Monday, 18 December 2017 12:55

“የዕውር የድንብሩን ከሚሮጥ ፈረስ፣ መንገድ የምታውቅ አይጥ ትሻላለች”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

አንዳንድ ዕውነተኛ ታሪክ ሲቆይ ተረት ይመስላል፡፡ የሚከተለውን እንደዚያው ነው።
ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ፣ አገር ሳያውቀው የሞተ ሰዓሊ ነበረ፡፡ ይህ ሰዓሊ የአገሩን ባንዲራ በልዩ እሳቤ ያስጌጠ፣ ማንም ያልደረሰበት ረቂቅ ሰዓሊ ነበረ። ስለሰራው ሥራ ዋጋው አልተከፈለውም፡፡ ስለዚህም ወዳጆቹ፤ ያንን ባንዲራ “ያልተከፈለ ዕዳ” በሚል የቅፅል ስም ይጠሩታል፡፡
ይህ ሰዓሊ የተከራየው ግቢ ውስጥ አንድ ካቲካላ ‹አረቄ› የሚሸጥበት ቤት አለ፡፡ እዚህ ቤት የሚጠጡት ሰዎች ሁሉ ሰዓሊውን፤ ፀጉሩ የተንጨባረረና ነጠላ ጫማ (ሸበጥ) የሚያደርግ ስለሆነ ሰላይ ነው ብለው ይጠረጥሩታል፡፡ ስለሆነም እሱ ወደ ካቲካላው ቤት ሲገባ አፍ ሁሉ ይዘጋል፡፡ የተጀመረ ታሪክ ይቋረጣል፡፡ ሰው ሁሉ አፉ ላይ ማብሪያና ማጥፊያ የተገጠመለት ይመስል፣ በማጥፊያው ጠቅ አድርገው እንዳጠፉት ሁሉ አንዴ ጭጭ ይላል፡፡
አንድ ቀን ሰዓሊው ወደ ግቢው ሲመጣ፣ የግቢው ውሻ ይጮኽበታል፡፡ ይሄኔ ሰዓሊው ኮሮጆውን ከትከሻው ያወርድና አስፋቱ ላይ ያስቀምጣል፡፡ ከዚያም ከውሻው ፊት ለፊት ይንበረከካል፡፡ ቀጥሎም፤ “ው! ው! ው! ው!” አለ ውሻው ላይ ይጮህበታል። ውሻው ደንግጦ ዝም፤ ጭጭ ይላል፡፡ “ሁለተኛ ትጮህና እጮህብሃለሁ!” ይለዋል፡፡ ይሄንን ሲያደርግ ከሰዓሊው ጀርባ እየመጡ ያሉ ካቲካላ ጠጪዎች፣ ሁኔታውን ሁሉ ይከታተሉ ኖሯል፡፡ ቀድመው ወደ ካቲካላ ቤት ሄደው ሁኔታውን ሁሉ ለጠጪዎቹ ይናገራሉ፡፡ ሰዓሊው ቆይቶ ወደ አረቄው ቤት ሲመጣ፤
አንዱ፤ “ሁለት ስጡት!”
ሌላው፤ “ሶስት ጨምሩለት!”
ሌላው፤ “ሰው ማለት ይሄ ነው! እንጋብዘው እንጂ ጎበዝ!” እያለ ሰዓሊውን በግብዣ አንበሸበሹት፡፡
በሰላይነት መጠርጠሩ ቀርቶ እንደ ሰው ተጋበዘ! እንደ ሰው ተከበረ! ይህንን የተገነዘበው ሰዓሊ፤
“እዚህ አገር ሰው ለመሆን እንደ ውሻ መጮህ ያስፈልጋል!” አለ፡፡
የዚህን፤ የውሻን አፍ ያስዘጋ፤ የሰውን አፍ ያስከፈተ፣ ታላቅ ሰዓሊ ነብስ ይማር!!
*        *      *
