Saturday, 23 December 2017 15:33

አ ዲ ስ አበባ ከየት (በየት) ወደየት1

Written by  ሺመልስ ቦንሣ (ዶ/ር) ሱኒ ስቶኒ ብሩክ ዩኒቨርሲቲ (ኒውዮርክ)]
Rate this item
(9 votes)

ጥቂት ስለታሪክ2

ሰዎች ታሪክን ለምንና እንዴትስ ያስታዉሳሉ? ለምንስ፣ እንዴትስ ያጠናሉ?
ብዙውን ጊዜ ወደታሪክ የምንመለሰው፣ ታሪክን እየመረጥን የምናስታወሰዉና
የምንረሳው፣ አንዱን ዘመን ወስደን ሌላውን የምንተወው፣ አሁናችንን እና
የወደፊታችንን በምንፈልገው መንገድ መቅረጽ ስለምንፈልግ ነው። ብዙዉን
ጊዜ አሸናፊዎች ታሪክን ስለሚጽፉ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚጨፈለቁ እውነቶች፣
የሚጨቆኑ ታሪኮች ፣ ገንግነው የሚወጡ ትርክቶች (narratives) ይኖራሉ።
ታሪክን የመመርመር፣ የመዘከር ስራ፣ ትርክቶች ብዙ እንደሆኑ፣ እንደሚደራረቡ ፣
እርስ በርስም እንደሚታገሉ፣ አንዱ ትርክት ሌላውን እንደሚደብቅ ሊያሳይ
ይገባል። ይህንን የታሪክ ንብርብርነት (multiplicity) የተቀበለ ፣ ለትርክቶቹም ቦታ
የሰጠ፣ የተነተነ የታሪክ ጥናት ፣ ድሎችን ብቻ ሳይሆን የታሪክ በደሎችንም፣
አውቆ ተጸጽቶ የተሻለ አሁንን እና ወደፊትን ለመስራት ይረዳል። በተቃራኒውም፣
አንዱን ትርክት ነቅሶ አውጥቶ አግንኖ ሌሎችን ክዶ ወይም ሸፍኖ የሚመጣ
የታሪክ ትንተና ጭቆናን፣ ማግለልን፣ የበላይነትን ለማስቀጠል መሳሪያ ሆኖ
ያገለግላል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በደሎች አልነበሩም ፣ ግፎች አልተሰሩም ብሎ
መከራከር አይቻልም። ስለኢትዮጵያዊያን መከራዎች፣ ስልጣንና ሀብት
በነበራቸው {አሁንም ባላቸው} ሰዎች ፣ ፍትሃዊና የሁሉም ሆነው ባልተሰሩ
ስርዓቶች የተፈጸሙና የሚፈጸሙ ጭቆናዎች በጽሁፍ ብቻ ሳይሆን፣ በዕለት
ተዕለት ህይወቶቻችን፣ ትዉስታዎቻችን ያሉ፣ የምናውቃቸው የምንኖራቸው
እውነታዎች ነበሩም፣ አሁንም ናቸው። አይካድም።

የ ሚ ሻ ለ ው ታሪካችንን፣ በታሪካችንም ውስጥ የሰራናቸውን ፣ ያለፍንባቸውን
መልካም ጎናችንን ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍሩ ጠባሳዎቻችንን አውቀን ከነሱም
ተምረን የተሻለችና ለሁሉም እኩል የምትሆን አገር ለመፍጠር መልፋት ነው።
ወደታሪክ የምንመለሰው በደሎችን፣ ጭቆናዎችን ላለመድገም፣ መልካም
በሆነው የታሪካችን ክፍል ላይ ተመስርተን የተሻለ፣ የሁሉም የሆነች አገር፣ የጋራ
የሆነ አሁንና ወደፊት ለመስራት ነዉና በዚህ ላይ ብንተጋስ?

እንጦጦ ፥ አዲስ አበባ 3

የዛሬ አንድ መቶ ሠላሳ አንድ አመት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1878
ንጉሰነገስት ምንሊክ አርሲን ለማስገበር ሰራዊታቸውን ይዘው በዘመቱበት ወቅት
ባልተቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ደግሞ እንጦጦ የነበረውን የመንግስት መቀመጫ
ወደ አሁኗ አዲስ አበባ ያዛውራሉ። ለጤና ተመራጭ የሆነው ፍልውሃ ፊንፊን
ይልበት የነበረው ቦታ ለከተማው መቀየር አንዱ ግብዐት ቢሆንም የአድዋ ድል፣
የመንግስቱ መረጋጋት፣ የእንጦጦ ቀዝቃዛነትና ባካባቢው የነበረው የማገዶ
እንጨት እጥረት የአገሪቷን ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ ለመቀየር ተጨማሪ
ምክንያቶች ሆነው አገልግለዋል። ንግስቲቷ የአገሪቷን መናገሻ አዲስ አበባ ብለው
ሲሰይሟት ሌላ ማለትም ስድስተኛ፡ እሱም ታሪክ የሚባል ምክንያት እንድንፈልግ
እንድንመረምርም ያደርገናል።

በስያሜ ውስጥ ምን አለ? አዲስና አበባ 4

አዲስ አበባ የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፣ አዲስ እና አበባ። የቦታውን
ልምላሜና ውበት ከሚወክለው አበባ ከሚለው ስያሜ ይልቅ እንደገና መጀመርን፣
መታደስን፣ መነሳትን የሚያሳየው አዲስ የሚለው ቃል የተለቀ ትርጉም የተሸከመ
ስም ይመስላል። ባንድ በኩል ስያሜው የውጭ ወራሪ ጠላትን በማሸነፍ
ከ መ ጣ ው መረጋጋትና እርግጠኝነት በተጨማሪ ስለወደፊቱ የነበረውን ብሩህ
ተስፋን፣ ወደፊት ማደግን መመንደግን፣ በአለም ማህበረሰብ ውስጥ ተገቢውን
ቦታ አግኝቶ መከበርን ሲያመለክት በሌላ በኩል ደግሞ ወደሁዋላ ተመልሶ
ማስታወስን፣ የጠፋን መመለስን ፣ የፈረሰ መገንባትን፣ እንደገና መታደስን ያሳያል።
እዚህ ላይ እንደገና መታደስ ሲባል ምን አይነት መታደስ፣ የማንስ መታደስ፣
መታደሱ የሚያመጣው ጥቅም ብቻ ሳይሆን መከራስ {ለምሳሌ የሌሎች ታሪኮች፣
ማህበረሰቦች፣ መገለል ወይም መጨፍለቅ} ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። የአዲስ
አበባ ታሪክ ሲነሳ የጠፋውን መመለስ ፣ የፈረሰውን መገንባት ከሚለው ትርክት
ጎን የመንቀል፣ የማፈናቀል ታሪክም ፣ ትርክትም እንዳለ መገንዘብ ይኖርብናል።
ትልቁ ጥያቄ ይህንን የከተማውን፣ ያካባቢውን፣ ከፍ ሲልም ያገሪቷን ታሪክ
እንዴት እንጻፈው ፣ እንዴትስ እንተርከው የሚለው ነው። የትኛውስ መንገድ
ወደፍትህ፣ እውነተኛ እኩልነት፣ ወደነጻነት ይወስደናል ነው ጥያቄው፤
  

       ልክ እንደተለያዩ፣ እርስበርስ እንደሚቃረኑ፣ የወራሪና የተወራሪ፣ ያፈናቃይና
       የተፈናቃይ ታሪኮች (compartmentalized histories) አድርገን ወይንስ          
       እንደሚቃረኑ ፣ እንደሚጋጩ ነገር ግን እንደተጋመዱ ፣ እንደተነባበሩ፣          
        አንዱ ባንዱ ውስጥ እንደተጠላለፉ {ለምሳሌም በማፈናቀል ውስጥ          
       መፈናቀል ፣ በመጨቆን ውስጥ መጨቆን እንዳሉ እንደሚያሳዩ} ታሪኮችና
       ትርክቶች?     

