Saturday, 23 December 2017 09:53

የ“አደፍርስ” ሁሌ እሸትነት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)


    “…ነጭ ቀ ሚስ እ ለብሳለሁ… በ ዚያ ላ ይ ካ ባ እ ደርባለሁ… ሚ ዜዎቹ እ ኔ ል ዘል፣ እ ኔ ል ዘል እ ያሉ ይ ጣላሉ…. ከ ዚያም…ምንድነው ነ ገሩ…የለም፣ የለም… ቆይ…መጀመሪያ፤ እኔን ለማየት ይፈልጋል… እንዲያው ላይኑ ያህል… እደበቅበታለሁ፤ እኔ ደሞ … ውሃ መቅጃ እንኳ አልሄድም … ከዚያ ምንድነው ነገሩ … ለጓደኛዬ ጉቦ ይሰጥና … ጫማዋን ይስምና፣ አንድ ምክኛት ፈጥራ እንድትጠራኝ ያደርጋል--”
      
    በታሪክ እንደ ፈርጥ የሚንቦገቦጉ አምስት ዓመታት አሉ፡፡ የእነዚያን ዓመታት ያህል በሥነ ጽሑፍ ታሪካችን “ወርቃማ” የሚያሰኝ ካባ የደረቡ እድለኞች የሉም። ሁልጊዜ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍን በተመለከተ ስናወሳ፣ ከፊታችን ድቅን፣ ከከንፈራችን ብቅ የሚሉት እነርሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ዓመታት ከ1958 እስከ 1962 ዓ.ም ያሉት ናቸው፡፡
1958 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ (በአማርኛ የዘመናዊውን ልብ ወለድ መስክ ለሀገራችን ያስተዋወቀው “ፍቅር እስከ መቃብር” ለህትመት የበቃበት ዓመት ነው። ከዚያ ቀጥሎ በ1962 ዓ.ም “አደፍርስ” እና “ከአድማስ ባሻገር” ታትመው፣ የአማርኛውን ሥነ - ጽሑፍ እልፍኝ፣ በውበት ጉዝጓዝ አድምቀውታል፡፡
የእነዚህ ሦስት ታላላቅ መጽሐፍት ደራሲዎች ማለትም ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ዳኛቸው ወርቁና በዐሉ ግርማ በዘመኑ የምዕራቡን ዓለም ጣዕም ቀምሰው፣ ስልጣኔውን ገምግመውና አንብበው የመጡ፣ ስልጡን ደራሲያን ነበሩ፡፡ ስለዚህም ጭብጦቻቸው ዘመናዊውን ዓለም የተጎዳኙ፣ ስልጣኔና ለውጥ የሚናፍቁ፣ አሮጌውን የሚተቹና አዲሱን ተስፋ የሚጠቁሙ ነበሩ፡፡ “ፍቅር እስከ መቃብር” ውስጥ ጉዱ ካሳ፣ “ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ ደግሞ አበራ ወርቁ፣ ፍትህና ነፃነትን የሚናፍቁ፣ ጭቆናና ኋላቀርነትን የሚቃረኑ ነበሩ፡፡
እነዚህን ሦስት የታሪክ ብርቅዬ መጻሕፍት ለፍንጭ ያህል በቡድን አቀረብኳቸው እንጂ የኔ ትኩረት ከሦስቱ በተለየ ሁኔታ ትውልድ ያልተስማማበትንና ጎራ ለይቶ የሚከራከርበትን “አደፍርስ”ን በጥቂቱ ማየት ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ከታተመበት ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ በደራሲንና ሃያሲያን መካከል አከራካሪ የነበረና እስካሁንም ድረስ አንባቢውን ግራ እያጋባ፣ ተደራሲውን እየፈተነ የሚገኝ የጥበብ ውጤት ነው፡፡
ለምሳሌ “አደፍርስ” ታትሞ በወጣበት 1962 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ  በታተመው መነን መጽሔት ላይ የጻፈው ደራሲ ብርሃኑ ዘርይሁን፣ ስለ መጽሐፉ ቀጣይ አከራካሪነት እንዲህ ሲል ጠቁሟል፡-  
