Sunday, 10 December 2017 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)

“ያንተ ነፃነት የሚያበቃው የሌላው ሰው አፍንጫ መጀመርያ ላይ ነው”
               
   ሶስት የስለት ዳቦዎች ለቤተ እምነቱ ተበረከቱ፡፡ ስርዓተ ፀሎቱ እንዳበቃ አባ ትልቁን ዳቦ አንስተው “ምዕመን ሆይ፤ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዜርን ደግሞ ለእግዜር ተብሎ የተፃፈውን ታስታውሳላችሁ?” … ሲሉ ጠየቁ
“አዎ” አለ፤ ምዕመኑ፡፡
“እንግዲያውስ ለቃሉ ክብር ይሆን ዘንድ ይህ ህብስት የአምላካችን ድርሻ ነው” … አሉ … አባ፡፡ ሕብስቱንም ከመሶቡ ውስጥ አኖሩት፡፡ … ሁለተኛውን ዳቦ አነሱና … “ይህ ደግሞ የአገልጋዩና የወኪሉ የኔ ድርሻ ነው፡፡ … አይደለምን?”… በማለት ጠየቁ እንደገና፡፡
 ምዕመኑም… “ይገባዎታል” በማለት አረጋገጠላቸው፡፡ እሱንም ከመሶቡ ጨመሩት። … “ይኸኛው ደግሞ” … አሉ አባ፤ ሰባተኛውን ዳቦ አንስተው “ቆርሰን እንዳንቃመሰው ያንሰናል፡፡ ስለዚህ አሻማውና ዕድል የባረከለት ይውሰደው” አሉ፡፡
ምዕመኑም “ደግ ነው” … በማለት ብድግ አለ፡፡ … አባም ዳቦውን ትንሽ ከግንባራቸው ከፍ አድርገው “ሻሞ!” … በማለት ወደ ላይ ወረወሩና በዛው ቅጽበት ቅልብ በማድረግ፤ “እኔ ቀደምኩ!” አሉ፡፡
… አባ ሶስቱንም ዳቦዎች አታለው ወሰዱ፡፡ … ይህን ቀልድ ሳስታውስ … “ማንን እንመን?” … እያልኩ አስባለሁ፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በመንግስት ቴሌቪዥን ቀርበው እጃቸውን እያሳዩ … “ሙሰኛ ጣቱ ይቆረጣል፣ ሙሰኛ ወየውለት” … እያሉ አስፈራርተው ትንሽ እንኳ ሳይሰነብቱ እሳቸው ራሳቸውን “ዋናው ሙሰኛ በቁጥጥር ስር ዋለ” … በማለት ያው ጉደኛ ቴሌቪዥን፤ ጓዳቸውን እየበረበረ አጋለጣቸው፡፡ … ታዲያ ማንን እንመን?
ሰሞኑን ደግሞ አራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች “አታለዋል፣ የአገሪቱን ህግ በጣሰ መንገድ ነው የተቋቋሙት” ተብሎ ሲነገር አዳምጠናል፡፡ .. እና የማን ነው ጥፋቱ? … ማንን እንመን?
ወዳጄ፤ የሃይማኖት ድርጅቶች ያታልሉናል፣ የእርዳታ ድርጅቶች ያታልሉናል፣ ጠንቋይ ያታልለናል፣ ማስታወቂያ ያታልለናል፣ ፌስ ቡክ ያታልለናል፣ ደላላ ያታልለናል፣ ነጋዴ ያታልለናል፣ ፖለቲከኞች ያታልሉናል፡፡ … ማንን እመን?
ግሪክ አካባቢ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ የነበሩ መነኮሳት እርስ በርሳቸው እየተጣሉ፣ መከባበርና መተጋገዝ አቃታቸው፡፡ የገዳሙ ግቢ በሀሜትና በንትርክ ተበከለ፡፡ የገዳሙ አለቃ መነኮሳቱን ሰብስበው ጉዳዩ ያሳሰባቸው መሆኑን ከገለፁላቸው በኋላ፤ “ምንድነው ችግራችሁ?” ብለው ቢጠይቋቸው፣ ማንም ደፍሮ መናገር አልፈቀደም፡፡ … ዝም፣ ጭጭ ብቻ ሆነ፡፡ ለሰዓታት ተፋጠው ቆይተው ተበተኑ፡፡ … ሲውል ሲያድር መናቆሩ እየባሰበት መጣ፡፡ … አለቃ አሁንም ሰበሰቧቸውና ምክንያታቸውን በድጋሚ ጠየቁ። ምንም ፍንጭ አልተገኘም፡፡ … “ምናልባት” አሉና አለቃ፤ “ያ .. ከይሲ ገብቶብን ይሆን እንዴ?” በማለት እንደ ሀሳብም፣ እንደ ጥያቄም ሲያቀርቡ መነኮሳቱ ባንድነት፡- “ቢሆን ነው፣ እሱ ነው እንዲህ የሚያደርገው” በማለት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ፡፡ ችግሩ በመታወቁም ደስ ብሏቸው አጨበጨቡ፡፡ በሚያስቀና ትብብር ግቢያቸውን በዕጣን፣ በከርቤና በዕፅ አጠኑት፣ ፀበል ተረጨ፡፡ ከይሲው ሁለተኛ ዝር እንዳይል ታስቦ የአጥራቸው ቀዳዳዎች ሁሉ ተደፈኑ፡፡ … ይህ በሆነ በጥቂት ቀናት ውስጥ ግን አለመግባባቱና መቃረኑ እንደገና አገረሸ፡፡ አለቃም መነኮሳቱን መልሰው በመሰብሰብ፤ “ርኩስ መንፈስ ቢኖር ኖሮ፣ ግቢው ሲታጠንና ፀበል ሲረጭበት ይሸሽ ነበር፣ ስለዚህ በአንዳችሁ ተመስሎ በመሃላችን የሚኖር ሰይጣን አለ፡፡ መፍትሄው እርስ በራሳችሁ በዓይነ ቁራኛ መጠባበቅ ነው፡፡ ከወትሮው ለየት ያለ እንቅስቃሴ የሚያደርግ መነኩሴ ከተገኘ፣ ለኔ በሚስጢር አሳውቁኝ” በማለት መክረው አሰናበቷቸው፡፡ …
