Saturday, 16 December 2017 00:00

የዚምባቡዌ መንግስት “ኮ/ል መንግስቱ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው አይሰጡም” አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

በዚምባቡዌ የመንግስት ለውጥ ከተደረገ በኋላ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው እንዲሰጡ የሚጠይቁ ወገኖች የተበራከቱ ሲሆን የሀገሪቱ መንግስት በበኩሉ፤ “ኮ/ል መንግስቱን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የማይታሰብ ነው” ብሏል፡፡
ዚምባቡዌን ለ38 ዓመታት የመሩት ሮበርት ሙጋቤ፤ በወታደሩ ድጋፍ ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ የአገሪቱ የፕሬዚዳንትነት ቦታውን የተኩት ኤምርሰን ማኒንግዋ፣ ስልጣን ከያዙ ማግስት ጀምሮ መንግስቱ ኃ/ማርያምን ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፈው እንዲሰጡ የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ኢትዮጵያውያን እየወተወቱ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
ዴኪሳሞ የተባሉ የሀገሪቱ ፖለቲከኛ በትዊተር ገፃቸው  ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ዚምባቡዌያውያን ለፍትህ ፅኑ አቋም ያላቸው ናቸው፤ ከዚህ አንፃር አምባገነኑና ለብዙዎች ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሆኑትን ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያምን የአገራቸው መንግስት አሳልፎ እንዲሰጥ ግፊት መፍጠር አለባቸው” ሲሉ መፃፋቸውን “ሜል ኤንድ ዘ ጋርዲያን” ዘግቧል፡፡ ዛክ አስፋው የተባሉ ኢትዮጵያዊ በበኩላቸው ለፕሬዚዳንት ማኒንጋዋን ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ፍትህ ለማግኘት የሚጠባበቁ ኢትዮጵውያን እናቶችን እባክዎ ያስታውሷቸው፤ መንግስቱ ኃ/ማርያምን ከሃገርዎ ያስወጡ” በማለት በትዊተር ገፃቸው እንደፃፉ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በለንደን የኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር አወል ቃሲም የተባሉ ኢትዮጵያዊም በተመሳሳይ፤ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው እንዲሰጡ መጠየቃቸውን “ሜል ኤንድ ዘ ጋርዲያን” ዘግቧል፡፡
ኤመርሰን ማኒንግዋ የቀድሞ የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን ተክተው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ጥያቄዎች እየተቀበሉ መሆኑን የጠቆሙት የዚምባቡዌ መንግስት ቃል አቀባይ ጆርጅ ቻራምባ በበኩላቸው፤ “ጉዳዩ የዚምባቡዌያውያን ሀገራዊ አጀንዳ አይደለም፣ ጥቂት ተቃዋሚዎች በማያውቁት ጉዳይ ገብተው የሚፈጥሩት ችግር ነው” ብለዋል፡፡ ቃል አቀባዩ አያይዘውም፤ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያንም ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የማይታሰብ ነው ብለዋል፡፡
“የዚምባቡዌ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ኮሎኔል መንግስቱ እንዴት ወደ ሀገሪቱ እንደመጡና ጥገኝነት እንዳገኙ እንኳን አያውቁም” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ “የጉዳዩ ባለቤት የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ጥያቄ ባላቀረበበት ሁኔታ የተቃዋሚዎች ጉንተላ  ምን ሊባል ነው?” ሲሉ መጠየቃቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡ በሀገሪቱ የሩዋንዳ፣ የኮንጎና የሞዛምቢክ ዜጎች በጥገኝነት እንደሚኖሩ ያወሱት ቃል አቀባዩ፤ “ተቃዋሚዎች ለምን በመንግስቱ ኃ/ማርያም ላይ እንዲህ በረቱ?” ብለዋል - በዘገባው፡፡
ኮ/ል መንግስቱ፤ ሮበርት ሙጋቤን በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ለዓመታት ሲያማክሯቸው እንደነበር የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ ለአገሪቱ ውድቀትም ተጠያቂ ናቸው ብለው እንደሚከራከሩ የጠቆመው ዘገባው፤ ኮሎኔል መንግስቱም መፈንቅለ መንግስቱ ከተደረገ በኋላ በአደባባይ አለመታየታቸውን ገልጿል፡፡   

Read 3906 times