Monday, 18 December 2017 13:52

“ሴና” 1 ሚ. ዶላር፣ “ራፒድኢ” ከሩብ ሚ. ዶላር በላይ ተተምነዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የመጀመሪያዎቹ 655 መኪኖች በሙሉ ከወዲሁ ተሸጠው አልቀዋል

    ማክላረን እና ቴስላ የተባሉት ታዋቂ የዓለማችን ኩባንያዎች ያመረቷቸው እጅግ ውድ የቤት መኪኖች ዋጋ፣ የአለምን ትኩረት ስበው መሰንበታቸውን  ዘ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡
ማክላረን የተባለው ኩባንያ ከለንደን አቅራቢያ በሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ሴና የሚል ስያሜ ለሰጠው የስፖርት መኪናው 1 ሚሊዮን ዶላር የመሸጫ ዋጋ ማውጣቱን ያስታወቀ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ለገበያ ሊያቀርባቸው ያመረታቸውን 500 መኪኖቹን በሙሉ ከወዲሁ ሸጦ መጨረሱን አስታውቋል፡፡
789 የፈረስ ጉልበት አቅም ያለው ሴና፣እጅግ ፈጣንና ምቾት ያለው ልዩ መኪና እንደሆነ ያስታወቀው ኩባንያው፤ የመጀመሪያዎቹን መኪኖቹን በመጪው መጋቢት ወር ጄኔቫ ውስጥ በሚካሄደው አውደ ርዕይ ላይ በይፋ እንደሚያስመርቅ ገልጧል፡፡
ታዋቂው ኩባንያ ቴስላ በበኩሉ፤ በ2019 የፈረንጆች አመት በገበያ ላይ የሚያውለው የመጀመሪያው በኤሌክትሪክ የሚሰራ መኪና የመሸጫ ዋጋው 255 ሺህ ዶላር እንዲሆን መወሰኑን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ዘ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡ ራፒድኢ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ እጅግ ዘመናዊ የቤት መኪና፣ በአይነቱ የተለየ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ኩባንያው ለመጀመሪያ ጊዜ አምርቶ ለገበያ የሚያቀርበውም 155 መኪኖችን ብቻ እንደሚሆን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን አመልክቷል፡፡ ኩባንያው ገና መኪናዎቹን በማምረት ሂደት ላይ ቢሆንም፣ ለገበያ ሊያቀርባቸው ያቀዳቸውንና እጅግ ውድ የሆኑትን 155 መኪኖቹን በሙሉ ገና ከወዲሁ ለደንበኞቹ ሸጦ መጨረሱን የጠቆመው ዘገባው፤ መኪናዎቹ አንድ ጊዜ ቻርጅ በተደረጉት የኤሌክትሪክ ሃይል እስከ 200 ማይል ርቀት መጓዝ እንደሚችሉም አስረድቷል፡፡ እስከ 1ሺህ የፈረስ ጉልበት የሚደርስ አቅም እንደሚኖረው የተነገረለትን ራፒድኢ በማምረት ላይ የሚገኘው ቴስላ፤ በቅርቡም ሞዴል 3ኤስ የተባሉ የኤሌክትሪክ መኪኖቹን ለመግዛት ከ450 ሺህ ደምበኞቹ የግዢ ጥያቄ እንደቀረበለት ያስታወሰው ዘገባው፤ ኩባንያው የመኪኖቹን ባትሪ በበቂ ሁኔታ ለማምረት ባለመቻሉ 260ዎቹን ብቻ ሊያመርት መቻሉን ጠቁሟል፡፡

Read 1540 times