Saturday, 09 December 2017 13:02

ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ከታክስ በፊት 471.4 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

   ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባካሄደው እንቅስቃሴ፣ ከታክስ በፊት 471.4 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቆ፣ ትርፉ አምና በዚሁ ወቅት ከተገኘው ጋር ሲነፃፀር፣ የ34.8 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጿል፡፡ ለመንግሥት 122.8 ሚሊዮን ብር የትርፍ ግብር ከከፈሉ በኋላ 348.6 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ባለአክሲዮኖች ባወጡት መጠን የሚያገኙት የትርፍ ድርሻ፣ 32.8 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ፣ ዛሬ ስምንተኛ መደበኛና 4ኛ ድንገተኛ ጉባኤውን በሚሌኒየም አዳራሽ እያካሄደ ሲሆን የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን አለምሰገድ ለባለ አክሲዮኖች ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፤ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው ከ731 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር፣ የ91 በመቶ ዕድገት በማሳየት፣ 1.4 ቢሊዮን ብር መድረሱን አመልክተዋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃም አላሮ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፤ ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ውድድሩ በከበደበት በዚህ ወቅት እጅግ አመርቂ ውጤት ያሳየ መሆኑንና ይህም ይበልጥ ተግቶ ለመሥራት የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ በእርሻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ በአገር ውስጥ ንግድና ወጪ ንግድ፣ በትራንስፖርትና በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር በመሥራትና የፋይንናስ ድጋፍ በማድረግ፣ አገሪቱ እያስመዘገበች ባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም፤ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 10.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቅሰው፣ ይህ ውጤት ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር፣ የ45.8 በመቶ ብልጫ ማሳየቱንና ጠቅላላ ካፒታሉን 77.8 በመቶ ዕድገት በማሳየት፣ 1.9 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
እንዲሁም ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተቀማጭ ሂሳቡን 7.6 በመቶ በማድረሱ፣ ካለፈው ዓመት የ43.3 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አስረድተው፣ 5.4 ቢሊዮን ብር ማበደሩንና ይህም ከአምናው ውጤት ጋር ሲነፃፀር፣ የ42.1 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

Read 2165 times