Saturday, 09 December 2017 13:36

የጦርነት “ባለሞያው” መጽሐፍ ሲቃኝ

Written by 
Rate this item
(8 votes)


        “--የዚህ ጦርነት “ባለሞያው” ናቸው ስንል፣ እንዲኹ ከሜዳው ተነስተን አይደለም፡፡ ጥላሁን ይጽፋሉ፤ ከጻፉም ሌላ ጉዳይ የላቸውም- ይኼው የኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት ብቻ!---”

    ርእስ- የኢትዮጵያና የጣሊያን ሁለተኛው ጦርነት ታሪክ
ደራሲ- ጥላሁን ጣሰው
የህትመት ዘመን -  2009 ዓ.ም
ገጽ- 209
ዋጋ- ብር 82.00  ($25.00)
ዳሰሳ፡- ሰሎሞን አበበ ቸኮል
ስለ ኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት የትኛውንም ዓይነት መጽሐፍ ያነበበም፣ የትኛውንም ያህል የተማረውና የተመራመረውም ቢኾን፣ ይህን የጥላሁን ጣሰውን መጽሐፍ ካላነበበ፣ የተሟላ ወይም የተፈፀመ ግንዛቤ ሊኖረው አይችልም፡፡ ሌላው ቢቀር፣ “የጦርነቱ ጠቅላይ አዛዥ” ስለነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከጦርነቱ ጋር ያላቸውን የታወቀ ስም ፈጽሞ የሚቀይረው ነው፡፡ ይህ የጥላሁን ጣሰው የጦርነቱ ታሪክ መጽሐፍ ዕድለ ቢሱን ንጉሠ ነገሥት፣ ታላላቅ ጦርነቶችን በሚገባ ከመሩ የጦር መሪዎች እንደ አንዱ ይቆጥራቸዋል፡፡ እስከ ማይጨው ውሎአቸው ድረስ፣ ከዚያም በስደት ላይ ሳሉም የጦር መሪም ነበሩ፡፡ እንዲያውም፣ ይህ “ኹለተኛው” የተባለው የኢትዮጵያ ጣሊያን ጦርነት ታሪክ ተከታይ ዒላማውም፣ ይኼው የንጉሠ ነገሥቱ የጦር ምሪት ታሪክ ነው ሊባል ይችላል፡፡
ወልወል ላይ በ1927፣ ኅዳር 27 ቀን ድንገት በፈጸመችው ድብደባ፣ ጣሊያን “በይፋ ሳታሳውቅ” የከፈተችው የዚህ ጦርነት “ዓዋቂ” ወይም “ተጠያቂ” (ኤክስፐርት) ሊባሉ የሚበቁት ጥላሁን ጣሰው፤ የጦርነቱን ሙሉ ታሪክ ከእነ ትንታኔው፣ በ11 ምዕራፎች፣ ከ200 እምብዛም በማይጨምሩ ገጾች ክሽን አድርገው አቅርበውታል፡፡ በ1975 ዓ.ም በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የታተመ፣ “አዳባይ” የተባለ በዚኹ ጦርነት ላይ የተደረገ ረዥም የውጊያ ታሪካዊ ልብ ወለድ ጽፈዋል፡፡ “ትራይንግ ታይምስ” እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1911፣ በሻማ ቡክስ የታተመላቸው፣ ሌላው “የኹለተኛው ኢታሎ- ኢትዮጵያን” ጦርነት ልብወለድ መጽሐፋቸው ነው፡፡ ከዚህ ጦርነት ማግስት የነበረችውን ኢትዮጵያ፣ የኒዮ ፋሽስቶች መነሳትና መውደቅ፣ አብዮታውያኑንና ደርጋዊውያኑን የተመለከተ ታሪክን “ፎር ላቭ፡ ሎያሊቲ ፍሪደም ኤንድ ዲግኒቲ” በሚል ርእስ የጻፉም ናቸው፡፡ ከዚህ አርበኝነት ቀጥሎ ስለነበረው የ50ዎቹና 60ዎቹ ኢትዮጵያ ኹኔታ “ፍትሕና ርትዕ” የተባለ ሥራ በአማዞን አሳትመዋል፡፡
