Saturday, 23 December 2017 09:44

“ኦፌኮ በኦሮሚያ ነገሮችን ማረጋጋት አይከብደውም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 “--የኦሮሞ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ፣ የቁመቱን ያህል ጃኬት ማግኘት ነው፡፡ ለሱ ቁመት የሚሆን ጃኬት ማግኘት ነው ጥያቄው፡፡ የስልጣን፣ በሀብት የመጠቀም፣ መብቱ ተከብሮለት የመኖር ጥያቄ ነው፤ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ከእነዚህ ጥያቄዎች ባለፈ፣ ልገንጠል ብሎ ጠይቆ አያውቅም፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ብለዋል፤ ግን ህዝቡ አላለም፡፡--”

         • የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን አለማክበሩ ነው
         • የሰብአዊ መብት ህገ ደንቦች በመንግስት ተፈፅመው አያውቁም
         • የኦሮሞ ህዝብ ልገንጠል ብሎ ጠይቆ አያውቅም”
         • በኦሮሞ ህዝብ መሃል አክራሪ ብሔርተኝነት የለም

   በርካታ አመራሮቹን በእስር ያጣው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ አመራር የሆኑትና የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ገብሩ ገብረማርያም በፓርቲያቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና በወቅታሪ የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል እነሆ፡-

    በአሁን ወቅት በአገሪቱ የሚታየውን የፖለቲካ ቀውስ  ኦፌኮ እንዴት ያየዋል?
ኢህአዴግ የመድብለ ፓርቲ ስርአት አሰፍናለሁ ብሎ ሃገሪቱን መምራት ከጀመረ ከ25 ዓመት በላይ ሆኗል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ግን የመድብለ ፓርቲ ስርአቱ መስፈኑ ቀርቶ ጭራሽ ተቀልብሶ ወደ ኋላ የተመለሰበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ጠንካራ ፓርቲዎች በየጊዜው በኢህአዴግ እየተደፈጠጡ፣ ጥንካሬያቸውን አጥተው፣ በሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ግንባታ ውስጥ መሳተፍ አልቻሉም፡፡ ከእነዚህ እጅ እግራቸው ከታሰረ ፓርቲዎች መካከል ደግሞ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አንዱ ነው፡፡ ይህ ፓርቲ የኦሮሞን እንዲሁም በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ሁኔታ በአትኩሮት እየተከታተለ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው፡፡ በዚህ ክትትላችን ያረጋገጥነው ደግሞ የሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ ተቀልብሶ፣ ውጥረቶች አይለው፣ ሃገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኗን ነው፡፡
ኢህአዴግ ራሱ ያወጣውን ህገ መንግስት አለማክበሩ ብሶበት፣ ዛሬ ከምንጊዜውም በባሰ  ዜጎች ያለ ፍርድ ተይዘው እየታሰሩ ዓመታትን በወህኒ ቤት እያስቆጠሩ ነው፡፡ የኛ ድርጅት መሪ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ለአንድ አመት ምንም ፍትህ ሳያገኙ በወህኒ አስቆጥረዋል። በእነዚህ መንገዶች ነው ፓርቲዎች የተዳከሙት፡፡ የእነዚህ ድምፆች መታፈን፣ ከመድረኩ መገለል ደግሞ አሁን በሀገሪቱ የምናየውን ቀውስ ፈጥሯል፡፡ ኢህአዴግ የምናወጣቸውን የማስጠንቀቂያ መግለጫዎች፣ ከቁም ነገር ባለመቁጠሩ፣ በየጊዜው የተከማቹ ችግሮች ናቸው፣ በየቦታው እየፈነዱ፣ መያዣ መጨበጫ ያሳጡት፡፡ በህገ መንግስቱ አለመመራት ደግሞ የእነዚህ ችግሮች መነሻ ነው፡፡ ዛሬ ሀገሪቷ አስቸጋሪ ወቅት ላይ ለመሆኗ እነዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡  
ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን እያከበረ አይደለም ብለዋል፡፡ ማስረጃ ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
ህገ መንግስቱ እየተከበረ ላለመሆኑ አንደኛው ዜጎች ያለ ፍርድ ማሰር ነው፡፡ የዜጎችን ሰብአዊ መብት መጣስ፣ የስቃይ ምርመራዎች፣ ግርፋቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። የዜጎችን የመፃፍ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብቶች መከልከል ኢ-ህገመንግስታዊ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የህገ መንግስት ጥሰቶች ደግሞ ህገ መንግስቱ ከፀደቀ ማግስት ጀምሮ በተግባር ታይተዋል፡፡ አሁንም ጥሰቶቹ እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ ሌላው መከላከያ ሰራዊትን፣ በሰላም ተቃውሞ ወደሚያሰማ ህዝብ ማዝመት፣ ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው፡፡ ያለ አንድ ክልል እውቅና እና ጥያቄ፣ መከላከያ ሰራዊት ገብቶ መተኮስ፣ህገ መንግስት መጣስ ነው፡፡  ህገ መንግስትን በጥቂት ሰአታት ውስጥ አርቅቆ ማፅደቅ ይቻላል፤ ቁም ነገሩ  መተግበሩ ላይ ነው፡፡ በዚህች ሀገር ደግሞ የፀደቁ  የሰብአዊ መብት ህገ ደንቦች በመንግስት ተፈፅመው አያውቁም፡፡
ኢህአዴግ በአገሪቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ምን ማድረግ ነው ያለበት?
