Tuesday, 02 January 2018 09:43

በጎሰኝነት መጋጨት ይብቃን!

Written by  መሐመድ ነስሩ (ሶፎኒያስ አቢስ)
Rate this item
(1 Vote)

        ባለፈው ሳምንት ‹‹የኦቦ ለማ፣ የኦሮሞ ህዝብና የኦሮሞ ልሂቃን ንቃት›› በሚል ርዕስ አንድ ጽሁፍ ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ በዛ ጽሑፍ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መዘመሩ መልካምና ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ጠቅሼ፣ የታሪኩን ሌላኛውን ገፅታ (The other side of the story) በዚህኛው ሳምንት እንደምመለስበት ቃል ገብቼ ነበር፡፡ እነሆ ቃሌን አክብሬአለሁ፡፡ እስኪ ሌላኛውን ገፅ ደግሞ አብረን እንግለጥ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ በባሌ ግጭት ተከስቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በብሄር እየተቧደኑ፣ እርስበርስ እየተገዳደሉና እየተቧቀሱ ነው፡፡ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ አሳዛኝና አሳፋሪ የሆነ ግድያና መፈናቀል ተከስቷል። ይሄ ያሳስባል፡፡ ሀገር እንደ ጣቃ እየተተረተረች ያለች ይመስላል፡፡ የጥላቻ አረም በየሰዉ ልብ ውስጥ በቅሎ፣ የጠብ አራሙቻ በየክልሉ አብቦ፤ መፈናቀልና እልቂት እንደ እንጉዳይ ሲወረን… ባንገረም ነው የሚገርም! … ሰው እንደ ዋዛ ወድቆ ሲገኝ የትም የትም! … ባይገርመን ነው የሚገርም! …
አድገናል ይባላል፡፡ ተለውጠናል ተብሎ ይወራል፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነት ግን ከዚህ ይቃረናል፡፡ ነገሩ በዕውቀቱ ስዩም እንዳለው ነው፡፡ በዕውቄ ምን አለ?! …
‹‹ኀሰሳ ሰላም
ማጭድ ይሆነን ዘንድ ምንሽር ቀለጠ
ዳሩ ብረት እንጂ ልብ አልተለወጠ
ለሳር ያልነው ስለት እልፍ አንገት ቆረጠ፡፡››
ልክ ነው፤ ልብ ካልተለወጠ የትኛውም ዓይነት ለውጥ ትርጉም የለውም፡፡ ለዚህ ነው ኢኮኖሚውን ከመገንባት የበለጠ ሰው መገንባት ይቅደም የምንለው፡፡ የሰው ልማት፣ የሰው ግንባታ ይፍጠን ብለን የምንጮኸው፡፡ መንግስት ግን ሊሰማ አልቻለም፡፡ ይልቁኑ በተቃራኒ ተንቀሳቀሰ፡፡ ልዩነት እያሰፋ … ቁርሾ እያነገሰ … ብሔር ከብሔር እያጋጨ … ዓለሙን ቀጨ፡፡ ዘና ፈታ ብሎ በስልጣን ላይ ቆየ። ዕድሜውን ለማራዘም እርስበርስ ሲያባላን ከረመ፡፡ ከስልጣን ውጪ ምንም ነገር አልታየው አለ፡፡
ነገር ግን በመንግስት ብቻ ሳይሆን በህዝቡም ላይ መሰራት ያለበት ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው አሁን የኢህአዴግ ትውልድ ደርሷል፡፡ ኢህአዴግ ሲገባ የተወለደ ልጅ፣ 26ኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ትውልድ ደግሞ የሌላውን ቋንቋ እንዲንቅ፤ የራሱን ብቻ እንዲንከባከብና እንዲጠብቅ፤ አንድነትን እንዲጠላ ተደርጎ ነው ያደገው፡፡ ወጣቱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግርፍ፣ የልማታዊ መንግስት ጥልፍ፤ የጎሳ ፌደራሊዝም ንድፍ ነው፡፡ ስለዚህ በመነጋገርና በመወያየት ፈንታ መናቆርና መገዳደል በርክቷል፡፡
አንዱ በሌላው ሀዘን ይደሰታል፡፡
በሌላው እንባ መፍሰስ እንባው ይታበሳል፡፡
የወንድሙ ደስታና ፌሽታ ያሳዝንና ያስለቅሰዋል፡፡
የወንድም ህዝቦች ጥጋብ፣ ረሀብ ያስርበዋል፡፡
ለውድቀትና ለጥፋት ይባጃል፡፡
በሌላው ሞት ህይወትን ይቀዳጃል፡፡ …ወዘተ…
ያሳዝናል!
