Sunday, 03 December 2017 00:00

የአቋም መግለጫ ወይስ ኑዛዜ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

“የህወኃትን የአቋም መግለጫ ስሰማ…”
               
   ህወኃት ከ1ወር በላይ ባደረገው ግምገማ የድርጅቱን ሊቀመንበር ከስልጣን በማውረድ ምክትል ሊቀ መንበር የነበሩትን ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ 9 የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትንም መርጧል፡፡ የዘንድሮ የኃወሐት ስብሰባና ግምገማ በድርጅቱ የስብሰባ ታሪክ ረዥም ጊዜ በመውሰድ ሪከርድ አስመዝግቧል ተብሏል፡፡
ህወኃት በየጉባኤው ላይ ራሱን ማጥላላትና እንደሌላ ቡድን ራሱን መወንጀሉ የተለመደ ቢሆንም የመቼውም ጊዜ ቢሆን ሰሞኑን ካወጣው የአቋም መግለጫ ጋር አይወዳደርም፡፡ እንኳንስ በሥልጣን ለመቀጠል ያሰበ ድርጅት ከሥልጣን እንዲወርድ የተፈረደበትም ቢሆን እንዲህ ያለ ከኑዛዜ የማይተናነስ የአቋም መግለጫ ያወጣል ብሎ አይታሰብም፡፡
“ፀረ- ዲሞክራሲ፣ አገልጋይ ሳይሆን ተገልጋይ፣ ለአዲስ አመራር መውጣት እንቅፋት የሆነ፣ የፌደራል ሥርዓቱን የሸረሸረ፣ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የራሱን ክብር ያስቀደመ…” ብዙ ብዙ ውንጀላ ነው በራሱ ላይ ያቀረበው፡፡ በሰላም ነው? በጤና ነው? ያሰኛል፡፡ ለመሆኑ ፖለቲከኞች የአቋም መግለጫውን ሲሰሙ ምን አሉ? አለቀሱ? ተገረሙ?
“የህወኃትን መግለጫ ከሠማሁ በኋላ አልቅሻለሁ”
አቶ ጥሩነህ ገሞታ
(የኤፌኮ አመራር)
በአቋም መግለጫቸው ላይ በግልፅ በህዝብ ላይ ወንጀል ሠርተናል ካሉ በኋላ እንዴት ስልጣን ላይ ለመቀጠል አሁንም ይቋምጣሉ? እኔ መግለጫቸው ከሠማሁ በኋላ ሌሊቱን አልቅሼ ነው ያደርኩት፡፡ እኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንደዚህ አይነት ወንጀል ሠርቼ ህዝብ ፊት የምቆምበት ሞራል የለኝም፡፡ ያሣዝናል! ሰዎቹ እንዴት እያሠቡ እንደሆነ ለመረዳት ችግሮኛል፡፡
ይሄንን ብቻ ነው ማለት የምችለው፡፡ የግምገማ ውጤታቸውም ምንም አዲስ ለውጥ አያመጣም፡፡

