Monday, 18 December 2017 13:12

ያለንበት ሁኔታ ያሳስበኛል!

Written by  ሀብታሙ ማሞ
Rate this item
(8 votes)


   “--በሀገራችን አንዳንድ ክልሎች በተደጋጋሚ የሚፈጠሩና ከማንነት፣ ከድንበርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ቅሬታዎችና አልፎ አልፎም ገንፍለው ለሚወጡ ቁጣዎች ዘላቂ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ አድበስብሶ የማለፍ ውጤቱ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እየሆነ መምጣቱን ሳስተውል ቀጣዩ ሂደት ያስበረግገኛል፡፡---”
 

    መንፈሴ ለጥበብ ቅርብ ነው:: ነፍሴም አብዝታ ኪነትን ታፈቅራለች፡፡ የህይወቴ የመጀመሪያው ምዕራፍ የተሟሸው በማራኪ ጥበብ ነው፡፡ በሥነ-ጥበባዊ ክንውን ያላሸበረቀ ትዕይንት አይኖቼ ማየትን አይሹም፡፡ ይህ ብቻ ነው የኔ እውነት! ይህንንም ሀቅ በትምህርት ብቻ ያገኘሁት ወይም በተጋ ልምምድ ያበለፀግሁት ጸጋ አይደለም፡፡ ከረቀቀ መለኮታዊ ኃይል የተቀባሁት ገፀ-በረከትም ጭምር ነው እንጂ። ስለዚህም ነው የሚያሳስበኝ፡፡
በነፍሴ የሚነደው እምነት የመታደል ወይም የመመረጥ ምልክት ነው ብዬ አልታበይም። መረገምም እንዳልሆነ በልበ ሙሉነት መናገር እችላለሁ፡፡ ብቻ ግን በደፈናው ያለንበት ሁኔታ እጅግ ያሳስበኛል፡፡ በተለይም ደግሞ የሀገሬን ታሪክ የሚያጠለሽ፣ የወደፊት እጣ ፈንታዋን ከል የሚያለብስ ከፉ ጋሬጣ እንደተጋረጠባት ሳስብ ነፍሴ አብዝታ በጭንቀት ትታመሳለች፡፡
ዜጎች በዘር፣ በሐይማኖት፣ በጎሣ እንዲቧደኑ በተገነባባቸው የጥላቻ ካብ፣ በአጥቂና ተጠቂነት መንፈስ እንደ ቀላል የሚፈሰው የንፁሀን ደም ፤እንደ ቀልድ የሚወድመው የሀገር ሀብትና ንብረት እስከ ምን ድረስ ሊከፋ እንደሚችል ሳስብ ያስፈራኛል፡፡
በሌላም በኩል “ችግርህን እንቀርፍልሀለን፣ ሸክምህን እናቀልልሀለን” በሚሉ የአፈ ቀላጤዎች ተልካሻ ስብከት፣ መንበረ ሥልጣኑን የሙጥኝ ያሉ የፖለቲካ ሹመኞች፣ መልሰው የህዝብ ሸክም መሆናቸውን ሳስብ ያስጨንቀኛል፡፡ ሌላው ቢቀር በልማት ስም ከዓለም መንግስታትና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ባንኮች በብድር የሚገኙ ዶላሮች በጉምቱ የመንግስት ባለሥልጣናት ሲዘረፍና ሲመዘበር መስማት የማያስገርምና የማያስደንቅ ጉዳይ እየሆነ የመምጣቱ ነገር ከምንም በላይ ያሳስበኛል፡፡
በሀገራችን አንዳንድ ክልሎች በተደጋጋሚ የሚፈጠሩና ከማንነት፣ ከድንበርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ቅሬታዎችና አልፎ አልፎም ገንፍለው ለሚወጡ ቁጣዎች ዘላቂ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ አድበስብሶ የማለፍ ውጤቱ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እየሆነ መምጣቱን ሳስተውል  ቀጣዩ ሂደት ያስበረግገኛል፡፡
