Monday, 04 December 2017 12:57

ታላቁ ሩጫና የሙዚቃ ኮንሰርት!

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)


             • “ኢትዮጵያውያን ተዋደዱ፤ ልዩነት አያስፈልግም” - ካሊ ፒ
             • አልበሜን ለገበያ ያበቃሁት በኢትዮጵያ አርበኞች የድል ቀን ነው - ታሻ ቲ
             • ስለ ኢትዮጵያ ገና ብዙ መዝፈን እፈልጋለሁ - ቲዎኒ
             
    ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከኤችአይኤም ኢንተርናሽናል ኤቨንትስ እና ከቢግ በዝ ማርኬቲንግ ፒኤልሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የመጀመርያው ‹‹ግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት›› ባለፈው ሳምንት እሁድ በድምቀትና በስኬት ተካሂዷል፡፡ ከ17ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሜ  የጎዳና ላይ ሩጫ በኋላ በጊዮን ሆቴል ዩኒቲ ፓርክ በተካሄደው ኮንሰርት ላይ ከ3ሺ በላይ ታዳሚዎች እንደተገኙ ተገምቷል፡፡ በርግጥ አዘጋጆቹ ከ10ሺ በላይ ታዳሚዎችን ነበር የጠበቁት፡፡ ኮንሰርቱ የጎዳና ላይ ሩጫው እንደተጠናቀቀ ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ ሊጀመር ነበር የታሰበው፡፡ ሆኖም አላስፈላጊ ግርግርና የፀጥታ ችግር ይፈጠራል በሚል፣ ከ8 ሰዓት ከሰዓት በኋላ በመጀመሩ፣ የተጠበቀውን ያህል ህዝብ ሊገባ አለመቻሉን አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
በኮንሰርቱ ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ታዋቂ የሬጌ ሙዚቃኞች አቀንቅነዋል፡፡ ታዳሚዎች ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን ‹‹ግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት›› ብዙ ተስፋ ሰጭ ሁኔታዎች ታይተውበታል ብለዋል፡፡ ሰላማዊና ፍቅር የሞላበት ነበር፡፡
ሉችያኖ ዘሜሰንጃህ እና ያጀበው ማፊያን ፍለክስ ባንድ-ከእንግሊዝ ፣ ካሊ ፒ ከስዊዘርላንድ ፤ ቲዋይኔ-  ከፈረንሳይ እንዲሁም ትውልዷ ጃማይካ የሆነችው ታሻ ቲ- ከካናዳ… ግሬት ኢትዮጵያ ኮንሰርት ላይ የተሳተፉ እውቅ የሬጌ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡ ከአገር ውስጥ ደግሞ እውቆቹ ድምፃውያን ራስ ጃኒ፤ ማዲንጎ አፈወርቅ፤ ንዋይ ደበበ፤ በኮንሰርቱ በዚሁ ኮንሰርት ላይ ሥራቸውን አቅርበዋል፡፡ የኮንሰርቱ መሪ ድምፃዊ ሉችያኖ ሙዚቃውን ያቀረበው ከእንግሊዝ ከመጣው ባንድ ጋር ሲሆን ታሻቲ ደግሞ  ከዘመን ባንድ ጋር ተጫውታለች፡፡ “መሃሪ ብራዘርስ ባንድ” እውቆቹን የሬጌ ሙዚቀኞች ካሉ ፒ እና ቲዋይኔ  በአጭር ጊዜ ልምምድ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ከማጀባቸውም በላይ ከራስ ጃኒ፣ ማዲንጎ አፈወርቅና ንዋይ ደበበ ጋርም ተጫውተዋል፡፡   
ከጃማይካ ለ6ኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውና በዓለም ዙርያ በተለያዩ አገራት ከ120 በላይ ኮንሰርቶችን ያቀረበው ሉችያኖ፤ በኮንሰርቱ ላይ በእንግሊዝ አሉ ከሚባሉና ዓለም አቀፍ ደረጃ ካላቸው ማፊያን ፍለክስ ባንድ ጋር ለ45 ደቂቃዎች ተጫውቷል፡፡ አርቲስቱ ያሰበው ለ90 ደቂቃ ለማቀንቀን ነበር፡፡ በሰዓት መጣበብ  
በ”ግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት” ላይ ሥራቸውን ያቀረቡ የሬጌ አርቲስቶች የተሳተፉት ካሊ ፒ፤ ታሻ ቲ እና ቲዎኒ በኮንሰርቱ፣ በኢትዮጵያ፣ በሬጌ ሙዚቃና በግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት መጀመር ዙሪያ የሰጡት አስተያየት እንዲህ አጠናቅረነዋል፡፡
በመላው ዓለም  ከ1500 በላይ  ግዙፍ የሙዚቃ ፌስቲቫሎች እንደሚካሄዱ ይገመታል፡፡ እንግሊዝና አሜሪካ በተሳታፊ ብዛት፤ በትርፋማነት፤ በረጅም ጊዜ  ልምድ የተገነቡ ታላላቅ የሙዚቃ ፌስቲቫሎች በማዘጋጀት የአንበሳውን ድርሻ ሊወስዱ ይወስዳሉ። ከዓለማችን ደማቅና ግዙፍ የሙዚቃ ፌስቲቫሎች መካከል በሞሮኮዋ ከተማ ራባት ውስጥ የሚዘጋጀው የሙዋዚን ሙዚቃ ፌስቲቫልም ይጠቀሳል፡፡ እንደ ሪሃና፤ አንጀሊኬ ኮጆ እና ኤነሪክ ኢግላስያስን የመሳሳሉ ምርጥ ሙዚቀኞችን የሚያሳትፈው ሙዋዚን፤ ብዙ ታዳሚዎችን በመማረክ ከዓለም ግዙፍ ፌስቲቫሎች ተርታ  ለመሰለፍ የበቃና በአፍሪካ እንደተምሳሌት የሚታይ ነው፡፡ በሌላ በኩል በቡልጋርያዋ ቡዳፔስት እና በብራዚሏ ሪዮ ዲጄኔሮ ከተሞችም በየዓመቱ የሚካሄዱ ትልልቅ የሙዚቃ ፌስቲቫሎች አሉ፡፡