        በደልን፣ ግፍን የረሳ ትርክት ወይንስ እኛነታችን                             
       {ከተማችን፣አገራችን፣ ኢትዮጵያዊነታችን} የሁሉም ታሪኮቻችን               
       {የከፍታችን፣ የውድቀታችን፣ የግፎቻችን፣ የመቻቻላችን ብቻ               
       ሳይሆን የማግለላችን} ውጤትና ወራሽ መሆኑን የተቀበለ ትንተና?

ከተማናታሪክ፡ በራራ ፥ አዲስ አበባ

የከተሜነት ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥንታዊነቱን ለመረዳት በትንሹም ቢሆን
የአገሪቷን ታሪክ ማንበብ ከተቻለም የከተሜነት ስልጣኔዋን የሚመሰክሩ
የከተሞች ፍርስራሾችን {ለምሳሌም የሃን፣ አዱሊስን፣ ቆሃይቶን }፣ ወይንም
እስካሁን ያልጠፉትን ፣ ህይወት ያለባቸውን እነአክሱምን፣ ሃረርን፣ ጎንደርን
መመልከት ይበቃል። በስነህንጻ፣ በስነጽሁፍ፣ በስነመንግስትና በኪነጥበብ
አክሱም የደረሰችበትን የስልጣኔ ከፍታ የተረዳው ማኒ የተባለው ፐርሻዊ ጸሓፊ
አክሱማዊት ኢትዮጵያን ከክርስቶስ ልደት በሁዋላ በአራተኛው ክፍለዘመን
ከነበሩት አራት ታላላቅ ስልጣኔዎች አንዷ ናት ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ሃረርና
ጎንደርም የከተማነት ዝናቸው በብዙ ቦታ የናኘ መሆኑ ሰፊው ታሪካቸው ቆመው
የሚታዩትም የስነሕንጻ ቅሪቶችም ማረጋገጫዎች ናቸው። ይህንን ስንመለከት
የአሁኗ አዲስ አበባ የዚህ ጥንታዊና ጥልቅ የከተማ ስልጣኔ ወራሽ እንጂ ጀማሪ
እንዳይደለች እንረዳለን ማለት ነው። እስቲ ስለአዲስ አበባ ትንሽም ቢሆን ታሪክን
ወደሁዋላ እንበል።

የኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳናትም፣ ሆነ የውጭ ሀገር ጸሐፍት የሚያረጋግጡት አሁን
ሸዋ ተብሎ የሚጠራውና የአገሪቱ መናገሻ አዲስ አበባ የሚገኝበት አካባቢ ከዛሬ
700 አመት በፊት ማለትም የሰለሞናዊው መንግስት ከተመሰረተበት ከ13ኛው
ክፍለዘመን ጀምሮ እስከ ጎንደር ዘመነመንግስት ድረስ ቁልፍ የፖለቲካ፣
የወታደራዊ፣ የኢኮኖሚና፣ የባህል ማዕከል ሆኖ ያገለግል እንደነበረ ነው። በጊዜው
የነበረው ማዕከላዊው መንግስት ከቦታ ቦታ ተዘዋዋሪ ቢሆንም በተለያዩ የአገሪቱ
አካባቢዎች ከተሞችን የመሰረተ ሲሆን ትልቁና በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው ግን
በራራ የተሰኘው ከተማ ነበር። ወረብ በራራ የምትገኝበት ግዛት ሲሆን
በመሐከለኛው ዘመን ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት ፥የነገስታቱ ቤተመንግስትና
ሌሎች አነስተኛ ከተሞች የነበሩበት ፥ በ16ኛው ክፍለዘመን ደግሞ ብዙ የውጭ

ሀ ገ ሮ ች ን ለመጎበኘት የቻሉት አባ ዳንኤል የተባሉ ኢትዮጵያዊ መነኩሴም
ከኢየሩሳሌም ጋር ሁሉ ያመሳሰሉት ሀብታም አካባቢ ነበር። ሺሃብ አድ ዲን
{በቅጽል ስሙ አረብ ፋቂህ} የተባለው የመናዊ የፍቱህ አል ሃበሻ {የሃበሻ
መወረር} መጽሃፍ ጸሐፊ የአህመድ ኢብን ኢብራሂም አል ጋአዚን {በቅጽል ስሙ
አህመድ ‘ግራኝ’} ጦር በማጀብ ወረብንና በራራን ያየ ሲሆን ወረብን የሀበሾች
ገነት ብሎ ጽፎላታል።

የበራራ ከተማ በአሁኗ አዲስ አበባ አካባቢ በተለይም እንጦጦ ዙርያ ላይ
የተመሠረተ ሲሆን የኢትዮጵያ መዲናነት ታሪኩ የሚጀምረው በአጼ ዳዊት ዘመነ
መንግስት {1373-1406 አ. ም.} ሲሆን የሚያበቃውም በአህመድ ጦር
በሚቃጠልበት የአጼ ልብነ ድንግል {1500-1532 አ.ም.} ዘመን ነው። በ1443
አ.ም. (እኤአ በ1450) ለመጀመሪያ ጊዜ ከተማው ፍራ ማዉሮ የተባለ ቬኒሲያዊ
{ጣልያናዊ} ባዘጋጀው የዘመኑ ፈር ቀዳጅ በሆነው የአለም ካርታ ላይም ለመስፈር
በቅቷል። ካርታው መሬት ላይ ባሉ መረጃዎች ተመስርቶ የተሰራ ሲሆን እነሱም
አዉሮፓ ከነበሩ ኢትዮጵያዉያንና በተለያየ ወቅት በተለይም በአጼ ይስሀቅ
{1407-1423 አ.ም.} እና አጼ ዘርዓ ያዕቆብ {1426-1460 አ.ም.} ዘመን ኢትዮጵያን
ከጎበኙ አዉሮፓዉያን የተገኙ ነበሩ። ሰዓሊ ማዉሮም ይህንን አስመልክቶ እንዲህ
ይላል፤
      …{በካርታው ላይ የተመለከቱትን ስለአፍሪካ} ደቡባዊ ክፍሎች ማዉራቴ          
      ለአንዳንዶች አዲስ ነገር ሊሆን ስለሚችል በጥንቶችም {በባለሙያዎች}          
      ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ስለማይታወቁ ከሰይቶ ጀምሮ ወደላይ ያለውን
      ጠቅላላ ስዕል ያገኘሁት ከቦታው ተወላጆች ነው ብዬ እመልሳለሁ።              
      እነርሱም ቄሶች ሲሆኑ {በካርታው ላይ ያሉትን} ክፍለ ግዛቶች፣ ከተሞች፣          
      ወንዞችና ተራሮችን ከነስማቸው በእጃቸው ለእኔ የሳሉልኝ እነርሱ ናቸው።

ካ ርታ ው አሁን ድረስ ያሉ፣ እንዲሁም ስማቸው የማይታወቅ ቦታዎችን የጠቀሰ
ሲሆን አቀማመጣቸውንም በመረጃ አስደግፎ ለማሳየት ሞክሯል። ለምሳሌም
ከዘረዘራቸው ውስጥ የየረር፣ የዝቋላ፣ የመናገሻና የወጨጫ ተራሮች፣ የዱከምና
አዋሽ ወንዞች፣ በወጨጫ ተራራ አካባቢ የሚገኙ የቤተመንግስት ፍርስራሾች፣
ይገኙባቸዋል።

ከማዉሮ ካርታ በተጨማሪም በዘመኑ የነበሩ ኢትዮጵያዉያንና የውጭ ሰዎች
ስለበራራና አካባቢው ብዙ መረጃዎችን ትተውልን አልፈዋል። አንዳንዶቹን
ለመጥቀስ ያህል አሌሳንድሮ ዞርዚ የተባለ የቬኒስ ጣልያናዊ {15ተኛዉና
16ተኛው ክፍለዘመን} ፣ የመናዊው ሺሃብ አድ ዲን {16ተኛው ክፍለዘመን} ፣ እና
አዉሮፓ የነበሩ የኢትዮጵያ መነኮሳት፡ አባ ዞርጊ፣ አባ ሩፋኤል፣ አባ ቶማስና አባ
እንጦንዮስ {15ተኛዉና 16ተኛዉ ክፍለዘመን} ይገኙበታል።