“አመራሩ አጠፋ
ከተባለ እርምጃ መኖር አለበት”
በፍቃዱ ሃይሉ
(ጦማሪ)
የግምገማው ውጤትና መግለጫው አፋዊ ብቻ ነው፡፡ ሁልጊዜ ህውሓት ራሱን በግምገማዎቹ ይወቅሳል፤ ይተቻል ግን ጥፋት ፈፃሚዎች ላይ የሚወሠድ የህግ እርምጃ የለም፡፡ ይሄ በፊትም የነበረ አሁንም የቀጠለ የድርጅቱ ባህል ነው፡፡ ሹም ሽር አድርገናል ቢሉም በፊትም በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ከነበሩ 45 ሰዎች ነው መርጠው ወደ ስራ አስፈፃሚ ያመጧቸው እንጂ አዲስ ነገር አልፈጠሩም። ለሣምንታት የደከሙበት ግምገማቸው ዝም ብሎ የሊቀ መንበርነቱን ቦታ ለመያዝ የተደከመበት ካልሆነ በስተቀር ምንም አዲስ ለውጥ አላመጣም፡፡ ከዚህ በኋላም ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡
አመራሩ አጠፋ ከተባለ እርምጃ መኖር አለበት፤ ግን አሁን የት አለ እርምጃው? ያችን የሊቀ መንበርነት ቦታ ለመውሠድ የተደረገ ጥረት ብቻ ነው እኔ የተመለከትኩት፡፡
“የህወኃት ግምገማ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም”
ዶ/ር ባንትይርጉ
(የኢዴፓ ም/ፕሬዚዳንት)
ህወሓት ረጅም ጊዜ በፈጀው ስብሠባው ያደረገው የስልጣን መተካካት ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብዙ ለውጥ አያመጣም።
ምክንያቱም በአመራሩ መካከል ያለው የርዕዮተ አለም ልዩነት የሃሣብ ፍጭት ሣይሆን አንዱ አንዱን አመራር ለመተካትና በትረ ስልጣኑን ለመቆናጠጥ የተደረገ ሽኩቻ ነው፡፡ የድርጅቱን አካሄድ ፈፅሞ የሚቀይር አይደለም፡፡ አዲስ የተሾሙት ሠዎችም በፊትም ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩ ናቸው፤ አዲስ ነገር የለም፡፡
ሌላው በመግለጫቸው ያሉት አመራሩ፤ ህዝቡን  በድሏል፣ ጎድቷል  ነው፤ ግን ይህን ወንጀል የፈፀመ ሠው በህግ ተጠያቂ ሲደረግ አላየንም፡፡ እነዚህ ሰዎች አጥፍተዋል ከተባሉ በህግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ዝም ብሎ ከስልጣን ዝቅ ማድረግ ብቻ ከሆነ፣ እነሡን የተካው አመራርም በስልጣን ለመባለግ ተረኛ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አስተማሪ እርምጃ አይወሠድም፤ ግፉ በል ከስልጣን ዝቅ መደረግ ነው፡፡ ይሄ በሠውየው ላይ የሚያመጣው ምንም ጉዳት የለም፡፡
“የአቋም መግለጫው ስልጣን ለመቀጠል ህዝቡን ደጅ መጥኚያ ነው”
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
(ፖለቲካኛ)
እኔ ከአቋም መግለጫቸው የተረዳሁት፣ ምንም አዲስ ነገር ሣይፈጥሩ የኢትዮጵያ ህዝብ በስልጣን እንዲያስቀጥላቸው ደጅ የመጥናት አድርጌ ነው።
ዛሬ እነሡ ገምግመናል ብለው የዘረዘሯቸው ችግሮች ለበርካታ አመታት ከተለያዩ ወገኖች በግልፅ ሲነገሯቸው የነበሩ ናቸው፡፡ አዲስ አይደሉም። አዲስ ይሆን የነበረው የእነዚህ ችግሮች ምንጭ ምንድን ነው? ለወደፊት ምን ማስተካከያ መደረግ አለበት? የሚለው ላይ አሣማኝ ነጥብ ቢቀርብ ነበር።
የኢትዮጵያ ችግር በድርጅት ግምገማ ሣይሆን በአጠቃላይ እይታ ላይ ለውጥ በማምጣት ነው ሊፈታ የሚችለው፡፡
አሁን ግን የመፍትሄ አቅጣጫ አላቀረቡም፤ የሃገሪቱን ችግሮች በመረዳት ረገድ ምንም አዲስ ግንዛቤ አላመጣም። የአመራር ለውጡም ቢሆን ምክትል የነበሩት ዋና ሆኑ ይሄው ነው ለውጡ። በቃ፡፡ በቡድንተኝነት ላይ የነበረውን መተጋገል፣ አንዱ ቡድን አሸንፎ ስልጣን ያዘ። ይሄ ነው የታየው።
ከህዝቡ በመጣበት ግፊት የመደናገጥና ይሄን የመከላከል ጥረት ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በድለዋል የተባሉም ያለመቀጣታቸው ጉዳይ የድርጅቱ ባህል ሆኖ የዘለቀ በመሆኑ ምንም የሚደንቅ አይሆንም፡፡

Read 4497 times