ከእነዚህም በተጨማሪ፣ በተለይ በ”ሪፖርተር” ጋዜጣ በዚሁ ጦርነት ላይ የተለያዩ ጽሑፎችን በአማርኛና በእንግሊዝኛ አቅርበዋል፡፡ “ኢትዮጵያን ኬዝ ኦፍ ዎር ክራይምስ አጌይንስት ሙሶሊኒ፣ ባደግሊዮ፣ ግራዝያኒ” (ሪፖ፣ ሴፕቴ፣ 2012)፤  እና “ዲፋይኒንግ ካራክተርስቲክስ ኦፍ ዘ ሰከንድ ኢትዮ - ኢታሊያን ዎር” (አፕ. 28፣ 2012) በኹለቱም የቀረበ ጽሑፎቻቸው ናቸው፡፡
የዚህ ጦርነት “ባለሞያው” ናቸው ስንል፣ እንዲኹ ከሜዳው ተነስተን አይደለም፡፡ ጥላሁን ይጽፋሉ፤ ከጻፉም ሌላ ጉዳይ የላቸውም- ይኼው የኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት ብቻ! ይህ መጽሐፍ ለጦርነቱ “የኢትዮጵያና የጣሊያን ኹለተኛው ጦርነት” የሚል መጠርያን ሰጥቶታል፡፡ ጦርነቱን “ከአድዋው ጦርነት” ለይቶ ለመጥራት “የማይጨው ጦርነት” ሲባል የኖረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጦርነቱ ማይጨው ላይ ብቻ የተደረገ ሊያስመስለው ችሏል፡፡ ስለዚህ “ኹለተኛው የኢትዮጵያ- ጣሊያን ጦርነት ጥሩ መለያ ነው፡፡ ግልጽም ነው፤ በ1888 የተደረገው ጦርነት አንደኛ፣ ከ1927 እስከ 1933 ድረስ የነበረው ይኸኛው ደግሞ ኹለተኛው፡፡
ነገር ግን እንዲህ በቁጥር ሲለይ አብሮ መታየት የሚገባው ሌሎች ጦርነቶች የነበሩ መኾኑን ማሳጣት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ከሮማውያን ጋር ያደረገቻቸውን ጦርነቶች ምሁራዊው ዓለም ባያጤነውም  ከእነአካቴው እንዳልተፈጸሙና የሌሉ አድርጎ ቢተዋቸውም፣ ለዘላለሙ እንዳይቆፈርና እንዳይወጣ፤ ራሱን የቻለ ተጨማሪ አትሞ መዝጊያ እስካልኾነ ድረስ ይህ ስያሜ አያነጋግርም፡፡ (ሮማ ዓለምን በመላ በመያዝ የዓለማቱ ኃያል መንግሥት በነበረችባቸው የጥንት ዘመኖቿ ውስጥ፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተዋግታለች፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ምሑራንና ተመራማሪዎች ጽሑፍ በሚቀርብበት የአካዳሚክ ዶት ኢዲዩ (Academic.edu) መካነ ድር፤ እንዲኹም፣ የጥንት ክት ሥራዎች መጽሔት በኾነው በኮሎራዶው ዩኒቨርሲቲ ክላሲክ አንቲክ ጆርናል በፈረንጆች 2013፣ በዲ-ሴልደን (ፕሮፌሰር) የቀረበው “ሃው ዘ ኢትዮጵያን ቼንጅ ሂዝ ስኪን” የተባለው የምርምር ሥራ ይህንኑ ይጠቁማል፡፡ “በግብፅ ፈርዖናዊ እና ከሮማዊው ወረራና ጥቃት” ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ጠብቀው፣ የደረሱባቸውን መክተው እያጠቁና እየረቱ የኖሩ መኾናቸውን ሲገልፅ በራሱ በቄሳር አውግስጦስ “ጌስቴው” ሳይቀር የተጠቀሰ ውጊያ እንደነበረ ይጠቁማል፡፡ በእንደነ ፕሊኒ ዓይነቱ የሮማን ዘመን ታሪክና መልክዓ ምድር ጸሐፊዎችም ያነሳሱት እንደኾነ ይገልጻል፡፡
በሌላ በኩል፣ አሜሪትስ- አንድ ዐይናዋ ሕንደኬ ታሪክ ላይም የሮማን ቄሳራዊ ጦር መግጠምዋ፣ የሮማን አዛዦች ሳይቀር እንዳስደነቀች ይነገራል፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ተለቅመው በዘመን ቅደም ተከተል ቢደረደሩ ኢትዮጵያ ከሮም/ ጣሊያን ጋር ኹለቴ ብቻ በጦር ሜዳ እንዳልተሰለፈች ያሳውቃሉ፡፡ ከኹሉም በላይ፣ እነዚህን ታላላቅና ታናናሽ ዓውደ ውጊያዎች የሚገልጹት ግን የኢትዮጵያ የታሪክ ትውፊቶች ናቸው፡፡ በጥንቲቱ የንግሥና ሥርዓት መንግሥት መፈጸሚያ ከተማ፣ ከፓታ የተገኙት የኑቢያ ሠነዶች ይህን በየዘመኑ አቅርበዋል፡፡ እነዚህም በሌሎች የታሪክና አርኬዎሎጂዎች ግኝት ሊረጋገጡ የሚችሉ ናቸው፡፡ እንግዲህ እነዚያን ጦርነቶች ለዘላለሙ ድፍንፍን አድርጎ በማተም የሚያጠፋቸው እስካልኾነ ድረስ “ኹለተኛ” መባሉ አይከፋም፡፡ (ሮማንና ኢጣሊያን አንለይም ካልተባለ፡፡)
*    *    *
መጽሐፉ ከጦርነቱ አስቀድሞ የነበረውን የኢትዮጵያ የዓለም አጠቃላይ ኹኔታ፣ በተለይም የኢትዮ-ጣሊያንን ጨምሮ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ጋር የሚሰናሰሉ ጉዳዮችን በመግለጥ ይጀምራል፡፡ በቀዳሚው ምዕራፍ አርበኛና አርበኝነት የተባሉትን ቃሎችና ጽንሰ ሐሳቦች በመፍታትና በመተርጎም መጀመሩ የመጽሐፉን ጥልቀት ገና ከወዲሁ ያመለክተናል፡፡ በየዘመኑና  በየፖለቲካዊ ፍላጎት እነዚህ ቃላት ልዩ ልዩ ኮነው ይያዛሉ፡፡ ከነበረው ብሔራዊ (ሀገራዊ) ትውፊት የወጣ አዲስ ዜግነት ለመፍጠር አስፈላጊ ኾኖ በተጀመረው የ“ሲቪክስ” ትምህርት “(ለማንኛውም ነገር) የሚኖር አለቅጥ የበዛ ፍቅር” ተብሎ የተፈታው አርበኝነት፤ በጦርነቱ ወቅት ለጣልያኖቹ ሽፍትነት ነበረ፡፡ “ከ1966 ዓመጽ (አብዮት) በኋላ ደግሞ ከደፈጣ ውጊያ ጋር” እንደተተነተነ በመጠቆም፣ እንደምን ኾኖ የታሪኩን ግንዛቤያችንን ሊያስለውጥ እንደቻለ ያስረዳል፡፡
“የአርበኝነቱ ጦርነት ያለ መንግሥት መሪነት፣ ሕዝብ በየመንደሩ እየተሰበሰበ ያካሔደው ዓመጽ ተደርጎ ተተርጉሟል፡፡ የግራ ዘመም ኮሚኒስት አብዮተኞች በቬትናም በኋላም በእነቼጎቬራ ከተካሔዱ ዓመጾች ጋር በማመሳሰል ለመተርጎም ሞክረዋል፡፡” (ገጽ 22)