በ1521 አ.ም. ሽምብራ ኩሬ {ቢሾፍቱና ሞጆ መሃል ያለ ቦታ} ላይ በተደረገ ጦርነት
ንጉስ ልብነ ድንግል መሸነፉና ወደሰሜን ማፈግፈጉ ወረብንና የንጉሱ መዲናን
በራራን ለጥቃት ያጋለጠ ሲሆን በ1522 አ.ም. ቦታዎቹ በአህመድ ጦር ለመያዝ ፥
ከተማዋም ለመቃጠል በቅተዋል። እንደሺሃብ አድ ዲን ትረካ ከሆነ የአህመድ
ሰራዊት በአስር ቀናት ውስጥ ከአዋሽ ወንዝ መነሻ {የአሁኗ ግንጪ} ተነስቶ
በራራ በመድረስ አጭር ቆይታ አድርጓል፣ ከበራራም ሆኖ አህመድ የተወሰኑ
ወታደሮቹን የስድስት ቀን የእግር መንገድ ወደሚፈጀው ደብረ ሊባኖስ ልኮ
እንዳቃጠለ ይዘረዝራል። የተቃጠለው የመንግስቱ መዲና የነበረው በራራ ከተማ
የሚገኝበትን የወረብ ግዛት እንዲያስተዳድር ሙጃሂድ የተባለውን ታማኙን
መሾሙንም ይጽፋል። ከዚህ ጊዜ አንስቶ እስከ 19ተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ
ስለበራራ የሚዘግብ ምንም የጽሁፍ መረጃ አልተገኘም።

በ19ተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ግን የጥንቱን በራራ ታሪክ
የሚያስታዉሱ ግኝቶች መታየት ይጀምራሉ። በ1873 አ.ም. በንጉስ ምኒልክ
የሚመራው የሸዋ ፣ ከ1881 .ም. በሁዋላም የኢትዮጵያ መንግስት መዲናውን
እንጦጦ ላይ ያደርጋል። እንደዘመኑ ትርክት ከሆነ {ድርሳነ ራጉኤል ላይ
እንደተጻፈው} የንጉስ ምንሊክ እንጦጦ ላይ መከተም ከስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ
በተጨማሪ ታሪካዊ ትርጉም ነበረዉ፣ እሱም ታሪክ የዘከረዉን የጥንቱን የአጼ
ዳዊት ከተማን እንደገና መገንባት፣ ወደአገሪቱ መዲናነትም መመለስ ነበር።
ንግርቱም ታሪካዊ መሰረት እንደነበረው የሚያመላክቱ መረጃዎች በእንጦጦ
{የጥንቱ በራራ ክፍል} የተገኙ ሲሆን ይህንንም በጊዜው ሀገሪቷን የጎበኙ የውጭ
ሀገር ሰዎች {ዲፕሎማቶች፣ ተጓዦችና ወታደራዊ ባለሙያዎች} ዘግበዉታል።
ቻርለስ ማይክል፣ ሲልቬይን ቪኘራስ፣ ሻለቃ ፓወል ኮተን፣ አልበርት ግሌይቸን፣ እና
ቸዛሬ ኔራዚኒ፣ ጥቂቶቹ ሲሆኑ ሁሉም በቦታው የነበረዉን ጥንታዊ የመከላከያ
ቅጽሩን ተመልክተው ስለጥንካሬዉና ግዙፍነቱ አድናቆታቸውን በጽሁፍ
አስፍረዋል። እንጦጦ ላይ የፔንታገን ቅርጽ {አምስት ጫፎች ያሉት} ያለው
በዙርያውም 12 መመልከቻ ማማዎች የያዘ እንደመከላከያ የሚያገለግል
ቤተመንግስትና ግንብ የተገኘ ሲሆን ርዝመቱም 520 ሜትር ከፍታውም እስከ 5
ሜትር እንደሚደርስ ታውቋል። የስነህንጻና አርኪዎሎጂ ባለሙያዎች {ለምሳሌም
ዴቪድ ፊሊፕሰን፣ ማይክል ዎከርና ማርክ ቪጋኖ} እንደተነተኑት ግንቡ ከ1543
አ.ም. (እኤአ ከ1550) በፊት የነበረዉን የፖርቱጋልና ስፔን የመከላከያ ግንብ
አሰራር ዘዴ የተከተል ሲመስል ቢያንስ የ400 አመት ወይም በላይ ዕድሜ ያለዉና
በ16ተኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ አጋማሽ ምናልባትም በአጼ ልብነ ድንግል
የተገነባ እንደሚሆን ነው።

ኦሮሞ ና አዲስ አበባ

ይህ የበራራ ታሪክ ግን የኦሮሞ አርሶአደር በቦታው የነበረዉን ፣ አሁንም ድረስ
ያለውን ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት፣ በታሪክም ሆነ በከተማ መስፋፋት
እንዲሁም በልማት ስም የደረሰበትንና የሚሸከመውን በደል ለምሳሌም
መፈናቀል የማይጨምር ከሆነ ሙሉ አይሆንም። የእየመረጡ መርሳትና ማስታወስ
ትርክት ሰለባም ይሆናል። ላሁናችንም ሆነ ለወደፊታችን አይጠቅምም።
የታሪክንም ሆነ የትርክትን አግላይነት ወይም ሰዋሪነት {historical and
historiographical erasures} ለማስቀረት የታሪክ አረዳዳችንን እንደገና በጥልቀት
መመርመር፣ መቀየር ይኖርብናል ማለት ነው። ለምሳሌ በቋሚነትና ወጥነት (fixity,
linearity, singularity) ምትክ ለውጥን፣ ጠመዝማዛነትን፣ንብርብርነትን (mobility,
non-linearity, multiplicity) መሰረት ያደረገ የታሪክ አጠናን፣ አተናተን ኢትዮጵያን
በኢትዮጵያም ውስጥ የኦሮሞን (የሌሎች ኢትዮጵያዉያንንም) ቦታ በተሻለ
መንገድ ለመረዳት ያግዝናል። ታሪክም ሆነ ማንነት በለውጥ ሂደት ውስጥ
ይኖራሉ፣ ይለዋወጣሉም። ድንበሮችም ዝግና የረጉ (closed) ሳይሆኑ በየጊዜው
የሚቀያየሩ (fluid) ናቸው። የኢትዮጵያን ታሪክ በወረራ፣ በዘመቻ፣ በአጥቂና
በተጠቂ ፥ በነባርነትና በመጤነት መነጽር ብቻ መመልከት፣ እና መተንተን
ውስብስብ የነበረችዉን፣ የሆነችውን ኢትዮጵያ በጥልቀት እንዳንረዳ ያደርጋል።
ከዛ ይልቅ በዘመናት ውስጥ በተለያየ አቅጣጫ የተደረገ፣ የሚደረግ የህዝብ
እንቅስቃሴን፣ በንግድ፣ በጋብቻ፣ በሰላም ፣ በጦርነት የመጣ መቀላቀልን፣
መስተጋብርን፣ ከዚህ ድብልቅልቅ ውስጥ የወጣ ፣ የሚወጣ ብዙ መልክ ያለው
ማንነትን፣ ብዝሃነትን ማሳየት ፣ መተንተን የሚችል የታሪክ እይታ ያስፈልገናል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያን ታሪክ መሰረታዊ በሆነ መንገድ ከቀየሩት ሃይሎች
ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚነሳው የኦሮሞ ህዝብ ነው። በመሐከለኛውም
{በተለይ ከ16ተኛው5 ክፍለዘመን በሗላ} ሆነ በዘመናዊቷ {ከ19ተኛው
ክፍለዘመን ጀምሮ} ኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮሞ ተወላጆች ያልገቡበት፣ የህዝቡንም
ሆነ የአገሪቷን ታሪክና ህይወት ያልለወጠ ወሳኝ ጉዳይ አልነበረም። ኦሮሞዎች
በአገሪቱ አስተዳደርና ጦር ውስጥ በብዛት እንደተሳተፉ፣ ቁልፍ የሆኑ
የወታደራዊና የፖለቲካ ስልጣን እንደያዙ፣ ነገስታትን እንደወለዱና እንዳነገሱ
የታሪክ ሰነዶችም ፣ ጥናቶችም ያረጋግጣሉ። እንደምሳሌም የጎንደር
ዘመነመንግስትን {ከ17ኛ - 19ኛ ክፍለዘመናት}፣ እና የዘመነመሳፍንትን {18ኛና
19ኛ ክፍለዘመናት} ጊዜን መጥቀስ ይቻላል። በዚህም የተነሳ የመጣው የባህል፣
የቋንቋ፣ የሃይማኖት መስተጋብር፣ የህዝብ መቀላቀል፣ የተፈጠረው ንብርብር
ታሪክ፣ ውስብስብ ማንነት የአገሪቷን መልክ በዘላቂነት ቀይሮታል። እንደምሳሌም
ሸዋና ወሎን መጥቀስ ይቻላል።

