Print this page
Saturday, 23 December 2017 10:43

በአስመጭ ነጋዴዎች ላይ የተጣለው ደንብ!?

Written by  ተስፋ በላይነህ
Rate this item
(12 votes)

መንግስት አሁንም የዶላር እጥረቱን ችግር ለመቋቋም በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሬያቸውን በመጠቀም “ዲያስፖራ አካውንት” እንዲከፍቱ በማድረግ፤ ከሚኖሩበት አገር የውጭ ምንዛሬን በመላክ እቃ እንዲገዙ ያደርጋል፡፡
    
   ብሔራዊ ባንክ በያዝነው ወር ታሕሳስ 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስመጭዎች ላይ አዲስ ደንብ አውጥቷል፡፡ ይሕ ደንብ ለዓመታት ይሰራበት የነበረውን የአቋራጭ መንገድ ግብይት የሚገታና በአስመጭዎች ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው፡፡ (ብሔራዊ ባንክ ባለ 7 አንቀጽ መመሪያ (FX/52/2017) እ.ኤ.አ ዲሴምበር 1 2017 ዓ.ም ለሁሉም ባንኮች አስተላልፏል)
ከአስመጭነትም ሆነ ከንግዱ ዓለም  ውጭ የሆኑ ሰዎች እንዲረዱት፤ አንድ አስመጭ ነጋዴ የሚያልፍባቸውን ሂደቶች በአጭሩ መመልከት ይኖርብናል፡፡
ነጋዴው ከውጭ ለሚያስገባቸው (ለሚያስመጣቸው እቃዎች) መግዣ የሚሆን ዓለም አቀፍ መገበያያ ገንዘብ (ፎሬይን ከረንሲ) ያስፈልገዋል፡፡ ይህም በአገሪቷ ሕግ መሰረት፤ አስመጭው የውጭ ምንዛሬ የሚያገኘው ከባንኮች ነው፡፡ የውጭ ምንዛሬ እንዲሁ በቀላሉ የሚገኝ ነገር ስለማይሆን ነጋዴው የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሬ መጠን ከሚፈልገው እቃ ዝርዝር ጋር አስቀድሞ ባንኩን (በፕሮፎርማ ኢንቮይስ) ይጠይቃል፡፡ ይሕም የሚገዛቸውንየእቃ ዝርዝሮች ከነዋጋቸው“ፕሮፎርማ ኢንቮይስ” (በዶላር ዋጋ) ሲያቀርብ፤ ባንኩ ለቀረበለት የዋጋ መጠን ዶላር ይሰጠዋል፡፡ ዶላሩን የሚሰጠው በካሽ ሳይሆን፤ እቃውን ለሚያቀርብለት ድርጅት ማለትም በፕሮፎርማ ኢንቮይሱ ለተጠቀሰው የውጭ ድርጅት ባንክ ሒሳብ ቁጥር፣ ገንዘቡን በባንክ ያስተላልፋል፡፡ ይህንንም ብሔራዊ ባንክ በኃላፊነት ይቆጣጠራል፡፡
ገንዘቡ በተለያዩ መንገዶች መተላለፍ ይችላል፡፡ መጠነኛ የዶላር መጠን(አብዛኛውን ጊዜ እስከ 5ሺ ዶላር ከሆነ) በ “ቲቲ” (በቴሌግራፊክ ትራንስፈር) መልክ ይልከዋል፡፡ ወይንም ደግሞ በሲ.ኤ.ዲ (ካሽ ኢን አድቫንስ) አሊያም ደግሞ በኤል.ሲ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) መልክ ያስተላልፋል፡፡