“ለሀገር ህልውና፣ ለሥርዓት፣ ለኑሮው ዘይቤ የሚደረገውን” ጦርነት በዚያ ዘመን ሠርጾ ከነበረ ፀረ ቅኝ አገዛዝና ፀረ ፋሽስት እንዲኹም በየሀገሩ ከነበረው ከጨቋኝና ተራማጅ ካልተባሉ ገዥዎች ጋር ኹሉ ያለ የቅዋሜ ስሜትና ትግል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህን የመሰለ “አብዮታዊ አተረጓጎም” መስጠቱ የነበረውን የአርበኝነት እንቅስቃሴ ጣሊያኖች ይከራከሩበት ከነበረው ሐሳብ ጋር ሠምሮ እስከመገኘት ድረስ አድርሷል፡፡ በአምስት ዓመቱ ውስጥም፤ በኢትዮጵያ የጣሊያን አስተዳደር በከተሞችና ጥቂት መንደሮች ላይ ብቻ ካልኾነ በሰፊው የሀገሪቱ ክፍል ፈጽሞ ያልሠፈነ እንደነበረ ከሚገለጸው ጋር የሚጣላና ጣሊያንም በዓለም ዓቀፍ መድረክ ትሟገትበት በነበረው አገነዛዘብ ተስተካክሎ እስከ መገኘት ድረስ የሚታይ አተረጓጎም ይኾናል፡፡ ይልቁንም፣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ይህን ቃል/ ጽንሰ ሐሳብ የመግለጹ አላስፈላጊነት የሚታየው የንጉሠ ነገሥቱን አርበኝነት ለመናገርም ማስቻሉ ነው፡፡
ይኼው ጦርነት በአርበኝነት ውስጥ ኹለት የአርበኝነት ዓይነቶች የተፈጠሩበትና የታዩበት መኾኑንም፣ “የጦርነቱ ሒደት የፈጠራቸው አዳዲስ ጽንሰ ሐሳቦች” በሚለው ንዑስ ርእስ ሥር ይቆጠራሉ። ቀድሞም ከነበረው “ተጋዳይ አርበኛ” ሌላ “የውስጥ አርበኛ” እና “የስደት ተሟጋች አርበኛ” የተባሉ የአርበኝነት ዓይነቶችን ይጠቅሳሉ - ጸሐፊው፡፡
በኢትዮጵያውን ዘንድ የነበረው “ወራሪዎችን የመዋጋትና የመቋቋም ልምድ ቻይናውያን እንዲቀስሙ” ማኦሴቱንግ ሕዝባቸውን ወይም ሕዝባዊ ቀይ ጦራቸውን ሲመክሩ እንደነበረም በዚኹ መጽሐፍ ውስጥ እናገኛለን። ከጦርነቱ ቀደም ብሎ የነበረው የዓለም ኹኔታ ተብለው የሚገለጹት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው የየመንግሥታቱ አወጋገን፣ ከዚያ ጦርነት በኋላ የተፈጠረው የዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን” ይባል የነበረው) እና አሠራሩ የመሳሰሉት ኹሉ ከዚኹ ጦርነት ጋር የሚያያዙበት ስላላቸው ነው፡፡ ይልቁንም ደግሞ፣ ጦርነቱ በኋላ በየሀገራቱ መንግሥታት (በአሸናፊውና በተሸናፊው) ይደረጉ የነበሩት ውሎችና አፈጻጸማቸው ላይ እንደ መሠረተ ሐሳብ የተያዙት፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰን እና የሶቭየት ኅብረቱ ቭላድሚር ኢልይች ሌኒን “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን” እሳቤዎች፣ ከጦርነቱ በፊት የኢትዮጵያን መንግሥት ማዳከምያ ፕሮፓጋንዳ ኾኖ እንደቆየ፣ ጥላሁን ይገልጹልናል፡፡