ይህ ሁሉ ግን የዉስብስብ ታሪካችን አንዱ ገጽታ ብቻ ነው። ሌላው ክፍል ደግሞ
የመገለል፣ የመፈናቀል፥ የመጨቆን ታሪካችን ነው። በሁለት መንገድ እንየዉ።
ባንድ በኩል ከኦሮሞ ህዝብ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ ጋፋትን በመሳሰሉ
ማህበረሰቦችና ስልጣኔዎች ላይ የመጣው የመለወጥ፥ የመዋጥ፥ የመጥፋት
ታሪክ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ ላይ (አብዛኛዉን ኢትዮጵያዊ
ጨምሮ) ለዘመናት በገዢዎቹና ስርዓቶቹ የደረሰበት የግፍ ታሪክ ነዉ።

እስቲ አዲስ አበባ በሚገኝበት የሸዋ ግዛት ላይ እናተኩር፡፡ የሸዋ ነገስታት በተለይ
ከንጉስ ሳህለስላሴ {1805-1840 አ. ም.} ጀምሮ ግዛታቸውን ለማስፋት
በሚያደርጉት የማስገበር ጦርነት፣ ግንባር ቀደም ተጠቂ የነበረው በአካባቢያቸው
፣ አዲስ አበባን ያለበትን ቦታ ጨምሮ ፣ ይኖር የነበረው የኦሮሞ ህዝብ ነበር።
ዘመኑን የዘገቡት በተለይ በአዉሮፓውያኖቹ ዊሊያም ሃሪስ {William C. Harris}፣
ዮሃን ክራፍ {Johann L. Krapf} እና ኢዝንበርግ {Isenberg} እንደ ኢትዮጵያ
አቆጣጠር በ1820ዎቹ እና 1830ዎቹ የተጻፉት ሰነዶች የቱለማ ኦሮሞ መሬትን፣

የ አ ሁ ኑ አዲስ አበባ አካባቢን ጨምሮ ፣ ለማስገበር የተደረጉት ረጅም ጦርነቶች
ብዙ ውድመት ማድረሳቸውን፣ ግድያዎች መፈጸማችውን ፣ ህዝቡም
ከባለአገርነት ወደገባርነት መለወጡን ይተርካሉ። በ19ኛው ክፍለዘመን መጨረሻ
ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሲመሰረትና ፣ ከዛ በሗላ ባሉት አመታትም የመሬት
ነጠቃው የቀጠለ ሲሆን እንደጉለሌ ኦሮሞ ያሉትም ከቦታቸው ተነቅለው
ወደአርሲና ሌሎች አካባቢዎች እንደተሰደዱ ይታወቃል። ይህም የሚያሳየን አሁን
በዘመናዊነትም ሆነ በልማት ስም በአዲስ አበባና በዙሪያዋ፣ በሌሎች የኢትዮጵያ
ከተሞችና ገጠሮች የሚካሄደው መፈናቀል አሁን ያልተጀመረ ፥ ረጅምና ብዙ
ጉዳት ያስከተለ ታሪክ ያለው መሆኑን ነው።

የአዲስ አበባ ምንነት

እንግዲህ በጥንቷ በራራና በአሁኗ አዲስ አበባ እንዲሁም በኦሮሞ ህዝብና
በከተማዋ መሐከል ታሪካዊ ግኑኝነት እንዳለ ካየን አሁን ደግሞ የሁለቱን
ከተሞች በተለይም የአዲስ አበባን መልኮች ወይንም መገለጫ ባህርያት ምን
እንደሚመስሉ እንመልከት። የኢትዮጵያ ከተሞችና መዲናዎች {ለምሳሌም
አክሱም፣ ጎንደር} ልክ እንደአገሪቷ ህብረብሄራዊ ገጽታ የነበራቸው ሲሆን
በውስጣቸው የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ፣ የተለያየ እምነትና ባህል ተከታይ የሆኑና፣
በተለያየ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያዉያን እንዲሁም የዉጭ ሀገር ተወላጆች
የሚኖሩባቸው ቦታዎች ነበሩ። ጥንታዊቷ አክሱም በሶስት ቋንቋ {ግዕዝ፣ግሪክ፣
ሳባ} የምትጽፍ፣ ከሶስት ቋንቋ በላይ የምትናገር፣ ከኢትዮጵያዉያን በተጨማሪ
ግብጻዉያን፣ የመረዌ {ሱዳን} ሰዎች፣ የመናዉያን፣ የምስራቅ ሜድትራንያን
{ፊንቄያዉያን፣ ግሪኮች፣ የጥንት ሶሪያዉያን} ተወላጆች እንዲሁም ህንዶችና
ቻይናዉያን የኖሩባት ወይም ደግሞ የሰሩባት ታላቅ ከተማ ነበረች። ጎንደርም
ብትሆን የክርስትና፣ የእስልምናና የአይሁድ እምነት ተከታዮች ተጎራብተው
{ተለይተው መስፈራቸውና እኩል አለመታየታቸውም ሳይረሳ} ፣ በስራና በህይወት
ተ ስ ተ ጋ ብ ረ ው መልኳንና ታሪኳን ዥንጉርጉር አድርገው የቀረጿት ከተማ
እንደነበረች ታሪኳ ይመሰክራል። ሀረርም ከአራቱ የእስልምና ቅዱሳን ቦታዎች
አንዷ ስትሆን በብዝሀነቷ እና በእምነት ማዕከልነቷ የምትታወቅ፣ በዚህም እንደ
ታዋቂዉ የፈረንሳይ ገጣሚ አርተር ራምቦ እና እንግሊዛዊዉ ሪቻርድ በርተን ያሉ
የውጭ ሰዎችን ለመማረክ የቻለች ምስራቃዊ እንቁ ነበረች፣ ነችም።
በራራም ብትሆን የተለያዩ ማህበረሰቦች መኖርያ እንደነበረች መረጃዎች ያሳያሉ።
በከተማዉም ሆነ በዙሪያው ባሉ እንደ ወረብ ባሉ ግዛቶች ይኖር የነበረው ህዝብ
በብዛት ተቀራራቢ ቋንቋዋች ከሚናገሩት የአምሃራ፣ የጉራጌ እና የጋፋት
ማህበረሰቦች የተዉጣጣ እና የክርስትና እምነት ተከታይ የነበረ ሲሆን
በተጨማሪም የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎችና እምነት ተከታዮች ይገኙበት
እንደነበረም ይታሰባል። ለዚህም ምክንያቱ ከተማው ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች
በተለይም ከምስራቅ ኢትዮጵያ በዛም በኩል አድርጎ ከአረቡና ህንዱ ስልጣኔ ጋር
በንግድ እና በባህል የተገናኘ ስለነበረ ነው። በበራራ የታሪክና የስነህንጻ አሻራ ላይ
የተገነቡት ሁለቱ ወራሽ ከተሞችም {እንጦጦና አዲስ አበባ} የነዋሪዎቻቸው
ያሰፋፈር ታሪክ ከዚህ በተለየ መንገድ የተቃኘ አልነበረም፣ ይልቁንም የበፊቱን
ታሪክ መሰረት አድርጎ ፣ ብዙነትን አቅፎ፣ ያደገ ማንነት ነው ያላቸው፣ በፊትም
አሁንም።