ለምሳሌ አንድ አስመጭ፣ የአምስት ሺሕ ዶላር እቃ ዝርዝር ሲያቀርብ፤ አስመጭው የአምስት ሺሕ ዶላር (በብር) ከሒሳብ ቁጥሩ እንዲቀነስ ያዛል፡፡ ባንኩ በእለቱ ምንዛሪ መሰረት የታሰበ የብር መጠን ከደምበኛው ሒሳብ ቁጥር ይቀንሳል፡፡ በወቅቱ ምንዛሬ በ2010 ዓ.ም አምስት ሺሕ ዶላር በ27 ብር አስቦ ማለትም (ወደ 135ሺ ብር አካባቢ) አስመጭው ይከፍላል፡፡ አስመጭው በከፈተው የዶላር አካውንት ውስጥ ዶላሩ ይቀመጥለታል፡፡ ከዚሁ ሒሳብ ላይ ተቀናሽ ሆኖም ይተላለፋል፡፡  የአስመጭነት ፈቃድ አግኝተው፣ የኢትዮጵያ ብር ይዘው፣ ከባንኮች ዶላር በማጣት ብቻ ለዓመታት የተቀመጡ ነጋዴዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡
የዶላር ነገር እጅግ አሳሳቢ ነገር በመሆኑ፣ ይሕ አስመጭ ይሕንን ዶላር የሚያገኘው በመከራ ነው፡፡ በዚህች ውስን ዶላር በርካታ እቃዎችን ለማስመጣትም ይገደዳል፡፡ ባንኩም በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር መሰረት፣ ወደ ተፈለገበት አገር የሻጭ ድርጅት ሂሳብ ቁጥር ገንዘቡን መላኩን ሲፈቅድ በተለምዶ “ፐርሚት ነምበር” የምንለውን ለአስመጭው ይሠጣል፡፡
“ፐርሚት ነምበር” ወይንም የፈቃድ ቁጥር የያዘ አስመጭ (አንዳንዴ በባንኩ ፈቃደኝነት) እቃዎችን እቀያየረ ማስገባት ይችላል፡፡ ነገሩ አሁንም በቀላሉ እንዲገባን ከውጭ አገር የሚመጣ እቃ (መኪናን) እንውሰድ!
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ላይ የሚገቡ መኪኖች፣ አብዛኛው ከዱባይ የሚጫኑ ናቸው፡፡ በተለይም የጃፓን ምርት የሆነው የቶዮታ መኪና ምርቶች ከተማችንን አጥለቅልቀውት እናያለን፡፡ አንድ የመኪና አስመጭ፣ ከመንግሥት ያገኘውን 5000 ዶላር፣ አንድ መኪና ልግዛበት ብሎ ቢያስፈቅድ፤ አንድ መኪና ካስገባ በኋላ አጁን አጣጥፎ ሌላ የዶላር ፈቃድ መጠበቅ ስለሚኖርበት፤ ይሕችን 5000 ዶላር መሸንሸን ግዴታ ይሆንበታል፡፡ ይሕም ማለት የአንዱን የመኪና መግዣ ዋጋ ማሳነስ፣ እስከ ዛሬ የሚስተዋለው አማራጭ ነበር፡፡ “አንደር ኢንቮይስ” የሚባለውም ይሄው ነው፡፡
የአንድ መኪና ዋጋ 500 ዶላር ነው ብሎ ለባንኩ ቢጠይቅ በ5000 ዶላር አስር መኪኖችን ማስገባት ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ አሰራር በተከታታይ ሲሰራበት የቆየ ቢሆንም፤ የመኪና ፈላጊው ቁጥር እጅግ ስለጨመረ፤ አስመጭው በመከራ የተገኘችውን “የሞት መድሃኒት” 5000 ዶላር፤ አሁንም ወደ ዝቅተኛ ክፍልፋዮች መሸንሸን ግድ ይሆንበታል፡፡ በነጻ ገበያ መርህ መሰረት፤ አንድ ነጋዴ እቃውን ያዋጣኛል ባለው ዋጋ መሸጥ ስለሚችል (መግዛትም ስለሚችል)፤ አስመጭው አንዷን መኪና በ100 ዶላር ልገዛው ነው ብሎ ባንኩን ይጠይቃል፡፡ ማለትም 5000 ዶላር ለአንድ መቶ ሲካፈል ሃምሳ መኪኖችን ማስገባት ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ አሰራር እስካሁን ሲሰራበት የነበረ ሐቅ ነው!