ለውድ ሀገሬ ይጠቅማታል ብለው ያሰቡትን አልያም አይተው የታዘቡትን ፖለቲካዊ ህፀፅ፣ ህገ-መንግስቱ ባጎናፀፋቸው ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ  መብት ተጠቅመው የጠቆሙ፣ ያጋለጡና የነቀፉ ጋዜጠኞችን ማሰር፣ ማዋከብና ለስደት መዳረግ መዘዙን የከፋ እያደረገው እንጂ የተሻለ መፍትሄ እያመጣ እንዳልሆነ ለመገመት ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡
በተለይም ወጣቱን ትውልድ ማዕከል ያላደረገ እስትራቴጂ አልያም ከወረቀት የማይዘልና ተግባራዊነት የጎደለው ተራ ፖሊሲ መኖር፣ ትውልድ እንዲደነዝዝና በተስፋ-ቢስነት በሱስ እንዲፈዝ የማድረግ ውጤት መዘዙ ምን እንደሆነ ለማሳየት እማኝ መጥቀስ የሚያስፈልገው ጉዳይም አይደለም፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እየተስፋፋና ስር እየሰደደ በመጣው የኑሮ ውድነት ሰበብ ታዳጊ ህፃናትን ለልመና እና ለጎዳና ተዳዳሪነት፣ ወጣት ወንዶችን ለስደትና ለዝርፊያ፣ ታዳጊ ሴቶችን ለዝሙት አዳሪነት እየዳረጋቸው እንደሚገኝ  በመዲናችን በየምሽቱ የሚበተኑ ህፃናትን፣ታዳጊዎችንና ወጣቶችን ማየት በቂ ነው፡፡ ኧረ! እንዲያው ግን ወዴት እየሄድን ነው? ይሄንንስ የጋራ ህመም የማከም ሀላፊነቱ የማነው?
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች
እንደኔ እንደኔ በግልም እንደ ኪነ-ጥበብ ባለሙያ ሆኜ ሳስበው፣ በሀገራችን የኪነ-ጥበብ ባለሙያ፣ ኪነ-ጥበባዊ ክህሎቱ እራሱን እንደ ኤሊ በድንጋይ ቅርቃር ውስጥ ወሽቆ ዝምታን የመምረጡ ጉዳይ ውሉ አልፈታ ብሎኛል፡፡ እጅግም ያሳስበኛል፡፡ “የኪነ-ጥበብ ሰው ቆዳውን ገልብጦ የለበሰ ነው” የሚል አንድ ዘልማዳዊ አባባል እንዳለ አውቃለሁ። ይህም ማለት የዜጎች እንግልት፣ እርዛት፣ ስደትና ሞት ከየትኛውም የማህበረሰብ ክፍል ቀድሞ የሚያመው፣ ስቃዩና መከራውም እየጠዘጠዘ እረፍት የሚነሳው የኪነ-ጥበብ ባለሙያን ነው እንደ ማለት ይመስለኛል፡፡
ነገር ግን ፊልማችን፣ ሙዚቃችን፣ ስዕላችን፣ ተውኔታችን ወዘተ-- ከላይ የጠቀስናቸውንና መሰል ስንክሳሮች በሰው ልጆች ላይ እንዳይደርሱ የሚያወግዙ፣ በተከሰተም ጊዜ ባፋጣኝ እንዲታረሙ የሚጠቁሙና የመፍትሄ ሀሳብ የሚያመነጩ አይደሉም፡፡ በደፈናው በሀገራችን ያለው የኪነ-ጥበብ እንቅስቃሴም ሆነ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ፣ ህብረተሰባዊ ወገንተኝነት የጎደለው፣ “የጨበራ ተስካር” እየሆነ ከመጣ ቆይቷል፡፡ እዚህ ጋ በዓለም የኪነ-ጥበብ መድረክ ላይ ተካሂዶ ስለነበር አንድ ጥበባዊ አብዮትና ታሪካዊ ክስተቱ ማስታወስ እሻለሁ፡፡ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት እ.ኤ.አ በ1914(5) ገደማ በአውሮፓ ዙሪክ፣ ስዊዘርላንድና በሌሎችም አጎራባች ሀገሮች፣ የኪነ-ጥበብን ቅርፅ ወዳልተለመደ ገፅታ የሚቀይር አንድ ታሪካዊ ክስተት ተፀነሰ፡፡ ይህም በአንደኛው የዓለም ከጦርነት ፍልሚያ  በህይወት የተረፉና ሌሎችም ጥቂት ህብረተሰባዊ ወገንተኝነት የሚሰማቸው የኪነጥበብ ሰዎችን ከፍተኛ ቁጣ፣ ሀዘንና ቁጭት ላይ የጣላቸው ክስተት ነበር፡፡