አዲስ አበባ ስትመሰረት የነበራትን ህብረብሄራዊነት፥ ጥልፍልፍና ድርብርብ ታሪክ
በ19ኛውና በ20ኛ ክፍለዘመን መባቻ ላይ በሃገርኛና በጎብኝዎች የተጻፉ ስራዎች
ዘግበውታል። ነገስታቱ በተለይም አጼ ሀይለ ስላሴ ከተማዋ ዘመናዊ ብቻ ሳይሆን
ብሄራዊ ሆና እንድትፈጠር ወይንም እንድታድግ ያቀዱና የሰሩ ስለነበር አዲስ
አበባ ከተማም፣ የሀገርም ምልክት ሆና በእሷ ውስጥ ኢትዮጵያን በኢትዮጵያ
ውስጥም እሷን እንድትታይ (city as nation)፣ እኛም እንድናይ ሆና ነበር
የተቀረጸችው። በእርግጥ በአገሪቱ መሪዎች እና በከተማ ቀራጮች አእምሮ

ው ስጥ የታለመችው አዲስ አበባ እንደታሰበችው ሁሉ መሬት ላይ ባትሰራም
{ለምሳሌ ሁሉንም እኩል ባታይ፣ የመሰረታዊ አገልግሎቶች እጥረት፣ የስራ አጥነት፣
ድህነት፣ የሀብት ልዩነት ቢስፋፋባትም} ከተማዋ ኢትዮጵያን ከነዥንጉርጉር
ውበቷና ከነውስብስብ ችግሯ መስላና፣ ተመስላ፣ እንደአፍሪካም የአፍሪካም ሆና
እስካሁን አለች። አዲስ አበባ ከብዙ የአፍሪካዉያን ከተሞች በተለየ ድሃና
ሀብታም ተሰባጥረው የሚኖሩባት፣ ነዋሪዎቿን ከነብዝሃነታቸው አቅፋ የኖረች፣
ያኖረች፣ የምታኖር የኢትዮጵያ የልብ ትርታ፣ ነርቭ ማዕከል የሆነች ከተማችን፣
ማረፊያችን፣ ችግሯም ችግራችን፣ ፍቅራችን እንደገናም ተስፋችን ሆናለች።

የአዲስ አበባ ማንነት

ይህችን ስብጥር የሆነች ከተማ፣ ንብርብር ታሪክ የተሸከመች ምድር፣ ከመሪዎቿ
በላይ የብዙሃን ነዋሪዎቿ ድምር ውጤት፣ የእጅ ስራ ነጸብራቅ ሆና የኖረች
ግማደ-ኢትዮጵያ የማን ናት? በብዝሃነት ጥልፍልፍ ተጸንሳ ለተወለደች፣ አድጋም
ለጎለመሰች አዲስ አበባ ምንነቷና የማንነቷ ምስጢር በአንድነት ተጋምዶ፣
በልዩነት ውበት አሸብርቆ ደምቆ የተፈጠረ የሃገርነት ቋጠሮ ነው። አዲስ አበባ
ልክ እንደኢትዮጵያ የነዋሪዎቿ ስብስብ ውጤት ብቻ ሳትሆን፣ ከድምርነትም በላይ
እጅግ የጠበቀ፣ የጠለቀ ጥልፍ ስብጥር ናት። ለመሆኑ እዲስ አበባን ለመፍጠር
ያልተጋ ኢትዮጵያዊ እጅ የት አለ? ኦሮሞው ከአማራው፣ ጉራጌ ከትግሬው፣ ዶርዜ
ከሀረሪው፣ ሶማሌ ከወላይታው፣ ምስራቁ ከደቡብ፣ ሰሜኑ ከምዕራብ፣ ወንዱ ሴቱ፣
ልጅ አዋቂዉ፣ አማኙ የማያምነው፣ ነጋዴው ከምሁሩ፣ ሀገሬዉ ከሌላው ተዋዶ፣
ተዋልዶ፣ ተናግዶ፣ ተቀናጅቶ የፈጠራት፣ ከተማ ከሚባል ነገር በላይ የሆነች
‘ምስጢር’ አይደለችምን?

ሌላ ዋ አዲስ አበባ

አዲስ አበባ የብዝሀነት ሀገር፣ የኢትዮጵያነት መገለጫ ከተማ ናት ማለት ግን
ሁሉም እኩል ነበር፣ እኩል ታይቶም ነበር፣ ብዙው አዲስ አበቤ አልተገለለም ነበር
ማለት ግን አይደለም። እስቲ እንደዚህ ብለን እንጠይቅ። እውነት አዲስ አበባ
ከቦታነት በላይ የዘለቀች ሁሉም እምነቷን ካመኑ፣ ሕይወቷን ኖረው ትርጉሟን
ካወቁ አባል የምታደርግ፣ እጆቿን ዘርግታ የምትቀበል፣ የራሷ የምታደርግ ትልቅ
ሃሳብ ሆናለች? ከተማዋ አግላይ ከሆነ የኔነት፣ የኔ ናት ከሚል እሳቤ ወጥታ፣ ርቃ
አልፋ ሄዳ፣ የኛነት፣ የእኛ ናት ወደሚል ሰብሳቢ ሃሳብነት ያደገች ከተማ ለመሆን
በቅታለች? አዲስ አበባን ዘመናዊና ብሄራዊ አድርጎ ለመፍጠር ቢታለምም ምን
ያህል ብሄራዊ፣ ምን ያህል ዘመናዊ፣ ምን ያህልስ ፍትሀዊ ከተማ ነበረች፣ አሁንስ
ነች ብለን እንመርምር።

በምሳሌ እናስረዳ። በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን በ1960ዎቹ አመታት በቁጥር 1768
የሆኑ ግለሰቦች 58% የሚሆነውን የከተማውን ቦታ ተቆጣጥረው ነበር። 24,000
የሚሆኑት የከተማው ነዋሪዎች 7.4% {በግለሰብ 150 ካሬ ሜትር ማለት ነው}
የከተማውን ቦታ ሲይዙ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የከተማው ህዝብ የራሱ የሆነ
መሬትም ሆነ መኖርያ አልነበረውም። ከተማው ድሆችን፣ ባለእጆችን (ቀጨኔን
ያስታዉሷል)፥ ሴቶችን፣ ሙስሊሞችን እና ሌሎች ማህበረሰቦች እኩል ያላስተናገደ፣
በአብሮነት ውስጥ ወይም በተጨማሪ ልዩነቶችን ፣ ተቃርኖዎችን የተሸከመ
ነበር። በሰፈሮች መሐከል የነበረው የሀብት ልዩነት ፣ በከተማውና በተቀረው
የአገሪቱ ክፍል በተለይም በአቅራቢያው ካለው አርሶአደር ጋር የነበረውና
የቀጠለው የተዛባ ፣ አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን ተጎጂ ያደረገ ኢ-ፍትሃዊ
ግኑኝነት፣ አብዛኛውን ያገሪቷን መሰረታዊ አገልግሎቶችና ሀብቶች በከተማው
ያከማቸ ልማትና ዘመናዊነት የአዲስ አበባ ሌላው ታሪክ ፣ ሌላው መገለጫ ነው።