መንግስትና ነጋዴ ለዓመታት በዚህ አሰራር “እየተጋገዙ” የውጭ ምንዛሬውን እጥረት ሲሞሉት ነበር፡፡ አሰራሩ ለሁለቱም አካላት ግልጽ ቢሆንም ይህንን ችግር ያመጣው የዶላር እጥረት በመሆኑ ሳቢያ፤ በዝምታ እየታለፈ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ በ2010 ዓ.ም ይሕ አሰራር እንዲቆም ተወሰነ፡፡
መንግስት አሁንም የዶላር እጥረቱን ችግር ለመቋቋም በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሬያቸውን በመጠቀም “ዲያስፖራ አካውንት” እንዲከፍቱ በማድረግ፤ ከሚኖሩበት አገር የውጭ ምንዛሬን በመላክ እቃ እንዲገዙ ያደርጋል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ውጭ አገር የሚኖር ከሆነ እና በስሙ የአስመጭነት ፈቃድ በማውጣት የዶላር ሒሳብ ቁጥር (ዲያስፖራ አካውንት) በፈለገበት ባንክ መክፈት ይችላል፡፡ ከፍቶም ከፈለገበት አገር ዶላር እየላከ፣ የመግዣ ፈቃድ ማግኘት ይችላል፡፡
አሁን ላይ መንግሥት ያወጣው ሕግ አንድ አስመጭ በተጋነነ ዝቅተኛ ዋጋ እቃ ማስገባት እንደማይችል ሲሆን፤ ለዚህም ከውጭ አገር ለሚመጡ እቃዎች የራሴን የዋጋ ዝርዘር አስቀምጣለሁ በማለት፤ ለምሳሌ አስመጭው 100 ዶላር ገዛሁት የሚለውን አንድ መኪና፣ ከአራት ሺህ አምስት መቶ ዶላር በታች አትገዛውም በማለት፤ ከውጭ ለሚገቡ እቃዎች የዋጋ ተመን አቅርቧል፡፡
አንድ 5000 ዶላር በመከራ የሚያገኝ አስመጭ፤ አንድ መኪና ብቻ ገዝቶ፤ በመርከብ ልኮ፤ የሚያገኘው ትርፍ ስንት ሊሆን እንደሚችል ማሰብ አያዳግትም፡፡ ለጅቡቲ የምንከፍለው የወደብ ኪራይ በራሱ ራስ ምታት በሆነበት ወቅት፤ ለሰራተኛው፣ ለቤት ኪራይና መኪናውን ለመግዛት የሚያወጣው ወጭ ሁሉ ተደምሮ፣ የአንድ መኪና ዋጋ ሰማይ እንደሚነካ መገንዘብ ይቻላል፡፡
አስመጭው 5000 ዶላር ይዞ፣ 50 መኪኖችን እንዴት መግዛት ይቻላል? ብለን ለመጠየቅ  መገደዳችን አይቀርም፡፡ አስመጭው 5000 ዶላሯን የሚጠቀምባት ሕጋዊ የባንክ ፈቃድ (ፐርሚት) ለማግኘት እንጂ ሌላውን የመኪና መግዣ (የውጭ ምንዛሬ) የሚያገኘው አገር ውስጥ ካሉ “የውጭ ምንዛሬ ሻጮች” አልያም በውጭ ከሚኖሩ መደበኛ ያልሆኑ  “ሐዋላ አቅራቢዎች” አማካኝነት ነው፡፡ ይሕም ከባንክ የዶላር መግዣ ዋጋ በውድበመግዛት ነው፡፡አስመጭዎች  በባንክ 27 ብር የሚሸጥን ዶላር እስከ 32 ብር ድርስ በመክፈል ዶላር በመግዛት እቃዎችን ይገዛሉ፡፡ ይሕም የእቃውን ዋጋ ከሚያንሩት ምክንያቶች አንደኛው ነው፡፡
ስለዚህ አሁን የተቀየረውን አሰራር ስንመለከት፤ አንድ መኪና አስመጭ፣ አንድ መኪና ለመግዛት መጠየቅ ያለበት ዶላር ዝቅተኛው መጠን 4500 ዶላር ከሆነ፤ እያንዳንዱ እቃብሄራዊ ባንክ የተመነውን ዋጋ በመመርኮዝ፣ ከመንግስት ዶላር  ይጠይቃል፡፡ ይህም ማለት አንድ መኪና አስመጭ፣ 10 ቪትዝ መጫን ቢፈልግ፣ 45ሺ ዶላር ከመንግስት መጠየቅ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ዋነኛው እና ትልቁም ጥያቄም 5000 ዶላር ማግኘት መከራ የሆነችበት አስመጭ፤ እንዴት ብሎ ነው 45 ሺሕ ዶላር በቀላሉ ከባንኩ ማግኘት የሚችለው? ይሕ አሰራር የዶላር አጥረት ለማያሳስባት አገር ቀላል ሊሆን ይችላል፤ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ግን ከፍተኛ ችግርን መፍጠሩ እይቀሬ ነው፡፡ መንግሥት ይሕን ለምን አደረገ? አሁንስ ለምን ሆነ? ብለው የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡
መንግሥት በበኩሉ፤ ከዚህ በኋላ ምንም አይነት የምንዛሬ እጥረት አይኖርብኝም፤ ጠይቁን የሚል ምላሽ እንዳቀረበ፤ አልያም ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ እንዲሁም የአገር ውስጥ ምርቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመረጠው መንገድ መሆኑን ማሰብ ይቻላል፡፡ በተለይ መኪኖችን ስንመለከት፣ አገር ውስጥ የሚገጣጠሙ መኪኖች ወደ ገበያው እንዲስፋፉ ማድረግ እንደ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የጃፓን መኪና መግዛትን ይመርጣል፡፡ ይሕም ማለት የገዛውን መኪና ከተወሰነ ዓመት በኋላ ለመሸጥ አስቦ የመግዛት ባህል አለው፡፡ አንድ አገር ውስጥ የተገጣጠመን አዲስ መኪና ከሚገዛ፣ ተጨማሪ ከፍሎ ዋጋ ከ15 ዓመት በፊት የተመረተ፣ ያውም ያገለገለ የጃፓን መኪናን መግዛት ይመርጣል፡፡
የአገር ምርትመጠቀምን የመሰለ እድገት/ሥልጣኔ እንደሌለ ይታወቃል፡፡ አንድ ግለሰብ በአገሩ ምርት መኩራት የሚጀምረው በቅድሚያ ስለ አገሩ ልባዊ ፍቅርና ኩራት ሲኖረው፣ የአገር ምጣኔ ሐብት እድገትን መከታተል ሲችልና ተጠቃሚነቱን ማስተዋል ሲጀምር ሲሆን፤ በተከታይም የእቃው ጥራትና አገልግሎት ሰጭነት፣ ሰፊውን ድርሻ የሚወሰድ ገፊ ምክንያት ነው፡፡ የዋጋ መቀነስ ሊጠቀስ የሚችል ምክንያት ቢሆንም ሰዉ ጥራትን በገንዘብ መሸመት እንደሚፈልግ ይስተዋላል፡፡
መንግስት አሁን ያወጣው የእቃዎች ግዥ መተመኛ ዝርዝር፣ ነባራዊውን ገበያ ያላማከለ እንደሆነ በርካቶች ይመሰክራሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ቪትዝ መኪና 4500 ዶላር ድረስ ዋጋ አላት ብሎ ማቅረብ ፈጽሞ ተጨባጭ የሆነውን የግብይት ሂደት ያላማከለ ነው፡፡ መንግሥት የእቃዎችን ዋጋ ተመን ያወጣው በምን ሒሳብ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም፡፡ይሕን