Monday, 18 December 2017 13:27

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

 በቀደም ባለ ጊዜ ነው፡፡ አንድ ጓደኛችን ጥርሱን ማፅዳት ፈለገ፡፡ የጥርስ ሳሙናውን በአንድ እጁ ይዞ በሌላኛው ብሩሹን ፍለጋ ዕቃዎቹን ይበረብራል። … አንዱን ሲያነሳ፣ አንዱን ሲጥል አካባቢውን አተራመሰ፡፡ … ብሩሹ አልተገኘም፡፡ … ቢቸግረው ቆሞ ማሰብ ጀመረ፡፡ ይህን ያስተዋለው ባልደረባ፡-
“ምንድነው የጠፋብህ?” ብሎ ቢጠይቀው … አጅሬ “የጥርስ ብሩሽ” ለማለት አፉን መክፈት አቃተው፡፡ … ብሩሹን ሰክቶበት ነበረና!!
ወዳጄ፤ አንዳንድ ጊዜ በእጃችን ያለውን ሌላ ቦታ እንፈልገዋለን፡፡ ቅርብ ያስቀመጥነው ሩቅ ይሆንብናል፡፡ ለአገራዊ ችግሮቻችንም መፍትሄዎች በእጃችን እያሉ ሌሎች ሰዎች እስኪነግሩን አናስታውሳቸውም፡፡ … ይህ ማለት አልፎ አልፎም ቢሆን የሌሎች ሰዎች ወይም ተቋሞች ሀሳብና ድጋፍ ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡ .. የኛም ደግሞ ለነሱ፡፡
ወዳጄ፤ እንኳን የአንድ አገር ቀርቶ የዓለም ስርዓት የቆመው በተለያዩ ህዝቦች መደጋገፍና መረዳዳት መርህ ላይ ተመስርቶ ይመስለኛል፡፡ … አምርተን ለሌሎች ህዝቦች እንሸጣለን፣ የሌለንን ከነሱ እንገዛለን፡፡ ዓቅም ቢኖረን የሌላቸውን እንረዳለን፣ ዓቅም ስለሌለን አቅም ባላቸው እንረዳለን፡፡ … ዕውቀታችንና ልምዳችንን ይካፈላሉ፣ የነሱንም እንማራለን፡፡ … ስራ ፍለጋ ወደነሱ እንሄዳለን፣ ሰላም በሚጠፋበት ጊዜ ወይም ጭቆና ሲጫነን ወደ እነሱ እንሰደዳለን፡፡ እኛም ከሌሎች ቦታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀገራችን በስደት የሚመጡትን ወገኖች እየተቀበልን እናስተናግዳለን፡፡
አላስፈላጊ ባልሆነ ጦርነት አገራቸው የሚታመሰው ሊቢያ፣ ሶርያ፣ ፍልስጥኤም፣ የመን፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሌሎች ሀገራት ዜጎች ከሃገራቸው እየሸሹ፣ በሌሎች ሀገራትና ሌሎች ህዝቦች ድጋፍ ይኖራሉ፡፡ አገራቸው ሰላም ሆኖ ፍትሃዊ የአስተዳደር ስርዓት ቢኖራቸው እነሱም ለሌሎች ግፉዓን መጠለያ ይሆኑ ነበር፡፡ ወዳጄ፤ አገር የሌለው ህዝብ ያሳዝናል!!
ከተማን መገንባት አያስቸግርም ይባላል፡፡ ሐገር መስራት ግን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሃገር ለቁጥር የሚታክት የዘመን ጉዞ ውልደት ናትና!! … ሰማይ ለሰማይ የምትበረውን ወፍ ስታዳንቅ በእጅህ ያለችው እንዳታፈተልክ ተጠንቀቅ የሚባለው ያለ ምክንያት እንዳልሆነ ከሌሎች መማር ብልህነት ይመስኛል፡፡
ለማንኛውም ወዳጄ፤ በዚህ ዘመን የህዝቦች መተጋገዝና መተባበር አማራጭ የሌለው የህልውና ጉዳይ ሆኗል፡፡ .. የመኖር ወይ ያለመኖር!! …
ዎልፍ ጋንግ ገተ፡- “… ሰው በራሱ መንገድ ህይወቱን የሚመራ ይመስለዋል፡፡ ቆም ብሎ ካሰበ ግን ዕጣ ፈንታው እየጎተተ ወደ አላሰበው ግብ እየነዳው መሆኑ ይገባዋል፡፡” (“… man thinks he directs his life; but his innermost being is irresistably drawn in the direction of his destiny) … ይለናል፡፡ .. የነገን ማን ያውቃል ወዳጄ?
