Saturday, 09 December 2017 12:58

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ፣ የእግር ጉዞ ይደረጋል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

“ለወንጌል እጓዛለሁ፤ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እተጋለሁ”
                  
    የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን ተሀድሶ 500ኛ ዓመትና የመካነ ኢየሱስ አለም አቀፍ ሚሲዮን ማህበር ምስረታን 10ኛ ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ፣ የትራፊክ አደጋ ላይ ያተኮረ የ5 ኪ.ሜ የእግር ጉዞ፣ ዛሬ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ ይደረጋል፡፡
“ለወንጌል እጓዛለሁ፤የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እተጋለሁ” በሚል መሪ ቃል የሚደረገው ጉዞ፤ ከፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በትብብር የሚካሄድ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋና እየባሰ በመምጣት፣ በሰው ልጅ ህይወትና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት ለመግታት የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ይሆናል በሚል አላማ ጉዞው መዘጋጀቱን የመካነ ኢየሱስ የዓለም አቀፍ ሚሲዮን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መነሻውን 22 አደባባይ ትራፊክ ጽ/ቤት አጠገብ አድርጎ፣ መድረሻውን ስታዲየም ባደረገው በዚህ ጉዞ ላይ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ የመካነ ኢየሱስና የሌሎች ወንጌላውያን ቤተ-ክርስቲያናት ምዕመናን፣ መሪዎችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በጉዞው የሚሳተፉ ሲሆን በጉዞው መነሻና መድረሻ ላይ ስለ ትራፊክ አደጋ አስከፊነት፣ አሽከርካሪውና እግረኛው ይህንን አስከፊ አደጋ ለመግታት ማድረግ በሚገባው ጥንቃቄና ተሳትፎ ዙሪያ መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አለም አቀፍ ሚሲዮን ማህበሩ በላከው መግለጫ ጨምሮ አስታውቋል፡፡

Read 2375 times