በሰሜን አሜሪካ ብቻ በየዓመቱ ከ250 በላይ፣ በአውሮፓ ደግሞ ከ500 በላይ ግዙፍ የሙዚቃ ፌስቲቫሎችና ኮንሰርቶች እንደሚካሄዱ የሚያመለክቱ መረጃዎች፤ በኤስያና በአፍሪካ አህጉራት በእያንዳንዳቸው እስከ 10 ፌስቲቫሎች እንደሚዘጋጁ ይጠቁማል፡፡ በቻይና 5 ፤ በህንድ እስከ 10፤ በምስራቅ አውሮፓ ከ50 በላይ፤ በፈረንሳይና በጀርመን፣ በጣሊያን በሆላንድና በስፔን በእያንዳንዳቸው እስከ 15 የሚደረሱ  ዓመታዊ ፌስቲቫሎች አሏቸው፡፡ እንዳሏቸውም ይዘረዝራሉ፡፡ በአፍሪካ ቢያንስ አምስት ዓለምአቀፍ እውቅና ያላቸው የሙዚቃ ፌስቲቫሎች ይዘጋጃሉ፡፡  ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ሴኔጋል ግዙፎችን ፌስቲቫሎች በማዘጋጀት ከአፍሪካ የሚጠቀሱ አገራት ናቸው፡፡ የአፍሪካ መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ ከዚህ ከፍተኛ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ የድርሻዋን ታገኝ ዘንድ በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል፡፡
የሙዚቃ ፌስቲቫሎች አዳዲስ የሙዚቃ አርቲስቶችና ሙዚቀኞችን ለማፍራት፣ ምርጥ የሙዚቃ ቅንብርና ብቃት ያለው ባንድን ለመፍጠር፤ ገቢ ለማስገኘት ፤ ገፅታ ለመገንባት የተለያዩ ዘመቻዎችን ለማካሄድ፤ ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፤ ለእርዳታ ገቢ ማሰባሰቢያ ፤ለልምድ ልውውጥ አመቺ መድረኮችና ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ፡፡ በተለያዩ ተቋማት የቀረቡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ትርፋማዎቹ ፌስቲቫሎች ከአንድ ቀን በላይ የሚካሄዱ ናቸው፡፡ ከትኬት ሽያጭ፤ ከስፖንሰርሺፕና ተያያዥ ንግዶች የሚያገኙት የገቢ መጠንም የሚያስጎዥ ነው። የሙዚቃ ፌስቲቫሎቹ ለስፖንሰሮች ብዙ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡
የንግድ ምልክትን ለማስተዋወቅና ለመገንባት፤ የምርቶችን እውቅና ለማሳደግና ገበያ ለማነቃቃት፤ አዲስ ምርትን አስተዋውቆ ለመጀመር ሁነኛ መድረኮች ናቸው፡፡ ከሙዚቃ ሙያም ጋር በተያያዘም የፌስቲቫሎች ሚና ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ሙዚቀኞች፤ ቡድኖቻቸው እና ባንዶቻቸው በተለያየ አገራት በመዞር ከሚያገኙት ገቢ ይልቅ  በፌስቲቫል ወይምን ኮንሰርት በመስራት የተሻለ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ አዳዳዲስ አድናቂዎችን ለማፍራት፤ የገፅታ ግንባታቸውን ለማጠናከር፤ በመድረክ ላይ አጨዋወታቸውና አቀራረባቸው ትኩረት ለማግኘት፤ እንዲሁም ያሳተሟቸው አልበሞችን ለማሻሻጥ ፌስቲቫሎች በእጅጉ ያግዛቸዋል፡፡ ብዙዎቹ የዓለማችን ትልልቅ የሙዚቃ ፌስቲቫሎች በየዓመቱ ሳይቆረጡ የሚካሄዱና ከ10 እስከ 50 ዓመታት ታሪክና ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ግዙፍ ፌስቲቫሎች በአማካይ እስከ 4 ቀናት የሚቆዩ፤  ከ50 ሺ እስከ 150ሺ ታዳሚዎች ይኖሯቸዋል። የትኬት ዋጋቸው በሰው ከ50  እስከ 450 ዶላር ይደርሳል።
በመላው ዓለም የሚካሄዱት ትላልቅ የሙዚቃ ፌስቲቫሎችና ኮንሰርቶች በየዓመቱ ከትኬት ሽያጭ፤ ከስፖንሰርሺፕና ተያያዥ ንግዶች እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይሰባሰባሉ፡፡ የፌስቲቫልና ኮንሰርት ኢንዱስትሪ ባለፉት 10 ዓመታት በማያቋርጥ እድገት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከሙዚቃ ኢንዱስትሪው አጠቃላይ ገቢ እስከ 60 በመቶ ድርሻ እየያዘ ይገኛል።  በከፍተኛ ገቢያቸው የሚታወቁት በአብዛኛው በአሜሪካ የሚካሄዱት ሲሆኑ እያንዳንዳቸው  ከ50 እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በየዓመቱ እንደሚገኝባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