ኢህአዴግ አርጅቷል፤ይበቃዋል፡፡ አንድ መንግስት ወይም ገዥ ፓርቲ ሲያረጅ ወይም ሊወድቅ ሲቃረብ ሶስት ምልክቶች ያሳያል ይባላል፤ በፖለቲካል ሳይንስ አስተምህሮ፡፡ አንደኛው፡- በገዥው ፓርቲ መካከል የሚፈጠር የእርስ በእርስ ክፍፍል ነው፡፡ በዚህ በኩል የሃሳቦች መዛባትና አለመስማማት ይመጣል፡፡ ይሄ በተጨባጭ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ነው። አሁን ግማሹ በራሱ ጥሎ እየወጣ ነው፡፡ ግማሹ እዚያው እርስ በእርሱ እየተዳቆሰ ነው፡፡ መንግስቱ በየጊዜው የካቢኔ ለውጥ እያደረገ ነው፤ይሄ የእርጅና ምልክት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መመሪያዎች፣ ህግ፣ ደንቦች አይከበሩም። ከታች ያለው፣ የላይኛው ያወጣውን አያከብርም፡፡ ይሄ በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡ ሶስተኛው የውድቀት ወይም የእርጅና ምልክት ቀድሞ ሰጥ ለጥ ብሎ ይገዛ የነበረ ህዝብ፣ ባህሪው ሲቀየርና ለመንግስቱ ትዕዛዛት አልገዛም ሲል ነው፡፡ በአጭሩ የህግ የበላይነት ሲጠፋ ነው፡፡ እነዚህ ናቸው ምልክቶቹ፡፡ ለዚህ መፍትሄው ደግሞ መታደስ አይደለም፡፡ ነፃ፣ ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ነው፡፡ የዚህን መደላደል ፈጥሮ ወደ ምርጫ ገብቶ፣ለተመረጠው ስልጣን ማስረከብ ነው የሚበጀው፡፡
ፓርቲያችሁ ባልተሳተፈበት ድርድር፣ አዲስ የምርጫ ስርዓት ተዘጋጅቷል፤ ገና መጽደቅ ቢቀረውም፡፡  በአዲሱ የምርጫ ስርአት ላይ አስተያየትዎ ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ እኛ በደቦ ድርድር ስለማናምን፣ ”በተናጥል እንደራደር” ብለን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳውቀን ነው ከድርድሩ የወጣነው፡፡ በሌላ በኩል የምርጫ ስርአት ዝም ብሎ አይቀየርም፡፡ የህገ መንግስት ማሻሻያ የሚያስፈልገው ነው፡፡ የህገ መንግስቱን ጉዳይ ወደ ጎን ብለው፣ ዛሬ ተስማምተንበታል ያሉትን ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርአት ደግሞ መድረክ ለዓመታት ሲያቀርበው የነበረ ጥያቄ ነው፡፡ ለኛ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን አሁንም ተመጣጣኝ የተባለው ይህ ስርአት የተጭበረበረ ነው፡፡ 20 በ 80 በመቶ ነው የተሰላው፡፡ ይሄ ጥቅም የለውም፡፡ ስለዚህ ምንም የረባ ውጤት አያመጣም፡፡ ዝም ብሎ የፖለቲካ ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡ እንደ እኔ ሀገሪቱ ለገባችበት የፖለቲካ ቀውስም መፍትሄ አይሆንም፡፡
ሀገሪቱን አሁን ከሚታዩ ችግሮችና የፖለቲካ ቀውስ ለማውጣት የተቃዋሚዎች ድርሻ ምንድን ነው ይላሉ?