በጣም ያሳዝናል!
እጅግ በጣም ያሳዝናል! … (‹‹አናሳዝንም ወይ?!›› ማለት ያለብን አሁን ነው!...)
ፌስቡክ ላይ የሚለጠፉ አንዳንድ ሀሳቦች ሲታዩ ቆሽት ያሳርራሉ፡፡ ወዴት እየሄድን ነው? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድዳሉ፡፡ የጥላቻ ዘመቻ ይካሄዳል፡፡ ዘር እየለዩ፣ ስም እየጠሩ … እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚያሳስቡና የሚቀሰቅሱ አሉ፡፡
በእውነት ወዴት እየሔድን ነው??!!
ያጠያይቃል፡፡
ያሳስባል፡፡
ያስቆዝማል፡፡
በኢህአዴግ አማካኝነት ስለ ጎመራው የጎሳ ፌደራሊዝም (Ethnic federalism) ሳስብ ሁሌ የምጠቅሰው አንድ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ምሳሌ ትዝ ይለኛል፡፡
ፕሮፌሰሩ ‹‹ኢትዮጵያ በ2020 ከየት ወዴት?›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ፤ ያንዣበብንን አደጋ ሲገልፁ እንዲህ ነበር ያሉት፤ የተረት ቃና ባለው ድምፀት!
‹‹… በሸምበቆ አጥር የተለያዩና የሚተራመሱ ጎሳዎችን ጭኖ የሚከንፍ ባቡር ይታየኛል፣ ነጂው መትረየሱን ይዞ ፊቱን አዙሮ የተቀመጠው ወደሚነዳበት አቅጣጫ ሳይሆን ወደ ተሳፋሪዎቹ ነው፤ ተሳፋሪዎቹ የሚያዩት ወደፊት ነው፡፡ ነጂው የሚያየው ወደ ኋላ ነው፡፡ ስለዚህ ነጂው ገደሉን ስለማያይ ይበልጥ የሚያስፈራው የተሳፋሪዎቹ ትርምስ ነው፡፡ ተሳፋሪዎቹን የሚያስፈራቸው የሚታየው መትረየስና ገደል ነው፡፡ በባቡሩ ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎች ሁሉ በባቡሩ ፍጥነት ላይ ሆነ አቅጣጫ ላይ ምንም አይነት ቁጥጥር የላቸውም፤ የባቡሩ ነጂ ተሳፋሪዎቹ የሚያዩትን አያይም፤ እንዲነግሩትም አይፈልግም፤ የነጂውና የተሳፋሪዎቹ አስተሳሰብ ለየቅል ነው፤ አይነጋገሩም፤ ተሳፋሪዎቹ በዝምታ ነጂው የማያየው ገደል ውስጥ ለመግባት ቆርጠዋል፤ ባቡሩን አቁም ብለው ቢጮሁ መልሱ መትረየስ መሆኑን ያውቃሉ፤ በዝምታ አብሮ ገደል መግባት ነው፡፡ በዚህ አጣብቂኝና የፍርሀት ቆፈን ተይዘናል፣ ከተረዳንለት ነጂውም አጣብቂኝና የፍርሃት ቆፈን ውስጥ ነው፤ ነጂውና ተሳፋሪዎቹ ካልተነጋገሩ ባቡሩም፣ ተሳፋሪዎቹም፣ ነጂውም ከገደሉ ማምለጥ አይችሉም፡፡…››
ጎምቱው ምሁርና ፖለቲከኛ ይህን ያሉት ከአስራ አራት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ምን አይነት አስገራሚ ትንቢት ነው?!...
