Tuesday, 02 January 2018 09:48

የአዲስ አበባ “ልዩ ተጠቃሚነት” ጥያቄ፤ የፌደራል አወቃቀሩ ሌላው ችግር!

Written by  ከዐቦቴ ደራ
Rate this item
(2 votes)


    በ1987 ዓ.ም በጸደቀው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ̄̄̄−መንግስት ላይ ከሚሰነዘሩት አበይት ትችቶች፤ እንደውም ዋነኛው ማለት ይቻላል፣ ክልሎች የተዋቀሩበት መንገድ ነው። የፌደራል ስርዐትን በሚከተሉ ሀገራት፣ ስልጣንን ለማከፋፈልና በአግባቡም ለማስተዳደር ይረዳ ዘንድ የተለያየ ስያሜን እየሰጡ (እንደ ክፍለ−ሀገር፣ ክልል፣ ኔሽን(ብሔር) እና የመሳሰሉትን) በፌደራል መንግስቱ ስር የሚገኙ ራሳቸውን የቻሉ የአስተዳደር አካላትን ይመሰርታሉ። በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢትዮጵያ ሕገ̄̄−መንግስትም ክልሎች ብሎ በሚጠራቸው ዘጠኝ የአስዳደር አካላትና  በፌደራል መንግስቱ ስር በሚገኙ ሁለት ከተሞች ተዋቅሯል።
የኢትዮጵያ ሕገ−መንግስት የሀገሪቷን ክልሎች ያዋቀረበት መንገድ፣ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ብሔርን በመፍጠር ሲሆን (ከዛ በፊት ብሔር መኖሩ ስለሚያጠራጥር) ይህም የአወቃቀር ዓይነት ወደ የትኛው አቅጣጫ ሊያመራ እንደሚችል ያልታወቀ የቤተ−ሙከራ ዓይነት አወቃቀር ነበር። ይህን ዘረኛ የፌደራል አወቃቀር የሚተቹ  ምሁራን፣ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ዘርፈ ብዙ ልዩነቶች ባሉባት ሀገር፣ ዘርን መሰረት ያደረገ የፌደራል አወቃቀር፣ ለሀገሪቱ በረከትን ከማምጣት ይልቅ መርገምትን ሊያስከትል እንደሚችል አዘወትሮው ወትውተዋል። ከሁለት ዐስርተ ዓመታት በላይ ሲብላላ የቆየው ይኽ የፌደራል አወቃቀር፣ ዛሬ ከበረከትነቱ ይልቅ ይዞት እየመጣ ያለው መዘዝ ጎልቶ እየታየ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ኢህአዴጋውያን፤ “ይኽ የፌደራል አወቃቀር፣ የኢትዮጵያ ዳግም ውልደትና እንደ ሀገር በሰላም የመቀጠል ዋስትናችን ነው” ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና፣ የቀደሙት ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ወቅት በዚህ ጉዳይ ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “በዚህ የፌደራል አወቃቀር ኢትዮጵያ የማትኖር ከሆነ በፊትም አልነበረችም፤ወደ ፊትም አትኖርም” ብለው ነበር። ምንም እንኳን ዛሬ ላይ የስህተታቸው ውጤት እየታየ ቢሆንም።