ይህን እሳቤ የኹለቱ ሀገር መሪዎች ከተለያየ ጥያቄና መነሻ ፍላጎታቸው የተነሳ ነበር ያቀነቀኗቸው። በአንደኛው ዓለም ጦርነት ወቅት አሜሪካ በዓለም ላይ ልቃና በልጽጋ ብቅ ያለችበት ጊዜ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜዋ አውሮፓ በጦርነትና በአብዮቶች ትተረማመስ ነበር። የመጀመርያው የዓለም ጦርነት ፍትሐዊ መርሕ ላይ በተመሠረተ ስምምነት ጦርነቱ እንዲዘጋ ሩስያ ጥሪ አደረገች፡፡ ይህንን በመያዝ፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ድሮው ዊልሰን “በአውሮፓ የተያዙት ግዛቶችን ቅድሚያ ከአውሮፓውያን እጅ ውጭ ማድረግ ስላለባቸው” አጋርነታቸውን በነፃነት ቢወስኑ ለአሜሪካ ወዳጅ ይኾናሉ በማለት “የራስን ዕድል በራስ” አለ፤ የሩስያው ሌኒናዊ ኮሚኒዝም “ዓለም የወዛደሮች ትኾናለች” በሚል ሕልም (ወታደራዊ ዓለም አቀፋዊነት) በአንድ ኮሚዩኒስታዊ ፓርቲ ሥር በማደራጀት የጀመረውን አብዮት በመላው ዓለም ለማድረስ ሲል፣ “የብሔር ጥያቄ” የሚል መፍትሔ ይዞ ተነሳ፡፡ (በኹለተኛው የዓለም ጦርነት ዘመን የነበረችው ሶቭየት ኅብረት በሩሲያ ዙርያ ያሉ ሀገሮችን በኅብረቱ ውስጥ ለመቀላቀል ሲል ስታሊን አጥብቆ ያቀነቅነው ስለነበረ ብዙውን ጊዜ ይህ “የብሔር ጥያቄ” የተባለው ሐሳብ፤ ከእርሱ ጋር ተያይዞ፣በተለይ በኛይቱ ሀገር ሲገለጽና ሲተነተን እናገኘዋለን፡፡)
*     *     *
ስለ ጦርነቱ ጠቅላይ አዛዥ ስለ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያለውን ከጦርነቱ ጋር የተያያዘ ግንዛቤ እናውቀዋለን፡፡ “ማይጨው ላይ አንድ መድፍ ተደግፎ ፎቶ ተነሳ” ይላሉ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም፡፡ ከዚያ ሸሽተው፣ በስደት እንግሊዝ ቆዩ፤ ከአምስት ዓመት በኋላ በኦሜድላ በበላያ በኩል አድርገው፣ ሚያዝያ 27ቀን 1933 አዲስ አበባ ገቡ፡፡ እሳቸው የገቡበት ቀንም የነፃነት ቀን ተብሎ ይከበራል፡፡
ይህ ነው እንግዲህ በትንሽ ትልቁ የሚታወቀው የንጉሠ ነገሥቱ የጦርነት ታሪክ፡፡ ብዙ ታሪኮችም፣ የታሪክ መምህራንና ጸሐፊዎችም የሚያጎሉት ጉዳይ ነው። የጥላሁን ጣሰው የጦርነቱ ታሪክ ውስጥ ግን የንጉሠ ነገሥቱ ታላቅ የጦር መሪነት በተጨባጭ ጎልቶ ይታያል። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን እንደ ጠቅላይ አዛዥ የጦር መሪ ለመመልከትና ለመያዝ ያልተቻለበትን ምክንያት ሲያስቡት በውኑ ራስን በጥያቄ ማዕበል ማንገላታት ብቻ ነው የሚተርፈው፡፡ ግራ አጋቢ ነው! ይህ መጽሐፍ ነው እንዲህ ባለ ጥያቄ ውስጥም የሚያስገባዎት! ንጉሠ ነገሥቱ በእርግጥም የዚያ ጦርነት ጠቅላይ አዛዥ ነበሩ፡፡ ይህን ጦርነት ከአዲስ አበባ ሳይነሱ ጀምሮ፣ ማይጨው ላይም የጦርነቱ መሪ ወይም የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ እንደነበሩ የሚያዩበት መጽሐፍ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ውጭ ከወጡ በኋላ በየገጠሩ፣ በየቀበሌው፣ በየጎበዝ አለቃው እየተሰባሰበ በያለበት በእንቢተኝነት እንዲተጋተግ ለማሳመን የባተሉት ጣሊያኖች እንደነበሩ በማስረጃ አስደግፈው ያቀርቡልናል፡፡ ንጉሡ ሸሽቶ ፈረጠጠ ማስባሉም ቢኾን የጣሊያኖች መቀስቀሻ እንደነበረ ተወስቷል፡፡ እነዚህኑ በመቀበል ይዘን እንደኖርንም ጭምር፡፡
በዚህ በመጨረሻው የኢትዮ ጣሊያን ጦርነት፣ በየትኛውም ጦርነት ያልተገኘ ጥቅምና ውጤት ለኢትዮጵያ እንደተገኘም ነው ጥላሁን የጻፉት፡፡ መልካም ውጤቶች ያሏቸውንም ይቆጥሩልናል፡-
“ከመረብ ወዲህና ወዲያ ማዶ” ተለያይተው የነበሩት ሕዝቦቿ ተዋሃዱ፤የኤርትራና የቀሪው ኢትዮጵያ ጸረ ፋሺስት ታጋዮች በኀብረት ቆሙ፤
ኢትዮጵያ ትመኝ የነበረውን የባህር በር ባለቤትነት አሳካች፤
በሺ ኪ. ሜትር የሚቆጠር የባሕር ጠረፍ ድንበር ባለቤት ኾነች፡፡ (ገጽ 14)
ከነዚህም ሌላ ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ ኢትዮጵያ የተባበሩ መንግሥታት ድርጅትን ለመመሥረት ከበቁት ሀገሮች አንደኛዋ ኾናለች፡፡ የአፍሪካ ነፃነት እውን እንዲኾንም የጦርነቱ ውጤት ግፊት አድርጓል፡፡ (ገጽ 14)
የጥላሁን ጣሰው የጦርነቱ ታሪክ መጽሐፍ ከሚተርክልን በተጨማሪ የዚህን የጦርነት ታሪክ ዘመን፣ ከኅዳር 27 ቀን 1927 ዓ.ም ጀምሮ፣ ከጦርነቱ በኋላ በ1934 ዓ.ም ጥር 23 ከእንግሊዝ መንግስት ጋር የስምምነት ውል እስከተፈረመበት ዕለት ድረስ ያሉትን፣ በዓመት፣ ወርና ቀን ቅደም ተከተል የደረደረልንም መጽሐፍ ነው፡፡ በወቅቱ ፖለቲካዊ ካርቱን ያቀርብ የነበረው ዴቪድ ሎው፣ በሞሶሊኒና በሊጉ ይዘብትባቸው የነበሩትን ጨምሮ በርካታ ፎቶዎችም ተካትተውበታል። ብዙውን ጊዜ በመሰል ታሪክ ጸሐፊዎች (በአማርኛ) ዘንድ የማያጋጥመን የፊደል ተራ ማውጫም ያለው መጽሐፍ ነው፡፡
በአጠቃላይ ስለ ጦርነቱ እስከ ዛሬ ብዙ መጻሕፍት የቀረቡልን ቢመስልም፣ በተሟላ መጠን የቀረበበት ግን ይሄው የጥላሁን ጣሰው መጽሀፍ ነው ብለን ለመናገር ያስደፍረናል፡፡ ራሳቸው አስቀድመው እንደገለጹትም፤ስለ ጦርነቱ ለታሪክ ተመራማሪዎችና መርማሪዎችም ብሔራዊ አተረጓጎም እስከ መሆን ድረስ የበቃ ነው፡፡

Read 2612 times