አሁን በእርግጥም የገደሉ አፋፍ ላይ የደረስን ይመስላል፡፡ እርስበርስ እየተበላላንና እየተቦጫጨቅን ነው፡፡ ‹‹ተሳፋሪው›› ህዝብ እየተበጣበጠ ነው፡፡ ‹‹ነጂው›› መንግስት እየተረበሸና እየተናጠ ነው፡፡ ምን ይሻላል?!! ….
ተቀራርቦ መነጋገር ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ። እያንዳንዱ ብሄር ወይም የብሄሩ አባል የራሱን ጩኸት ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ጩኸት ማድመጥ አለበት፡፡ የራሱን ስሜት ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ስሜት ለመረዳት መትጋት አለበት፡፡ የራሱን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ፍላጎት ማወቅና በአግባቡ ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ እርስበርስ መተሳሰብና መተዛዘን ይኖርብናል፡፡ አንዳችን ለሌላችን ካልቆምን ማን መጥቶ ይቆምልናል?! ወገን ለወገን ደራሽ መሆንና ምንም ይሁን ምን፣ የወገንን አስተሳሰብና ሀሳብ ተረድቶ ሊያከብርለት ይገባል፡፡ ሊያከብርለት ብቻ ሳይሆን እንዲከበርለትም ዘብ መቆም፣ ግዴታው እንደሆነ ማወቅ ይገባዋል፡፡ ለሱም መብት ጥብቅና ሊቆምለት የሚችለው ጥብቅና ሲቆም ብቻ ነው፡፡ እግር ተወርች የጠፈረንን የጎሰኝነት ካቴና መበጠስ ይኖርብናል፡፡ ሰንሰለቱን ብጥስ!
ሌላ ተመሳሳይ ሀሳብ ደሞ ላንሳ፡፡
ጥላቻ ተወግዶ፣ ፍቅር ሊነግስ፣ ልዩነት ጠፍቶ፣ አንድነት ሊመለስ የሚችለው ስለ አንድነት በመስበክና በመናገር፣ ስለ ትብብር አስፈላጊነት በመወትወትና በመፃፍ ብቻ አይደለም፡፡ … ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይፈልጋል፡፡ እርስ በርስ ተቀራርቦ መነጋገርና መወያየትን ይጠይቃል። ያጠፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ የተበደለ ተክሶ እርቀ ሰላም እንዲወርድ ይጠበቃል፡፡ አብሮ መብላትና አብሮ መጠጣት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ እርስ በእርስ የሚያጋጩንን ሰዎች ማንነትና ምንነት በመለየት፣ ግጭት እንዳይከሰት መጣር ግድ ይላል፡፡ አንዱ ሌላውን በመረዳት (understand በማድረግ) ችግሮችን መፍታትም ተገቢ ነው፡፡ በርግጥ መግባባቱ በታሪካዊውና ተግባራዊ የህዝብ ንቃተ ህሊና መቃኘት፣ በህዝብ ሀሳብና ፍላጎት መዳኘት፣ በመሬት ላይ ያለውን እውነት ማገናዘብ እንዳለበት እገነዘባለሁ፡፡ ታሪክን ማንበብና ማወቅ፣ እውነትን ማጥለልና ማንጠር፣ እውቀትን መፈተሽና መበርበር፣ በመጨረሻም ጠንካራ አቋም መያዝና አንድ ስለመሆን በአፅንኦት መደምደም! አስፈላጊ ነው፡፡ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው። …በያለንበት ሁሉ ህብረትና አንድነት ይከተለን! ቸር ያሰማን!

Read 1945 times