“አደፍርስ” የተሰኘው አዲሱ የዳኛቸው መጽሐፍ፣ በአንባቢያን ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት እንደሚኖረው፣ ምን ያህል አድናቆትም እንደሚፈጥር ገና ወደፊት የሚታይ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን “አደፍርስ” በስነ ጽሑፍ አቀራረቡም ሆነ በመሰረተ ሀሳቡ ከፍተኛ ክርክር እንደሚያስነሳ አይጠረጠርም፡፡ በእርግጥ አከራካሪ መጽሃፍ ነው፡፡ ደራሲ ብርሃኑ ዘርይሁን፣ የተነበየው ትንቢት እውን ሆኖ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፡፡ ከዚህ ቀደምም በርካታ መጽሔቶችና ጋዜጦች “አደፍርስ”ን በተመለከተ የተለያዩ ሃሳቦችን አንሸራሽረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ደራሲያን መጽሔት የሆነችው “ብሌን”፣ በርካታ የስነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን አወያይታለች፡፡ በ”ብሌን” መጽሔት ቅጽ 1 ቁጥር አንድ ላይ ደራሲያን፣ ሃያሲያንና የስነ ጽሑፍ መምህራን፣ እንዲሁም አርታኢው አቶ አማረ ማሞ ስለ መጽሐፉ ብዙ ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጽሑፍ መምህርና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ ዘሪሁን አስፋው እንደሚሉት፤ የአጻጻፍ ስልቱ፣ የፈሰሰ ዐቅል ፍንጭ እንደሚታይበት ጠቁመው ነበር፡፡ ዶ/ር ታዬ አሰፋ፤ ይህንን የአጻጻፍ ስልት እንዲህ ይገልጡታል፡-
ይህ አጻጻፍ የራሱ መለያ ባህርያት አሉት። ዋና ዋናዎቹ የእሳቤው አወራረድ ቅደም ተከተል መመሰቃቀል፣ በአሳቦቹ መካከል ያለው ግንኙነት በነፃ ተዛምዶ (Free association) ላይ መመስረትና ትልምን የማራመድ ወይም ጭብጥን የማስተላለፍ ዐላማ ማጣት፣ በገፀ ባህርይው አእምሮ ውስጥ ስለሚዥጎደጎደው እሳቤ ምንነት፣ የተራኪው ጣልቃ ገብቶ ያለመጠቆም እንዲሁም የዕሰቡ ለአንባቢው ሲባል በትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ ተለይቶ ያለመቅረብ ናቸው፡፡” ካሉ በኋላ “ውስጣዊ መነባንብ ወይም (Interior monologue) የአሁን ጊዜ የሚያሳይ ዕሳቤው የሚጠቀስባቸው ተውላጠ ስሞችም አንደኛ መደብ መሆን አለባቸው” የሚለውን አስፍረዋል።
ለዚህም ይመስለኛል አንድ እንግሊዛዊ ደራሲ “The stream of conciousness techinque is characterized by the inwardness of the author” የሚሉት፡፡ የእኛ ሀገር የስነ ጽሑፍ ምሁራን ደግሞ የዳኛቸውን አጻጻፍ ማለትም የትረካውን አንጻር፣ ተውኔታዊ በማለት ይገልፁታል፡፡ ይህ ደግሞ ከላይ “የፈሰሰ አቅል አጻጻፍ ባህርይ ነው” በሚል ዶ/ር ታዬ አሰፋ ከጠቀሱት ጋር ይመሳሰላል። ደራሲው በጉዳዩ እጁን ሳያስገባ ዳር ሆኖ፣ ገፀ ባህርያቱ እንደ ተዋናዮች፣ የየራሳቸውን ሀሳብ ሲገልጡ ቆሞ ያያል፤ ያሳያልም፡፡ ለምሳሌ፡- ምዕራፍ 35 - ገፅ 216፣ እንዲህ ተቀምጧል፡-
እሁድ ለት ከቤተ ክርስቲያን መልስ፣ ወደ ዋርካው ጥላ ሲያመሩ፣ “ስሚኝ ፍሬዋ፣ ጋሼ ጥሶ፣ የሚያመጣው የባህል ተጠየቅ ሁሉ ሳይገባኝ ቀርቶ አይምሰልሽ በየጊዜው ስንከራከር የምትሰሚው…” ይወተውታል አደፍርስ፡፡
“እንዲሁ ስትከራከር ነው የሚመሽልህ፣ በየጊዜው አንዱን ነገር! እኔ የማመጣው አንድ ነገር ብቻ አይደለም፤ ብዙ ነገር ነው …
“እምልህ … ስለ ባህላችን፣ ስለ ሕጋችንም ሆነ ስለ ሌላው … አሁን ለምሳሌ ኢትዮጵያ ነበሩ፣ አሉ፣ ይመጣሉም ብላ ስለምታምንባቸው መሪዎችና ጀግኖች፣ ጻድቃንና ሰማዕታት … ከኔም ይሁን ከባዬ ጋር ስንት ስንት ጊዜ ነው የተከራከርከው …
“ነበሩ ስለሚባሉት መቼም፣ አሁንም ቢሆን የማውቀው፣ ነገር የለኝም .. ይመጣሉ ስለሚባሉትም በሰማየ ላም አለኝ …
“እንዴት በሰማይ ላም አለኝ ይሆናል? ደግሞስ ስለነበሩት እንዴት አታውቅም? ባይሆን እያወቅህ አላምንም ወይም አልቀበልም በል እንጂ ጨርሰህ አላውቅም የምትለውን ነገር አልሰማም … እንኳን አንተ ብዙ የተማርከው እኔም ዐውቃለሁ፣ እላለሁ..”
