Tuesday, 02 January 2018 09:36

ጠ/ሚኒስትሩ ተገደው ፍ/ቤት ይቅረቡ በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ለአርብ ቀጠሮ ተይዟል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 አቶ በቀለ ገርባ የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ ተላለፈ

    በሃገሪቱ ከተፈጠሩ ተቃውሞና ግጭቶች ጋር ተያይዘው የወንጀልና የሽብር ክስ የቀረበባቸው የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች፣ በምስክርነት እንዲቀርቡላቸው የጠቀሷቸው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በስብሰባ ምክንያት ፍ/ቤት መቅረብ እንዳልቻሉ ገልፀው፣ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን ፍ/ቤቱም ባለስልጣናቱ የምስክርነት አቀራረብ ላይ እና ጠ/ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተገደው ቀርበው፣ ይመስክሩ በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት፣ ለታህሳስ 27 ቀጠሮ ይዟል፡፡
ከታህሳስ 17 እስከ 19 ቀን 2010 ዓ.ም የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ በፍ/ቤት የታዘዙት ጠ/ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ ምክትላቸው ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የቀድሞው አፈ-ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ እና የለገጣፎ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ጫልቱ ሣኒ በተሰጣቸው ቀጠሮ፣ ፍ/ቤት ተገኝተው፣ የምስክርነት ቃላቸውን እንዳልሰጡ ታውቋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም፣በሥራ ጫና ምክንያት በፍ/ቤት ተገኝተው መመስከር እንዳልቻሉ፣ በፅ/ቤታቸው በኩል ለፍ/ቤቱ ያስታወቁ ሲሆን ባለፈው ሃሙስ ይመሰክራሉ ተብለው የተጠበቁት እነ አቶ ለማ መገርሳም በጋራ ለፍ/ቤቱ በላኩት ደብዳቤ፣ በአስቸኳይ ሃገራዊ ስብሰባ ምክንያት ቀርበው መመስከር ስለማይችሉ ፍ/ቤቱ ችግራቸውን በመረዳት፣ተለዋጭ  ቀጠሮ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍ/ቤቱ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ብይን፣ አቶ በቀለ ገርባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፖሊስ ተገድደው ቀርበው ይመስክሩ ባሉት ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ለመጪው አርብ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ እንዲሁም ቀሪዎቹ ባለስልጣናት በፍ/ቤቱ ቀርበው ምስክር በሚሰጡበት የአቀራረብ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጥሯል፡፡
በሌላ በኩል የአቶ በቀለ ገርባ የጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ህክምና ማግኘት እንዲችሉ ለፍ/ቤት የቀረበው አቤቱታ  ተቀባይነት አግኝቶ፣ የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ፍ/ቤቱ አዝዟል፡፡     

Read 3193 times