በ እርግ ጥ በንጉሳዊው ዘመን፣ ከስርዓቱም መውደቅ በሁዋላ ባሉት መንግስታት
ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተመዝግበዋል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ
በአፍሪካ ዉስጥ ተወዳዳሪ የለዉም በሚባል ፍጥነትና ስፋት ከተሞችን
የማሳደግና የማዘመን ስራ ፥ በተለይም የጋራ መኖሪያ ቤቶች የመገንባት ሂደት
እየተካሄደ ይገኛል። የስራ እድሎች ተፈጥረዋል፥ ጥቂት የማይባሉ ከድህነት
ተላቀዉ ከተጎሳቆሉ ሰፈሮች እየወጡ ወደተሻሉ አካባቢዎች ለመግባት ችለዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታም ጥቂቶችን በጠቀመ ልማትና ዘመናዊነት ስም አብዛኛዉ
ከተሜ የድህነትን ህይወት ይገፋል (እንደምሳሌም ቆሼንና ቆሼ የተሸከመዉን
ግፍና ግፉአንን መጥቀስ ይበቃል) ፥ ሌላዉም ከኖረበት ቀዬው እየተነሳ
ይፈናቀላል፣ ከከተማው ዳርቻም ይጣላል። ከኑሮውም ከማህበራዊ ህይወቱም
ይቆራረጣል። በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ዙሪያ የሚኖሩት አርሶአደሮችም
{ለምሳሌ ኦሮሞው በአዲስ አበባ፣ አማራው በባህርዳር፣ ትግሬው በመቀሌ፣
ሲዳማው በሐዋሳ እና ሌሎች ኢትዮያውያን በሌሎች ከተሞች} በአነስተኛ ካሳ
መሬታቸውን ይቀማሉ፣ ሰርቶ የመኖር መብታቸውን ይነጠቃሉ። ይህ ልዩ የሆነ ፥
ብዙ ተስፋ የተጣለበት የዝመናና የልማት ‘ዘመቻ’ ታዲያ ሁሉንም ከሚያለማ
ልማትና ዝመና ይልቅ በልማትና ዝመና ስም የሚካሄድ ጥቂቶችን የጠቀመ
የሃብት ሽግግር አልሆነምን? በድህነት ላይ የታወጀዉ ጦርነት በድሆች ላይ
ኣላነጣጠረም?

እንግዲህ ይህ የከተማዉ ዝብርቅርቅነት ፥ የተቃርኖ ታሪክና ህይወት የሚያሳየን
አዲስ አበባ መዘመን ብቻ ሳይሆን መሰይጠንንም፣ ከመሰብሰብ በተጨማሪ
ማግለልን፣ እየተከለች መንቀልንም፣ የተማረች ፥ያስተማረች ከተማም መሆኗን
ነዉ። ከተማዋ የተወሰኑት ነዋሪዎቿ ከብረው አስከብራ፣ ብዙሀኑን ግን ነጥቃ
አስነጥቃ አደህይታ የሁለት ኢትዮጵያዎች ኢትዮጵያ መቀመጫ ፣ መገለጫ ሆና
ትገኛለች ማለት ነው። እንግዲህ የአዲስ አበባንና የሌሎች ከተሞቻችንን
በዛውም የሃገራችንን ታሪክ ስንተርክ እነኝህንና ሌሎች ታሪካዊ በደሎችን፣
ዘ መ ና ዊ ነጠቃዎችን፣ መገለሎችን፣ የድህነት፣ የበላይና የበታችነት እውነቶችን
የተሸከመ ሀገርነት፣ከተሜነትና ዘመናዊነት ይዘን መሆኑን ሳንዘነጋ ነው።

አዲስ አበባና የዘመኑ ትርክት

በአሁኑ ሰዓት፣ እንደ በፊቱ ሁሉ፣ የአገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ቅራኔዎች
የሚፈጠሩባት፣ እንዲሁም የሚንጸባረቁባት ቦታ ሆናለች። ውጥረቶቹ
በመሠረታዊነት መደባዊ ሆነው በብሄር ማንነት መነጽር ይተነተናሉ፣ በዛም ላይ
ተንተርሶ ህዝብን ለትግል ማደራጃ ማነሳሻ ሆነው ያገለግላሉ። በአሁኑ ጊዜ ሁለት
ዋና ትርክቶች የከተማውንም ሆነ የአገሪቱን ትኩረት ስበው ይገኛሉ። ሁለቱም
ታሪክን በተለያየ መንገድ ይመለከታሉ የራሳቸውንም በደሎች ያጣቅሳሉ።
አንደኛው ህብረብሄራዊ ሆኖ ረጅም የታሪክ ምልከታ ይዞ አዲስ አበባን፣ ከፍ
ሲልም ኢትዮጵያን በህብረብሄራዊ መነጽር እያየ በከተማውም ሆነ በአገሪቱ ያሉ
የተንከባለሉ ብሶቶችን በመደብ መነጽር ይተነትናል። ሁለተኛው ብሄርን ማዕከል
አድርጎ በቅርቡ የታሪክ እይታ ተመስርቶ ከተማውን፣ በከተማዉና በአገሪቱ ያሉ
የተከማቹ በደሎችን በብሄር መነጽር ይሞግታል፣ አማራጮችንም ይጠቁማል።
ሁለቱም እይታዎች፣ እነሱም ላይ የቆሙ ትንተናዎች የየራሳቸው እዉነቶች
አሏቸዉ። የከተማዉን ብሎም የአገሪቷን ታሪክ እና ነባራዊ ሁኔታ በራሳቸው
መንገድ ይተርካሉ ፣ ይሞግታሉ። ነገር ግን አዲስ አበባን በሁለቱ መነጽሮች ብቻ
መመልከት የከተማዋን በዛውም የአገሪቷን ንብርብር እና ቁልፍልፍ ታሪክና
እውነት አበጥሮ ፣ አብጠርጥሮ ለመረዳት የተሻለ አማራጭም ለመጠቆም
የሚያስችል መንገድ አይሆንም። ብዥታን፣ የጎደለ እይታን፣ የተንሻፈፈ ትንተናን
ይፈጥራልና። እስቲ በምሳሌ እናስረዳ።

አ ንደ ኛ ፣ {በብሄርም ሆነ ሀገራዊ} ማንነት ላይ ብቻ ተመስርቶ የተቃኘ ፖለቲካ
ሌሎች ወሳኝ የሆኑ ሀገራዊና አለምአቀፋዊ ጉዳዮችን እንዳንመለከት፣
እንዳንመረምር ያደርገናል፣ በዚህም የተነሳ የልማትና የድህነት ጥያቄዎች፣
የመሬት ብሎም የሀገር ባለቤትነት ጉዳዮች፣ የዜግነት፣ የፍትህና እኩልነት
ህሳቤዎች፣ በልሂቃንና በአለማቀፍ ካፒታል {የምዕራቡን ኒዎሊብራሊዝም
የቻይናውን ገበያ መር ሶሻሊዝምን ይዞ} መሓል ባለ የጥቅም ሽርክና ምክንያት
በእድገት፣ በልማት ስም ተመስሎ፣ ተሳቦ ስለመጣው የመሬት ቅሚያ፣ የተፈጥሮ
ሀብት ዝርፊያ፣ የአካባቢ ውድመት፣ አንስተን፣ ለምን ብለን እንዳንወያይ፣ በዚህም
ላይ ተመስርተን እንዳንደራጅ ሆነናል። ህይወቶቻችን፣ ማንነቶቻችን ተወሳስበው፣
ፍጹም ተጠላልፈው እንዳሉባቸው እንደከተሞቻችን በተለይ እንደአዲስ አበባ
ባሉ ቦታዎች ሁሉንም ነገር በማንነት ፖለቲካ ብቻ ነው የሚታየው ወይም
የሚተነተነው፣ የሚፈታውም ማለት መከራዎቻችንን ከማርዘም ሌላ ምን ፋይዳ
ይኖራቸዋል?