-------

      ካሊ ፒ (ስዊዘርላንድ)
ስለ ኢትዮጵያ ህይወቴን በሙሉ ስዘምርላት እንደመኖሬ፣ ዘንድሮ  ለመጀመርያ ጊዜ ስመጣ፣ የተሰማኝ ወደ ቤቴ እንደመጣሁ ነው፡፡ በቆይታዬ ልዩ የመንፈስ ጥንካሬና ብርታት አግኝቻለሁ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ገና ብዙ ሙዚቃዎችን መስራት እፈልጋለሁ፡፡ ከ18 አመቴ ጀምሮ ከማውቃት ኢትዮጵያዊት ጓደኛዬና ከ6 ዓመት ሴት ልጃችን ጋር በስዊዘርላንድ ነው የምንኖረው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ባህልና ቋንቋ በቤቴም የማውቀው ነው፡፡ ትንሽ ትንሽ አማርኛ ያወቅኩትም ከቤተሰቤ ጋር በማሳለፍው ህይወት ነው፡፡ “አባታችን ሆይ እያልኩ” በአማርኛ ፀሎት ማድረግ እችላለሁ፡፡ ወደፊትም ቋንቋውን  በደንብ ለመማር እፈልጋለሁ፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን  በመሳተፌ እጅግ ልዩ ክብር ተሰምቶኛል፡፡ 44ሺ ተሳታፊዎች በአንድ አይነት የቲሸርት ቀለም፣ በጎዳናው ላይ በልዩ ድምቀትና አንድነት ሲተሙ መመልከቴ አስደንቆኛል፡፡ በአንድነት ሆነን፤ በፍቅር ተሳስረን፣ ቀኑን በደስታ ያሳለፍንበት ሁኔታ ለእኔ እንደ መባረክ የሚቆጠር ነው፡፡ በየትኛውም የዓለም ክፍል አይቼው የማላውቅ ልምድ ነው፡፡
ሬጌ ሙዚቃና ሬጌ ሙዚቀኞች በአራቱም የዓለም ማዕዘኖች ኢትዮጵያን ያስተዋውቃሉ፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚካሄዱ ትልልቅ የሬጌ ሙዚቃ ፌስቲቫሎች ላይ የኢትዮጵያ ስሟ፤ ታሪኳ፤ ቀለሟ… ድባብ ሆኖ እንደሚያጅብም ይታወቃል፡፡ ስለዚህም ታላቁ የሬጌ ሙዚቃ ንቅናቄ አዎ በኢትዮጵያ መሆን ይኖርበታል። ኢትዮጵያ በሬጌ ሙዚቃ የዓለም መዲና የምትሆነው፣ በእኛ የሬጌ ሙዚቀኞች ፍላጎት ብቻ አይደለም፡፡  ሁሉም ኢትዮጵያዊ የባለቤትነት መንፈስ በመፍጠር የጋራ ተልዕኮው ሊያደርገው ይገባል፡፡ ማሰብ ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ እንደተሳተፍንበት ‹‹ግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት››  በተግባር መንቀሳቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያና የአፍሪካን ታሪክ እያጠናሁ ነው ያደግሁት፡፡ የአፍሪካ ህብረት  ዛሬም በእኛ ዘመን ትልቅ ራዕይ ነው፡፡ እናም በኢትዮጵያ ቆይታዬ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበትን ህንፃ በመጎብኘቴ ልዩ ክብር ተሰምቶኛል፡፡ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቀበሉን ሰዎች ልዩ ጉብኝት አመቻችተውልን፣ በፅህፈት ቤቱ ህንፃ የሚገኙ ሁሉም በሮች እየተከፈቱ፣ ታሪኮችን ለመመልከት በቅተናል፡፡ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፅህፈት