Tuesday, 02 January 2018 09:38

ዶ/ር መረራና በቀለ ገርባ በኦፌኮ አመራርነት እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፣ የተሻሻሉትን የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና የፖለቲካ ፕሮግራም ያጸደቀ ሲሆን የአመራር ለውጥ አለማድረጉን ለአዲስ አድማስ አስታውቋል። በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራና በቀለ ገርባ በኦፌኮ አመራርነት እንደሚቀጥሉ ታውቋል፡፡
የፓርቲው አመራር አቶ ጥሩነህ ገምታ ስለ ጠቅላላ ጉባኤው ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ፤ ኦፌኮ የሁለት ድርጅቶች ውህደት መሆኑን ጠቅሰው፣ የሁለቱ ፓርቲዎችን መተዳደሪያ ደንብ በማዋሃድ አንድ መተዳደሪያ ደንብ መውጣቱን ተናግረዋል፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው ምርጫ ማድረግ የሚቻለው አሁን በፓርቲው ጉባኤ የፀደቀው የመተዳደሪያ ደንብ፣ በምርጫ ቦርድ እውቅና ሲሰጠው እንደሆነ በመግለጽም፣ የአመራር ምርጫ ማድረግ አለመቻሉንና በእስር ላይ የሚገኙት አመራሮች በአመራርነታቸው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲው አንድ ወጥ የፖለቲካ ፕሮግራም አውጥቶ፣ በዚሁ ጉባኤ ላይ ማፅደቁን የገለፁት አቶ ጥሩነህ፤ የሃገሪቱ አስተዳደር ፌደራላዊ እንዲሆን፣ ኦሮሚፋ የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲደረግ፣ መሬት የህዝብ ሆኖ አስተዳደሩ በመንግስት በሚወጣ ተጨማሪ መመሪያ እንዲዋቀር የሚሉ መሰረታዊ የፖለቲካ ፕሮግራሞች መካተታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም የመንግስት ስርአቱ ፓርላሜንታዊ እንዲሆንና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የመንግስት ስርአት እንዲቋቋም የሚል ፕሮግራም መጽደቁንም ጠቁመዋል፡፡  
እስከ ቀጣዩ የፓርቲው ጉባኤ ድረስም በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና በሊቀመንበርነት፣ አቶ በቀለ ገርባ በተቀዳሚ ም/ሊቀ መንበርነት እንደሚቀጥሉም አቶ ጥሩነህ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡  

Read 3767 times