የጽሁፌ ርዕሰ ጉዳይ የአዲስ አበባ “ልዩ ተጠቃሚነት” ጥያቄ ነው፡፡ አዲስ አበባን ደግሞ ከፌደራል ስርዐት አወቃቀሩ ጋር ምን ያገናኛታል የሚል ጥያቄን ሊያስነሳ ይችላል። እንደኔ እንደኔ ግንኙነት አላቸው ባይ ነኝ። እንዴት ቢሉኝ፣ እኔም ይህን የፌደራል አወቃቀር ከማይደግፉት ወገን ስለሆንኩ ሳይሆን፤ የኔ የምለው ምክንያት ስላለኝ ነው። የፌደራል ስርዓት፣ መንግስትን የመመስረቻ ስርዐት መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ፤ የፌደራል ዐወቃቀሩ ግን ምንን መሰረት ያድርግ የሚለው ወሳኙ ነጥብ ነው፡፡ እንግዲህ በብዙ ሀገራት ተግባር ላይ የዋለው የቦታ አቀማመጥን (ጂኦግራፊያዊ  የሚባለውን) መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም፣ አንደኛው የፌደራሉን ክልሎች የማዋቀሪያ መንገድ ነው።
በዚህ ቦታን መሰረት ባደረገ የፌደራሊዝም ስርዓት ደግሞ የፌደራል ስርዓቱ እንዲቋቋም ዋና ዋና ምክንያት ሆነው የተቀመጡትን ፤ ራስን በራስ የማስተዳደርና የስልጣን ባለቤትነት፣ ከዚህም ጋር የሚያያዘውን መልካም ስርዓትን ለህዝቦች የማምጣትን ግብ የበለጠ ያሳካል እንጂ እንቅፋት አይሆንም። ይልቁንም አሁንም የስርዓቱ በረከቶች ተደርገው የሚቆጠሩትን ፍትህ ፣ ዲሞክራሲ ፣ የህግ የበላይነት ፣ እኩልነትና ሌሎችም ከዚህ የፌደራል አወቃቀር ጋር እጅና ጓንት ነው የሚሆኑት። ምናልባት ብሔርተኞቹና ጎሰኞቹ እንደሚያስቡት፣ ግለሰብንም ሆነ ህዝብን በብሔሩ ወይም በጎሳው ብቻ ከመስፈር ይልቅ እንደ ሰው ማየቱ ቅሬታን ካልፈጠረባቸው በቀር።
ስለሆነም የፌደራል አወቃቀራችን ጂኦግራፊያዊ ቢሆን ኖሮ፣ ለምሳሌ ደርግ የተጠቀመበትን አከላለል እንደ አከላለል ብቻ፣  ብንወስደው፣ በአብዛኛው በአስራ አራት ክፍላተ−ሀገሮች (በዛሬው ቋንቋ ክልሎች) ነበር ኢትዮጵያ የተዋቀረችው። በዚያን ግዜ  አማራ የሚባልም ሆነ ኦሮሞ የሚባል ክፍለ−ሀገር አልነበረም። ጎንደር (በጌምድር)፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ አሩሲ፣ ባሌ፣ ከፋ፣ ወለጋ እያለ የሚሄድ ነበር። ታዲያ በዚህ መንገድ ሄደን፣ የፌደራል ስርዓቱን ብንመሰርተው ምን ነበር ችግሩ?! የፌደራሊዝሙ በረከቶች ይቀሩብን ነበር ወይስ መዘዞቹን እናስወግድ ነበር?!
አሁንም ወደ ተነሳሁበት፤ ከላይ በጀመርኩት ጂኦግራፊያዊውን በተከተለው  አወቃቀር ስንቀጥል፣ ሸዋን ያመጣልን እንደሆነ እንጂ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ የሚባል ነገር አይኖርም። በርግጥ ሸዋ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ህዝቦች ይኖራሉ፤ በአንድ የጎሳ ከረጢት ውስጥ የሚጠቀለሉ ግን አይሆኑም። በመሆኑም ከ1987ቱ የፌደራል አወቃቀር ጋር ተያይዞ ከሚነሳው አንደኛው፣ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫና የኦሮሚያ ክልል መንግስት መቀመጫ ጥያቄ፣ የሸዋ ክፍለ−ሀገር ጥያቄ ሆነ ማለት ነው።
