Monday, 18 December 2017 13:06

የፍልስጤም አምባሳደር በተለይ ለአዲስ አድማስ(በአወዛጋቢው የኢየሩሳሌም መዲናነት ዙሪያ ምን ይላሉ?)

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 · “የትራምፕ ውሳኔ ፍልስጤምን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የሚጎዳ ነው”
    · “ለመሆኑ ከ3 ሺህ ዓመት በፊት እስራኤል የምትባል አገር ነበረች?”
    · “ንጉስ ሰለሞን፣ ዳዊትም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍልስጤማዊያን ናቸው”
    · “በምንም አይነት መልኩ የዋሽንግተንና የትራምፕን ውሳኔ አንቀበልም”

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲያ ከቴል አቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲዛወር መወሰናቸው ዓለምን እያነጋገረና እያወዛገበ ነው፡፡ እስካሁን 12 የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ተመርጠው ዋይት ሃውስ ሲገቡ ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና መሆኗን ዕውቅና እንደሚሰጡ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም አንዳቸውም አልተገበሩትም ነበር፡፡ ትራምፕ ግን ዓለም ያለውን ይበል ብለው ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና መሆኗን ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት፣ አፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፣ የአረብ ሊግ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የትራምፕን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ከፍልስጤም ጎን ቆመዋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ረፋድ ላይ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ዓመታዊው “የፍልስጤም የአንድነት ቀን” በተከበረበት ወቅት የተገኙ ብዙዎቹ የአለም አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተመሳሳይ አቋማቸውን ገልፀዋል፡፡
በፍልስጤም የአንድነት ቀን ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በኢትዮጵያ በኡጋንዳና በኬንያ የፍልስጤም አምባሳደር፣ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጤም ተወካይ ከሆኑት ዶ/ር ናስሪ ካህሊል አቡጃይሽ ጋር በአወዛጋቢው የኢየሩሳሌም መዲናነት ፣በዶናልድ ትራምፕ ያልተጠበቀ ውሳኔና በፍልስጤምና እስራኤል ዘመናትን ያስቆጠረ ጦርነት፣ እንዲሁም ታሪካዊ ዳራ ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-


    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፉት ውሳኔ ምንድን ነው የተሰማዎት?
እርግጥ ነው በውሳኔው በጣም አዝኛለሁ፤ በጣም ከፍቶኛል፤ ነገር ግን ጉዳዩ የስሜት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ኢየሩሳሌም ሁሌም በእኛ በፍልስጤማዊያን ልብ ውስጥ ናት። ይህ እንግዲህ ከሀይማኖትም ከታሪክም አኳያ የሚታይ ነው፡፡ በእኛ በፍልስጤማዊያን እምነትም ሆነ ዓለም እንደሚያውቀው፤ ኢየሩሳሌም ማለት የፍልስጤም ናት፡፡ ያለ ኢየሩሳሌም ፍልስጤም የለችም፡፡ ብዙ ፍልስጤማዊያን ለኢየሩሳሌም ህይወታቸውን ከፍለዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ትራምፕን ውሳኔ ለመቀበል ለፍልስጤማዊያን ከባድ ነው። ፕሬዚዳንቱም ሆነ ሚኒስትሮች ወይም ሌላው የፍልስጤም ህዝብ፣ ይህንን ውሳኔ ሊቀበሉ ቀርቶ ለማሰብም ይከብዳቸዋል፡፡
ግን ፕሬዚዳንቱ ይህንን ውሳኔ እንዲያሳልፉ ያነሳሳቸው ምክንያት ምን ይመስልዎታል?
ትራምፕ፤ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው፡፡
ምን አይነት ጥቅም---?
