Sunday, 24 December 2017 00:00

በ3 ወራት ውስጥ ግማሹ የደ/ ሱዳን ህዝብ በረሃብ ሊጠቃ ይችላል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በየመን የኮሌራ ተጠቂዎች ቁጥር 1 ሚ. ደርሷል ተባለ

    በደቡብ ሱዳን ላለፉት አራት አመታት ያህል የዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭት አፋጣኝ መፍትሄ ሳይበጅለት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ከ5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ወይም ከመላው የአገሪቱ ህዝብ ግማሽ ያህሉ የከፋ የምግብ እጥረት ተጠቂ ሊሆን ይችላል ሲል ተመድ አስጠነቀቀ፡፡
በአገሪቱ 1.2 ሚሊዮን ያህል ደቡብ ሱዳናውያን የረሃብ ተጠቂዎች መሆናቸውን የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ በተለይም አዮድ በተባለቺው የአገሪቱ አውራጃ ችግሩ የከፋ መሆኑንና 8 ሺህ ያህል ዜጎች፣ የከፋ ረሃብ ሰለባ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በየመን የተከሰተው አስከፊ የኮሌራ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ እንደሚገኝና በበሽታው የተጠቁ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥርም 1 ሚሊዮን ያህል መድረሱን አለማቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ ለአመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭት ግማሽ ያህሉን የጤና ተቋማት ማውደሙን ያስታወሰው ዘገባው፤ በስራ ላይ የሚገኙ ተቋማትም ቢሆኑ የባለሙያና የመድሃኒት አቅርቦት ችግር ያለባቸው ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ወረርሽኙን ለመግታትም ሆነ ለታመሙት ተገቢ ህክምና ለመስጠት ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ በሽታው እጅግ እየተስፋፋና ብዙ ዜጎችን ተጠቂ እያደረገ መቀጠሉን አመልክቷል፡፡
ከውጭ አገራትና ከለጋሾች የሚላኩ ወረርሽኙን ለመግታትና ታማሚዎችን ለመታደግ የሚያስችሉ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች፣በእርስ በርስ ግጭቱ ሳቢያ መንገዶች በመዘጋጋታቸውና በወቅቱ ሊደርሱ ባለመቻላቸው ችግሩን የበለጠ እንዳከፋውም ተነግሯል፡፡
ባለፉት ሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ2 ሺህ 226 በላይ የመናውያን በኮሌራ ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በሰኔ ወር ላይ ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት ከአገሪተ 23 ግዛቶች በ22ቱ፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን ማጥቃቱን አክሎ ገልጧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ፣ ባለፈው ሳምንት ብቻ 7 ሺህ 600 ያህል የመናውያን በኮሌራ ወረርሽኝ ተጠቂ ሆነዋል ተብሎ እንደሚገመት ማክሰኞ ዕለት ይፋ ባደረገው መረጃ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ህዝብ 80 በመቶ ያህሉ የምግብ፣ የንጹህ ውሃና የህክምና አገልግሎት እንደማያገኙና መፍትሄ ያልተገኘለት የኮሌራ ወረርሽኝም የመናውያኑ ን ለተጨማሪ የከፋ ስቃይ እየዳረገ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
በየመን ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ከ2015 አንስቶ 8 ሺህ 670 ያህል የአገሪቱ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉንም ዘገባው አስታውሷል፡፡


Read 1713 times