Tuesday, 02 January 2018 09:37

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ የ300 ሺህ ብር ካሳ እንዲከፈላቸው ፍ/ቤት ወሰነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  “የዳኛቸው ሃሳቦች” በሚል የተሰራጨው መፅሐፍ ተሰብስቦ እንዲወገድ ታዟል

     አንጋፋው የፍልስፍና ምሁር  ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ሃሳቦችን፣ ያለ ፍቃዳቸው ወስደው፣ “የዳኛቸው ሃሳቦች” በማለት ወደ መፅሐፍ ቀይረዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው አቶ መሃመድ ሀሰን እና መፅሐፉን ለገበያ በማከፋፈል ድርሻ ነበራቸው የተባሉት አቶ አስራት አብርሃም፣ የ300 ሺህ ብር ካሣ እንዲከፍሉ  ተፈረደባቸው፡፡
አንደኛ ተከሳሽ አቶ መሃመድ ሀሰን፣ የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች፣ በሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲሁም መድረኮች ያቀረቧቸውን ሃሳቦች በመጽሐፍ አሰባስበው፣ ያለ ባለቤቱ ፍቃድ አሳትመው በመሸጥ፣ ጥቅም ማግኘታቸው እንዲሁም ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ አስራት አብርሃም፣ የታተመውን መፅሐፍ፣ ለሽያጭ በማከፋፈል፣ የጥቅሙ ተካፋይ ሆነዋል በሚል መከሰሳቸውን፣ የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጠበቃ፣ አቶ ጌትነት የሻነህ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡  
ሁለቱ ግለሰቦች በ2006 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዲሪ የቅጂና ተዛማጅ መብት አዋጅ ድንጋጌዎች መተላለፋቸውን በመዘርዘር ክሱን ለፍ/ቤት ማቅረባቸውን የጠቆሙት ጠበቃው፤ ተከሳሾችም መከላከያ  ያሉትን ማስረጃ አቅርበው ሲከራከሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡  
ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው ፍ/ቤቱም፤ ባለፈው ረቡዕ ታህሳስ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን  በመግለፅ፣ ሁለቱ ተከሳሾች በጋራ 100 ሺህ ብር የሞራል ካሣ እና 2 መቶ ሺህ ብር የጉዳት ካሣ ለተበዳይ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡  
የሰውን ሃሳብ ወስዶ እንደ ራስ አድርጎ የመጠቀም የቅጂ መብት ጉዳይ የወንጀል ክስም እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ ያመለከቱት ጠበቃ ጌትነት፤ ውሳኔ ከተሰጠው የፍትሃ ብሄር ክሱ ጎን ለጎንም የወንጀል ክስ መመስረቱንና ጉዳዩም በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡  
“የዳኛቸው ሃሳቦች” የተሰኘው መጽሐፍ  በ2008 ዓ.ም በ3ሺ ኮፒዎች ታትሞ በ80 ብር ዋጋ ለገበያ መቅረቡ  የተገለፀ ሲሆን የተሰራጩት መጽሐፍት ተሰብስበው እንዲወገዱ ፍ/ቤት ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ 

Read 5989 times