ትራምፕ ውሳኔውን ያስተላለፈው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው፣ በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻው ወቅት የገባው ቃል አለ፡፡ የምርጫ ቅስቀሳው ጊዜ ከፍተኛ የገንዘብ ልገሳ የተደረገለት ከአይሁዶች ነው፡፡ እንደውም አሁን ስሙን ማስታወስ ያልቻልኩት አንድ አይሁዳዊ፣ ለምርጫ ቅስቀሳው ዘመቻ 27 ሚ. ዶላር ለግሶታል፡፡ ስሙን በመርሳቴ በጣም አዝናለሁ፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ፣ ትራምፕ አመራሩ ላይ የሚያጋጥመውን የውስጥ ጫና እንዲከላከሉና እንዲጠብቁት የሚተማመነው በእስራኤሎች ነው። ለዚህ ደግሞ ኢየሩሳሌምን ለእነሱ አሳልፎ መስጠት ነበረበት፡፡
በነገራችን ላይ ይህ ኢየሩሳሌምን ለአይሁዳዊያን ለመስጠት የተገባ ሁለተኛው ቃል ኪዳን ነው፡፡ የታላቋ ብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ቢልፎር፣ ከመቶ አመት በፊት ኢየሩሳሌምን ለአይሁዳዊያን ለመስጠት ቃል ገብቶ ነበር። ይህ ቢልፎር ዲክላሬሽን እየተባለ ይጠራል። እንደሚታወቀው ኢየሩሳሌም ለሙስሊሙም ለክርስቲያኑም ሆነ ለአይሁድ አማኒያን የተቀደሰች የሀይማኖት ቦታ ናት፡፡ እነዚህ አማኒያን በሺህ ለሚቆጠሩ አመታት አብረው ተከባብረውና ተዋደው ኖረውባታል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ከ50 ዓመታት ወዲህ እስራኤል ኢየሩሳሌምን በሀይል ከተቆጣጠረች በኋላ ይህ የእምነት ቦታ ነፃ መሆኑ ቀርቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለሙስሊምም ሆነ ለክርስቲያን ፍልስጤማዊያን ወደዚህ የተቀደሰ ቦታ መግባት ክልክል ነው፡፡ ፍልስጤማዊ ክርስቲያን ከቤተልሄምም ሆነ ከጋዛ ወደ ኢየሩሳሌም መግባትና መፀለይ አይችልም፡፡ በተመሳሳይ የፍልስጤም ሙስሊምም ወደዚህ ቦታ ገብቶ መፀለይ በፍፁም አይታሰብም፡፡ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ያውም በረመዳን ፆም ወቅት ብቻ ነው ሙስሊሞች ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው፣ አላስካ መስጊድ ውስጥ እንዲፀልዩና እንዲሰግዱ የተፈቀደላቸው። ተመልከቺ … በአመት አንድ ጊዜ ለረመዷን ፆም ብቻ፡፡ ይሄ ላለፈው ሀምሳ ዓመት የዘለቀ ነው፡፡ በጣም ከባድና አስቸጋሪ ነው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ--- ይህንን ውሳኔ ለማሳለፍ ህጋዊ መሰረት አላቸው?
በፍፁም ህጋዊ መሰረት የለውም፡፡ ህገ ወጥ ውሳኔ ለመወሰኑ ማሳያው አንደኛ፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ስምምነቶች ናቸው፡፡ እስራኤል በሀይል የያዘቻት ኢየሩሳሌም፣ የፍልስጤም ግዛት ናት። ኢትዮጵያና መላው የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ 140 አገራት በ1967 ስምምነት ላይ ኢየሩሳሌም የፍልስጤም ስለመሆኗ እውቅና ሰጥተዋል፡፡ ወደ አለም አቀፍ ሪዘሊዩሽንስ ስንመጣ፣ ሁሉም የፀጥታው ምክር ቤት ሪዘሊሽኖች ከ242 ጀምሮ 338፣ 476፣ 478፣ 2334 ብንመለከት፣ ኢየሩሳሌም በእስራኤል በሀይል የተያዘች፣ የፍልስጤም ግዛትና የፍልስጤም ዋና ከተማ ስለመሆኗ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ከነዚህ ስምምነቶች የተነሳ የፀጥታው ምክር ቤት 40 አባል አገራትና የተባበሩት መንግስታትና አፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የትራምፕ ውሳኔን ውድቅ አድርገውታል፡፡
እንደሚታየው ብዙ አገራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ጭምር ለፍልስጤም ድጋፍ እየሰጡ ነው፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው የሚፈለገውን ያህል ጫና ፈጥረው፣ በሰላማዊ መንገድ ለሁለቱም አገራት መፍትሄ ማምጣት ያልቻሉት?
ለዚህ ጥያቄ በጣም አመሰግናለሁ። የዚህ ሁሉ ችግር ዋና ምንጭ አሜሪካ ናት፡፡ በተለይ ለፍልስጤማዊያን መብት አለመከበር ዋና እንቅፋታችን አሜሪካ ናት። የተባበሩት መንግስታት አባል አገር ለመሆን ምን ያህል ጊዜ አመልክተን እንዳልተሳካልን ታውቂያለሽ? እስራኤል በፍልስጤም ላይ የምታደርሰውን ጫና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲያወግዝ ጠይቀን፣ አሜሪካ እስራኤልን ለመከላከል 78 ጊዜ ጥያቄያችን ውድቅ ሆኗል፡፡ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው፣ የእኛን ጥያቄ 78 ጊዜ ውድቅ አድርገው፣ እስራኤልን ሲከላከሉ ቆይተዋል፡፡ እስካሁንም እኛ አሜሪካ አደራዳሪ እንድትሆን ጥሪ አቅርበናል፡፡ እነሱ ግን ምንም አደራዳሪ አይደሉም፤ መሆንም አይፈልጉም፡፡ በእስራኤል ወገንተኝነት፣ ለእስራኤል ዘብ የቆሙና የእስራኤልን ጥቅም የሚያስጠብቁ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እስራኤሎች በሁሉም ዘርፍ የአሜሪካዊያንን ህይወት መቆጣጠር ችለዋል። ለምሳሌ ሚዲያውን፣ ኢኮኖሚውን … ሌላው ቀርቶ የአሜሪካን ምርጫ መቆጣጠር ችለዋል። እርግጥ በአሜሪካ የሚኖሩት የእስራኤላዊያን ቁጥር ከአሜሪካ ህዝብ ሁለት በመቶ ብቻ ነው፤ ግን ሁሉንም ነገር ተቆጣጥረውታል፡፡ እውነት ለመናገር አሜሪካዊያን በአይሁዶች ምክንያት ብዙ ይሰቃያሉ። ሀይላቸው ደግሞ ገንዘብ ነው፡፡ አይሁዶች በጣም ሀብታሞች ናቸው። የአሜሪካንን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ኢኮኖሚ ጭምር እየተቆጣጠሩ ነው፡፡ ቅድም ወደነገርኩሽ የቢልፎር ቃልኪዳን ልመልስሽ … ታላቋ ብሪታኒያ ከመቶ አመት በፊት ለአይሁዶች ለምን ኢየሩሳሌምን ለመስጠት ቃል እንደገባች ልንገርሽ፡፡ በ1914 ዓ.ም በነበረው አንደኛው የአለም ጦርነት፣ ታላቋ ብሪታኒያ ወታደራዊ ሀይሏን ለመገንባት ጀርመናዊያን የነበሩና ብሪታኒያ የሚኖሩ “ሮቼልት ፋሚሊ” ከተባሉ አይሁዳዊያን በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ይበደራሉ፡፡ ከጦርነቱ በኋላ የብሪታኒያ ኢኮኖሚ ተሽመድምዶ ወድቆ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አይሁዶቹ “ያበደርናችሁን ገንዘብ መልሱ” ሲሉ፣ ታላቋ ብሪታኒያ ያንን ገንዘብ ከየት አምጥታ ትክፈል፡፡ “ገንዘባችንን የማትመልሱ ከሆነ ፍልስጤምን ስጡንና አገራችንንና ህልውናችንን እዚያ እንመስርት” ብለው ጠየቁ፡፡ ታላቋ ብሪታኒያ ቅኝ ግዛቷ የነበረችው አፍሪካዊቷን ኡጋንዳን እንዲወስዱ ምርጫ አቀረበች፡፡ አይሁዶች አንቀበልም አሉ፡፡ አርጀንቲና ውስጥ ያለችዋን ሞሪሺየስ እንዲወስዱ ቢቀርብላቸውም አንቀበልም፤ የምንፈልገው ፍልስጤምን ነው አሉ፡፡ ይሄ እውነተኛ ታሪክ እንጂ ተረት አይደለም፡፡ የአሁኑ የአሜሪካና የትራምፕም ውሳኔ ከቤልፎር ቃልኪዳን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ምንም ልዩነት የለውም፡፡
የፍልስጤም ችግር ከውጭ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን የራሳቸው የውስጥ ችግርም ጭምር ነው ይባላል፡፡ ለምሳሌ ጎላ ብለው የሚወጡ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ የአገሪቱ ሌላው ጫና ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
