Monday, 18 December 2017 13:24

“ሁለተኛው መምጣት” የትኛው ነው?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ሁለተኛው ምጣት “The second coming” የትኛው “ምጣት” ነው? ዊሊያም በትለር ዬትስ “Things fall apart/the center can not hold/… ያለው ማለቴ ነው፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አይደለም፡፡ እሱ አልፏል፡፡ … በወቅቱ የነበሩት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የዓለም ፍፃሜ መስሏቸው ነበር፡፡ አሁን እኔ እየተመለከትኩ ካለሁት ዓለም ጋር ሳነፃፅረው፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንደ ፍፃሜ ሳይሆን እንደ መልካም መጀመሪያ ውብና የሚናፈቅ ሆኖ ነው፡፡
በአጭሩ አሁን ያለሁበትን፣ የሚታየኝን ዓለም ልገልፀው ፈለግሁኝ፡፡ መግለፅ መፍጠር ነው፡፡ የዊሊያም በትለር ዬትስ “Second coming” የተፃፈው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ቀደም ብሎ ነው፡፡ በቅርብ የተነጣጠረ ራዕይ ሊባል ይችላል፡፡ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት እንደ ክርስቶስ መምጫ አድርጎ ነበር የቆጠረው፡፡ ዊሊያም በትለር ዬትስ “በቅርቡ የዓለም ፍፃሜ ይከሰታል” ለማለት ነበር ግጥሙን የፃፈው፡፡
ዓለም እንደ ግጥሙ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ዳር እስከ ዳር ተንጣለች፡፡ ግን ፍፃሜ ደረጃ አልደረሰችም፡፡ ገጣሚው ራዕዩን ለቅርብና ለሩቅ እንዲሆን አነጣጥሮ ነው የተኮሰው፡፡ ለሰማይና ለጣራ በአንድ ጊዜ አልሞ ነው ግጥሙን ራዕይ አድርጎ የፃፈው፡፡ ጣራው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሆነ፡፡ ሰማዩ የመጨረሻው የዓለም ፍፃሜ፣ የክርስቶስ መምጫ፣ የቅያማ ቀን … ወዘተ፡፡ የዊሊያም በትለር ዬትስ ግጥም፣ ለአጭር ጊዜና ለመጨረሻውም ጊዜ የሚሰራ ነው፡፡ የመጨረሻው ዘመን በቅርቡ ከመጣ ጣራው ሰማይ ይሆናል፡፡ መጨረሻ መስሎ ማለፊያ የሆነ የሰቆቃ መሸጋገሪያ ከተገኘም ግጥሙ መጨረሻውን ለመጠባበቂያ ይሆናል፡፡
ምናልባት ልዕለ ጥበበኛ “በጥበብ ዘመን ተሻጋሪ ይሆናል” የሚባለው እንዲህ በስራው ውስጥ የረጅምና የአጭር ጊዜ አላማ እያስቀመጠ ስለሚያልፍ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጥበበኛው ዬትስ በ“second coming” ግጥሙ እጅግ ስኬታማ ሆኗል፡፡ ግጥሙ በሌሎች ከባድ ሚዛን ገጣሚያንና ደራሲያን ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ የቺኑዋ አቼቤ “Things fall apart” የሚለው የአንዱ ድርሰት ስራው አርዕስት በዚሁ “የሁለተኛ ምጣት” ግጥም አንጓ የተቀነጠሰ ነው፡፡
