Monday, 18 December 2017 13:43

በመተሃራ ተቀብሯል የተባለው ከ3700 ኩንታል በላይ ስኳር ጥያቄ አስነስቷል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 · ዋናው ኦዲተር የተባለው ስኳር መቀበሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላገኘሁም ብሏል
          · ስኳሩ ስለተበላሸ በአፈር ለውሰው መቅበራቸውን የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ተናግረዋል
          · የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ፤ አሳማኝ ማስረጃ እንዲቀርብ ጠይቋል
          · ኮርፖሬሽኑ የሰራተኛ ደመወዝ መክፈል ወደማይችልበት ደረጃ ደርሷል
          
    በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ተገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ከገባው ሁለት መርከብ ስኳር 3 ሺ 777 ኩንታሉ ተበላሽቷል በሚል ምክንያት፣ በስኳር ኮርፖሬሽን እንዲቀበር ተደርጓል የተባለው ስኳር ጉዳይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡
ፌደራል ዋናው ኦዲተር፤ ስኳሩ ስለመቀበሩ የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳልቀረበለት ገልጿል፡፡
ዋናው ኦዲተሩ ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ እንደገለፀው፤ ኮርፖሬሽኑ በውጪ ምንዛሪ ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ካስገባው 2 መርከብ ስኳር፣ 3777 ኩንታሉ ተበላሽቷል በሚል መቀበሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላገኘሁም ብሏል፡፡ በጉዳዩ ላይ የተወያዩት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ ኮርፖሬሽኑ ስኳሩም ከተበላሸ በአግባቡ ካሳ መጠየቅና ማስከፈል ሲገባው ማረጋገጫ ማቅረብ ባልቻለበት ሁኔታ ቀብሬዋለሁ ማለቱን በግልፅ እንዲያብራራ ጠይቀዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ የፋይናንስ ማሻሻያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሳ ዘይኑ መሀመድ ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ማብራሪያ፤ ስኳሩ ከውጪ ተገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ መተሃራ ላይ እንዲከማች ተደርጓል፤ ስኳሩ በመርከብ ሲመጣ ተበላሽቶ ነው የመጣው፡፡ በዚህ ምክንያትም የስኳሩ ናሙና በላብራቶሪ እንዲታይ ሲደረግ ለጤና ተስማሚ እንዳልሆነ በመረጋገጡና ለምግብነት የማይውል በመሆኑ እንዲወገድ ተደርጓል ብለዋል። ስኳሩን ለማቃጠል ፈልገው ለአካባቢው ጥበቃ ጥያቄ ቢያቀርቡም “ማቃጠል አትችሉም” በመባሉ ምክንያት ሰዎች ቆፍረው በማውጣት ጥቅም ላይ እንዳያውሉት በአፈር ለውሰን ቀብረነዋል ብለዋል - የአይን እማኞች እንዳሏቸው በመግለፅ፡፡
ጉዳዩን ሲመረምር የዋለው የመንግስት ልማት ድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ፤ ኮርፖሬሽኑ በዋናው ኦዲተር የቀረበበትን የኦዲት ግኝት ሪፖርት ለማስተባበል የሚያስችል በቂ መረጃ አላቀረበም፤ በኃላፊዎቹ የተሰጠው ምላሽም አጥጋቢ አይደለም ብሏል፡፡
የፌደራል ዋናው ኦዲተር መ/ቤት በስኳር ኮርፖሬሽን ላይ ያቀረበው ኦዲት ግኝት ሪፖርት፤ መካከል ኮርፖሬሽኑ የጀመራቸውን አዳዲስ ፕሮጀክቶች በተባለው ጊዜና ወቅት ሳይፈፅም ለአመታት የሚቆይ መጓተቶችን በመፍጠር፤ አገሪቱን ለተጨማሪ ከፍተኛ ወጪ እየዳረጋት ነው የሚል ይገኝበታል፡፡ የፕሮጀክቶቹ መዘግየት አገሪቱን ትልቅ ፈተና ላይ ከቷታል ያለው የኦዲት ሪፖርቱ፤ ለመንግስትም ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኗል ሲል ገልጿል፡፡    
ኮርፖሬሽኑ ለየፋብሪካው የገዛቸው አዳዲስና ዘመናዊ ማሽነሪዎች አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ምክንያት ቆመው እንደሚገኙና ይህም አገሪቱን ለታላቅ ኪሳራ እንደዳረጋት ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ የአዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደቶችም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
በጉዳዩ ላይ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች፤ ኮርፖሬሽኑ እጅግ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው ፋይናንሱ ጤናማ ያልሆነ፣ እዳው የበዛና በችግሮች የተተበተበ ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አዳዲሶቹን ፕሮጀክቶች እያኖሩ ያሉት ነባር ፋብሪካዎቹ ናቸው ያሉት የሥራ ኃላፊዎቹ፤ አስቀድሞ ታስቦ የነበረው ፕሮጀክቶቹ በቶሎ ተጠናቀው በሚያስገኙት ገቢ መስራት ይችላል የሚል ቢሆንም ሃሳቡ አለመሳካቱን ጠቁመዋል። በዚህ ምክንያትም አዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች ነባሮቹን እያገደሏቸው ነው፡፡ ነባሮቹ እንደ ልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ አድርገው ተብትበው የያዟቸው የአዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች ሥራቸው አልቆ በጊዜ ወደ ስራ መግባት አለመቻላቸው መሆኑን ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑ የሠራተኛ ደመወዝ መክፈል እማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴው፤ የኮርፖሬሽኑ አሠራር ህግና ደንብን በተከተለ ሁኔታ መሆን እንደሚገባው አስታውቆ፣ ችግር ካለ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚችል ገልጿል፡፡
ስኳሩ ከውጭ አገር በመርከብ ሲመጣ ተበላሽቶ በመገኘቱና በላብራቶሪ ናሙናው ሲታይ ለጤና ተስማሚ እንዳልሆነ በመረጋገጡ በአፈር ተለውሶ ተቀብሯል የተባለውን 3777 ኩንታል ስኳር በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ በቂና አጥጋቢ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚገባው የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

Read 2377 times