ሊቃውንት፡- “ሌሎች ሰዎች ሌሎች ሰዎች ውስጥ፣ ሌሎች ነገሮች ሌሎች ነገሮች ውስጥ፣ ሌሎች ሃሳቦች ሌሎች ሃሳቦች ውስጥ አሉ፡፡” ይሉናል፡፡ … ሌሎች ሰዎች ውስጥ ሌሎች ሰዎች አሉ ማለት ከትልልቆቹ ስረ ነገዶች ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለውን የሰው ልጆችን የዘር ሃረግ ተዛማጅነት ለማመልከት ሲሆን ሌሎች ነገሮች ውስጥ ሌሎች ነገሮች አሉ መባሉ ደግሞ … ለምሳሌ አንድ ወንበር፣ መድኃኒት ወይም ሌላ ዕቃ የታነፀበት ስረ ነገር ሲመረመር ሶስቱንም አንድ የሚያደርጋቸው ንጥረ ነገር አለ ለማለት ነው፡፡ … ቀጥ ያለ መስመርና ክብ ወይም አራት ማዕዘን የተሰሩት ከትንንሽ ነጥቦች ነው እንደ ማለት፡፡ …
እንዲሁም ሌሎች ሃሳቦች ውስጥ ሌሎች ሃሳቦች አሉ ሲባል፣ የተፈጥሮና የህብረተሰብ ሳይንስ ተመራማሪዎችን ምሳሌ ማድረግ ይቻላል። ተመራማሪዎቹ ተያያዥነት ባለው መንገድ አንዱ የጀመረውን ንድፈ ሃሳብ ወይም ሙከራ ውጤት እስኪገኝ ድረስ ሌላው እየተቀበለ ያሳድገዋል ለማለት ሲሆን ቁም ነገሩ የሰው ልጅ እስካለ ድረስ ማህበራዊነት አይቀሬ ነው ለማለት ነው፡፡ … ሰው ደግሞ ሁሌም አለ!!
አርስቶትል፡- “ሰዎች ይመጣሉ፤ ይሄዳሉ፤ ሰው ግን ለዘለዓለም ይኖራል፡፡” … (Men come and go but man goes forever` …በማለት ይህንኑ ሃቅ አረጋግጧል፡፡… ትውልድ ትውልድን እየተካ፣ የሰው ልጅ እያወቀና እየነቃ፤ ድንቁርናን እያሸማቀቀ ይጓዛል፡፡… በጎ በጎውን እየመረጠ፤ ባህል እየተባሉ የተጫኑበትን ጎታች ወግና ልማዶች እያስወገደ ወደፊት ይራመዳል፡፡
ወዳጄ ልቤ፤ ወደ መጀመሪያ ሃሳባችን ስንመለስ፣ በእጃችን ያለን ነገር ሌላ ቦታ እንፈልገዋለን ወይ ሌላ ሰው ያስታውሰናል ብዬህ ነበር፡፡… አንዲት mystic ተረት ልጨምርልህ፡፡
ሰውየው አዲስ ቤት ለመስራት ምሰሶ አስፈለገው፡፡ መጥረቢያውን ስሎ ዱር ወረደ። ለብዙ ሰዓታት ሲፈላለግ ቆይቶ የሚሆነው ዛፍ አገኘ።… ሊቆርጠው ሲዘጋጅ “አትቁረጠኝ” የሚል ድምፅ ተሰማው፡፡… ደነገጠ፡፡… አካባቢውን እየተዟዟረ ተመለከተ፡፡… ከአእዋፍ፣ ትላትሎችና ጥቃቅን ነፍሳት በስተቀር ምንም የለም፡፡… ቢጠብቅ፤ ቢጠብቅ ድምጹ አልተደገመም፡፡.. ሰዓቱ ደርሶ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ አልጋው ላይ ሆኖ ሲያስብ ድምፅ መስማቱ ትክክል መሆኑን አልተጠራጠረም።… የሰማውን ድምፅ ማመን ግን አልፈለገም፡፡
በማግስቱ ሄዶ ቆረጠው፡፡… ቤቱን ሰርቶ ጨርሶ እንደገባ ግን “አትቁረጠኝ እያልኩህ ቆረጥከኝ”…የሚል ድምፅ ጆሮው ውስጥ መጮህ ጀመረ፡፡ ዕንቅልፍ አጥቶ ሲጨነቅ አደረ፡፡… ጠዋት ተነስቶ ቤቱን አቃጠለና ወደ ቀድሞ መኖሪያው ተመለሰ፡፡… አልለቀቀውም፡፡… ሰፈር ለወጠ…ያው ነው፡፡ ከተማ ቀየረ… ባሰበት፡፡ በመጨረሻም አበደ፡፡… እንዳበደ ድምፁ ቆመ፡፡… እሱ ግን “አትቁረጠኝ እያልኩ ቆረጥከኝ”… እያለ በየሄደበት መለፍለፍ ጀመረ፡፡…
አንድ ቀን አንድ መንገደኛ ላይ እንደለመደው “አትቁረጠኝ እያልኩ ቆረጥከኝ”…ብሎ ሲጮህበት…መንገደኛው በመደናገጥ… “ይቅርታ!” ብሎት አረፈ። ዕብዱ “ይቅርታ!”
የሚለውን ቃል ከመስማቱ ዕብደቱ ቆመ፡፡ … በትክክል የሆነውን ሁሉ አስታወሰ፡፡ … “ይህ ሰው ምንም ሳያጠፋ ይቅርታ ጠየቀኝ፡፡ እኔ ግን የስንት ፍጡራን መኖሪያ የሆነውን ዛፍ ስቆርጥ ጥፋት አልመሰለኝም ነበር፡፡” አለ ለራሱ፡፡ ዱሩን ይቅርታ ለመጠየቅ ወደ ነበረበት ከተማ ተመለሰ፡፡ ቦታው ተቀያየረበት፡፡ … አካባቢው ተለውጧል፡፡ … በእጅጉ አዘነ፡፡ … ተፀፀተ፡፡
ወዳጄ፤ ሰውየው የሰራው ስራ ጥፋት መሆኑን ጆሮው ውስጥ ድረስ ሲያቃጭልበት ወዲያውኑ ይቅርታ ጠይቆ ህሊናውን ማፅዳት ሲችል፣ ሌላ ሰው እስኪያስታውሰው ድረስ ጠበቀ፡፡ … ሌርሞንቶቭ፡- “ደወሎቹ ይጮሃሉ፣ ነጎድጓዳው ነፋስ ደግሞ ኡኡታቸውን እየነጠቀ ይሸሻል፡፡” እንደሚለው መሆኑ አይመስልህም?
ሠላም!      


Read 1064 times