ከዛን ቀን በኋላ እያንዳንዱ መነኩሴ፣ የራሱን ንፅህና ለማሳየት ሲል ሌላውን “እሱ ይመስለኛል፣ እሱን እጠረጥረዋለሁ” እያለ እርስ በራሱ መወነጃጀልን ስራ አደረገው፡፡ ጠቡ እየተካረረም ሄዶ፣ በዱላ መደባደብና መፈነካከት ቀጠለ፡፡ እያለ … እያለ ግቢው ወደ ገሃነምነት ተቀየረ፡፡ አንዳንዶቹ እንደማይሆን ሆነው አለፉ፡፡ ብዙዎቹ ተሰደዱ፡፡
የገዳሙ አለቃና ጥቂት ወዳጆቻቸው ብቻ ቀሩ፡፡ … አለቃም አለቃ ነበራቸውና፤ ስልካቸውን አንስተው በግሪክኛ .. “አለቀ! ደቀቀ!” …( Mission accomplished!!) አሉ፤ እየሳቁ፡፡ ለካስ “ሰይጣኑ” እሳቸው ራሳቸው ነበሩ፡፡ … ይኸስ ቢሆን… ማንን እንመን አያሰኝም?
ወዳጄ! ግሪክን ካነሳን አይቀር ታላቁን ደራሲ ኒኮላስ ካዛንቲዚያኪስ እናስታውስ፡፡ ሰውየው ብዙ የሚያስገርሙ መጽሃፍቶችን ፅፏል፡፡ ለጥቂት ጊዜም የመንግስቱ ሚኒስትር በመሆንም አገልግሏል፡፡ ከመጽሐፍቶቹ አንደኛው “የክርስቶስ ፈተና” … (The last Temptation of Christ) የተባለው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጥቁር መዝገብ (Black list) ውስጥ የሰፈረ ነው፡፡ ይህ መጽሃፍ ማርቲን ስኮርሲስ በተባለ ታዋቂ የፊልም አምራችና ዳይሬክተር መሪነት ወደ ሲኒማ እየተቀየረ በነበረበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ ተፅዕኖዋን በመጠቀም ለማሳገድ ሞክራ ነበር፡፡ … ነገር ግን የሌሎችን መብት መንካትና ስልጣኔን መጋፋት ስለመሰላት ተወችው፡፡
በነገራችን ላይ ደራሲ ሳልማን ሩሽቲ “ሳታኒክ ቨርስስ” (Satanic Verses) የተባለውን መጽሃፍ በማሳተሙ፣ የኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላ ሆሚኒ “በተገኘበት ይገደል” ብለው የሞት ፍርድ ሲያውጁበት ሌላው ዓለም “ኒኮላስ ካዛንቲዚያኪስ የክርስቶስ ፈተናን የመሰለ መጽሃፍ በመፃፉ ምንም የደረሰበት ነገር የለም፡፡ ሳልማን ሩሽቲ ተረት ስለነገረን እስልምናን አንኳሰሃል ተብሎ ሞት የሚታወጅበት ምክንያት ተገቢ አይደለም፡፡” በማለት ፍርዱን “ከድንቁርና የመነጨ” ነው በማለት አውግዞታል፡፡
በዚህ “የክርስቶስ ፈተና” በተሰኘው ፊልም ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሚስት አግብቶና ልጆች ወልዶ ሲኖር ይታያል፡፡ ብዙ ጊዜ ተለይቶት የነበረው ጓደኛው ይሁዳ፣ ቤቱን ፈልጎ በመምጣት ያገኘውና … “እዚህ ምን ታደርጋለህ? … ያንተ ቦታ መስቀል ላይ ነው” (Your place is on the cross) በማለት ምፀት ባለው ቃና ይናገረዋል፡፡
ወዳጄ፤ የመልካምነት ዋጋ መቸንከር ሲሆን ሊያሳዝነን ይገባል፡፡ አለቃችን፣ የነፍስ አባታችን፣ ኢማማችንም ሆኑ ማንም ስህተት የሆነውን፣ ሚዛናዊነት የጎደለውን፣ ከስሜት ብቻ የሚመነጭን ነገር “ልክ ነውና ተቀበሉ” ሲሉን “አዎን ልክ ነው” ብለን ከተቀበልን፣ የኋላ ኋላ ፀፀት ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ህሊናችን የማይቀበለውን፣ ውስጣችን የማይመቸውን ድርጊትም ሆነ ወሬ “እንቢ አልሰማም” ብለን የመከራከር፣ “ለምን?” ብለን የመጠየቅ ሞራላዊ ግዴታ አለብን፡፡ ቅን አመለካከትን የሚያሳክር፣ ስልጣኔን የሚቃረን፣ ጎታችና ኋላ ቀር ለሆኑ አስተሳሰቦች ማጎንበስ፣ ነፃነትን አሳልፎ መስጠት ብቻ ሳይሆን ፍትህ ራሷን ማዋረድ ይሆናል፡፡
“ያንተ ነፃነት የሚያበቃው የሌላው ሰው አፍንጫ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡” (Your freedom ends where the other man nose begins) … ያለው ማን ነበር፤ ወዳጄ?
ሠላም!!

Read 1252 times