Print this page
Sunday, 10 December 2017 00:00

በዲሞክራቲክ ኮንጎ ዘንድሮ ብቻ 1.7 ሚ. ዜጎች ተፈናቅለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ለአመታት ተባብሶ በቀጠለው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የእርስ በእርስ ግጭት ሳቢያ፣ እየተገባደደ ባለው የፈረንጆች አመት 2017 ብቻ 1.7 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች፣ከመኖሪያ ቦታቸው መፈናቀላቸውንና ወደ ሌሎች አገራት መሰደዳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ ለአመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት ዜጎችን ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ መዳረጉን ቀጥሏል ያለው ዘገባው፤ ባለፈው አመት መከናወን የነበረበት ምርጫ በታቀደለት ጊዜ አለመካሄዱ የእርስ በእርስ ግጭቱን ወደከፋ ሁኔታ እንዳሸጋገረውና ግጭቱን በመሸሽ ከመኖሪያ ቦታቸው የሚፈናቀሉና ወደተለያዩ አገራት የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል፡፡ ኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር የተባለው ተቋም ባወጣው አዲስ ሪፖርት፤ በዘንድሮው አመት ብቻ በየዕለቱ በአማካይ 5 ሺህ 500 የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸውን አስታውቋል ያለው ዘገባው፤ የመፈናቀሉ መጠን በአለማቀፍ ደረጃ የከፋውና ብዙዎችን ተጠቂ ያደረገ ነው ማለቱን ገልጧል፡፡
በአገሪቱ ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር በድምሩ አራት ሚሊዮን ያህል መድረሱንና ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዜጎችም የምግብ እጥረት ተጎጂ መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ሰብዓዊ ቀውሱን ለመግታት የሚደረገው አለማቀፍ ድጋፍ ግን እጅግ አናሳ ነው መባሉን አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ካሳኢ በተባለው የአገሪቱ አካባቢ ተባብሶ በቀጠለው የእርስ በእርስ ግጭት ሳቢያ ግማሽ ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች ለምግብ እጥረት መዳረጋቸውንና ተገቢ እርዳታ አለማግኘታቸውን የአለም የምግብ ፕሮግራም ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Read 1226 times
Administrator

Latest from Administrator