ቤት አዳራሽ ገብተን፣ በአዲስ አበባ የእያንዳንዱ አፍሪካዊ አገር ወንበርን የመመልከት እድል ማግኘቴን እንደመባረክ ቆጥሬዋለሁ፡፡ ሌላው ለመጎብኘት የበቃነው የኃይለስላሴ የመጀመርያውን ቤተ-መንግስት ነው፡፡ ለዩኒቨርስቲ በስጦታ ያበረከቱት ይህ ቤተ መንግስት ተዘዋውረን፣ የኃይለስላሴን አልባሳት፤ የተለያዩ ስራዎችን የሚያከናውኑባቸው ክፍሎች እና ሌሎችንም ንብረቶችን ተመልክተናል፡፡
ከኢትዮጵያ የተማርኩት ልዩ ቃል “ፍቅር” የሚለውን ነው፡፡ ፍቅር ሁሉን ይገዛል፤ ኢትዮጵያውያን ተዋዳዱ፤ ልዩነት አያስፈልግም ነው መልዕክቴ፡፡ ኢትዮጵያ ከ88 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች፤ ቋንቋዎችና ባህሎች በአንድነት የተዋደዱባት ውብ አገር እኮ ናት፡፡ ስለዚህም የበለጠ እንዋደድ፤ እንፋቀር፡፡ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!፡፡

-------

       ቲዎኒ  (ፈረንሳይ)

ሁሌም ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ልዩ ክብር ይሰማኛል፡፡ በኮንሰርት ላይ ለመሳተፍ የመጣሁት ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ለሚሊኒዬሙ ክብረበዓል መጥቼ፣ በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀ ኮንሰርት ላይ ተሳትፌ ነበር፡፡ ያ ልምድ በሙዚቃ ህይወቴ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የፈጠረ ነበር፡፡ በሻሸመኔ መሬት የገዛሁትም ያኔ ነበር፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የአፍሪካን መልካም ገፅታ የሚያንፀባርቅ፤ ትልቅ ትርጉምና ዋጋ ያለው ዝግጅት ነው፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ ይህን ታላቅ ዝግጅት በመጀመሩ፣ ታላቅ ክብርና ምስጋና ይገባዋል፡፡
ሬጌ ሙዚቃ ግዙፍ ቤተሰብ ነው፡፡ በግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት ላይ የሬጌ ሙዚቀኞች ከስዊዘርላንድ፤ ከጉዋድሉፕ፤ ከካሜሮን፤ከካናዳ፤ ከእንግሊዝና ከጃማይካ ተሰባስበን በመምጣት፣ በአንድ ላይ መስራታችን ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ወደፊት ሙዚቀኞች በቡድን ሆነው ወይም በብዛት መጥተው እንዲሰሩ የሚያነሳሳ ስለሆነ፣ ሁላችንንም ለሰበሰበው ራስ ኬሽ ምስጋና ይገባዋል፡፡ በምዕራብ አፍሪካ በሴኔጋልና በአይቮሪኮስት ከሚካሄዱ የሬጌ ፌስቲቫሎች የገዘፈ ዓመታዊ የሬጌ ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ይቻላል፡፡
ሁሌም እንግዳ ተቀባዩን የኢትዮጵያ ህዝብ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር፡፡