እውነት ለመናገር የፍልስጤም ችግር አሁን አንቺ በምትይው መጠን አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ችግሩ ነበር፡፡ በፍልስጤማዊያን ታሪክ፣ የፍልስጤም ሁሉም ድርጅቶች ተባብረው የእስራኤል ወረራን ሲከላከሉ ኖረዋል፡፡ ይህ ላለፉት 50 ዓመታት የቀጠለ ነው፡፡ እርግጥ ነው ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በሁለት ትልልቅ ድርጅቶች ማለትም በፈታህና ሀማስ መካከል ችግር ነበር፡፡ እንደመታደል ሆኖ ከሁለት ወራት በፊት እርቅ አውርደው፣ ችግሮቻቸውን ፈትተዋል፡፡ እንዳልሺው እነዚህ ፓርቲዎች ለፍልስጤም አንዱ እንቅፋት ነበሩ፡፡  
እስራኤልና ኢትዮጵያ የጠበቀና ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ነገር ግን ከፍልስጤማውያን ጎን ቆመው፣ የፕሬዚዳንት ትራምፕን ውሳኔ ውድቅ ካደረጉ አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ፍልስጤማዊያን ይህንን ጉዳይ በምን መልኩ ነው የሚገነዘቡት?
በመጀመሪያ ደረጃ እስራኤልና ኢትዮጵያ ከ3 ሺህ ዓመት በላይ ግንኙነት አላቸው የሚለው ታሪክ ከየት የመጣ ነው? ለመሆኑ ከ3 ሺህ ዓመት በፊት እስራኤል የምትባል አገር ነበረች እንዴ?
ከንጉስ ሰለሞንና ከንግስት ሳባ ግንኙነት ቀዳማዊ ምኒልክ የተባለ ልጃቸውን ከወለዱ አንስቶ ትስስሩ መጀመሩ ይነገራል …
በነገራችን ላይ ንጉስ ሰለሞን፣ ዳዊትም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍልስጤማዊያን ናቸው፡፡ ኢየሱስ ቤቴልሄምና ናዝሬት ኖሯል፡፡ እስራኤል የነብይ ስም እንጂ የአገር ስም አይደለም፡፡ እርግጥ በዛ ዘመን በፍልስጤም ሁሉም ህዝብ የጁዲሂዝም እምነት ተከታይ ነበር፡፡ ጁዲሂዝም እምነት እንጂ አገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንቺ በአሁኑ ወቅት ክርስቲያን ልትሆኚ ትችያለሽ ግን ኢትዮጵያዊት ነሽ፡፡ ነገ ሙስሊም ብትሆኚ የተቀየረው ሀይማኖትሽ እንጂ ዜግነትሽ አይደለም፡፡ ከዚያ በኋላ ጁዲሂስት ብትሆኚም በቃ ኢትዮጵያዊት ነሽ አለቀ፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ ክርስቲያንም ሙስሊምም ጁዲሂስትም ሆነ ሌላ እምነት የሚከተሉ ህዝቦች ናቸው ያሉት፡፡ ሀይማኖት ሊቀያይሩ ይችላሉ ግን ዜግነታቸው አይቀየርም፡፡ ኢትዮጵያን ለቅቀው የኬንያ ዜግነት ካገኙ ኬንያዊ ይሆናሉ፤ አለቀ። ወደ ኋላ ታሪክ ስንመለስ ወይም ወደ መፅሀፍ ቅዱስ ስንገባ፣ ፍልስጤም ግዛትና አገር እንደሆነች 17 ጊዜ በመፅሀፍ ቅዱስ ተጠቅሳለች፡፡ ነገር ግን እስራኤል የሚባል ነብይ እንጂ አገር በመፅሀፍ ቅዱስ ተጠቅሶ አንድም ቦታ አታገኚም፡፡ እስራኤል እንደ አገር እውቅና ያገኘችው ከ50 ዓመት ወዲህ ነው፡፡ በነዚህ ዓመታት እስራኤልና ኢትዮጵያ ጥብቅ ግንኙነት እንዳላቸው ይታወቃል፤ ያም ቢሆን ኢትዮጵያ የትራምፕን የተሳሳተ ውሳኔ ለመሻር ከእስራኤል ጋር ያላት የጠበቀ ግንኙነትና ወዳጅነት አያግዳትም፤ ምክንያቱም ያሉትን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ያለውን እውነታ ጠንቅቃ ታውቃለችና፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያና ፍልስጤም የጠበቀ ግንኙነትና ወዳጅነት አላቸው፡፡ ወዳጅነታቸው የቅርብ ጊዜም አይደለም፤ ከ1972 ዓ.