ውሳኔ ሲወስን ነባራዊውን ሁኔታ በአካል ቀርቦ አመሳክሯል ወይ? ብለን እንጠይቃለን፡፡ ለምሳሌ አሁንም አንድ የቶዮታ ቪትዝ መኪና በዱባይ መሸጫ ዋጋዋ፣ ከአንድ ሺ ዶላር እስከ 1400 ዶላር ድረስ ብቻ ነው፡፡ አብዛኛው የዱባይ መኪኖች የኢትዮጵያን ገበያ የተቆጣጠሩበት ዋነኛው ጉዳይም ኢትዮጵያ የምትከተለውን የቀረጥ አከፋፈል ዋጋ መሰረት ያደረገ በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵየ መንግሥት መኪኖችን እንደ ቅንጦት እቃዎች ስለሚያያቸው፣ ወደ አገር ውስጥ በቀላሉ እንዳይገቡ የቀረጥ ተመኑን አሳድጓል፡፡ አንድ መኪና ባለው የነዳጅ ፍጆታ መጠን መሰረት ዋጋው ይለያያል፡፡
የመኪናው ሞተር ጉልበት ከፍተኛ የሆነ መኪና፣ ከፍተኛ የሆነ ቀረጥ ስለሚከፈልበት፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝቅተኛ የፈረስ ጉልበት ያለውን መኪና መግዛት ይመርጣል /ይገደዳል/፡፡ ለምሳሌ በተለምዶ አንድ ሲሲ የመኪና ጉልበት ያላቸው መኪኖች (ቪትዝ፣ ያሪስ ወዘተ…) የሚከፈልባቸው የቀረጥ መጠን በአንጻራዊ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ሰዉ ይህችን መኪና ለመግዛት ይመርጣል/ መርጦ ሳይሆን ተገዶ ብንለው የሚያስማማን ይመስለኛል፡፡ 1.3 ሲሲ ያለውም መኪና በአንጻራዊነት ተፈላጊ ሲሆን፤ አገር ውስጥም ለመንዳት ጥሩ የሆነ አቅም ስለሚኖረው በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊነቱ ይጨምራል፡፡ ዱባይ ውስጥ 15 ዓመት የተነዳ 1.3 ሲሲ መኪና፣ 3 ዓመት ከተነዳ መኪና ዋጋ እጅግ የበለጠ መሆኑ ዱባይ ነዋሪ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎችን ማስደቀኑ አልቀረም፡፡  
1.3 ሲሲ የያዘ መኪና (ቶዮታ ኮሮላ) ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈለግበት ምክንያትም ይሄው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ገበያ የሚያቀርቡ ዱባይ የሚገኙ የመኪና ነጋዴዎች፣ የሲሊንደር መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ መኪኖችን ይይዛሉ፡፡ ዝቅተኛ የሲሊንደር መጠን ያላቸው መኪኖች፣ በአብዛኛው ዓለም አቀፍ አገራት ውስጥ ተፈላጊ አይደሉም፡፡ እነዚህ ዝቅተኛ የሞተር አቅም ያላቸው መኪኖች፣ ከ90 በመቶ በላይ የኢትዮጵያን ገበያ ያማከሉም ናቸው፡፡