እውነት ለመናገር ለአንድ ቀን በሩ ቢከፈትልን፣ ኦፌኮ፤ በኦሮሚያ ነገሮችን ለማረጋጋት አይከብደውም። ህዝቡ የሰለቸው የእነሱን ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች እድሉን ቢያገኙ፣ የህዝቡን ጥያቄ ወደ አንድ ቅርፅ በማምጣት፣ሰላምን ማስጠበቅና በሰላም ጥያቄ የማቅረብ ባህል ይዳብር ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመጀመሪያውኑ ባይታፈኑ ኖሮ ይሄ አይፈጠርም ነበር። ፖለቲካዊ ቀውሱን በመፍታት ረገድ የድርሻችንን ባለመወጣታችን ብዙ ችግር ደርሷል፡፡ ኢህአዴግም ይሄን ያህል ጭንቅ ውስጥ አይገባም ነበር፡፡
በአሁን ወቅት ኦፌኮ በስራ ያሉት አመራሮች ሶስት ያህል መሆናቸውንና ሊቀመንበሩን፣ ተ/ም ሊቀመንበሩን ጨምሮ በርካታ አመራር ታስሯል ይህ ለምን ሆነ?
ኢህአዴግ ኦፌኮን ለማጥፋት ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አንዱ አመራሩን ማሰር ነው፡፡ አሁን በተለይ በእስር ቤት የሚገኙት እኛን እንዲተኩን ያዘጋጀናቸው ወጣት አመራሮች ናቸው፡፡ በአሁኑ ጉባኤ እኛን እንዲተኩን ነበር እነዚህን ወጣቶች ያዘጋጀነው፡- እነ ደጀኔ ጣፋ፣ እነ ጉርሜሳ አያኖ፣ እነ ደስታ--- ለአመራር ያዘጋጀናቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቢታሰሩም ኦፌኮ በኦሮሞ ህዝብ ውስጥ መንፈስ ሆኗል፤ እንዲህ በቀላሉ አይጠፋም፡፡
ኦፌኮ ፌደራላዊ ስርአትን ነው የሚከተለው፡፡ ኢህአዴግ ከሚከተለው በምን ይለያል?
አሁን ያለውን የፌደራሊዝም አስተሳሰብ እንቀበለዋለን፡፡ ፌደራሊዝም ነው ይህቺን ሀገር በአንድነት ሊጠብቃት የሚችለው፡፡ አሃዳዊ ስርአት ከዚህ በኋላ አይመጣም፡፡ ይህቺ ሃገር ስትታመስ የቆየችው የብሔር ብሔረሰቦች መልስ ባለመመለሱ ነው፡፡ ይሄ ፌደራሊዝም በአግባቡ ባይሆንም አቅጣጫውን አስቀምጧል፡፡ ትልቁ ችግር ያለው አተገባበሩ ላይ ነው እንጂ ፌደራሊዝሙ ብሄር ተኮር መሆኑ አይደለም፡፡ በብሄር መደረጃት ኢትዮጵያዊነትን የሚያስክድ አይደለም፡፡ ማንነትን ማወቅ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ማንነታችንን አውቀን ኢትዮጵያዊነትን ማበልፀግ እንችላለን፡፡
በኦሮሞ እና በአማራ፣ በትግራይ እና በአማራ እንዲሁም በሌሎችም መካከል እየተደረጉ ያሉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ፓርቲያችሁ እንዴት ይመለከተዋል?
ይሄ ዝም ብሎ የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ፣ የአማራ እና የትግራይ ህዝብ መች ተጣላ፡፡ የተጣሉት ፖለቲከኞቹ ናቸው፡፡ ህዝብ ከህዝብ ሊጣላ አይችልም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ አማራ ሲበደል፣ አማራው ኦሮሞው ሲበደል መናገሩን እኮ ዛሬ አይደለም የጀመረው፡፡ “የኦሮሞ ህዝብ ደም፣ የኔ ደም ነው” ብሎ የአማራ ህዝብ መፈክር ያሰማው’ኮ፣ህዝብ ለህዝብ ከመከናወኑ በፊት ነው፡፡ ህዝቡ የልብ ለልብ ትስስር ያለው ነው፡፡ አሁን ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ ፖለቲካዊ ጨዋታ ነው፡፡ ምናልባት ለየዋህ ሰዎች ጉዳዩ ቀና ይመስላል፡፡
የኦሮሚያ ክልል አዲሱ አመራር እንቅስቃሴ ፓርቲያችሁ እንዴት ነው የሚመለከተው?
