Saturday, 23 December 2017 10:48

ትራምፕ በኢየሩሳሌም ጉዳይ ከጎኔ ላልቆሙ አገራት፣ የቢሊዮኖች ዶ. እርዳታ እቀንሳለሁ አሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የትራምፕን ውሳኔ፡
128 አገራት ተቃውመውታል፤
9 አገራት ደግፈውታል፤
35 አገራት “ከነገሩ ጦም እደሩ” ብለዋል
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ለመሆኗ የሰጡትን እውቅና ለመሰረዝ የተባበሩት መንግታት ድርጅት በጠራው የድምጽ መስጫ ጉባኤ ላይ ውሳኔያቸውን በመቃወም ድምጻቸውን ለሰጡ አገራት በእርዳታ መልክ ሊሰጡት የነበረውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንደሚያስቀሩ ዝተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት ከትናንት በስቲያ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም በመግለጽ ድምጽ ሰጥተል፡፡  128 አገራት ውሳኔውን በመቃወም፣9 አገራት በመደገፍ ድምጽ የሰጡ ሲሆን 35 አገራት ደግሞ ድምጸ ተዓቅቦ አድርገዋል።
ትራምፕ በቅርቡ ለኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲናነት የሰጡት እውቅና በበርካታ የአለም አገራት በጋራና በተናጠል ሲነቀፍ መሰንበቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጠራው ስብሰባ የአገራት ድምጽ ድምር ውጤትም የትራምፕን ውሳኔ እውቅና በመንፈግ፣ “የኢየሩሳሌም ጉዳይ በፍልስጤምና በእስራኤል መካከል በሚደረግ ሰላማዊ ድርድር ይቋጭ” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡
አሜሪካ፣ እስራኤል፣ ጓቲማላና ቶጎ የትራምፕ ውሳኔ እንዳይሻር፣ ድምጻቸውን ከሰጡ ዘጠኝ አገራት መካከል መሆናቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ካናዳ፣ ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክና ሮማንያ ደግሞ ድምጽ ተዓቅቦ ካደረጉት 35 የአለማችን አገራት መካከል እንደሚገኙበት ጠቁሟል፡፡
የትራምፕ ውሳኔ መሻሩን በመደገፍ ድምጽ በመስጠት ረገድ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት በብዛት ቀዳሚነቱን የያዙ ሲሆን ጀርመን፣ ፈረንሳይና እንግሊዝን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገራትም ይህንን ቡድን መቀላቀላቸውን ዘገባው አስረድቷል። ኢትዮጵያም ከእነዚህኞቹ ተርታ ተሰልፋለች፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ አሜሪካ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጽመዋል፤ በሙስና ተዘፍቀዋል በሚል 52 በሚሆኑ የደቡብ ሱዳን፣ ጋምቢያና ማይንማር ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ባለሃብቶችና ተቋማት ላይ ከትናንት በስቲያ ማዕቀብ መጣሏን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ማዕቀቡ ከተጣለባቸው መካከልም የሮሂንጋ ሙስሊሞች ለከፋ እልቂት ሲዳረጉ ችላ ብለዋል የተባሉት የማይንማሩ የጦር ሃይል አዛዥ፣ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር አማካሪና የቀድሞው የጋምቢያ መሪ ያያ ጃሜህ እንደሚገኙበት ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2280 times