በእርግጥ ዝቅተኛ የሞተር ጉልበት ያላቸው መኪኖች ጃፓን ውስጥ በብዛት አሉ፡፡ ጃፓን ቀኝ መሪን የምትጠቀም አገር ነች፡፡ ምንም እንኳ ለመላው አለም የምታቀርበው መኪና እንደ የአገራቱ ሕግ መሰረት (በግራ ወይምበቀኝ) መሪ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያን ብቻ ያማከለ ምርት ደግሞ የላትም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ዝቅተኛ የሞተር ጉልበት ያላቸው መኪኖች፣ ቀኝ መሪ በመሆናቸው፤ ኢትዮጵያዊያን ከቀኝ መሪ ወደ ግራ መሪ ማዞር ይጠብቅባቸዋል ማለት ነው፡፡ ይሕንንም ብቻ ለመስራት የተቋቋሙ በርካታ የአፍጋኒስታን፣ የፓኪስታን ጋራጆች በመኪና መሸጫ ዙርያዎች ይገኛሉ፡፡
ለዚህ ሐሳብ የተነሳንበት ነጥብ የመኪናው ዋጋ ሁኔታ ነው፡፡ አንድ መሪዋ ያልዞረ ቪትዝ፣ 1300 ዶላር ትገዛለች፤ 300 ዶላር ተከፍሎ መሪዋ ከቀኝ መሪ ወደ ግራ መሪ ይዞራል፤ ምናልባትም ጎማና አልሙኒየም ቸርኬ እንዲሁም የውስጥ ‹‹ማስዋቢያዎች›› ቢያስፈልጓት፣ እስከ 400 ዶላር ልትጨርስ ትችላለች፡፡ 1300፣ 300 እና 400 ዶላር በድምሩ 2000 ዶላር ይሆናል፡፡ አንድ ቪትዝ መኪና መግዣዋ ከሁለት ሺሕ ዶላር አይበልጥም ማለት ነው፡፡ አሁን መንግሥት ከዚህ ዋጋ በላይ ተመን ካስቀመጠ፣ በምን ሒሳብ አስልቶት እንደሆነም መጠየቅ ግድ ይላል፡፡ ከሆነ ለስራው የወሰደው ምክንያትን ስራውን እንዳይሰራ መፈለጉን የሚያሳይ ይሆናል!
እንደሚወራው ሙሉ በሙሉ የአስመጭውን ስራ ለማስቆምና ጥቂት ሐብታም ነጋዴዎች ብቻ እንዲጠቀሙ ከሆነ ያስተዛዝባል፡፡ የአገር ውስጥ መኪኖች እንዲሸጡ ብቻ ተብሎም ይህ “የዋጋ ተመን እና አሰራር ሕግ” ወጥቶም ከሆነ አሁንም ያስተዛዝባል፡፡ የዶላር እጥረቱን ለመሙላት እና የአሰራር ሂደቱን በመጠኑም ቢሆን ለማስቀረት ታቅዶም ከሆነ አያስኬድም፡፡ ምክንያቱም ሕዝብን አስገድዶ፣ ነገሮችን ተጠቃሚ ማስደረግ፣ የራሱ ጣጣ ይኖረዋል፡፡ የአገርን ምርት መጠቀም የማይፈልግ ማንም የለም፡፡ ዋጋ በተለይም ጥራት ያለው እቃ አገር ውስጥ ማቅረብ ከተቻለ እሰየው ነው፡፡ ይሕ ሳይሆን ግን በዚህ አስገዳጅ ምክንያት ተጠቃሚው በውድም ዋጋ ቢሆን እንኳ መግዛቱ አይቀርም፡፡ የኑሮ ውድነት ከምንጊዜውም በላይ ማሻቀቡን የሚገታው አይኖርም፡፡ ይህ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ተተኪ አቅርቦት ሊኖር በተገባ ነበር!
ማንኛውም የመንግሥት አሰራር ሕግን መከተል ይጠበቅበታል፡፡ ሕግን መከተል ብቻም ሳይሆን ማስከተል(ማስጠበቅም) የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡  በከፍተኛ ሁኔታ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ላይ የተመሰረተ የሸቀጥ አቅርቦት ላላት አገር ከውጭ የሚገባውን እቃ መጠን መቀነስ የሚቻለው በምን መልኩ ነው?