-------
             ታሻ ቲ (ካናዳ)

ወደ ኢትዮጵያ መምጣቴ ለሙዚቃ ህይወቴ እንደ ልዩ የስኬት ምእራፍ የሚቆጠር ነው፡፡ ‹‹ሪል ቶክ›› በሚለው አልበሜ ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ዘፍኛለሁ፡፡ በዚህ አልበም ውስጥ ከሚገኙ ዘፈኖች አንዱ፤ “ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የሰራሁት ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የምመጣበትን ምኞት የገለፅኩበት ነው፡፡ ‹‹ሃሌም ስላሴ›› በሚለው ሙዚቃዬ ደግሞ የኢትዮጵያን የአማርኛ ቋንቋ ፊደላት ከሀ እስከ ፐ በማነብነብ የምጫወት ሲሆን አማርኛ ቋንቋን ለማወቅ መነሻችን መሆን ያለባቸው ፊደላቱ ናቸው ብዬ በማመን የሰራሁት ነው፡፡ ሌላው ሙዚቃዬ ‹‹ኢትዮጵያን ሊብሬሽን›› በሚል ርእስ የሰራሁት ሲሆን ኢትዮጵያ  ከአምስት አመቱ የጣሊያን ወረራ ነፃነቷን የተቀዳጀችበት ቀን የሚዘክር ነው፡፡  የሚገርምህ ‹‹ሪል ቶክ›› አልበሜን ከሁለት ዓመት በፊት ለገበያ ያበቃሁት በኢትዮጵያ አርበኞች የድል ቀን ነው፡፡
ከዋናው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጰያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በፊት በዋዜማው ቀን በተካሄደውና 3500 ህፃናትና ቤተሰቦቻቸውን ባሳተፈ ውድድር ላይ ተጋብዤ ነበር፡፡ “ትምህርት የስኬት ቁልፍ ነው” በሚል ሙዚቃዬን እየተጫወትኩ፣ መልዕክቴን በማስተላለፌ ከፍተኛ ክብር ተሰምቶኛል፡፡ በተለይ ኃይሌ ገብረስላሴ ያስተላለፍኩት መልዕክት አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን በመግለፅ ሲያመሰግነኝ፣ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ነው የሆነኝ፡፡
እኔ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ  ወር ለመቆየት ወስኜ ነው፡፡ የመጣሁበትን አጋጣሚ ኮንሰርት ላይ በመስራት ብቻ ለመወሰን አልፈልግኩም፡፡ በኢትዮጵያ በሚኖረኝ ቆይታ ከምሰራቸው ኮንሰርቶች ባሻገር ትምህርት ቤቶችን የመጎብኘትና የበጎ አድራጎት ተግባራትን ለማከናወን አቅጄ ነው፡፡ በሻሸመኔ በኃይለስላሴ 87ኛ ዓመት በዓለ ሲመት መታሰቢያ ላይ ከተሳተፍኩ በኋላ በከተማዋ የሚገኘውን የራስ ተፈርያን ዴቨሎፕመንት ትምህርት ቤት ጎብኝቻለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ብራይት ስታር የተባለ ትምህርት ቤት በመገኘት፣ ከተማሪዎችና መምህራን ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ በቅቻለሁ፡፡ ወደ ባህርዳር ከተማም የ13 ሰዓታት የመኪና ጉዞ በማድረግ ከጎበኘሁት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባሻገር፣ ለዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች በተዘጋጀ ፓርቲ ልዩ ምሽት አሳልፌያለሁ፡፡ ላለፉት 6 ዓመታት “በሪድ አክሮስ ጃማይካ ፋውንዴሽን” የሙዚቃ አምባሳደርነት