ታላቅ ሰዎቻችንን እናክብር፡፡ ታላላቅ ሰዎቿን የቀበረች አገር ብዙ ያልተከፈለ ዕዳ ይኖርባታል፡፡ ዕዳው የትውልድ ነውና መጪውን ትውልድ ሳይቀር ባለዕዳ ታደርጋለች። የድንቁርና ዕዳ፣ ከዕዳ ሁሉ የከበደው ዕዳ ነው! የጤና ማጣት ዕዳ፣ ሁለተኛው ከባድ ዕዳ ነው! የዕብሪትና የማናለብኝ ዕዳ ቀጣዩ አባዜ ነው! ሁሉም ዋጋ እንደሚያስከፍለን በጭራሽ አንዘንጋ! ሁላችንም ባለሳምንት፣ የጠጣነውን ፅዋ በተራችን እንከፍላለን! ሌላው ብርቱ ችግራችን የመስባት ችግር ነው፡፡ (The fattening process እንዲሉ)
አንድ አዛውንት፤ “ስሙ አባታችን፤ እኛ እንደቀደሙት ገዢዎች ወፋፍራም አደለንም!” ቢሏቸው፤ “አዬ ልጄ፤ እነሱም ሲጀምሩ እንደናንተ ቀጫጭኖች ነበሩ!” አሉ፤ አሉ፡፡ የሀገራችን መሪዎች ችግር “አትፍረድ ይፈረድብሃል” የሚለውን መሪ ቃል መዘንጋት ነው! መጪዎች ከቀደሙት አይማሩም፡፡ የማይቀረውን ውድቀት እንደ ፅዋ መቀባበል አይቀሬ የሚሆነው ለዚህ ነው!
ጊዜያዊ የዘመቻ ሂደት ዘላቂ ለውጥን አያመጣም፡፡ የአፍታ - ለአፍታ የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ ዘላቂ ዕውቀትን አያሰርፅም! ይልቁንም ህዝብን ማሳወቅ፣ ማስተማርና ማንቃት ፈር የያዘ ብቃትን ይፈጥራል! ትውልድ ዘላቂ ንቃትና ብቃት ሲኖረው፣ እርባና ያለው ለውጥ፣ ብሎም እርባና ያለው ዕድገት ያመጣል፡፡ የአልሸነፍም ባይነት ግትርነት፣ ጊዜያዊ ሥልጣንን ሊያቆይ ይችላል እንጂ የአገርና የህዝብን ዘላቂ ዕድገት አይፈጥርም! ነባር ግንኙነቶች ቀስ በቀስ መላላታቸው፣ ቀስ በቀስ መለወጣቸው ግድ ነው፡፡ አዳዲስ የሰው ኃይል መደባለቅ ለለውጥ መምጣት አንዱ ግብዓት ነው፡፡
አዳዲስ አስተሳስብ እንዲመነጭ የአዳዲስ ሰው ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ነገሩ ሁሉ ባለበት እርገጥ ይሆናል፡፡ ምንም ያህል ብንሮጥ መላና ብልሃት ከሌለበት የጭፍን ሩጫ ነው የሚሆነው፡፡ የጣልነውን ስለረገጥነው የእኛን ዕድገት ማረጋገጫ አይሆንም፡፡
እርጋታና አደብ መግዛት ወሳኝ ነው፡፡ መንገዶች በሙሉ ሊሾ አይሆኑም። ኮረኮንቹ እንዳይበዛ መታገሉ ሁነኛ አማራጭ ነው፡፡ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” የሚለውን ተረት ሳንዘነጋ፣ ዛሬም ተለዋጭ ኃይል ማስፈለጉን እናስብ። ልዩነትን እናድንቅ፡፡ ሌጣ የሆነን አጓጓዝ እናስወግድ፡፡ የተለየ ሀሳብ አያስበርግገን። ጉዞአችን የጭፍን እንዳይሆን መሬት የያዘ ፍጥነት ይኑረን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰከነ መላ እንዘይድ፡፡ ለዚህም “የዕውር የድንብሩን ከሚሮጥ ፈረስ መንገድ የምታውቅ አይጥ ትሻላለች” የሚለውን ተረት እንገንዘብ!!

Read 3779 times