ይህ ከፍተኛ ጥናት የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ነው፣ ሆኖም ጥናቱ አስቸጋሪ ባይሆንም በተግባር ለማስፈጸም ግን ከፍተኛ አቅም፣ ርብርብና ጠንካራ መንግሥታዊ መዋቅር ያስፈልጋል፡፡ እንደው በአጋጣሚ የመኪናን ጉዳይ እንደ ምሳሌነት አቀረብን እንጂ፣ ብረታ ብረቶች፣ የእለት ተእለት አላቂ እቃዎችንም ሆነ ማናቸውንም ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን ስናስብ፣ በአሁኑ ወቅት የወጣው ህግ ከፍተኛ ተፅዕኖን ማሳረፉ እንደማይቀር ተመልክተናል፡፡ ይህም ከውጭ የሚገባወን እቃ ያስቀረዋል ብለን እናስብ ይሆናል፤ ነገር ግን ፈጽሞ የማይታሰብ እንደሆነ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡
ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች (የግለሰቦች በአገራቸው ጉዳይ የያገባኛል ስሜት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የዋጋ ልዩነትና የጥራት ሁኔታ)የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሩን ምርት ሙሉ በሙሉ የመጠቀም ደረጃ ላይ ባለመድረሱ፤ አሁንም ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን ማስቆም አይቻልም፡፡ ያው እንደተለመደው የዋጋ ጭማሪ ይደረግበትና መከረኛው ሕዝብ ጫንቃ ላይ ይጣላል፡፡ መሰረታዊ እቃዎች ላይ ዋጋ ጭማሪ ሆኖ፣ የኑሮ ውድነቱ በከፋ ሁኔታ ይንራል፡፡
ከፍተኛ የሆነ የሰሊጥ ምርት ይዘን በተጋነነ ሁኔታ ዘይት እንሸምታለን፡፡ ለቲማቲም እርሻ ሰፊ አቅርቦት ያላት አገር ሆነን፣ የቲማቲም ድልህ እናስመጣለን፡፡ አገር ውስጥ መኪና እየገጣጠምን ነው እያልን፤ እጅግ በተጋነነ ሁኔታ ያገለገለ መኪናን በወድ ዋጋ እንገዛለን፡፡ ለምሳሌ ኮሮላ መኪና እስከ 700ሺህ ብር መሸጥ ተጀምሯል፡፡ ሚሊዮን መግባቱ አይጠረጠርም፡፡ ብር ከጆንያ ግባ በለው እንደሚሆን የምንመለከተው ጉዳይ ይሆናል፡፡
አሁንም በተጨማሪ አስመጭዎች ላይ የተጣለው ዋነኛ ጋሬጣ አለ፡፡ ለምሳሌ 10 መኪና የሚጭን አስመጭ፣ ለአንዱ ዋጋ አራት ሺሕ አምስት መቶ ዶላር ታስቦ፣ ለአስሩ 45ሺህ ዶላር ከመንግሥት ተሰጠው እንበል (ላም አለኝ በሰማይ!)፡፡ ይሕ 45ሺህ ዶላር በ “ቲቲ” መልኩ ሊላክ ስለማይችል በሲኤዲ ካሽ ኢን አድቫንስ ይላካል፡፡ ካሽ ኢን አድቫንስ በአጭሩ  ከውጭ አገር ተገዝቶ የገባው እቃ፣ ከተላከበት አገር ኤክስፖርት ሆኖ፣ አገር ውስጥ መግባቱ ሲረጋገጥ የሚከፈል ገንዘብ ነው፡፡ ይሕ አስመጭ 45ሺ ዶላሩን በወቅቱ ምንዛሬ ከባንክ በአንድ ነጥብ ሁለት ሚልዮን ብር ገደማ ይገዛዋል፡፡ ሆኖም ይህ ገንዘብ ወዲያውኑ ተልኮ ለመኪና ሻጩ ድርጅት ስለማይገባ (45ሺ ዶላሩን የሚያገኘው መኪኖች ተጭነው አገር ውስጥ እንደገቡ ነው) መኪና ሻጩ መኪናውን አይሰጠውም! ይህም ቢያንስ አንድ እና ሁለት ወር ይደርሳል፡፡ ይሕ አስመጭ፣ ለመኪናው ሻጭ የሚከፈልበካሽ 45ሺሕ ዶላር ያስፈልገዋል፡፡ ምንም እንኳ የተላከው ገንዘብ ለሻጭ ዘግይቶ ቢደርሰው፤ ሻጭ ያለ ካሽ መኪኖችን ሊሰጠው አይችልም፡፡ ይህ አሰራር 20 እና 30 መኪና ለሚጭኑ፣ ነጋዴዎች በእጥፍ ተቀማጭ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው፡፡ ማንኛውም ነጋዴ ያለችውን ብር አሟጦ ነው ለግዥ የሚያውለው፡፡ ገንዘቡ ለሽያጭ የተገዙ መኪኖች ላይ የተቀመጠ ነው፡፡ ሌላ ተጨማሪ ተቀማጭ እጥፍ ገንዘብ ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ ተቀማጭ ገንዘብ የሌለው አስመጭ፣ ከገበያ ውጭ መሆኑ አይቀርም! “ጥቂት ሐብታሞች እንዲጠቀሙ ብዙ ድሃዎች መወገድ አለባቸው” የሚለው መርህ የሚተገበር ይመስላል!
