Sunday, 24 December 2017 00:00

ፌደራሊዝማችንን በፍልስፍና መነፅር

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(5 votes)

 እንደ መግቢያ
ታላቁ ጀርመናዊ ፈላስፋ ፍሬደሪክ ኒቼ፣ ብዙ እሳቤዎች አበርክቶት እንዳለው ቢታወቅም ከሁሉም በላይ ሚዛን የሚደፋው ግን በዘመናዊነት እሳቤ ላይ የሰነዘረው ጠንከር ያለ ሂስ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በዘርፉ ላይ ጥናት የሚያካሄዱ ልሂቃን፣ ፍሬደሪክ ኒቼን የድህረ ዘመናዊነት /Postmodernism/ የነፍስ አባት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
የዘመናዊነት አንጓ ጭብጥ የቆመውሁሉንም እውነታ ወደ ታዋቂነት በማውረድ ነው። በዘመናዊነት አስተምህሮት መሠረት፤ በስነ አምክንዮ ወይም በሳይንስ የማይፈታምንም አይነት ነባራዊ እውነታ የለም፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ዓለም በሙሉ ውዥንብር ነው፡፡  
የፖስት-ሞደርኒዝም ዋነኛ ፊታውራሪ ፍሬደሪክ ኒቼ ብቅ ያለው ይህንን በዘመናዊነት አስተምህሮት ላይ እንደ  ጉልላት የሚቆጠርን እሳቤ በመቀናቀን ነበር፡፡ ፈላስፋው በስነ አምክንዮ የተቀየደውን አስተምህሮት፣ ከጥቅም ውጪ በማድረግ፣ የአንጻራዊነትን ህያውነት ለማስረገጥ በብርቱ ተጠቧል፡፡ ለስነአምክንዮ የተሰጠውን ከገደብ ያለፈ ክብርን  በመሄስ አንጻራዊነት /perspective reality/ የሰው ልጅ ገዢ እውነታ እንደሆነ በስፋት አትቷል፡፡ ድፍን የሰው ዘርን ያለ አድሎ የሚያቅፍ ገዢ እውነት አለ ብሎ ማሰብ ቅዠት ነው፡፡ ሁላችንም የየራሳችን ትንንሽ ዓለም /universe/ ባለቤቶች ነን፡፡ እኩዩን ከበጎ የምንለይበት መነጥር ወጥ በሆነ መለኪያ ሳይሆን በአደግንበት የባህል፣ የትውፊት ወይም የሀይማኖት ማዕቀፍ ውስጥ ተበጃጅቶ፣ የዳበረ ጉራይማሌ ቀመር (ፐርሰፕሽን) ነው፡፡ ይላል ጠቢቡ፡፡
የሚሼል ፉኮ አስተምህሮት ምንድን ነው?  
ታላቁ ፈረንሳዊው ሚሼል ፉኮ፤ የፍሬደሪክ ኒቼን የአንጻራዊነት ምልከታን የበለጠ ገናና ያደረገ የድህረ ዘመናዊነት /ፖስትሞደርኒዝ/ አቀንቃኝ ነው፡፡ፉኮ ካራመደው ፍልስፍናዊ ምልከታው መሳ ለመሳ አወዛጋቢነቱም በእዛው ልክ እንደነበረ ስለ እርሱ አስተምህሮት በስፋት ከሚያትቱ ድርሳናት መገንዘብ እንችላለን፡፡
የፎኮቅራኔ አሀዱ ብሎ የሚጀምረው በባህል፣ በሀይማኖትና በአካባቢ ያልተቀነበበ፣ አንድ ወጥ እውነት አለ ብሎ ከሚሰብክ ንድፈሐሳባዊ ትንታኔ ጋር ነው፡፡ በዘመናት መፈራረቅ፣በቦታ ልዩነት፣ በቆዳ ቀለም መጥቆርና መንጣት የማትዛነፍ አንዲት እውነት እንዳለች የሚያትት ማንኛውም አስተምህሮት ቅቡል እንዳልሆነ ጠቢቡ ያስረግጣል። እውነት ትመነምናለች እንጂ አትበጠስም የሚለው የሀገራችን ብሂል፤ በፉኮ ፊት ፌዝ ነው፡፡ በፈላስፋው ትንታኔ መሰረት፤ እውነት ከባህል ወይም ከአካባቢያዊ ማዕቅፍ ነጻ መሆን በፍጹም አትችልም፡፡ ቀለሟና ባህሪዋ እንደ ባህል ብዝኃነት ጉራይማሌ ነው፡፡ ይህንን ብዝኃ እውነት ፉኮ “ሪዥም ኦፍ ትሩዝ” /regime of truth/ ብሎ ሰይሞታል፡፡ በየትኛውም የዓለማችን ጥግ ያለ የሰው ዘር እውነትን አጥልሎ የሚለካበት መለኪያ አንዱ ከአንዱ ጋር አይገጥምም፡፡ በዚህ መለኪያ መሠረት፤ የሚመዘንየእውነት ተፈጥሮ ህልቆ መሳፍርትነው፡፡
ስለዚህ ዓለማችን የእውነት ግሪሳ አንጂ አንድ መንምና የማትበጠስ እውነታን አልታደለችም፡፡ በዚህ ውጥንቅጥ አካባቢያዊ ገጽታ ላይ እንደ መርግ የሚጫን ርዕዮተዓለም እንደ በረከት የሚቆጠረውን ብዝኃነትን ደብዛውን ከእነ አካቴው የሚያጠፋው ነው የሚሆነው፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ጥቅል ማንነትን ለመጫን የተፍጨረጨሩ ኃይሎች፣ ለበርካታ ንጹሐን እልቂት ምክነያት ሆነዋል፡፡ የፋሺዝምና የናዚዝም ርዕዮተ ዓለምን እንደ ዋቢ መወሰድ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ለጥቅል ማንነት ፊት ሊሰጠው አይገባም፡፡ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ልዩነት ለዘላለም ይኑር!! ይለናል-ፋላስፋው
ፉኮን ከእኛ ጋር ምን አገናኘው?
