Tuesday, 02 January 2018 09:55

“ጊዜዋ የደረሰ ቀበሮ አዳኝን ታስመሰግናለች!”

Written by 
Rate this item
(11 votes)

  አንዳንድ ተረት አድማጭ ሲያጣ ተደጋግሞ ይነገር ዘንድ ግድ ይሆናል፡፡ ያ ከዓመታት በፊት ያቀረብነው ተረት ስለ ጅቦቹና ስለ አህዮች ነው፡፡ ጅቦቹም፣ አህዮቹም ዛሬም አሉ፡፡ ስለዚህ ደግመን እንተርከዋለን፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሶስት አህዮች በጠፍ ጨረቃ ሣር ሊግጡ ይወጣሉ-እንደ ሰው፡፡
አንድ ሣሩ የለመለመ መስክ ያገኙና መጋጥ ይጀምራሉ፡፡ ጥቂት እንደጋጡ ጅቦች ይመጡና ይከቧቸዋል፡፡ ጅቦቹ መደፈራቸው አናዷቸዋል፡፡ ስለዚህ ሊፈርዱባቸው ችሎት ተቀመጡ፡፡
1ኛ ጅብ ዳኛ፡- የመጀመሪያዋ አህያ እንድትቀርብ ያዛል፡፡
አህያ ገባች፡፡
የማህል ጅብ ዳኛ፡- “ወይዘሮ አህያ፤ በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ግዛት፣ ሣር ልትግጪ ለመውጣት የቻልሺው ማንን ተማምነሽ ነው?”
1ኛ አህያ፡- “አምላክን ተማምኜ ነው፡፡ አምላኬ ምንም አደጋ እንዳይደርስብኝ ይጠብቀኛል፡፡ አደጋም ከደረሰብኝ በሆነ መንገድ ይበቀልልኛል፡፡ ለእሱ ምን ይሳነዋል?”
ጅቡ ዳኛ ወደ ጥግ እንድትቆም ያዟታል፡፡
“ሁለተኛዋ አህያ ግቢ” ይላሉ፡፡
ሁለተኛዋ አህያ ገብታ ትቆማለች፡፡
የመሀል ዳኛው ጅብ፡- “ወይዘሮ አህያ፤
በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ግዛት፤ ሣር ልትግጪ ለመውጣት ያስቻለሽ ድፍረት ከየት መጣ? ማንን ተማምነሽ ነው?”
ሁለተኛዋ አህያ እንዲህ ስትል መለሰች፡-
“ጌታዬ፣ ባለቤቱን፣ እሱን ተማምኜ ነው፡፡ ማንም ጉዳት ቢያደርስብኝ ይበቀልልኛል፡፡ ንብረቱ ነኝና ንብረቱን በሚነካ ላይ እርምጃ መውሰዱ አይቀርም!”
ጅቡ መሀል ዳኛ፤ “ወደ ዳር ቁሚ” አላት፡፡
አህዩት ወደ ዳር ቆመች፡፡
“ሦስተኛዋ አህያ ግቢ” አሉ፤ የቀኝ ጅቡ ዳኛ፡፡
ገባች፡፡
“ወይዘሮ አህያ፤ በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ግዛት ሣር ልትግጪ የወጣሽው ማንን ተማምነሽ ነው?”
ሦስተኛዋ አህያ መለሰች፡-
“እናንተ ጌቶችን፤ ደጋጎቹን ጅቦች ተማምኜ ነው፡፡ ሩህሩህ በመሆናችሁ እንደማትጨክኑብኝ ስለማውቅ ነው!”
ወደ ጎን እንድትቆም ታዘዘች፡፡ የተባለችውን አደረገች፡፡
ሦስቱ ዳኞች ጅቦች ተመካከሩ፡-
“ያችን አምላክን የተማመነችውን ብንበላት ዕውነትም ነገ ከነግ-ወዲያ አምላክ ይበቀለናል”
“ጌታዋን የተማመነችውን ብንበላት፣ ነገ ከነግ-ወዲያ፣ ጌታዋ ፍለጋ ከወጣና ካገኘን አይምረንም”
“እቺን በእኛ የተማመነችውን ብንበላት ማን ይጠይቀናል?”
“ዕውነት ነው የማንጠየቅባትን ብንበላ ነው ሰላም የምናገኘው!”
በሃሳቡ ተስማምተው ሁለቱን አሰናብተው ሶስተኛዋን ተቀራመቷት፡፡