ም ከኃይለስላሴ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ንጉስ ኃይለስላሴ ከፍልስጤም ጎን በመቆም የፍልስጤም ህዝብ ፍትህ እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ነበር፡፡ የደርግ መንግስትም ይህንኑ ድጋፍ ሲያደርግልን ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ዘመንም እጅግ የምናከብራቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ለፍልስጤማዊያን ነፃነትና ፍትህ ድጋፋቸውን አልተለየንም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅትም የትራምፕን ውሳኔ ውድቅ ካደረጉ የዓለም አገራት አንዷና ግንባር ቀደሟ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ፣በፍትህ ፈላጊው የፍልስጤም ህዝብ ስም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተከበረው ዓመታዊው የፍልስጤም የአንድነት ቀን በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የትራምፕ ውሳኔ ፍልስጤምን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የሚጎዳ ነው ብለዋል፡፡ እስኪ በዚህ ውሳኔ እንዴት መላው ዓለም ሊጎዳ እንደሚችል ያስረዱኝ?
በሁለት ምክንያቶች መላው ዓለም ይጎዳል፡፡ የመጀመሪያው የትራምፕ ውሳኔ አለምአቀፍ ህጎችን የሚጋፋና የሚጥስ ነው፡፡ አንድ አገር አለም አቀፍ ህግን የሚጥስ ከሆነ “Rock State” ይባላል፡፡ ሮክ ስቴት ማለት ዓለም አቀፍ ህግን የማያከብር ማለት ነው፡፡ ከዲፕሎማሲያዊ ሂደት ይልቅ ሁሉን ነገር የሚያደርገው በሀይል ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የትራምፕ ውሳኔ ዓለም አቀፍ ህግን ጥሶ ከተተገበረ፣ ነገም ሌላው አገር እየተነሳ ዓለም አቀፍ ህጎችን ይጥሳል፡፡ ለምን? አሁን ህግ ሳይሆን ጉልበት ነው የሚሰራው ማለት ነው። በዚህ ምክንያት የትራምፕ ውሳኔ መላውን ዓለም ይጎዳል፡፡ ሀይል ያለው አገር፣ ሀይል የሌለውን በሀይል ይጨቁናል ይረግጣል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ነገር ኢየሩሳሌም የሙስሊሙም የክርስቲያኑም የአይሁድ እምነት ተከታዮችም የሀይማኖትና የእምነት ቅዱስ ቦታ ናት፡፡ ለእስራኤል ተሰጠች ማለት ሙስሊምና ክርስቲያን አማንያን ወደዚያ ቦታ ድርሽ አይሉም ማለት ነው፡፡ ይሄ ሌላው ሁሉንም ዓለም የሚጎዳ ጉዳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እስራኤላዊያን ሙስሊምም ሆነ ክርስቲያን የለም፤ የአይሁድ እምነት ተከታይ ብቻ ነው ያለው፡፡ እስራኤል ውስጥ ያሉት ክርስቲያኖችም ፍልስጤማዊ ናቸው፡፡ ማክሰኞ ዕለት በቴልአቪቭ የትራምፕ ውሳኔን በመቃወም ሰልፍ ተደርጎ ነበር፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ውሳኔው ዓለም አቀፍ ህጎችና ስምምነቶችን የሚጥስ ስለሆነ የዓለምን ህዝብ በሙሉ ይጎዳል፡፡
የትራምፕ ውሳኔ የማይለወጥ ቢሆን የፍልስጤማዊያን እርምጃ ምን ይሆናል?
