Sunday, 24 December 2017 00:00

ኢህአዴግ ሀገሪቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሷን አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)


      “ለተፈጠሩ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ዋነኛ ምክንያቱ የመንግስት አመራር ድክመት ነው” - የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ

    ነባር ታጋዮችን በማሳተፍ እየተካሄደ የሚገኘው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ላሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ዋነኛ ምክንያት የራሱ የአመራር ድክመት መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን በጉባኤው ተሳታፊ የሆኑ የአዲስ አድማስ ምንጮች በበኩላቸው፤ ውይይቱ በአጭር ቀናት ይጠናቀቃል ተብሎ አይጠበቅም ብለዋል፡፡
ሀገሪቱ አሁን አስጊ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የገለፀው የስራ አስፈፃሚው መግለጫው፤ አስጊ ሁኔታው የተፈጠረውም በዋናነት በአመራሩ ድክመት ነው ብሏል፡፡
በዋናነት ስራ አስፈፃሚው የችግሩ ባለቤት መሆኑንና ህዝባዊ ወገንተኝነቱ እየተሸረሸረ ችግሮችን በቁጭት ከመፍታት ይልቅ የእርስ በእርስ ንትርክ ላይ እንደሚያተኩር መገምገሙ ታውቋል፡፡
በአራቱ የድርጅቱ አባል ፓርቲዎች መካከልም የእርስ በእርስ መጠራጠር ያመዘነበትና አለመተማመን የነገሰበት ግንኙነት መፈጠሩን ያመለከተው የስራ አስፈፃሚው መግለጫ ለሁለት አመታት የተደረገው ጥልቅ ተሃድሶም፤ የሚፈለገውን ያህል ጥልቀት ያልነበረው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተመልሶ ወደ አዘቅት መውረዱን አስታውቋል፡፡
በድርጅቶቹ መካከል የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መታጣቱን የጠቆመው መግለጫው፤ የውስጠ ዲሞክራሲ እጦትና የህዝባዊ ወገንተኝነት መሸርሸር ተገቢው ውይይት ተደርጎባቸው የሚገኙ ውጤቶች ውይይቱ ሲጠናቀቅ ለህዝብ ይገለፃል ብሏል፡፡ እየተካሄደ ባለው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ በድርጅቱ የመተካካት መርህ ከስራ አስፈፃሚው መድረክ ተገልለው የነበሩ ነባር አመራሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት ምንጮች፤ ውይይቱ በ10 ቀናት ይጠናቀቃል ተብሎ መርሃ ግብር ተይዞለት የነበረ ቢሆንም አሁን ባለው አካሄድ በርካታ ቀናት ሊፈጅ ይችላል ብለዋል፡፡  


Read 8745 times