Monday, 18 December 2017 13:55

57 አገራት ለእየሩሳሌም የፍልስጤም መዲናነት እውቅና እንዲሰጥ ጠየቁ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 በሙስሊም አገራት መካከል ትብብርን የመፍጠር ዓላማ ይዞ የተቋቋመው ኦርጋናይዜሽን ኦፍ ኢስላሚክ ኮፕሬሽን ባለፈው ረቡዕ በቱርክ መዲና ኢስታንቡል ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ 57 የሙስሊም አገራት መንግስታት፣ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለምስራቃዊ እየሩሳሌም፣ የፍልስጤም መዲናነት እውቅና እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና መሆኗን በተመለከተ ላስተላለፉት ውሳኔ የጋራ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ በቱርኩ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶጋን በተጠራው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የአገራቱ መሪዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ለእየሩሳሌም የእስራኤል መዲናነት የሰጡትን እውቅናም ውድቅ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
“የትራምፕ ውሳኔ ህጋዊነት የጎደለውና ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው” በሚል በጋራ ያወገዙት መንግስታቱ፤ አሜሪካ ይህንን ውሳኔዋን እንድትሽር የጠየቁ ሲሆን ይህንን ባለማድረጓ ለሚከተሉት ጥፋቶችና ቀውሶች ሁሉ ሃላፊነቱን ለመውሰድ እንድትዘጋጅም ማስጠንቀቃቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአገራቱ መሪዎች በጉባኤው ማብቂያ ላይ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ አንዳንዶች እንደገመቱት በእስራኤልም ሆነ በአሜሪካ ላይ ምንም አይነት ማዕቀብ አለመጣላቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም ሆኖ ግን የአገራቱ የጋራ አቋም የአሜሪካን ውሳኔና አቋም ያስቀይራል ተብሎ እንደማይጠበቅ ጠቁሟል፡፡
“የትራምፕ ውሳኔ ዓለማቀፍ ህጎችን የሚጥስ ትልቅ ወንጀል ነው፤ እየሩሳሌም የፍልስጤም መዲና ነበረች፤ አሁንም ናት፤ ወደፊትም ሆና ትቀጥላለች” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ጠንካራ አቋም የገለጹት የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ፤ “ለእየሩሳሌም የፍልስጤም መዲናነት እውቅና እስካልተሰጠ ድረስ በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት የሚባል ነገር አይታሰብም” ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶጋን በበኩላቸው፤ ሃያላን አገራት እየሩሳሌም የፍልስጤም ዋና ከተማ ለመሆኗ እውቅና እንዲሰጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን “አሜሪካ ይህንን ተገቢነት የሌለው ውሳኔ መሻር ይገባታል” ማለታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2915 times