“እኮ ከመሪዎች ውስጥ እንደ ዘርዓ ያዕቆብ፣ እንደ አምደጽዮን ያሉትን … ከጀግኖች እንደ ልዑል ራስ መኮንን፣ ራስ ጎበና፣ ደጃች ባልቻ፣ ራስ አሉላ … ከጻድቃን እንደ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ እንደ ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ … ከሰማዕታት እንደ ቴዎድሮስ፣ እንደ ዮሐንስ፣ ዓይነቶቹን ማለትሽ ይሆናል ምናልባት ..
“ምን እኔ ብቻ፣ አንተም ማለትህ ይሁን እንጂ! በተዘረዘሩት ለማንኛዎቹም መስኮችኮ ቢሆን ሌላው ክፍለ ዐለም በጊዜያቸው ከነበሩት ባለታሪኮች የሚያንሱ አይደሉም…
አባ ዮሐንስ፤ አቶ ጥሶ፣ አቶ ወልዱ፣ ወይዘሮ አካላትና በላይ ሆነው እየተጨዋወቱ፣ ወደ ዋርካው ሥር ይመጣሉ፡፡
ከላይ የነበረው ምልልስ በተዘዋዋሪ ችሎት ዳኛው፣ አጎቱ የጥሶ- ልጅ ፍሬዋ ጋር- የሚለዋወጡትን ሀሣብ ወይም የሚሟገቱትን ሙግት-ነበር ያየነው፤ በዚህ ተውኔታዊ አጻጻፍ ስልት ደራሲው ገፀ ባህርይቱ የሚናገሩትን ያደምጣል፤ የሚከወኑትን ያጤናል እንጂ ጣልቃ ገብቶ ሀሣብ አይሰጥም፡፡ ስለዚህ ይህ ዐይነቱ ትረካ “ካሜራዊ አቀራረብ” ይባላል፡፡ እንደ መድረክ ቴአትር፣ ተዋዮቹ ህይወታቸውን ሲኖሩ፣ ዕጣቸውን ሲቀበሉ ከቃለ ተውኔቱ እንደምናውቅና- ታሪኩም ወደ ፊትና ወደ ኋላ ሲል እንደምናደምጥና እንደምናስተውል ሁሉ ደራሲው በዚህ አንጻር- ነፃ ሜዳ ይተውልናል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ተረት ለለመደውና፣ በተፋፋመ ግጭት፤ ታሪኩን የሚያፋጥነውን- ባለ ጥብቅ ሴራ-ትረካ፣ ለለመደ ተደራሲ፤ ጉዳዩ ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ ደራሲው ሀሳብ የተቋረጠ በመሰለን- ቁጥር ድልድይ እየዘረጋ፤ መሠላል እያቆመ አያሻግረንም…ይልቅስ አንባቢያን ከፊል ተሣታፊ በመሆን ጉዳዩን በአንክሮ እናጤናለን፡፡
የ”አደፍርስ” ሌላው ልዩ ባህርይ፣ ከዋናው ሴራ በተጨማሪ በየጣልቃው፣ ለብቻቸው ዳስ የጣሉት አነስተኛ ትልሞች፤ ንዑስ ሴራዎች ናቸው። መጽሐፉ ውስጥ የተወጠነው ዐቢይ ሴራ፣ በሁለት መደብ መካከል በተከፋፈሉ ገፀ ባህርይት የሚካሄድ ግጭት ነው፡፡ ወጣቱንና በዘመኑ የተማረና ለውጥ ፈላጊ የሆነው ገፀ ባህሪ አደፍርስ፤ ቀድሞ የነበረው ኋላ ቀርና ወግ አጥባቂ ስርዐት ደጋፊዎች ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ ነው፡፡ በዚህ ፍልሚያ ደግሞ -የመሬት ባለቤቷ ወይዘሮ አሰጋሽን ጨምሮ ጎርፉ፣ አቶ ጥሶ፣ አባ ሀዲስና ሌሎቹም ባንድ ወገን ሆነው፣ በታሪኩ ውስጥ ይፋጫሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአደፍርስና ጺዎኔ፣ በጴጥሮስና በሮማን መካከል ያለው የፍቅር ግንኙነት፤ እንዲሁም በቅንዐት የበቀለው የጎርፉና የአደፍርስ ቅራኔ፤ የጺዎኔና የሮማን- መቀናናት፣ በሌላ ንዑስ ሴራ ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡--- በማለት ዶ/ር ታዬ አሰፋ ይሸነሽኗቸዋል፡፡