ሁለተኛ፣ የማንነት ፖለቲካ ገኖ አገንግኖ መዉጣት ካመጣቸው ጉዳይች ውስጥ
ዋነኛው መጤ እና ነባር የሚለው ትርክት ሲሆን እሱም በአንድ አገር ዜጎች
መሐከል ደረጃ በማውጣት፣ እኛና እነሱ የሚል ክፍፍልን፣ አንደኛና ሁለተኛ የሚል
ዜግነትን በመፍጠር የማግለል ከዛም የመንቀል ከፍ ሲልም የማስወገድ ፖለቲካን
ወደሌተቀን ቋንቋችንና የፖለቲካ ሕይወታችን ውስጥ ሰርጎ እንዲገባ ማድረጉ
ነው። ይህ በዜጎች መሐል አጥር የሚሰራ፣ ደረጃ የሚያወጣ ትርክት፣ በሰዎች
ህይወት ላይ፣ በመኖር ያለመኖር ጉዳያቸው ላይ የሚወስን ነውና በጥንቃቄ ሊታይ
ይገባዋል። በማንነት ፖለቲካ ነጋዴዎች እጅ ሲገባም የህዝብ እልቂትን፣ ጅምላ
መፈናቀልን ሲያስከትል የሀገሪቷንም የመቀጠል ያለመቀጠል ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ
ያስገባል። እንደምሳሌም በቅርቡ በመንግስት የቀረበው ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ
ስላለው “ልዩ ጥቅም“ የሚደነግገው ረቂቅ አዋጅ፣ ከፍ ሲልም በአንዳንድ የዘውጌ
ልሂቃን የሚቀነቀነውን “የባለቤትነት“ ትርክት፣ እንመልከት።

ባንድ በኩል ጥያቄዉ ታሪክን ተንተርሶ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት አድርጎ
የመጣ ነዉና ምላሽ ያስፈልገዋል። እንደሚታወቀዉ የልዩ መብትም ሆነ
የባለቤትነት ትርክት ከአዲስ አበባ ዉጭ በሚገኙ ሌሎች የሃገራችን ከተሞችም
ያለ ነዉና ጥያቄውን እንዴት እናስተናግደዉ ፥ ምላሹስ ምን ይሁን ብለን ማሰብ
ይኖርብናል ማለት ነው። አሁን ግልጽ እየሆነ የመጣዉ ጉዳይ ከተሞቻችን
በልማት ስም ነዋሪዉን ሁሌ እያፈናቀሉ እንደማይቀጥሉ፥ ነዋሪዉም ቁልፍ
የሆነዉ የዜግነትና የመብት ጥያቄዉ በካሳ ጉዳይ ብቻ ታጥሮ ፥ ከልማቱም ርቆ ፥
ተገልሎ ኢትዮጵያዊ ነኝ ሊል እንደማይችል ነው። ስለዚህ ልማቱን ህግ ይግዛው፥
ለሁሉም ይዳረስ። ነዋሪዉም እንደዜግነቱ የከተሞቹ (በዛዉም ያገሪቱ) እዉነተኛ
ባለቤት ይሁን። ድምጹ የሚሰማበት ፥ ራሱን የሚያስተዳደርበት ስርአት ይበጅለት።
አዲስ አበባን በተመለከተም በከተማዉ ዙሪያ ያለዉ የኦሮሞ ማህበረሰብ
በከተማዉ እድገትና ልማት ተጎጂና የበይ ተመልካች መሆኑ ቀርቶ ተጠቃሚ
እንዲሆን የሚያስችል ህግ በመንግስት፥ በከተማዉና በክልሉ አስተዳደር
ተመክሮበት በቶሎ ይዉጣለት።

በሌላ በኩል ግን በተለይ ባለቤትነትን መሰረት አድርጎ የተነሳዉ ጥያቄ ፥ አንዱን
ነባርና ባለአገር ሌላዉን ደግሞ መጤና እንግዳ የሚያደርገው ትርክት ፥ ሌሎች
ዉስብስብ ጥያቄዎችንና ተቃዋሚ ትርክቶችን አስከትሎ መጥቷል። ይህም ነባር
ነኝ የሚለዉን መጤ፥ መጤ የተባለዉን ነባር ካደረገ ትንተና አንስቶ የኛ ያልሆኑት
ሁሉ (the ‘other’) ከኛ አንሰው ይኑሩ፥ የተለየ ግብር ይክፈሉ፥ ካልሆነም ይዉጡ
እስከሚለው ጥያቄ ድረስ ይዘልቃል። እንግዲህ የኛ የምንለው ነጻነት የሌሎችን
ነጻነት ከናደ፥ ወደ ሁለተኛም ዜጋ ካወረዳቸው ምን አይነት ነጻነት ሊሆን ነዉ?
ባንድ በኩል ይህ ከተሞችን በዛዉም አገሪቷን መሰረት አድርጎ የሚነሳው የልዩ
መብትና ባለቤትነት ትርክት ትንቅንቅ የሚያሳየው እስካሁን ያልተፈታው፣ በተለይ
በክልሎች ውስጥ አንዳንዴም ደም አፋሳሽ በሆነ መንገድ ሲንጸባረቅ የነበረው
የእነሱና እኛ፣ የመጤነትና የነዋሪነት ትርክትና ድርጊት ወደከተሞችም

መ ም ጣ ቱ ን ፥ በከተሞችና በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ዜጎችም እንደዜግነታቸው
በአገራቸው ውስጥ በነጻነት የመዘዋወር፥ የመስራትም ሆነ የመኖር መብታቸው
ምን ያህል መሸራረፉን ነው። የአዲስ አበባ የልዩ መብትም ሆነ የባለቤትነት
ፖለቲካ መታየትና መተንተን ያለበት እንደአንድ ተነጥሎ እንደቆመ ቁንጽል ጉዳይ
ሳይሆን በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ፈተና ላይ ያለው የዜግነት፣ የአገርነትና ፣ የአገር
ባለቤትነት ትልቅ ጥያቄ መገለጫ፣ በሌላ በኩል በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮት
ስም የሚተገበረው የአግላይ ኒዮሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ፍልስፍናና መዘዙ ዋና
“ማሳያ“ መሆኑን በማስረገጥ ነው። ታዲያ ምን ይሻላል?

የአዲስ አበባ መራሄ መንገድ

አዲስ አበባ በብዙ ሁኔታ የኢትዮጵያ ተምሳሌት መሆኗ በየቀኑ የሚታይ እውነታ
ነው። ከተማዋን ማወቅ ማለት አገሪቷን በተወሰነ ደረጃ መረዳት ማለት ነው።
የአዲስ አበባን ችግሮች ተረድተን መፍታት ከጀመርን የኢትዮጵያን ጥያቄዎች
የመሞገት ፣ ፈተናዎቿንም የመጋፈጥ ታላቅ ስራ ጀመርን ማለት ይሆናል።
ከተማዋን የምንመለከትበት መነጽር ፣ ከፍታዎቿን፣ ዝቅታዎቿንና ተስፋዎቿን
የምንተነትንበት መንገድ ለአገሪቷም ይሰራልና ለጊዜው እንደዚህ ብንጀምርስ፣

                                   በዋናነት

አንደኛ፣ የተሻለ አገር አልመን ያልተሻለ ከተማ {ከተሞች} እንዳንፈጥር፣ አዲስ
አበባችን (በዛዉም ኢትዮጵያችን) በውስጧም ሆነ ከሷ ውጭ ያሉ ብዙሃኖች
{አዲስ አበቤዎች፣ ኢትዮጵያውያኖች} በድህነትና በፍንቀላ ተገልለው፣ ተወግደው
ለጥቂቶች የምትሰራ ከተማ እንዳትሆን፣ ዘመናዊነቷና ብሄራዊነቷ አግላይ

ያልሆ ነ፣ ለሁሉም በሁሉም የምትሆን የምትበቃ ፍትሃዊ የሆነች ለአገራችንም
ተምሳሌት የምትሆን ከተማ ለማድረግ ብንተጋስ፣
ሁለተኛ፥ ከራሷም ከአለምም ጋር የታረቀች የሁሉም ለሁሉም የሆነች አገር
እንድትኖረን ጠቅላይ፥አግላይ ከሆነ ርእዮተአለማዊ ቀኖናዊነት፥ ጭፍንነት
ወጥተን፥ እስካሁን የሄድንባቸዉን፥ ያለሙንንም ያጠፉንንም፥ መንገዶች
እንደምሳሌም የብሄር ፌዴራሊዝምን፥ ዉጭተኮር ዘመናዊነትን፥ አግላይ ልማትን
ብንፈትሽ፤ ያልሄድንባቸዉንም የተዉሶ ፥የኩረጃ ሳይሆኑ በራሳችን ታሪክ የተቃኙ
፥ከራሳችን ልምዶችና ፈተናዎች የተቀዱ መንገዶችን መፍትሄዎችን
ብንመረምርስ፥               

