Monday, 18 December 2017 13:55

እነ ሙሴቬኒ የሙጋቤን ጠባሳ አይተውም በእሳት እየተጫወቱ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

- የብሩንዲው መሪ ስልጣናቸውን ለማራዘም ዘመቻ ጀምረዋል
             - የኡጋንዳው አቻቸውም ስልጣን ላለመልቀቅ ህግ ሊያሻሽሉ ደፋ ቀና እያሉ ነው

    የስልጣን ዘመናቸውን ሊያጠናቅቁ 2 አመታት ብቻ የቀራቸው የብሩንዲው ፕሬዚደንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ስልጣናቸውን ለማራዘም የሚያስችሏቸውን የህገ መንግስት ማሻሻያዎች በመደገፍ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ደጋፊዎቻቸውን የማግባባት ዘመቻ ባለፈው ማክሰኞ መጀመራቸውንና ይህም አገሪቱን ወደ ከፋ ብጥብጥና ቀውስ ሊያስገባት ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱን መሪ የስልጣን ዘመን ገደብ የሚወስነውን የህገ- መንግስት አንቀጽ ለማሻሻል በቅርቡ ህዝበ ውሳኔ እንደሚካሄድ የጠቆመው ዘገባው፤ስልጣናቸውን በወቅቱ ካልለቀቁ በአገሪቱ የባሰ ግጭትና ብጥብጥ እንደሚከሰት ከተቀናቃኞቻቸው ማስጠንቀቂያ ቢደርሳቸውም፣ ንኩሩንዚዛ ግን ጊቴጋ በተባለው የአገሪቱ ግዛት የቅስቀሳ ዘመቻ መጀመራቸውን አመልክቷል፡፡
ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ለሁለት የስልጣን ዘመናት አገሪቱን የመሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በ2015 ላይ ህገ መንግስቱን በማሻሻል ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን በይፋ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ በተቀሰቀሰው የከፋ ግጭትና ብጥብጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ንኩሩንዚዛን ለሁለት የስልጣን ዘመናት በመንበራቸው ላይ የሚያቆየውን የህገ መንግስት ማሻሻያ የማድረግ ሃሳቡን ያፈለቀው ፕሬዚዳንቱ መርጦ የሾመው የአገሪቱ ኮሚሽን እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ራሳቸው የሚመሩት ካቢኔም ሃሳቡን እንዳጸደቀውና ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ መፍቀዱን አመልክቷል፡፡ የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቱ የጀመሩትን የቅስቀሳ ዘመቻ ያወገዙ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ እድሜ ልካቸውን በስልጣን ላይ የመቆየት ጽኑ ፍላጎታቸውን ለማሳካት እስከቻሉ ድረስ አገሪቱ ወደ እልቂትና የእርስ በእርስ ግጭት ብትገባ ግድ እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡
ለ13 አመታት የዘለቀውን የብሩንዲ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ግጭት ለማቆም በሚል እ.ኤ.አ በ2005 የአሩሻው ስምምነት መደረጉን ተከትሎ ስልጣን የያዙት ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ፣ በ2010 በተካሄደውና ተቃዋሚዎች ባልተሳተፉበት ምርጫ  አሸንፈው በገዢነት መቀጠላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በ2015 ላይም ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን እወዳደራለሁ ማለታቸውን ተከትሎ እንዲካሄድ የተወሰነው ህዝበ ውሳኔ  ማሻሻያውን የሚደግፍ ከሆነ፣ ሰውዬው በስልጣን ላይ የቆዩበት ጊዜ በድምሩ 14 አመታት እንደሚደርስ አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ፣ የአገሪቱን መሪ የዕድሜ ገደብ በማራዘምና አምስት አመት የነበረውን የፕሬዚዳንቱ አንድ የስልጣን ዘመን ወደ ሰባት አመት ከፍ በማድረግ ስልጣናቸውን ለማስቀጠል ባቀረቡት ረቂቅ ሃሳብ ላይ የአገሪቱ ፓርላማ በቅርቡ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ላለፉት ከ30 በላይ አመታት አገሪቱን የገዙት ሙሴቬኒ፤ በቀጣዩ ምርጫ 77 አመት እንደሚሆናቸውና ህጉ ግን ለመሪነት መወዳደር የሚችለው ዕድሜው ቢበዛ 75 አመት የሆነ ሰው እንደሆነ የሚደነግግ በመሆኑ፣ በምርጫው ለመወዳደርና ስልጣናቸውን ለማራዘም ሲሉ ህጉን የማሻሻል ሃሳብ ማቅረባቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኡጋንዳ ፓርላማ የፕሬዚዳንቱ የዕድሜ ገደብ ይሻሻል በሚለው ሀሳብ ዙሪያ ለመምከር ከዚህ ቀደም በጠራቸው ስብሰባዎች ላይ ከፍተኛ አለመግባባትና ውዝግብ መፈጠሩን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ የፓርላማው አባላት በወንበር እየተወራወሩ እስከመፈነካከት ደርሰው እንደነበርም አመልክቷል፡፡
ረቂቅ ሃሳቡ ለፓርላማ ውሳኔ ከቀረበ ቆየት ቢልም፣ በአፋጣኝ ድምጽ ሊሰጥበት ያልቻለው የአገሪቱ ህግ አውጪዎች ውሳኔውን የሚያጸድቅ የድጋፍ ድምጽ ለመስጠት ከሙሴቬኒ መንግስት ለእያንዳንዳቸው 83 ሺህ ዶላር በሙስና መልክ እንዲከፈላቸው በመጠየቃቸው ነው መባሉን ኦልአፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡

Read 1483 times