የፖለቲካ ዙሪያ ገባችንን ከላይ እስከ ታች ለመበርበር በምንዳዳበት ጊዜ ከፋኮ አስተምህሮት ጋር ፊት ለፊት መላተማችን አይቀርም፡፡ ፈላስፋው በጥቅልና በአካባቢያው እውነታ መካከል ያለውን ቅራኔን አስመልክቶ ያኖረው ምልከታ፣ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ ጥቅል (Grand Concept) እና አካባቢያዊ እውነታ (Fragmented reality) እርስ በእርስ ተጣጥመው ሊሄዱ አይችሉም፡፡ በአንዱ መቃብር ላይ ሌላው አበባ ያኖራል፡፡ አንድ ጥቅል ማንነት አለቀጥ ሊጎመራ የሚችለው ጥቃቅንነባራዊ ሁኔታዎችንከጥቅም ውጪ በማድረግ ነው፡፡ ይህ ምልከታ፣ የእኛን ፖለቲካዊ ንፍቀ ክበብ ለመገምገም እንደ ጥሩ ማሳያ ሊሆንልን ይችላል፡፡
እንደሚታወቀው የ1987 ዓ.ም ሕገ-መንግሥት በኢትዮጵያዊነት ጥቅል ማንነት ኪሳራ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉአላዊ ሥልጣንን ጠቅልሎ ያሸክማል፡፡ በእርግጥ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚለው ጽንሰ ሐሳብ፣ የባእድ ቋንቋ ተውሶ ያመጣው ጣጣ እንጂ በሀገራችን መሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር ፈጽሞ የሚሄድ አይደለም፡፡ በዘርፉ በተሰማሩ ልሂቃን አጽንኦት እንደሚሰጡት ከሆነ፣ ለሀገራችን ሕዝቦች ትክክለኛው መገለጫ ከብሔር ይልቅ ዘውጌ ነው፡፡  
ፉኮ በብርቱ የሚሄሰው ጥቅል ማንነት፣ በ1987ቱ ሕገ መንግሥት ላይ ቦታ ከተነፈገው የኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ኩታገጠም ነው፡፡ በፉኮ መለኪያ ቅቡል የሆነው አካባቢያዊ እውነታን (fragmented reality) ምናልባትም ከብሔር ማንነት ጋር ማነጻጸር ይቻላል፡፡
ነገሩን ወለፈንዲ የሚያደርገውግን በህገ መንግስቱ መነጥር፣ እንደ የስለት ልጅ በስስት የሚታየውየብሔር ማንነት፣ በራሱ ጥቃቅን ዕውነታን በመድፈቅ ከላይ የተጫነ ጥቅል ማንነት መሆኑ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የፌደራል ስርዓቱ የአላማጣ ራያን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የማስተዳደር ጥያቄን የመለሰበት መንገድ ብንመለከት፣ እንኳን፣ ትግሪኛ ቋንቋንእንደ ብቸኛ መለኪያ በመውሰድ ትግራዊ ጥቅል ማንነትን በመጫን ነው በተግባር የተተረጎመው፡፡ በወልቃይት ሕዝብ ላይ የደረሰው እንግልትን እዚህ ጋ ልብ ይሏል፡፡ የአካባቢው ስነልቦና፣ ባህልና እምነት ከግምት ሳይጣፍ፣ በቋንቋ መመሳሰል ብቻ ወጥ ማንነትን መጫን ልክ ፉኮ አጥብቆ ከኮነነው አውዳሚ ቅኝት ጋር በአንድነት የሚሰለፍ አካሄድ ነው፡፡ የፌዴራላዊው አወቃቀር አንዱን ጥቅል ዕውነታን (ኢትዮጵያዊነትን) ለመሸሽ፣ በሌላ ጥቅል ዕውነታ (በብሔር ማንነት) ጠልፏል፡፡ ጥቃቅን ዕውነታዎች ፍጹም ባእድ በሆነ መለኪያ ተድጠዋል፡፡
እንግዲህ በቋንቋ መለኪያ ብቻ ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎችተገፍተውተግባር ላይ የዋለው ፌደራላዊው ሥርዓት፣ በጊዜ ሒደት በአንድ ክልል ውስጥ  አንደኛ ደረጃ ዜጋና ሁለተኛ ደረጃ ዜጋን ሊፈጥር ችሏል፡፡ ሥልታዊ በሆነ መንገድ የክልሉ ተወላጅ ባልሆኑ ዜጎች ላይ መጤዎች፣ ተስፋፊዎች ወይም ወራሪዎች የሚል ተቀጥላ ተለጥፎባቸው በእናት ሀገራቸው ባይተዋር እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይህም የፌደራላዊ ሥርዓት የተቀለሰበት መርህ ምን ያህል በህጸጽ የተሞላ እንደሆነ ምስክርሊሆን ይችላል፡፡ የፌደራላዊው ስርዓት ሀገራዊ አርበኝነትን በእጅጉ በማዳከም፣ በሕዝቦች መካከል “እኛ” እና “እነርሱ” በሚል የመጠፋፋት ስነልቦና ተበክሏል፡፡ በዚህም የተነሳላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት አንድ የተዋሀደ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ መፍጠር አልተቻለም፡፡
የሀገራችን ሕዝቦች ባላቸው የመልአምድራዊ ኩታገጠምነት፣የጋራ ታሪክ፣ባህልና  ሥነልቦና መመሳሰል ከቁጥር ሳይጣፍ፣ ከአመክንዮ በራቀ፣ ለደመ-ነፍሳዊ ቅርርብ የበለጠ ትኩረት በሚሰጥ፣ ከፋፋይ ቀመር እውን የሆነው ፌደራላዊው ስርዓት፤ ውሎ አድሮ ሀገሪቱን ወደ ማትወጣበት ቅርቃር ውስጥ ጨምሯታል፡፡
በአንድ ትልቅ የብሔረሰብ ጥላ ሥር አዲስ የተሰባሰበ ማንነት በጠነከረ ቁጥር ከመሀል የመነጠል /centrifugal force/  በእጅጉ እያየለ መሄዱ አይቀርም፡፡ በዚህ ላይ ክልሎች በጊዜ ሂደት “ባናና ሪፐብሊክ”መሆን እንደሚችሉ የልብ ልብ የሚሰጣቸው አንቀጽ 39 ሲደምርበት፣ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ ይህ በገደል የተከበበ ፌደላዊ ስርዓት፣ በጊዜ ካልተከለሰ መዘዙ እጅግ የከፋ እንደሚሆን ለመገመት የነብይነት ስጦታ አይጠይቅም፡፡
በየትኛው መንገድ እንሂድ?
