Saturday, 09 December 2017 13:07

ቃናና ኢቢኤስን ጨምሮ 4 የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የመዘጋት ዕጣ ፈንታ ተጋርጦባቸዋል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(7 votes)

     · “ቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ በውጪ ዜጎች እንደሚመሩ ደርሼበታለሁ” - ብሮድካስት ባለስልጣን
            · “ጣቢያው ህጋዊውን መስመር ተከትሎ መስራት አያዳግተውም” - ኢቢኤስ
            · “ቴሌቪዥን ጣቢያዎቹን መዝጋት ወደ ኋላ መሄድ ነው” - አስተያየት ሰጪዎች
                
   የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን፤ ቃና፣ ኢቢኤስ፣ ኤልቲቪ እና ናሁ ቴሌቪዥን በሚል ስያሜ የሚታወቁት አራት የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በውጪ አገር የተቋቋሙና ኢትዮጵያዊ ዜግነት በሌላቸው ሰዎች የሚመሩ መሆናቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ሰሞኑን ለፌደራል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ የባህልና ቱሪዝምና መገናኛ ብዙኃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የመ/ቤቱን የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ነው፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ አለባቸው ያለውን ችግር የገለፀው፡፡ ጣቢያዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሰሩ፣ በኢትዮጵያውያን ቋንቋ ፕሮግራማቸውን የሚያሰራጩና ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ቢሆኑም በአገሪቱ ፈቃድ ያልተሰጣቸውና ቁጥጥር የማይደረግባቸው መሆኑ በዘፈቀደ እንዲመሩና ለአገሪቱ ስርዓትና ህጎች ተገዥ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ብሏል - ባለስልጣን መ/ቤቱ፡፡
የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ እየሰሩ ባሉበት አገር ፍቃድ ማውጣትና ህጋዊ መሆን እንደሚገባቸው በተደጋጋሚ የተነገራቸው ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠትና ወደ ህጋዊ ማዕቀፍ ለመግባት ፈቃደኛ አልሆኑም ብለዋል፡፡ ከጣቢያዎቹ መካከል በውጪ አገር ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ሰዎች የሚተዳደሩ እንደሚገኙበት ደርሰንበታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ይህንኑ ችግር አስመልክተን ጣቢያዎቹ በአገሪቱ ህግና ስርዓት መሰረት ፈቃድ እንዲያወጡና በውጪ አገር ዜጎች የሚተዳደሩትም ባለቤትነቱን ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ሰዎች እንዲያስተላልፉ ስንጠይቅ ቆይተናል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እስከ አሁን ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ የሞከረ ጣቢያ ግን የለም ብለዋል። በጣቢዎቹ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የፓርላማውንና የህዝቡን ድጋፍ አጥብቀው እንደሚፈልጉም የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝምና መገናኛ ብዙኃን ቋሚ ኮሚቴ፤ በጉዳዩ ላይ ከመከረ በኋላ ባለስልጣን መ/ቤቱ ጣቢያዎቹ ህጋዊውን መስመር ተከትለው መስራት እንዲችሉ ማድረግ እንደሚገባው ጠቁሞ፣ በጉዳዩ ላይ የህዝብ ውይይት በማድረግ ተገቢ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
የብሮድካስት ባለስልጣን፣ ጣቢያዎቹ ወደ ህጋዊ መስመርና አሰራር ካልገቡ፣ እርምጃ ለመውሰድ እንድችል የህዝቡና የፓርላማው ድጋፍ ያስፈልገኛል ማለቱን ተከትሎ የቴሌቪዥን ተመልካቾቻችን አስተያየት ለማሰባሰብ ሞክረናል፡፡
አቶ ዳዊት ተመስገን የተባሉ አንድ ጎልማሳ በሰጡት አስተያየት፤ “ጣቢያዎቹ ለአገራችን የቴሌቪዥን ተመልካች ጥሩ አማራጮችን ይዘው የመጡ ናቸው። ለረዥም አመታት በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ብቻ ተይዘን፣ ግራና ቀኝ መመልከት እንዳንችል ተደርገን ለቆየነው ለእኛ ለኢትዮጵያውያን፣ ጣቢያዎቹን መዝጋት አማራጭ ማሳጣት ነው፡፡ ወደ ኋላ መመለስም ይመስለኛል፡፡ ምናልባት ጣቢያዎቹ ለባህልና ለስነ ምግባር ተፃራሪ የሆኑ ፕሮግራሞችን ያስተላልፋሉ ከተባለ፣ እነዚህን ነገሮች ለመቆጣጠር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ማስቀመጥ እንጂ መዝጋት መፍትሔ ሊሆን አይችልም” ብለዋል፡፡
የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ቋሚ ተከታታይ ነኝ ያሉ ሌላ ግለሰብ ደግሞ ጣቢያው ደረጃቸውን የጠበቁ ልዩ ልዩ አስተማሪና አዝናኝ ፕሮግራሞችን እያዘጋጀ፣ ለህብረተሰቡ የሚያቀርብ፣ ለሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም እንደ ማሳያ ሊጠቀስ የሚችል በመሆኑ ፈፅሞ ሊዘጋ አይገባም” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ ፅሁፍ ክፍል መምህር የሆኑ ሌላ ተመልካች በበኩላቸው፤ “ጣቢያዎቹ በተለይም ቃና አገሪቱን የቱርክና የብራዚል ባህልና አስቀያሚ ስነ ምግባር ማራገፊያ ከማድረግ የዘለለ አንዳችም ለህብረተሰቡ የሚጠቅም ፋይዳ የሌለው በመሆኑ ሊዘጋ ይገባዋል፤ ባለስልጣን መ/ቤቱ በዚህ ጣቢያ ላይ ሊወሰድ የሚገባውን እርምጃ እንደውም አዘግይቶታል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አንድ የባህል ኤክስፐርት ደግሞ ከብዙዎች የተለየ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ “እነዚህን ጣቢያዎች መዝጋቱም ሆነ መክፈቱ ቀድሞውኑም የአስተዳደርና የአሰራር ጉዳይ እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም፡፡ ህዝብና ፓርላማ መጠየቅ አያስፈልገውም፡፡ ምናልባት ፖለቲካዊ ፍላጎት ከሌለ በስተቀር!” ብለዋል - ኤክስፐርቱ፡፡
በፒያሳ፣ ካዛንቺስና ሃያ ሁለት አካባቢ እየተዘዋወርን ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች፤ “እነዚህ ጣቢያዎች ፈቃድ ሳይኖራቸው ነው የሚሰሩት ከተባለ፣ እስከ አሁን እንዴት ሳይዘጉ ቀሩ? እንኳንስ ሚዲያን ያህል ትልቅ ተቋም፣ አንድ ትንሽ ንግድ የሚሰራ ሰው ወይም መንገድ ላይ ቡና አፍልታ የምትሸጥ ሴት፣ ፈቃድ የለሽም ተብላ ሱቋ ይታሸግባት የለ? ጣቢያዎቹ እስከ አሁን ያለ ፈቃድ ሲሰሩ የቆዩ ከሆነ፣ ተጠያቂ መሆን ያለበት ፈቃድ ሰጪው አካል ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡  
የኢቢኤስ በኢትዮጵያ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አማን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከአዲስ አድማስ ተጠይቀው፤ “ኢቢኤስ በውጪ አገር የተቋቋመና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ባለሃብቶች የሚተዳደር ጣቢያ ሲሆን ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የብቃት ማረጋገጫ ያለውና ጣቢያው ላሉት የክሮስፖንዳንስ ሠራተኞች፣ ከፌደራል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት እውቅናና መታወቂያ በተሰጣቸው ጋዜጠኞች ሥራውን በመሥራት ላይ ነው” ብለዋል፡፡ ጣቢያው በርካታ ተመልካቾችን ያፈራና ደረጃቸውን የጠበቁ ፕሮግራሞችን በመሥራት ከፍተኛ ስምና ተቀባይነትን ያገኘ በመሆኑ፣ የብሮድካስት ባለስልጣን በሚያወጣው አሠራርና ስርዓት መሰረት፣ ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ ለመስራት እንደሚችል፣ ለዚህም ከማኔጅመንቱ ጋር እየተወያዩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጣቢያው ይዘጋል የሚለው ግን ከእውነት የራቀና ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል-አቶ አማን፡፡  
የቃና ቴሌቪዥን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሀይሉ ተክለሀይማኖት በበኩላቸው፤ ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በጉዳዩ ላይ እየተወያዩ መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የLTV የአስተዳደር ሀላፊ አቶ መስፍን ብሩ ደግሞ፤ ገና ቴሌቪዥኑ ሲከፈት ጀምሮ ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር ሲነጋገሩ እንደነበርና ጣቢያቸው ህግን ተከትሎ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ አሁን ባለስልጣኑ ባነሳው ሀሳብ ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑንና ከውይይቱ በኋላ ያለውን ጉዳይ ግልፅ እንደሚያደርጉ ሃላፊው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

Read 10670 times