የሰራሁበትን ልምድ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በመጎብኘት ማስተዋወቄ አስደስቶኛል፡፡ በነበሩን ጉብኝቶች  የንባብ ፕሮግራሞች ሰርተናል፡፡ የተለያዩ መፅሃፍትና የገፅ መያዣ እልባቶችን እንደ ስጦታ አበርክተናል፡፡ በተወሰነ ደረጃ የመማርያ ቁሳቁሶች የለገስን ሲሆን ስለ ትምህርት አስፈላጊነት፤ ስለ መፅሃፍ  ንባብና ጠቀሜታ የተለያዩ መልዕክቶችና የማነቃቂያ ንግግሮችም አድርገናል። ተማሪዎች በጉብኝታችን ደስተኞች ነበሩ፡፡ ይህንንም አብረን ሙዚቃ በመጫወት ባሳለፍናቸው መርሐግብሮች ያረጋገጥነው ነው፡፡ በሙዚቃዬ “ትምህርት የስኬት ቁልፍ ነው” በማለት የማስተላልፈውን መልዕክት በአድናቆት ተቀብለውታል፡፡  
ለየትምህርት ቤቶቹ የሚያስፈልጉ እርዳታዎችን በደንብ ለመገንዘብ ስለቻልን ወደፊት በተሻለ የምንሰራበትን እድል ለመፍጠር የተነሳሳንበት ነው፡፡ በትምህርት ቤቶቹ ባደረግኳቸው ጉብኝቶች፤ ወደፊት ምን አይነት ስራዎች ማከናወን እንዳለብኝ የምረዳበትን እድል ፈጥሮልኛል፡፡
ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ ብዙ ሰው ስለ ሚያውቋቸው የሬጌ ሙዚቀኞች በተደጋጋሚ ጠይቀውኛል፡፡ “ስለ ኢትዮጵያ ብዙ   ይዘፍናሉ፤ ግን ለምን አይመጡም” እያሉ፡፡ በእኔ እምነት በግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት ላይ አራትና አምስት ሆነን ለመስራት መምጣታችን ትልቅ ምልክት ነው። ለሌሎች ሙዚቀኞችም አሁንም ጊዜው ገና ነው፤ አልዘገየም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡም በእኛ በኩል ጥረት ማድረጋችን ይቀጥላል፡፡  ለኢትዮጵያና ለህዝቧ በተሰማራንበት ሙያ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። በመላው ዓለም በተለይ በሰሜን አሜሪካ፣ በደቡብ አሜሪካና በአውሮፓ ትልልቅ የሬጌ ፌስቲቫሎች ይካሄዳሉ፡፡ እነዚህ ፌስቲቫሎች በኢትዮጵያ በተለየ ድምቀትና ግዝፈት ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ፤ የሬጌ ሙዚቃና ሙዚቀኞችን የሚያስተሳስሩ  ሁኔታዎችን መፍጠር ይቻላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለባለድርሻ አካላት የማስተላልፈው መልዕክት፤ አንድ ቤተሰብ ሆነን  ፤ በጋራ ዓላማና ግብ እንስራ  የሚል ነው፡፡   እኔ  በሙዚቃዬ የማተኩረው  ለማስተላልፈው መልዕክት ነው፡፡ ለዚህም ነው በምሰራቸው ዘፈኖች የምጠቀማቸው ግጥሞች ልዩ መልዕክት እንዲኖራቸው የማደርገው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ብዙ መልዕክቶችን የማስተላልፈውም ለዚህ ነው፡፡ ገና ስለ ኢትዮጵያ ብዙ መዝፈን፤ ብዙ መልዕክት ማስተላለፍ ይኖርብናል። ኢትዮጵያን መጎብኘት፤ ማስተዋወቅ አለብን፡፡  ኢትዮጵያ ሰላማዊ አገር ናት፤ ህዝቦቿ ውብ ናቸው። የተፈጥሮ ሃብቷ፤ መልክዓ ምድሯ፤ ባህሏ… ገና ብዙዎችን እንዲስብ መስራት እፈልጋለሁ፡፡

Read 2552 times Last modified on Monday, 04 December 2017 13:03