አለም እንደሚያውቀው እኛ በእስራኤል ወረራ ስር ነን፡፡ ኢየሩሳሌም ተወራለች፡፡ ሁሉም የፍልስጤም ህዝብ በወረራ ስር ነው፡፡ ሆኖም እንደ እኛ እምነትም ሆነ እንደ አለም አቀፍ ህግና ስምምነት፣ ኢየሩሳሌም የፍልስጤም አካል ናት፡፡ ስለዚህ ልንወስዳቸው የምንችላቸው በርካታ እርምጃዎች አሉን፡፡ ሰሞኑንም በፍልስጤም በዚሁ ጉዳይ ላይ ስብሰባ እናደርጋለን፡፡ በስብሰባው ላይ ልንወስዳቸው በምንችላቸው አማራጮች ዙሪያ ጥልቅ ውይይት እናካሂዳለን፡፡ ዞሮ ዞሮ በምንም አይነት መልኩ የዋሽንግተንና የትራምፕን ውሳኔ አንቀበልም፡፡
የሁለቱ አገራት ግጭት “መጨረሻ አልባ” ወይም “የማያባራ ግጭት” ነው ተብሎ ይነገራል፡፡ በዚህ አባባል ይስማማሉ? ለሁለቱ አገራት ግጭት ዘላቂው መፍትሄስ ምንድን ነው ይላሉ?
የእኛ ግጭት መጨረሻ አልባ አይደለም፡፡ የፍልስጤምና የእስራኤል ግጭት መጨረሻ የሌለው ሳይሆን በአምስት ደቂቃ ሊፈታ የሚችል ነው፡፡
እንዴት? እስቲ ትንሽ ያብራሩልኝ …
እንዴት በአምስት ደቂቃ ሊፈታ እንደሚችል ላስረዳሽ፡፡ እስራኤል ዓለም በግልፅ የሚያውቀውን አለም አቀፍ ህግ፣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ስምምነትና የተቀመጡትን ሪዞሊሽኖች እንድትቀበል ጫና ቢደረግባትና ችግራችንን ጎን ለጎን ተነጋግረን መፍታት ብንችል፣ የአምስት ደቂቃ ስራ ነው፡፡ ነገር ግን እስራኤል የቅኝ ገዥነት አመለካከቷን እስካልለወጠች ድረስ ችግሩ አይፈታም፡፡ ሁለቱ አገራት “መጨረሻ የሌለው ግጭት” የሚያስብል የተለየ ታሪክ የላቸውም፡፡ እኛ ለህግ እንገዛለን ስንል፣ እስራኤል በጉልበቴ እቀጥላለሁ አለች- ይሄ ነው ችግሩ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያንና ኤርትራን ታሪክ እንውሰድ፡- ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ነበረች፡፡ በሁለቱ አገሮች ጦርነት ብዙ ህይወት ጠፍቷል፡፡ ነገር ግን እንደ መለስ ዜናዊ ያሉ ብልህ መሪዎች፣ ይህቺን አገር ነፃ እንድትሆን ለቀቋት፡፡ እርግጥ ነው ኤርትራ በመገንጠሏ ኢትዮጵያም ኤርትራም የሚያጡት ጥቅም ይኖራል፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በሁለቱም አገራት በኩል ደም መፋሰስ ቆሟል፡፡ ቢያንስ ክብሩ የሰው ልጅ ህይወት ከማለፍ ድኗል፡፡ በእስራኤልም በኩል ይህን የሚያጤን ብልህ መሪ፣ በኛም በኩል አጋር የሚሆነን አካል ብናገኝ፣ ሰላምና አብሮነትን አስፍነን፣ አብረን መኖር እንችላለን፡፡ ዓለም አቀፍ ህጎችና ስምምነቶች ካልተከበሩ ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እስራኤሎች ሳይሆኑ አይሁዶች ፍልስጤምን የተቆጣጠሩት ለ180 ዓመታት ብቻ ነው። ሙስሊሞች ደግሞ ለሁለት ሺህ አመታት ፍልስጤምን ተቆጣጥረዋል፡፡ አንዳንዴም ክርስቲያኖች፡፡ እስቲ ሁለት ሺህ ዓመታትንና 180 ዓመታትን አወዳድሪው…? እንዴት ነው የሚመጣጠነው? ዞሮ ዞሮ እስራኤል በዓለም አቀፉ ህግና ስምምነት የፍልስጤም ግዛትና ዋና ከተማ መሆኗ የተረጋገጠውን የኢየሩሳሌምን ሀቅ ከተቀበለች፣ ችግራችን በአምስት ደቂቃ ሊፈታ እንደሚችል በአፅንኦት መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ሀቁ ይሄው ነው፡፡

Read 1977 times