Saturday, 09 December 2017 13:55

ግማሽ ቢሊዮን ብር የወጣበት የመድኃኒት ፋብሪካ ስራ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

· ሁለተኛውና ሶስተኛው ማስፋፊያ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 2.7 ቢ. ብር ይፈጃል
      · ከ15 በላይ ግዙፍ መድኃኒት ኩባንያዎች፣ ከ10 ሺህ በላይ ሰራተኞች አሉት
    

    በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረ ማሪያም ወረዳ፤ ግማሽ ቢሊዮን ብር የወጣበት “ሂውማን ዌል” የተሰኘ የቻይና የመድኃኒት ፋብሪካ ተመርቆ ስራ ጀመረ፡፡ ባለፈው ሳምንት እሁድ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመረቀው የፋብሪካው የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን ሁለተኛውና ሶስተኛው ማስፋፊያ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ 2.7 ቢ. ብር እንደሚፈጅና ለ300 ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር በምርቃት ስነ - ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
ከአዲስ አበባ 65 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ቱላፋ ቀበሌ የተገነባው የመድኃኒት ፋብሪካ፣ “ሂውማን ዌል ሄልዝ ኬር” የተባለ የቻይና ኩባንያ ግሩፕ አካል ሲሆን በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በእስያና በአፍሪካ ከ20 በላይ በሚሆኑ አገራት ላይ እንደሚሰራ ኃላፊዎቹ ጠቁመው፤ በአገራችንም በክኒን፣ በሽሮፕና በመርፌ መልክ የሚሰጡ ከ30 በላይ የተለያዩ መድኃኒቶችን እንደሚያመርት ተገልጿል፡፡ በ1939 (እ.ኤ.አ) በጥቂት የቻይና የኮሌጅ ተማሪዎች የተመሰረተው “ሂውማን ዌል ሄልዝ ኬር”፤ በአሁኑ ሰዓት አድማሱን አስፍቶ ዓለም ላይ ከሚገኙ ትልልቅ መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ተርታ መሰለፍ መቻሉም ተነግሯል፡፡ በምርቃቱ ላይ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተጨማሪ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ፣ በቻይና ኤምባሲ የቻይና የንግድና የኢኮኖሚ አማካሪ ሚስ ሊ.ዩ፣ የፌደራል ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ አብተውና ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር መብራቱ መለሰ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አፈወርቅ ካሱ እንዲሁም የዞኑ የስራ ኃላፊዎች፣ የቱለፋ ቀበሌ አስተዳዳሪዎችና በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ፤ዞኑ ቀደም ሲል በኢንቨስትመንት በኩል ጉልህ ተጠቃሚ እንዳልነበረ አስታውሰው፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን አስደናቂ ለውጥ መምጣቱን ጠቁመዋል። እንደ አስተዳዳሪው ገለፃ፣ በአሁኑ ወቅት 34.3 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 646 በአምራች ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ፕሮጀክቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ ከነዚህ መካከል 301 ፕሮጀክቶች 526 ሄክታር የለማ መሬት መረከባቸውን፣ ከነዚህም ውስጥ 28 ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ሲገቡ፣ 84ቱ በግንባታ ላይ መሆናቸውንና በያዝነው ዓመት ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡ አቶ ግርማ አክለውም፤ በዞኑ 112 ፕሮጀክቶች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውንና ጉዳዩ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  
በቻይና ኤምባሲ የቻይና የንግድና ኢኮኖሚ አማካሪ ሚስ ሊ.ዩ. ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያና ቻይና እ.ኤ.አ ከ1970 አንስቶ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመራቸውንና ይህ ግንኙነት ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ ውጤታማ ሆኖ መቀጠሉን አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅትም ቻይና የኢትዮጵያ ዋና የንግድ አጋር ሆና መቀጠሏን ገልፀዋል፡፡ “እውነተኛ ጓደኛ ሲፈልጉት የሚገኝ ነው” ያሉት አማካሪው፤ እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም 20 ቡድን ያለው 360 የቻይና ዶክተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የኢትዮጵያን ህዝብ ሲያገለግሉ መቆየታቸውንና ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከልም ሁለቱ እዚሁ ህይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ አገሮች ከዲፕሎማሲ ግንኙነት ባለፈ በንግድና በኢንቨስትመንት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው የጠበቀ መሆኑን አመልክተው፤ “ሂውማን ዌል ፋርማሲዩቲካል” ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ በመቋቋሙ 85 በመቶ ከውጭ ለሚገባው መድኃኒት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረቱም በላይ በቴክኖሎጂ ሽግግር በኩል የሚያደርገውም አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሚሆን አማካሪዋ ተናግረዋል፡፡
የመሰረት ድንጋዩን ባስቀመጠ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት የገባው ይህ በአማራ ክልል የመጀመሪያው የሆነው የመድኃኒት ፋብሪካ፤ በዓለም ላይ ከ15 በላይ ግዙፍ መድኃኒት ኩባንያዎች፣ ከ10 ሺህ በላይ ሰራተኞች፣ 600 ከፍተኛ ተመራማሪዎችና ከ40 በላይ እጅግ ከፍተኛ ተመራማሪዎች ያሉትና ለጥናትና ምርምር ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ ኩባንያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ ቁጥር አንድ መድኃኒት ሻጭ ለመሆን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም የፋብሪካው ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡  

Read 2190 times