                                በመቀጠልም

ሶስተኛ፣ ታሪክም ሆነ ትርክቶች አንድና ወጥ በመሆን ፋንታ ብዙና ንብርብር
መሆናቸውን ተረድተን ፣ እይታዎቻችንንም በብሄር ወይንም በመደብ ምልከታ
ብቻ ከማጥበብ፣ ከመጥበብ፣ ሰፋ አድርገን፣ ሆደሰፊ ሆነን ፣ ሁለቱንም ተቀብለን
ሌሎችም አማራጮች እንዳሉ ግን አጥብቀን ተረድተን ፣ እነሱንም ፈልገን ፣
ሁሉን አቀፍ አገራዊ እይታ ብንፈጥርስ፥
አራተኛ፣ ከተማችን እንዲሁም አገራችን የብዙዎች እኛነቶች ጥምር ውጤት
መሆኗን አምነን፣ እኛም የመልካሙም የመጥፎውም ታሪኳ ወራሾችና ውጤቶች
መሆናችንን ተቀብለን፣ ያንዳችን ችግር ወይም ብሶት እንደራሳችን ወስደን
እይታቸውንም ዋጋ ሰጥተን ያጋመዱንን ገመዶች ብናጠብቅስ፥
አምስተኛ፣ በእኔነት እና በልዩነት ብቻ የገነገነውን ፖለቲካና ትርክታችንን በእኛነት
መሰረት ላይ በመገንባት፣ በአጥሮች ምትክ ድልድይ በማቆም ፣ ከእኛ ባሻገር ካሉ
የእኛዎች ጋር ባለን አንድነት ላይ አትኩረን ብንሰራስ፥  

ስ ድ ስ ተ ኛ ፥ ምርምሮቻችን፥ ትንተናችን፥ በዛም ላይ የሚቆመው ፖለቲካችን
ጥቂቶችን ከጠቀመ የልማትና ዝመና ትርክት ከመጠለፍ፥ ከመነጠቅ ወጥቶ
(ልማታዊ ፊልሞቻችንን ፣ ትያትሮቻችንን፥ ጋዜጠኝነትን ያስታዉሷል) ፥
አትኩሮቱን ስለልማቱና ስለዝመናው ገድሎች ብቻ ሳይሆን ኪሳራዎች፥ ሰለባዎች፥
ስለተገለሉ፥ ዳር ስለሚጣሉ ስለተጣሉ ግፉኣን፥ ተምረዉ ግን ስራአጥተዉ
ስለሚባክኑ ጉልበቶች፥ የአገር ተስፋዎች አድርጎ፣ ምን አለምን፣ ምን አተረፍን፣
ምንስ አጣን ብሎ ጠይቆ ፣ አማራጭ የልማትና የዝመና እዉቀቶችን፥ መዉጫ
መንገዶችን ቢፈጥርስ፥ ቢያመላክትስ፥
የሁሉም ማጠንጠኛ የሚሆነው ግን ህዝቡን ምንም እንደማያውቅ ተከታይ
ከማየት ፥ ድምጹንም ከማፈን ወይም ከመንጠቅ፥ በገዛ ሃገሩም ጉዳይ
እንደማያገባው ባይተዋር ከማድረግ ይልቅ ህዝቡ ምን ይላል፥ ምንስ ይጠይቃል፥
በማለት ከህዝቡ ጋር መነጋገር፥ ጥያቄዉን መመለስ፥ ፍላጎቱንም ማክበር።
ስለፍትህ፥ ስለእኩልነት፥ ስለነጻነት፥ ስለሃሳብና የማንነት ብዝሃነት፥ ስለአንድነት
ሲባል የታገለ፥ በታሪካችን ያልታየ ፥ ዘር ወይም ሃይማኖት ወይም መደብ ያለየ
መከራን ያሳለፈ ሃገር፥ ብዙ ዕልቂትን ያስተናገደ ህዝብ እንዴት ከዚህ የዘመናት
አዙሪት ዉስጥ ተመልሶ ይገባል፥ እንዲገባስ ይደረጋል? በዚህ ሁሉ ዉስጥ የተሻለ
መንገዱን፥ ዘላቂ መዉጫውን የሚያሳዩን፥ ህዝቡም የሚሰማቸው ሰዎቻችንስ
የታሉ?

ሺመልስ ቦንሣ (ዶ/ር)
በሱኒ ስቶኒ ብሩክ ዩኒቨርሲቲ (ኒውዮርክ) የአፍሪካ ታሪክና ፖለቲካ መምህር
ህዳር 21, 2010 ዓ.ም.

      1 ከየት ወደየት የሚለዉ አርዕስት ቀጥ ብሎ የሚፈስ ፥ የታወቀ ፥ የታሰበ መጀመሪያና መድረሻ ያለው ፥
      የታለመለት የታሪክ አካሄድ አለ ለማለት አለመሆኑን እዚህ ላይ ማስታወስ ያስፈልጋል። የጽሁፉ ትኩረትም
      ምንጭ (origin) የመፈለግ፥ የበቁ የተጠናቀቁ እዉነቶችን (the Truth) ‘ቆፍሮ የማዉጣት’ ፥ ማን ነዉ
      መጀመሪያ የመጣዉ፥ የቱ ነዉ የቀደመዉ (Firsters) ብሎ የመጠየቅ ሳይሆን፥ የህዝብን የማያቋርጥ
      እንቅስቃሴና ድብልቅልቅነት (mobility and interpenetration)፥ የታሪክን፥ የትርክትን ተለዋዋጭነትና
      ንብርብርነት (maleability, impermanence and multiplicity) ማሳየት ይሆናል።
      2 ይህን ጽሁፍ ስጽፍ ጥልቅ አስተያየቱን የሰጠኝን፥ ከዛም በላይ በሃገራችን ጉዳይ ሳይታክት
     የምንወያየዉን ሃሳቢ ወዳጄ ሱራፌል ወንድሙን ላመሰግን እወዳለሁ።
      3 ይህ ጽሁፍ የአዲስ አበባን 131 ኛ አመት በማስመልከት የተዘጋጀ ቢሆንም ከተማውን ይዞ ሌሎች
      ተያያዥ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮችንም ያነሳል።
      4 በኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ ከአዲስ አበባ ሌላ በተጨማሪ ሁለት ስያሜዎች ለዋና ከተማዉ
      እንደመጠሪያነት ያገለግላሉ፤ አንደኛው ሸገር የሚለውና በሸዋ ኦሮሞ ዘንድ በስፋት የሚዘወተረ ሲሆን
      ሁለተኛዉ ፊንፊኔ የተባለው፥ በአሁኑ ጊዜም ሰፊ ፖለቲካዊ ትርጉም እየያዘ የመጣዉና
      እንደአማራጭም እየቀረበ ያለው ነው።
      5 የኦሮሞ ህዝብ እንቅስቃሴ በአብዛኛዉ ከ16ኛዉ ክፍለዘመን ጋር ተያይዞ፥ በመጤነትና በወረራ ትርክት
      ታጥሮ ይተነተናል። እንደ ፕሮፌሰር መሃመድ ሃሰን ባሉ ምሁራኖች የሚሰሩ አዳዲስ ጥናቶች ግን ይህን
     ገዥና አንድ ወጥ ታሪክ (one dimensional story) እንደገና በመጠየቅ የኢትዮጵያን ታሪክ በህዝብ
      እንቅስቃሴ መነጽር በማየት የኦሮሞ ህዝብ ኢትዮጵያ ዉስጥ የቀደመ ፥ ከወረራና ግጭት በላይ
     ዉስብስብ የሆነ ታሪክ እንዳለው ያስረግጣሉ።      

Read 2245 times Last modified on Saturday, 23 December 2017 18:10