“የሰው ልጅ የሚኖርበትን ዓለም እጅግ ውብ፣ ምቹና ሰላማዊ ለማድረግ ይህንን ሁሉ የጥበብ ስራ ለዓለም አበርክቶ የሰው ልጅን አዕምሮ በመልካም ነገሮች መገንባትና ማንቃት ካልቻለ ወይም የዓለም ህዝብ ይህንን ሁሉ ስዕል እያየ፣ ይህንን ሁሉ ሙዚቃ እያዳመጠ፣ ይህንን ሁሉ ተውኔት እየተመለከተ፣ ይህንን ሁሉ መጸሐፍት እያነበበ --- አዛኝ፣ እሩህሩህና ታጋሽ መሆን ተስኖት፣ እንደ አውሬ እርስ በእርሱ የሚጨራረስ ከሆነ፣ ኪነ-ጥበብ ለሰው ልጅ አያስፈልገውም በማለት ሥነ -ጥበብብን  ዲስቶርት ማድረግ አለብን” የሚል ታላቅ መነሳት ነበር፤ በዚህም “ዳዳይዝም” የሚባል አዲስ የኪነ-ጥበብ ቅርፅ ተፈጠረ፡፡ በወቅቱም በርካታ አርቲስቶች ምስቅልቅሉ የወጣውን ይህንን ዳዳይዝም የተሰኘውን የጥበብ ዘውግ በመከተል በስዕል፣ በሙዚቃ፣ በተውኔት፣ በሥነ-ግጥም በስፋት ሥርዓቱን የመንቀፍ  ዘመቻ ጀመሩ፡፡
በብሔራዊነት ስምም በሰው ዘር ላይ የሚፈፀመዉን ሞት፣ እንግልትና ጭፍጨፋ በማውገዝ ተቃውሞአቸውን በስፋት ገለፁ። በዚህም ድርጊታቸው ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል። ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለስ፣ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች እንደዋዛ በየአደባባዩ ስለሚወድቁት ወጣቶች ነፍስ፣ የሱማሌና ኦሮሚያ ክልል ድንበር አዋሳኞች ላይ ስለሚፈጠረው የእርስ በእርስ ግጭት፣ ስለጠፋው ህይወትና ከትውልድ ቀዬው ስለሚፈናቀለው ዜጋ ወይም ከዚህም ወረድ ስንል የውርደታችንና የውድቀታችን ልክ ቅጡን ሲያጣ፣ በኳስ ጨዋታ ሰበብ የብሔርተኝነትን ጃኖ ደርቦና ተቧድኖ ስለሚቧቀሰው ወጣት--- ባጠቃላይ እነዚህንና ሌሎችንም ፈርጀ ብዙ አይረቤነትን እንድንጎናፀፍ ያደረጉንን ክፉ ሀሳቦች ከመንቀፍ፣ ከማውገዝና ከማረም አንፃር ሃላፊነታችንን ሳንወጣ መቅረታችን የታሪክ ተወቃሽ እንደሚያደርገን ሳስብ፣ ለራሴም ለሙያ አጋሮቼም እፈራለሁ፡፡
የሀይማኖት አባቶች
የአንድ ሀይማኖት አባት ቀዳሚ ስራው በመንፈሳዊና በሀይማኖታዊ አስተምህሮ፣ የሰው ልጅን እንደ አዲስ መስራት ይመስለኛል፤ ይህም ሲባል አስተዋይነት፣ ታጋሽነት፣ አዛኝነት፣ ለጋስነትና ሌሎችን ከመንፈሳዊ፣ ከማህበራዊና ከሰብአዊ ሞራሎች የተገነባ ትውልድ ማፍራት እንደሆነ አስባለሁ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግን የነዚህ አባቶች  መንፈሳዊ ትምህርቶች ትኩረት እየሆነ የመጣው ሰብአዊነትን ከመገንባት ይልቅ ቁሳዊ ነገሮችን የማልማት ተልዕኮ ላይ ትኩረት ያደረገ ይመስለኛል፡፡ የሀይማኖት ተከታዮችም ወደየ አምልኮ ስፍራዎች የሚሄዱት ሰብአዊ ማንነታቸውን በመንፈሳዊ አስተምህሮ ለመገንባት ሳይሆን  የእምነት ተቋማትን በድንጋይ ለማነፅና ለማስዋብ ብቻ እየሆነ የመምጣቱ ጉዳይ ያሳስባል፡፡
እስከሚገባኝ ድረስ የአንድን ትውልድ ሞራልና ማንነት ከሚገነቡ ምሰሶዎች  መካከል የሀይማኖት ተቋማት ያላቸው ሚና ቀላል አይደለም፤ ግና እኛም ሆንን ልጆቻችን በመንፈሳዊ፣ ሰብአዊና ማህበራዊ እውቀቶች የማንሰራበትን የእምነት ተቋም እንድንሰራ ብቻ የሚወተውቱን የሀይማኖት አባቶች እየበዙ መምጣታቸው ጉዳይ እንደ ቀላል ነገር መታየት ያለበት አይመስለኝም፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች
የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ መጥራት ያለበት ውዥንብር ያለ ይመስለኛል፡፡ መሰረቱ በአሸዋ ደለል ላይ የተጣለ ግንባር፣ ንቅናቄ፣ ህብረትና መድረክ የማቋቋም ትርፉ፣ በንፋስ የመበተን ሲሳይ ከመሆን በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የመገንዘብ ችግር እንዳለ በስፋት ይታያል፡፡
በሀገራችን በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ባህል፣ ታሪክ፣ ሀይማኖት፣ መልክአ  ምድራዊና ተፈጥሮአዊ መስተጋብር በጥልቀት በመረዳት፣ በጋራ የሚያስማሙና ታሪካዊውን አንድነት በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚያስችል የትግል እስትራቴጂ ቀርፆ፣ ታግሎ የማታገል ድክመት ጎልቶ ይስተዋላል፡፡ ምርጫ በደረሰ ቁጥር የምርጫው ንፋስ በነፈሰበት አብሮ መንፈስ፣ የባላጋራን ወይም የተፎካካሪን ድል ከማጀብ የዘለለ ውጤት እንደሌለው ከታሪክ መማር ያለመቻላችን በእጅጉ  ያሳስበኛል፡፡
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በፌስቡክ ገፁ ላይ በተለይም የፓርቲ አመራሮችና ደጋፊዎች ሊያስተውሉትና በጥልቀት ሊገነዘቡት የሚገባ ቁም ነገር አስፍሯል። “-- በሀገራችን ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊፈርሱ፣ ሊበተኑና ሊከስሙ ይችላሉ፤ በተለያየ ጊዜም ተበትነው ፈርሰውና ከስመው አይተናል፡፡ ሆኖም የምትበተንና የምትፈርስ ሀገር ግን የለችንም፤ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቅልም፣ እኔ ከሌለሁ ሀገር ትበተናለች ወዘተ… ማለት በዚህ የሠለጠነ ዘመን ከቶ አይሰራም፤ ኋላ ቀርነትም ጭምር ነው፡፡ ትላንት የነበሩት ሄደዋል፤ዛሬ ያሉትም ነገ ይሄዳሉ፤ ነገ የሚመጡትም በዚህ ታሪካዊ መንገድ ነው የሚያልፉት፡፡ ሀገርና ህዝብ ግን ለዘመናት ይኖራሉ!---”
ጋዜጠኛው ይህንን ሀሳብ በውብ ቋንቋ ገልፆታል፡፡ ሁላችንም አሁን ከ”አያገባኝም” መንፈስ መላቀቅ የሚገባን ሰዓት ላይ የደረስን ይመስለኛል። በየትኛውም ሙያና በማንኛውም ሁኔታ ላይ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ስለ ሀገሩ ሊያስብ ይገባል ብዬ አምናለሁ። አገሩን ከጥፋት ለማዳን የድርሻን መወጣት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡
ካለፈው ስህተት ተምረን መንገዳችንን ማቅናት አለብን እላለሁ፡፡ በታሪክ ፊት መቆማችንን አስተውለን፣ ነገርን በልክ፣ ተግባርን በማስተዋል፣ ቃልን በጣዕም፣ አንድነትን በከፍታ የምንገልፅ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ አቦ ቸር ይግጠመን!!

Read 2981 times