መንግሥት ይሕንን ሕግ የደነገገበት (እላይ ያልጠቀስነው) አንድ ምክንያት አለ፡፡ እርሱም የሕገ-ወጥ ሐዋላ ገንዝብ ዝውውርን አስቆማለሁ በሚል ነው፡፡ ይህንን በደንብ ስንመለከ 45ሺ ዶላር ፈቃድ ያገኘ አስመጭ፤ ገንዘቡ ቀጥታ ለሻጭ ድርጅት ባንዴ ስለማይተላለፍ፤ አቅም ያለው አስመጭ ይሕንን 45ሺ ዶላር ገዝቶ፣ ለመኪና ሻጭ ከፍሎ ያስጭናል፡፡ መኪኖቹ አገር ውስጥ እንደገቡም ገንዘቡ መግባቱ ሲረጋገጥ፣ ይሕንን ዶላር ያገኘዋል፡፡ ሆኖም ሌላ ዶላር ፈላጊ አስመጭ ስለማይጠፋ ዶላሩን በውድ መሸጡ አይቀርም፡፡ ትላልቆቹ ሐብታሞች ሌላ የገንዘብ ማግኛ በር ተከፈለታቸው፡፡ “ላለው ይጨመርለታል” እንዲል ቃሉ!
ይሄ አሰራር በገበያው ሁኔታ ከፍተኛ ተጽእኖ ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ቢያንስ አብዛኛው አስመጭ ከገበያ ውጭ መሆኑ ቀዳሚው ሲሆን ሌላው ቀርቶ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ሻጭ ነጋዴዎችንም (አፍጋኒስታዊያንን፣ ሕንዳዊያንን፣ ፓኪስታኒያዊያንን ቻይናዊያንን) ሳይቀር የመንካት ረዥም እጅ ይኖረዋል፡፡ በዚህ መልኩ የተገዛም እቃ የዋጋው መጠን መጨመሩ አይቀሬ ነው፡፡
ሆኖም በሕግ የመስራትን የመሰለ ስልጣኔ የለም፡፡ ሐበሻ ለችግሮቹ መውጪያ ቀዳዳ እንደማያጣ የታወቀ ነው፡፡ በችግሮች መውጫ ጠባብ መንገድ፣ ሰፊ ሕዝብ ማለፉ ግን አይቀርም፡፡ ሰፊ ሕዝብ በጠባብ መንገድ ሂድ ስትለው ይጨናነቃል፡፡ ፍትጊያው ያይላል፡፡ የኑሮው ሁኔታ ከትግል አልፎ በሕይወት የመኖርና ያለመኖር ይሆናል፡፡ ሌላ የመከራ ዘመን…እንጠብቅ? ወይንስ በምጣኔ ሐብት የዳበረች፤ የግብይት ስርዓቱ የተሻሻለባት፤ አስመጭዎች ላኪዎች የሚሆኑባት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የማያሳስባት፣ የግለሰቦች የኑሮ ሁኔታ የሚሻሻልባት፤ ዜጎች በአገራቸው ምርት የሚኮሩባት አገር ትኖረን ይሆን…?
ከሆነ የኋለኛውን የሚጠላ ኢትዮጵያዊ ፈጽሞ የለም.. ከሆነው ይልቅ የማይሆነው ሲያሸንፍ አይተናልና!

Read 4947 times