እርግጥ እኔ ገጣሚ አይደለሁም፡፡ ግን ፎርሙላው ገብቶኛል፡፡ ወደፊት የሚከሰተውን ለማወቅ እንደ ታሪክ አዋቂዎች የቀድሞውን ታሪክ ማጥናት አያስፈልገኝም፡፡ ከኋለኛው ታሪክ አንድ ነጥብ ብቻ እይዛለሁኝ፡፡ ወደ ኋላ ያለው ታሪክ “መጀመሪያ” አለው፡፡ ይኼ ነጥብ በቂ ነው፡፡ የኋለኛው ታሪክ መጀመሪያ እንዳለው ሁሉ … መጪው ታሪክ ደግሞ “መጨረሻ” አለው፡፡ ይኼንን የሚያውቅ ሁሉ ባለ ራዕይ ነው፡፡ የተጀመረው ነገር መጠናቀቁ አይቀርም፡፡ መጠናቀቁ እንደማይቀር በደመነፍስ ሳይሆን በሳይንስም ሆነ በፍልስፍና ሜታፊዚካል መጠይቅ መልክ ተጠቅመን ብንመረምር የምንደርሰው አንድ ነጥብ ላይ ነው፡፡ የተጀመረ ነገር ሁሉ መጠናቀቁ … በዚህም ተባለ በዛ አይቀርም፡፡
ምናልባት ልዩነትና የሀሳብ ግጭት ሊነሳ የሚችለው ከዚህ ጥልቅ ስምምነት ወደ ተናጠልና “specific” ጉዳዮች ስንመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ መጨረሻው መቼ ነው በእርግጥ የሚሆነው? … ያወዛግባል፡፡ ከጊዜ ጋር የ “ሳቢያ ወይንም መንስኤ” ጉዳይ ይመጣል፡፡  በምን ምክኒያት ነው መጨረሻው በተባለው (መቼ) ላይ የሚያርፈው፡፡ በግርድፉ ነጥብ፤ ማለትም “የተጀመረ ነገር መጠናቀቁ አይቀርም” የሚለውን በተመለከተ ሁላችንም ባለ ራዕይ ነን፡፡ ልዩ ባለ ራዕዮች የሚያስፈልጉት የጊዜና ቦታ፣ የሳቢያና መንስኤን … ትንንሽ ጥያቄዎች እንዲመልሱልን ብቻ ነው፡፡ ትልቁን እውነት ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ጥቅሉን እውነት በማወቅ ረገድ ሁላችንም አንድ አይነት ነን፡፡ ልዩነት የሚመጣው በትንንሾቹ ጥያቄዎች ላይ ነው፡፡
በአእምሮአችን የሚመጡ ሀይማኖታዊም ሆኑ ዓለማዊ ባለ ራዕዮች ወይንም ትንቢት ተናጋሪዎች ትንንሹን ጥያቄ ለመመለስ የቻሉ ናቸው፡፡ ግን ትንንሾቹን ጉዳዮች በደንብ ቢተነብዩም ስለ መጨረሻው ግን የሰጡት ትንበያ ትክክል መሆኑ የሚታወቀው ፍፃሜው ላይ ነው፡፡
ባለ ራዕይ ማለት፤ መጨረሻውን በቅርብና በሩቅ በሁለቱም አንፃር ገፍቶ ጥሩ ግምት ማስቀመጥ የቻለ ማለት ነው ለኔ፡፡ ዊሊያም በትለር ዬትስ ይሄን ነው በግጥም ያደረገው፡፡ ምጣት አንድ ሆኖ እንደማይቀር ገብቶታል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ይገባናል፡፡ ሁላችንም ባይገባን ኖሮ ግጥሙም በተለያዩ የፍፃሜ አደጋ ሞዴሎች ላይ እየለዋወጥን ባልሞከርን … ግጥሙም ተራ ሆኖ በተረሳ ነበር፡፡
