Monday, 11 December 2017 00:00

ፒዲዲ በ130 ሚ. ዶላር የአመቱ የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ድምጻዊ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቤል ተስፋዬ፤ በ92 ሚ. ዶላር 4ኛ ደረጃን ይዟል

    በአለማችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ አመታዊ ገቢ ያገኙ ድምጻውያንን ደረጃ የሚያወጣው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ ከሰሞኑም የ2017 የፈረንጆች አመት ከፍተኛ ተከፋይ የአለማችን ድምጻውያንን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን ፒዲዲ በ130 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ፒዲዲ ባለፉት 12 ወራት ብቻ በድምሩ 130 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው ፎርብስ፤ ከፍተኛ ገቢ ካስገኙለት መካከልም ሲሮክ ቮድካ ከተባለው ኩባንያ ጋር የገባው የንግድ ስምምነት፣ የኩባንያዎቹን ከፊል ድርሻ መሸጡና ባድቦይ ሪዩኒየን በሚል ርዕስ ያደረገው የሙዚቃ ኮንሰርት ጉዞው እንደሚጠቀሱ ገልጧል፡፡
አሜሪካዊቷ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ 105 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት በአመቱ ሁለተኛውን ከፍተኛ ገቢ ያገኘች የአለማችን ድምጻዊት ስትባል፣ ድሬክ በ94 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በቅጽል ስሙ ዘ ዊክንድ ተብሎ የሚጠራው ትውልደ ኢትዮጵያዊው የግራሚ ተሸላሚ አቤል ተስፋዬ፣ በ92 ሚሊዮን ዶላር አራተኛ ደረጃን መያዙን የጠቆመው የፎርብስ መግለጫ፤ የእንግሊዙ የሙዚቃ ቡድን ኮልድፕሌይ በበኩሉ፣ በ88 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ አምስተኛ ደረጃን መያዙን አመልክቷል፡፡
83.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት በደረጃ ሰንጠረዡ ሰባተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የ23 አመቱ ራፐር ጀስቲን ቢበር፤ ከአመቱ የፎርብስ የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ድምጻውያን መካከል በእድሜ ትንሹ ነው ተብሏል፡፡

Read 3045 times