እርግጥ ነው የማረጋጋት ስራ እየሰሩ ነው፤ ነገር ግን የህዝብ ጥያቄ እየመለሱ አይደለም፡፡ ህዝብን አረጋግቶ የኦህዴድን ህይወት እንደገና ለመዝራት እየታተሩ ነው። አንዳንድ “ያዝልቅላቸው” የሚያስብሉ ስራዎችን እየሠሩ ነው፡፡ ነገር ግን መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን አልነኳቸውም፡፡ የፍትህ፣ የዲሞክራሲ፣ የእኩልነት ጥያቄዎችን ገና አልነኳቸውም፡፡ እነዚህን እስካልነኩ ድረስ የህዝብን ጥያቄ እየመለሱ ነው ማለት አይቻልም። መሬት መልሶ መስጠት የመሳሰሉ የማባበያ የሚመስሉ ነገሮች ይታያሉ፡፡ ያላወቁት ነገር ግን ህዝቡ ከዚህ በላይ ርቆ መሄዱን ነው፡፡ የህዝቡ ጥያቄ፣ ከኛም ከእነሱም አልፎ ሄዷል፡፡
የኦሮሞ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ ምንድን ነው?
የኦሮሞ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ፣ የቁመቱን ያህል ጃኬት ማግኘት ነው፡፡ ለሱ ቁመት የሚሆን ጃኬት ማግኘት ነው ጥያቄው፡፡ የስልጣን፣ በሀብት የመጠቀም፣ መብቱ ተከብሮለት የመኖር ጥያቄ ነው፤ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ከእነዚህ ጥያቄዎች ባለፈ፣ ልገንጠል ብሎ ጠይቆ አያውቅም፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ብለዋል፤ ግን ህዝቡ አላለም፡፡ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ተፈቃቅዶ መኖር ነው ፍላጎቱ፡፡ በዚህች ሃገር ገዥው ፓርቲ እንደሚለው፣ በህዝቡ መሃል አክራሪ ብሄርተኝነት የለም፡፡ ፖለቲከኞቹ ጋ ሊኖር ይችላል፡፡ ህዝቡ ጋ ግን የለም፡፡
በሶማሌ ክልል እና በኦሮሚያ አዋሳኞች በተፈጠሩ ግጭቶች፣ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ደርሷል፡፡ ብዙዎች እንዴት ችግሩን መቆጣጠር አልተቻለም የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
እኛ በመሃሉ ሴራ እንዳለ እንረዳለን፡፡ አንደኛው የኦሮሞን ህዝብ ከመሰረታዊ ጥያቄው ለማዘናጋትና የትኩረት አቅጣጫውን ለማስለወጥ የሚደረግ ነው። በሂደቱ የተደራጀ አካል እንደተሳተፈበት መረጃዎች አሉን። ግጭቱ ህዝብ ለህዝብ እንዳልሆነ ብዙ ማረጋጋጫዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሁለቱ ብሄሮች ከፍተኛ መስተጋብር ያላቸው ናቸው፡፡ ይሄ አይነት ሴራ ደግሞ ለሃገርም የሚበጅ አይደለም፡፡ አንድ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር፣ ይህ በሴራ የታጀበ ግጭት፣ የቆየውን የሁለቱን ብሄሮች ታሪካዊ ግንኙነት መቼውንም ቢሆን አይበጥሰውም፡፡
ከእንዲህ ዓይነት ችግሮች  እንዴት መውጣት ይቻላል?
ይህቺ ሃገር ሠፊ ሃገር ነች፡፡ ኢህአዴግ ብቻው እንደ ድሮው ሊያስተዳድራት አይችልም፡፡ ስለዚህ ብሄራዊ የአንድነት መንግስት ጥሪ ማቅረብ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚል ግለሰብ ሣይቀር ጠርቶ፣ “ይህቺን ሃገር ምን እናድርጋት” ብሎ ማወያየት፣ አሁንም ብቸኛው መፍትሄ ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚሳተፍበት፣ በይቅር መባባል ላይ የተመሠረተ ብሄራዊ የአንድነት መንግስት መመስረት ያስፈልጋል፡፡ ከችግሮች የመውጫ ቀዳዳም ይሄ ነው። እንደዚህ እንቀጥላለን ከተባለ፣ መያዣ መጨበጫው ነው የሚጠፋው፡፡ ህዝብ ምን ሊያደርግ እንደሚችል አሳይቷል፡፡ ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከመድረክ ጋር በተናጠል ለመደራደር ቃል ገብተዋል። ይሄን ቃላቸውን ማክበርም፣ አንዱ ሃገርን የማዳን መንገድ ነው፡፡


Read 2318 times