እንዲሁም በክብረትና በፍሬዋ፤ በበላይና በፍሬዋ፣ በክብረትና በበላይ መካከል የሚፈጠረው  ፍቅር አዘልና ቅናታዊ ግንኙነት የሚመሠረተው በሌላ ንዑስ ሴራ ነው።
ከላይ ስላነሣሁትና ዶክተር ታዬ አሰፋ በጽሑፋቸው (የካቲት መጽሔት፤ 1983) ስለጠቀሱት (ውስጣዊ መነባነብ) Interior monologue አደፍርስ ገፅ 123-125- ያሉትን ገፆች ማንበብ ግድ ይላል፡፡
ገፅ 123- ላይ እንዲህ ለውስጧ ታወራለች- ሮማን፡፡ እኛና ደራሲው እናደምጣለን፡-
…ነጭ ቀሚስ እለብሳለሁ… በዚያ ላይ ካባ እደርባለሁ… ሚዜዎቹ እኔ ልዘል፣ እኔ ልዘል እያሉ ይጣላሉ…. ከዚያም…ምንድነው ነገሩ…የለም፣ የለም…ቆይ…መጀመሪያ፤ እኔን ለማየት ይፈልጋል… እንዲያው ላይኑ ያህል… እደበቅበታለሁ፤ እኔ ደሞ … ውሃ መቅጃ እንኳ አልሄድም … ከዚያ ምንድነው ነገሩ … ለጓደኛዬ ጉቦ ይሰጥና … ጫማዋን ይስምና፣ አንድ ምክኛት ፈጥራ እንድትጠራኝ ያደርጋል … ሞኝት፣ ተላሊት፣ ምንድነው ነገሩ … አገር ጤና ነው ብያለሁ በኔ ቤት፣ ፈሰስ፣ ፈሰስ ስል … አንድ ሪቅ ሥር ተደብቆ አየዋለሁ … ሪቅ! …ሪቅ! … አዲሳባ ሪቅ የለም! የብረት በርሜል ነው ብለዋል፣ የእህል ማስቀመጫቸው … ያላየሁት መስሎት ታዲያ አንገቱን ብ…ቅ ሲያደርግ ከበርሜሉ ስር … ምንድነው ነገሩ … እንደ መጮህ ብዬ እደነግጥና ወደ ቤት እበራለሁ፤ ምኑ ቅጡ …. አኮርፋታለሁ፣ ከዚያ በኋላ ጺወኔን አላነጋግራትም፣ አኮርፋታለሁ … አባ አዲሴ አማላጅ ሆነው ይመጣሉ፣ ይለምኑኛል … በቅዱስ ሚካኤል ይዤሻለሁ …” አላለቀም፣ ለማሳያ ያህል ይበቃል፡፡
ይህን ሁሉ በልብዋ የምታመላልሰው ሮማን ናት፡፡ ሮማን ወደ ኋላ አካባቢ፣ የአደፍርስ ልብ ውል የሚልባት ገፀ ባህሪ!
የአደፍርስ መጽሐፍ ዋና ገፀ ባህሪን ዳኛቸው ወርቁ ያስተዋወቀን እንዲህ ነው፡- “በአብዛኛው አፋዊ ድርጊቱ ግድየለሽ ነው፡፡ ፀጉሩ መላ የለው። ሲያሰኘው ባጭሩ ያስቆርጠዋል፡፡ ሲያሰኘው ያጎፍረዋል፡፡ ሲያሰኘው ደሞ ጨርሶ ተላጭቶ፣ ኮፍያ መሳይ እልጩ ላይ ጣል አድርጎ ብቅ ይላል፡፡
አለባበሱ መላ የለውም፣ አንዳንዴ ሸሚዝና ቁምጣ፣ አንዳንዴ ካናቴራ፣ ጃኬትና ቦላሌ፣ አንዳንዴ ሱፍ ኮትና ካኪ ሱሪ፣ አንዳንዴ ደግሞ አጊጦ የመጣለት ኮቱ አንድ አይነት፣ ሱሪው ሌላ ዓይነት፣ የሆነ ሱፍ ልብስ  መላ የሌለው፤ አረማመዱ መላ የሌለው …
ፈሰስ አቅል የተባለውን የአጻጻፍ ስልት ዳኛቸው ወርቁ፣ ወደ ሀገራችን አምጥቶታል፤ የዚህ አጻጻፍ ስልት ባለቤትና ፈር-ቀዳጅ የሚባለው ሰው በአንደኛው ዓለም ጦርነት ዋዜማ ሲያመጣው፣ መነሻዎቹ እነማን ናቸው የሚለውንም ማየት ያስፈልጋል፡፡ በጥቅሉ የአደፍርስ ታሪክና ጭብጥ፤ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ምንድነው? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ እውነት ምንድን ነው? ለዛሬ ግን ልሰናበታችሁ፡፡ ቸር ያገናኘን!!     

Read 817 times