Saturday, 23 December 2017 09:30

“ምርጫ ቦርድና መንግስት ኢዴፓን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው” - የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 በቅርቡ በብሄራዊ ም/ቤት አባላት ተመርጠው ወደ ፓርቲው አመራር መምጣታቸው በገለፁት አቶ አዳነ ታደሰ የሚመራው የኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፤ ምርጫ ቦርድና መንግስት ኤዴፓን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው ሲሉ አማረሩ፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፤ “ተመርጠን ወደ አመራር መጥተናል” ያሉበትን ጉዳይ አጣርቼ ውሳኔ እስከምሰጥ ድረስ በኢዴፓ አመራርነት የማውቀው ዶ/ር ጫኔ ከበደን ነው፤ ማለቱ ይታወሳል፡፡
የፓርቲው አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ፤ በፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት የተመረጠበትን አግባብ የሚያስረዳ ቃለ ጉባኤ  ለቦርዱ ቢያቀርብም ተቀባይነት አለማግኘቱን በመጠቆም፤ “ምርጫ ቦርድና መንግስት ኢዴፓን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው” ብሏል፡፡
“አገሪቱ ከምትገኝበት የፖለቲካ ውጥረት አንፃር የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአቱን ለማጠናከር መስራት ሲገባ ፓርቲን ለማዳከም እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠናል” ብለዋል- አመራሮቹ በሰጡት መግለጫ፡፡
የተቀናጀ በሚመስል መልኩ ምርጫ ቦርድና መንግስት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት ፓርቲያቸውን ለማፍረስ መንቀሳቀሳቸውን ማህበረሰቡና የሲቪክ ማህበራት በማጣራት ሃቁን ለህዝብ እንዲያቀርቡላቸውም ጠይቀዋል፡፡
በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን የአመራር ውዝግብ ለመፍታትም የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት አባላት ለታህሳስ 15 ልዩ ስብሰባ መጠራታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ስብሰባውን ጠርተዋል ተብለው ከተጠቀሱት መካከል የፓርቲው ስራ አስፈፃሚዎች መካከልም አቶ አዳነ ታደሰ፣ አቶ አስማማው ተሰማ፣ ወ/ሮ ሶፊያ ይልማ እና አቶ ልደቱ አያሌውን ጨምሮ 13 አመራሮች ይገኙበታል፡፡
በፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ውሳኔ ከሥራ አስፈጻሚነት ተነስተዋል ከተባሉት አንዱ የሆኑት አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፤ መግለጫውን አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት “ግለሰቦቹ ይሄን መግለጫ በፓርቲው ስም የመስጠት መብት የላቸውም፣ ምርጫ ቦርድም አያውቃቸውም የህግ ተጠያቂነትንም ያስከትላል” ብለዋል፡፡

Read 4032 times