልት ሊተክል ነው? ሁሉም የአሮጌው ሃሳብ አድናቂ ከሆነ መቸ ነው ዓይናችንን የምናሰራው?
ሌሎች ሀገራት ‹ነቅተናል፤ በስለናል፤ የዕውቀት ዕጸ በለስ በልተናል፤ ክፉና ደጉን ለይተናል› ብለው አማራጭ መንገዶችን ለማየትና ሰፍተው ለመስፋት ‹መንገድ ስጡኝ ሰፊ› ሲሉ፣ እንደኛ ያሉ ሀገራት ደግሞ ወደ ኋላ እየቀረን ወይም ስፍራችንን ላለመልቀቅ እየተንገታገትን ነው፡፡ ስፍራ ላለመልቀቅ መንገታገታችን ባልከፋ - አዲስ ዓይን አለን የሚሉትን ዓይናቸው ለማጥፋት የምናደርገው ርብርብ ሌሎችን አስደነገጠብን እንጂ፡፡
አብዛኛው ሕዝብ አንድን የኪነት ሥራ የሚያጣጥመው (እንደ አቢይ ተልዕኮ አድርጎ የሚወስደው) መልዕክት (ጭብጡ ምንድነው ይላሉ የሥነጽሑፍ መምሕራን) ለማግኘት ይመስለኛል፡፡ በቴአትሩም፣ በድርሰቱም፣ በሥዕሉም፣ በፊልሙም ሆነ በሌሎች የጥበባት ዘርፎች  ትምሕርት እንፈልጋለን፡፡ ያ ፈጠራ መንገድ እንዲያሳየን፣ ከጭለማ ነጻ የምንወጣበትን መንገድ እንዲጠቁመን እንመኛለን፡፡ ጥበቡን የመምሕርነትን  ሚና የሚጫወት መሲሕ ወይም ነቢይ  ብቻ አድርጎ የመመልከት አባዜ በብዙዎቻችን ጭንቅላት ውስጥ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡
አንዳንዱ የኪነቱን ውጤት ሊፈትነው ወይም ሊፈታተነው ይችል ይሆናል፡፡ በዚህ የተነሳ ከውበትና ከአዲስ ቅርጽ ጋር ከመተዋወቅ ይልቅ ልክ ልኩን እንዲነግረው ወይም እንዲነግርለት ይፈልጋል፡፡
 የአሊ ቢራን ዘፈኖች እሰማለሁ፤  ግን የተዘፈነበትን ቋንቋ ኦሮምኛን አላውቅም፤ የማሊያዊቷ  ኦማ ሳንጋሪን እሰማታለሁ፤ የምትለውን ግን አላውቀውም፤ ዘፈኖቻቸውን ለመውደድ አስረጅ አላስፈለገኝም፤ አያስፈልገኝም፤ እነዚህንም ሆነ ሌሎች በማላውቃቸው ቋንቋዎች የሚጫወቱ ድምጻውያን ለመረዳት የድምጽ አወጣጣቸው ከማረከኝ፣ ዜማውን ከሙዚቃው ጋር ለማዋሐድ የሚያደርጉት ጥረት ከገባኝ በቂ ነው፡፡ መልዕክቱ ምንድነው? ብዬ ራሴን አላስጨንቅም፡፡ ያ ማለት ግን በሙዚቃዎቹ ትምሕርት ለማግኘት መፈለግ ስህተት ነው ብዬ አይደለም- የሁልጊዜ ግባችን በየኪነጥበባቱ ትምሕርት መቅሰም ብቻ አናድርገው ማለቴ እንጂ!
በርግጥ ሌላውን ለማስተማር፣ ከድባቴው ለማንቃት፣ ከስንፍናው ለማትጋት የሚከየን ኪነት አለ - ለመቆስቆስ፣ ለመወስወስ የሚዘጋጅ። አንባቢውን ወደ አንድ አቅጣጫ ለመምራት የሚያስችሉ ሃሳቦችን እየቀሰቀሱ፣ ”አሁን እንዲህ የሆንከው እየሄድክበት ያለው መንገድ የተወላገደ ስለሆነ ነው” የሚለው የኪነጥበብ ውጤት የሚፈልግ ይመስላል፡፡
ቀደም ሲል እንደተገለጸው እኛ ኢትዮጵያውያን ትምሕርት የመፈለግ የረዥም ጊዜ ልምድ አለን። ተረታችንም፣ ታሪካችንም፣ ተረባችንም ይህንኑ ነው የሚያሳየው፡፡ በዘወርዋራ መንገድ ሳይሆን በቀጥታ አስተማሪዎች ናቸው፡፡ መንገድ ይጠቁማሉ፤ የማስጠንቀቂያ ደወል ያሰማሉ፤ ሰናይ ባሕርያትን አጽንተው ያቆያሉ፤ እኩይ ባሕርያትን ከተተከሉበት አውድማ የሚነቀሉበትን ሁኔታ ይዘረጋሉ፡፡
ሲጠቃለል፣ ”መማር ለሚፈልግ የማያስተምር ነገር የለም” ይባላል፡፡ “ምንም ትምሕርት አይሰጥም” የሚባልለት አንድ የፈጠራ ሥራ እንኳን፣ ቢያንስ ቢያንስ ትምሕርት የማይሰጥ ነገር እንዴት መስራት እንደሚቻል ማስተማርያ ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡ አንድ ኪነታዊ ሥራ ሌላውን ለማትጋት ወይም ለማቅናት ብቻ አይከየንም፡፡ አላማው ማስተማር ባይሆን እንኳን እግረ መንገዱን የሚለው ነገር ይኖራል፡፡ ወደደም ጠላ አንድ ነገር መናገሩ አይቀሬ ይሆናል፡፡

Read 2183 times