ግን ዊሊያም በትለር ዬትስ እኛ የምንፈራውን የሚፈራ፣ እኛ የምናውቀውን የሚያውቅ ገጣሚ ነው፡፡ እኛ የምንፈራው ፍፃሜውን ነው፤ እኛ የምናውቀው መጨረሻው እንደማይቀር ነው፡፡ አንዴ መጥቶ፣ የመጣበትን ግብ ሳይፈፅም የሄደ ጥፋት ተመልሶ መምጣቱ እንደማይቀር እንሰጋለን፡፡ ስጋታችን ከምናውቀው ነገር የመነጨ ነው፡፡ እውቀታችን ለሁላችንም አንድ ነው፡፡
ክርክሩ ያለው የጊዜና ሳቢያ መንስኤ ላይ እንጂ መምጣቱ የማይቀረው መጨረሻ “እንደወጣ እንደማይቀር” እናውቃለን፡፡ ክርክሩ ያለው “ጊዜው አልደረሰም” እና “ጊዜው ደርሷል” በሚሉ ገማቾች ላይ ነው፡፡ አሁን ባይደርስም መድረሱ ግን እንደማይቀር ሁሉም ያውቃል፡፡
ገጣሚ፣ ጥበበኛ ጥበቡን ዘላለማዊ ለማድረግ ካለው ፍላጎት የተነሳ እሱም ከጊዜ ጋር ጠበኛ ነው፡፡ ሀይማኖተኞች ወይንም ትንቢተኞች (ሳይንስም የትንቢተኛ አይነት ነው፤ የትንበያ ዘዬው ቢለያይም) “ጊዜው አልደረሰም/ደርሷል” ነው የሚያከራክራቸው፡፡ ለቅርብም የሚሆን ዜማ ይፈበርካል፡፡ ቅርበትና ርቀት መሀል ያለውን የጊዜ ትርጉም የሚዋጅ ግጥም ከተፈበረከ ጊዜ ከጥቅም ውጭ ይሆናል፡፡ ወይንም በገጣሚ ሰለሞን ደሬሳ አገላለፅ፡- “የጊዜ ቋንጃ ተበጥሷል፡፡” “የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ልኳንዳ ቤት ቀረ” የሚል የመዘባበቻ ሀረግ አብዝተን ስንጠቅስ እንደመጣለን፡፡ ጥጃውን መመሰል የተፈለገው በሰው ልጅ ነው፡፡ እንጂማ ጥጃ የት ይደርሳል፣ ከልኳንዳ ቤቱ ውጭ? …
ግን እቺ የጥጃ አባባል የቅርቡን ራዕይ የምትገልፅ ትመስለኛለች፡፡ የሰው ልጅ ስንት ጠፈር ቧጥጦ፣ ስንት ተአምር ይፈጥራል ሲባል፣ በሁለተኛው አለም ጦርነት ኒዩክለር ቦንብ እርስ በራሱ እጣ ተጣጥሎ ድምጥማጡ ጠፋ … እንደ ማለት ሊታይ ይችላል፡፡ ግን የፈለገ ጠፈር ቢቧጥጥም “በስተመጨረሻ እህሳ?!” ከተባለ፣ ያው ፍፃሜው ጋር ደረሰ ነው መልሱ፡፡ የጥጃውም መጨረሻ ልኳንዳ ቤቱ፣ የሰውም ፍፃሜ ሞቱ ነው፡፡ አሰቃቂ ወይንም ሰላማዊ ብለን ሞቱ የቀረበበትን ሁኔታ ብንገልፀውም በመጨረሻው ሞቱ ነው፡፡ መጨረሻው ይህ መሆኑን ሁሉም ያውቃል፡፡ የት ይደርሳል የተባለ! እያለ ይዘባበታል፡፡ ህይወቱን በተለያየ ሰው ሰራሽ ትርጉሙ ቅርፅ አንፆ፣ መጨረሻውን የረሳ ይመስላል፡፡ አንድ ባለ ራዕይ በገጣሚ ወይንም በትንቢት ተናጋሪ መልክ ተነስቶ ስለማይቀረው ነገር ሲያስታውሰው ይደነግጣል፡፡ የመደንገጥና የማስደንገጥ ሚና ለራሳቸው በይነው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አሉ፡፡ አስደንጋጮቹ “ጊዜ ደርሷል!” የሚሉት ናቸው፡፡ “ወይኔ ኖሬ ሳልጠግብ፣ መሞት ሳልለማመድበት” ብለው የሚደነግጡትን የሚያስጥሉ አላጋጭ ነን የሚሉ ይነሳሉ - “የዓለም ፍፃሜ ደርሷል” የሚሉት ውሸት ነው … ፀሐይ ተነፋፍታ እስክትፈነዳ 20 ቢሊዮን አመት ገና ይፈጃል ይላሉ፡፡