የአዲስ አበባም ጥያቄ (በመጀመሪያም እንደ ጥያቄ ከተነሳ ነው) የሸዋ ጥያቄ ይሆናል ማለት ነው። የሸዋ ጥያቄ ማለት ደግሞ የሸዋ ነዋሪዎች ጥያቄ ስለሚሆን በአብዛኛው የሸዋ ኦሮሞዎችና በዛሬው አነጋገር፣ የሸዋ አማሮች እንዲሁም የሌሎች ነዋሪዎች ጥያቄ ይሆናል። ይህን የምልበት ምክንያት ዛሬ  የአዲስ አበባ ጥያቄ፣ የአንድ ክልል ጥያቄ ሆኖ ስለተቆጠረ፣ ያኔም ጥያቄው እንደ አንድ የፌደራል መንግስቱ ክልል ጥያቄ ሆኖ ስለሚቆጠር ነው። አዲስ አበባን እንደ አንድ የተወሰነ ቦታ ከቆጠርን ግን ለጥያቄው ይበልጥ ሚዛን የሚደፉት የሸዋ ኦሮሞዎች ይሆናሉ።
አዲስ አበባን (ፊንፊኔን) በተመለከተ በሕገ−መንግስቱ አንቀፅ 49 .ላይ፣ የኦሮሚያን ክልል ልዩ ተጠቃሚነት ይገልፅና ዝርዝሩ በአዋጅ ወደፊት እንደሚወሰን ይገልፃል። አሁን በቅርቡ በ2009 ዓ.ም ደግሞ የኦሮሚያ ክልልና የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በፊንፊኔ ( አዲስ አበባ) ላይ በሚኖራቸው ልዩ ጥቅም ላይ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን የህዝብ ተወካዮችንና የሚኒስትሮችን ምክር ቤት ይሁንታ እየጠበቀ ይገኛል። በነገራችን ላይ ያሳለፍነው ሳምንት አንደኛው የፓርላማው መወዛገቢያ ይኸው ጉዳይ ነበር። እንደ ረቂቁ ሀተታ ከሆነ ፊንፊኔ አዲስ አበባ የኦሮሞዎች ይዞታና መኖሪያ የነበረች ስትሆን እነዚህ ነባር ነዋሪዎች በደረሰባቸው መገፋትና መወረር ከይዞታቸው ተፈናቅለዋል። በመሆኑም  ከአንድ መቶ ሰላሳ ዓመት በፊት በደል ለደረሰባቸው አያቶች፣ ዛሬ ላይ የልጅ ልጆቻቸው መካስና ልዩ ተጠቃሚም መሆን ይገባቸዋል ይላል። በርግጥ ረቂቅ ሰነዱ ላይ ነባር የፊንፊኔ ነዋሪዎች በማለት የቀጥታ ተበዳዮችን የመካስና ተጠቃሚ የማድረግ አዝማሚያ ቢያሳይም፣ አጠቃላይ ግንዛቤውና እውነታው ግን ማንንም የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ በጠቅላላው በኦሮሞነቱ ብቻ የሚያገኘው ልዩ ጥቅም ተደርጎ ተወስዷል። ይህም ከፍትህ፣ ከርትዕ፣ ከሞራል ወይም በየትኛውም መመዘኛ መዝነን ቅቡልነቱ ላይ የሚያሟግተን ቢሆንም፤ ጥያቄው እንደ ጥያቄ ህልውናን እንዲያገኝ የረዳው ግን ይኸው ቋንቋንና ብሔርን መሰረት ያደረገ የፌደራል አወቃቀር ነው።
ታዲያ ባሳለፍነው ዓመት እውነተኛ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግልፅ ባይታወቅም፣ ጉዳዩ እንደ አዲስ ተነስቶ በሕገ−መንግስቱ በይደር የቆየው ልዩ ተጠቃሚነት፣ ወደ ትግበራ እየተገባ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፤ ማንኛውም ብሔሩ ኦሮሞ የሆነ ሁሉ እንደ ግለሰብ የቤት መስሪያ ቦታ ከሊዝ ነፃ የማግኘት፣ የጋራ መኖሪያ ቤት እደላ ላይ አስራ አምስት በመቶ ከሌላው ብልጫ ማግኘትና የመሳሰሉትን ልዩ ጥቅሞች ሲጠቅስ፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ደግሞ እንደ መንግስትነቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዋና መቀመጫነት፣ ክልሉ ባሕሉን፣ ታሪኩን፣ ኢኮኖሚያዊና  ሌሎችም ሊያሳድጋቸው ለሚፈልገው ህዝባዊ አገልግሎቶች  የሚውሉ ህንፃዎችና ፋሲሊቲዎች የሚገነባበት በቂ መሬት፣ ከከተማ አስተዳድሩ ከሊዝ ነፃ የሚያገኝበትና ሌሎችም ጥቅሞች እንዳሉት ረቂቅ ልዩ ሰነዱ ያትታል።  ከረቂቅ ሰነዱ በዘለለ ደግሞ ነገር ማክረር ተሰጥኦዋቸው የሆኑ ግለሰቦች አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) የኦሮሚያ “ሀገር” (እነሱ እንደሚሉት) ይዞታና ይዞታ ብቻ ነች። በመጪው ግዜም ሊከወኑ ከሚገባቸው ነገሮች ዋነኛው “ኦሮሚያን ከቅኝ ተገዢነት ነፃ ማውጣትና ሉዓላዊ የሆነች የኦሮሞዎችን ሀገር መፍጠር ነው።” ከዛ በፊት ግን የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር አብሮ ለመኖር የሚወስን ከሆነ የፊንፊኔን ጉዳይ ለኦሮሞ ብቻ ትቶ፣  ሁሉም ተስማምቶ ለሚፈጥሯት አዲስ ሀገር፣ ሁሉም ክልል ቁራሽ መሬት እያዋጣ አዲስ ከተማ መቆርቆር ይኖርበታል እስከማለት ይደርሳሉ። ከብዙ ተጨባጭ እውነታዎች  በመነሳት ጥያቄውን ስንመረምረው የዋህ ጥያቄ ቢሆንም ከመነሳት ግን አልተቆጠበም።
መደምደሚያ
እንግዲህ እዚህ ሁሉ እሰጥ አገባ ውስጥ የከተተንና አሁንም መጨረሻው ምን እንደሚሆን ያልታወቀ ጥርጣሬና ስጋት ላይ የጣለን ይኽ የፌደራል አወቃቀር ነው። በተቃራኒው ግን ጂኦግራፊያዊው አከላለል ቢሆን ኖሮ እንደተባለው ልዩ ጥቅሙ ከተገባቸው በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆኑት የጉዳቱ ሰለባ የሆኑት ሰዎች ስለሚሆኑ ከፍትህም ሆነ ከርትዕ ፣ ከሞራልም ሆነ ከሰብአዊነት አንፃር ላያሟግተን የሚችል ይመስለኛል። ከዛ በተረፈ ግን አንደኛ፣ አዲስ አበባን በስምም ሆነ በአካል አይቷት የማያውቅ፣ በሰባት መቶና ስምንት መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቆ የሚገኝ የአንድ ብሔር ተወላጅ አሊያም እድሜውን ሙሉ አሜሪካ ሚኒሶታ የኖረን ግለሰብ፣ እሱ በማያውቀው ምክንያት የሆነ ብሔር አባል በመሆኑ ብቻ ተጠቃሚ አድርጎ፣ በውልደቱም ሆነ በዕድገቱ አዲስ አበባንና አዲስ አበባን ብቻ የሚያውቀውን መግፋት ፍትሀዊነቱ አይታየኝም። ሁለተኛ፣ ጂኦግራፊያዊው የፌደራል አከላለል ቢሆን ኖሮ፣ ቢሆን ኖሮ እያልኩ ከላይ ሳላዝን የነበረው፣ “የቢሆን ኖሮ ጨዋታ” እንደሌለ ሳይገባኝ ቀርቶ አይደለም። ይልቁንም የልዩ ተጠቃሚነትንም ሆነ ሌላውንም አጀንዳ ይዘው የሚያራግቡት፣ ጥያቄያቸው በዚህ በተንሸዋረረ የጎሳ ፌደራሊዝም ላይ መሰረት ያደረገ፣ የተንሸዋረረ ጥያቄ መሆኑን እንዲረዱና ከቻሉም ለዘብ ብለው ወደ እውነታው እንዲያተኩሩ መሞከሬ ነው።

Read 3323 times