ፌደራላዊው ስርዓቱን ለመከለስ ሕገ መንግሥቱን መነካካት የግድ ይሆንብናል። ሕገመንግሥት እንደ ወንጌል ቃል አይነኬ አይደለም፡፡ ምዕራባዊያን ሕገመንግሥታቸውን እንደ አየአስፈላጊነቱ በየጊዜው አሻሽለዋል፡፡ በሕገመንግሥቱ መሠረት፤ በፌደራላዊው አወቃቀር ውስጥ የተፈጠሩት አስተዳደራዊ ክልሎች፣ ከምክንያታዊነት  ይልቅ ዘርቆጠራን ያስቀድማሉ፡፡ ለዚህም ነው ለቁጥር የሚታክቱ የድንበር ግጭቶች በየአካባቢው ሲከሰቱ የምናስተውለው፡፡ ከፉኮ በተዋስነው አስተምህሮት መሠረት፣ አካባቢያዊ ገጽታዎችን ታሳቢ ያደረገ መልክአምድራዊ ፌደራላዊ አወቃቀር ብንከተል፣ ጦሱን በጊዜ ማብረድ ይቻላል፡፡
የፌደራል ስርዓታችን፣ ከምዕራቡ ዓለም ፌደራላዊ ሥርዓት ይልቅ ታሪክ ሆነው ለቀሩት ለቀድሞ የሶቪዬት ኅብረትና የጎዝላቪያ የቀረበ ነው፡፡ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፌደራል ስርዓትን ዘርግተው፣ ስኬታማ ከሆኑት እንደ ካናዳና ስዊዘርላንድ ካሉ ሀገራት ተሞክሮን በመወስድ በዙሪያችን እያንዣበበ ካለው የእልቂት ድግስ በጊዜ መጠበቅ እንችላለን፡፡
የሀገራችን የፌደራላዊ ስርዓት መርህ፣ አንድነት በልዩነት ውስጥን /Unity through diversity/ ታሳቢ ያደረገነው፡፡ የምዕራባዊያኑ በአንጻሩ በልዩነት ውስጥ አንድነት /Diversity through unity/ በሚል መርህ እውን የሆነ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ነው፡፡ የእኛ ፌደራላዊ ሥርዓት መደምደሚያው ልዩነት ሲሆን በተቃራኒው የምዕራባዊያኑ ዲሞክራሲያዊ ፌደራላዊው ሥርዓት ዋንኛ ዓላማ፤ ልዩነትን አጥብቦ፣ በማሳረጊያው አንድ የተዋሀደ ፖለተካዊ ማኅበረሰብን መፍጠር ይሆናል፡፡
ፉኮ በደምሳሳው ከሚኮንነው ጥቅል ማንነት ጋር ልዩነት ሊኖረን የሚችለው ስለ ኢትዮጵያዊነት ስናስብ ነው፡፡ ሊከለስ የሚገባውየፌደራላዊው አወቃቀር፣ ለአካባቢ ማንነቶችፊት መስጠት ያለበትን ያህል፣ የሀገራችን ሕዝቦች እንደ ዋርካ የሚጠለሉበት ጥቅል ማንነትም በእዛው ልክ ማጠናከር ይኖርበታል፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው፡፡ እዚህ ጋር ከፉኮ አስተምህሮት ጋር እንቃረናለን፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነትግን በግድ የሚጫን ርዕዮተ ዓለም በመሆን ፋንታ የሕግ የበላይነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነትየጎመራበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫው ይሆናል፡፡

እንደ ማጠቃለያ
ሀገራችን ኢትዮጵያን የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት እንደነበረች በማወጅ እውን የሆነው የ1987 ሕገመንግሥት፣ ቁመና በብዙ ረገድ ከቀድሞው የሶቪየት ኅብረቱ የስታሊን ሕገመንግሥት ጋር ይመሳሰላል፡፡
የ1987ቱን ሕገመንግሥት ተከትሎ የተተገበረው ፌደራላዊ ሥርዓት፤ ለኢትዮጵያዊነት ሥነ ልቦና ቦታ የለውም፡፡ በብሔር መኩራት እንደ በረከት፣ በኢትዮጵያዊነት መኩራት ደግሞ እንደ መርገም የሚቆጠርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ የጠነከረ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ያላቸውን ወገኖች ወይም ቡድኖች ትምህክተኛ፣ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ በሚል ተቀጽላ ቅስማቸው እንዲሰበር ተፈርዶባቸዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በእቅፏ ውስጥ ያሉት ብሔረሰቦች የመኖር ዋስትና የሚረጋገጠውዓመት ተጠብቆበሚዘጋጅየመድረክ ትርዒትአይደለም፡፡ይህ አይነት የባህል አከባበር በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ሪፐብሊክ የተለመደ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ዓይነት አካሄድ ዩጎዝላቪያን ከመበታተን ሊታደጋት አልቻለም፡፡ አሰፋ ፍሰሃ “Ethnic Federalism” በሚለው ድርሳን ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ይህንን ቁምነገር አስፍሯል፡፡ “The Ethiopian federal system is close to a confederation in form, but it is centralized in practice, and that the reasons for this centralization have to be sought at political rather than at constitution level.”  ፌደራላዊው ስርዓት የሚዘወረው ከዲሞክራሲያዊ መርህ ፍጹም ባፈነገጠየፓርቲ ማእከላዊነት ሥርዓትና ደንብ እንደሆነ ከልሂቁ ምልከታ መገንዘብ እንችላለን፡፡
ስለዚህ እውነተኛ የራስን ዕድል በራስ የመወስን ዋስትና ለፍሬ የሚበቃው እኩልነት፣የሕግ የበላይነትና ወንድማማችነት የናኘባት፣ ጠንካራ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለአይነ ሥጋ ስትበቃ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከላይ የሚጫን ሸክም ወይም ዱብዳ ከመሆን ይልቅዜጎች በተድላና ፍስህ ተፈቃቀድው የሚጋሩት አቃፊ ስነ ልቦናን መወከል ይኖርበታል፡፡

Read 4010 times