ካርል ፓፐር የሚባል በሳይንስ ላይ ጥሩ አድርጎ በመፈላሰፉ የሚከበር ሰው፣ ስለ ትንቢት የሚለው ነገር እኔ ከምለው ጋር በጣም ልዩነት እንዳለው መጠቆም እፈልጋለሁኝ፡፡ ፓፐር በመሰረቱ ትንቢትና ሳይንስ ሁለት በተለያዩ ቋንቋ የሚያወሩ፣ አንዱን ቋንቋ ወደ ሌላው መቀየር የማይቻል፣ የተለያዩ አለማት ፍጥረት ናቸው ይላል፡፡ ወይንም እንደማለት ይቃጣዋል፡፡
እሱ ትንቢትን እምነት በሚል መጠቅለያ ነው የሚጠራው፡፡ እምነት ማለት እኔ ከላይ ስፅፍ የመጣሁትን ሁሉ ሳያጓድል ይላል፡፡ ሀይማኖት ግን እኔ ስል ከመጣሁት በተጨማሪ ከማይቀረው መጨረሻ ማስጣያ መፍትሄው እኔው ዘንድ ነው ይላል፡፡ በዓለም ላይ የገነኑ ሀይማኖተኞች በተለይ ከክርስትና በኋላ ያሉት ይሄንን ነው የሚሉት፡፡ የማስጣያ መፍትሄው ሁሉም ሀይማኖቶች ጋር ሳይሆን “እኔ ብቻ” ጋር ነው የሚለው ያስማማቸዋል፡፡ … ለሁሉም የማይቀረው መጨረሻ “ከእኔ ብቻ ጋር ከሆንክ” ለአንተና እኔ የመጨረሻው መጀመሪያ ይሆንልናል…፡፡ ሁሉም በተናጠል … በእየ ዘውጋቸው ሆነው ይሄንን ይላሉ፡፡ ያሉትን ለማሳመን ይጥራሉ፡፡
ካርል ፓፐር “ትንቢት ወይም ሀይማኖት ሊመረመር (verify ሊደረግ) ስለማይችል ውሸት መሆኑንና ማረጋገጥ፣ ወይንም መፈተን አይቻልም” ይላል፡፡ በካርል ፓፐር ፍልስፍና፤ ዋነኛውና እና ቁልፉ ነገር “falsifibility” ነው፡፡ “አንድን ሀሳብ ወይንም ኩነት ውሸት መሆኑን ማረጋገጥ በሚያስችል ደረጃ ሊፈተን የሚችልበት ክፍተት ከሌለው … ይሄ ነገር ሃይማኖት ነው” ይላል፡፡ ይቀጥልናም፤ “ሁሉም “ሳይንስ” … ውሸት መሆኑን የሚያሳይ ክርክርን የማስተናገድና በቤተ ሙከራ የመፈተን ክፍት አቋም አለው” ይላል፡፡
በዚህ ሀሊዮት አንፃር እኔ እየፃፍኩ የመጣሁትን ምልከታዬን አጉልተን ስንመለከተው፣ ትንቢት እንጂ ሳይንስ እያወራሁ እንዳልሆነ ወዲያው ግልፅ ይሆንልናል፡፡ እኔ ከመነሻው እንደ ሚስማር እየደጋገምኩ ስቀጠቅጠው የነበረ አረፍተ ነገር ነበር፡፡ ይኼ አረፍተ ነገር “መጀመሪያው እንዳለ ሁሉ መጨረሻው መኖሩ አይቀርም” የሚል ነው፡፡ መጨረሻው ስለመኖሩ ከእምነት ውጭ ፍፃሜውን አቅርቦ በማሳያ መነፅር አስጠግተን ማጥናት ስለማንችል፣ ይህ አረፍተ ነገርን በሳይንሳዊ መንገድ “falsify” ማድረግ አንችልም፡፡ በሳይንሳዊ መንገድ ሊመረመሩና መረጃ ሊቀርብባቸው የማይችሉ ድምዳሜዎች ሁሉ በ“ሃይማኖት” ወይ “እምነት” ዘውግ ስር ለካርል ፓፐር የሚካተቱ ናቸው፡፡ … በሳይንስ ተመርምረው የእውነት (fact) እና የውሸት (belief) መጠናቸው ሊታወቅ (verify ሊደረግ) አይችልም፡፡ ስለማይችል አይመረመሩም፡፡ ስለማይመረመሩ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ሃይማኖት ከትንቢት ንጥረ ነገር የሚሰራ ርዕዮተ ዓለም (world view) ነው፡፡ ሳይንስ ደግሞ ከተጨባጭ መረጃ፡፡         

Read 1683 times