* * *
ከማያስተማምን ሰለባ የሚያስተማምን ሰለባ ይሻላል-ለበይው! የሀገራችን ፖለቲካ ህይወት በዚህ ተረት የተመሰለውን ዓይነት ነው! ስንቱ ካድሬ ቀልጧል! ስንቱ ባለሥልጣን ተበልቷል! ስንቱ ጅል “ሆዱን ያየ ሆዱን ተወጋ” ሆኗል! ስንቱ ነብሰ ገዳይ “አስተማማኝ መሳሪያ ነኝ”፣ ማንም አይነካኝ” ሲል፤ በሠፈረው ቁና ተሰፍሯል? ስንቱ በሰው ግዛት ሲግጥ ተግጧል! የሚገርመው አሁንም ባለተራው ታማኝ ነኝ እያለ እጁን አጣጥፎ መቀመጡ ነው! ክቡ ቀለበት “በዲሞክራሲያዊ” መንገድ ሰው መዋጥ መሰልቀጡን ይቀጥላል፡፡ በመላከክ (Blame-Shifting) አንዳች ፍሬ የምናገኝ እየመሰለን፣ በመጠቆም እንኮራለን! በማስወጋት እንተማመናለን! ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፡-  “እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ” በሚለው ግጥሙ…
ትቻቸዋለሁ ይተውኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ
ዕውነት ይተውኛል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?
የተወጋ በቅቶት ቢተኛ፣ የወጋ መች
እንቅልፍ አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው….” የሚለን ባላንጣችን፤ መቼም እንደማይተኛልን ለማስገንዘብ ነው! ልብና ልቦና ይስጠን፡፡
ማርክ ትዌይን ስለ ተራ ተርታ ሰዎችና ስለ ደናቁርት የሚያስገነዝበንን ነገር አንርሳ፡-
“ካለህበት የላቀ ቦታ ጎትተው ያወርዱህና በእነሱ ሜዳ፣ ባገኙት ልምድ በመጠቀም ያሸንፉሃል!”
ዛሬም ዘዴው ያው ነው!
ፍርድ እንዳይዛባ ብለን ብዙ መመሪያ አውጥተናል፡፡ የመጣነውን መንገድ ርዝመት በክፋታችን ልክ እንዳንለካ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
All men are equal but some men are more equal (ሁሉም ሰዎች እኩል ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን የበለጠ እኩል ናቸው እንደማለት ነው) ይለናል - ጆርጅ ኦርዌል በ “አኒማል ፋርም” ውስጥ። የእኛው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ጥሩ አድርጎ ያብራራዋል፡-
“ሞትን ለሚሻ ሞትን ነው መንፈግ!
ህይወትን አለመቸር፡፡
ማህል ቤት ነው ጥቅም የሚሰጥ፡፡
ሰው ሆኖ ካሹት ጥቅም የማይሰጥ የለም!” ይለናል፡፡ ይህ እንግዲህ ነገ ለሚገደልና እባካችሁ መሞቴ ካልቀረ አሁኑኑ ለምን አትገድሉኝም? ለሚለው እሥረኛ የሰጡት ምላሽ ነው፡፡ ይሄ ሟች ዓርበኛ፤
“የሚያባርረኝ ጣሊያን እንቅፋት መትቶት በሞተ ነብስ-ገዳይ ተብዬ ታሠርኩኝ እንጂ፤ እኔስ ዓርበኛ አይደለሁም” የሚል ነው! ግፍ ይህ ወሰንህ፣ ይህ ዲካህ የሚባል አይደለም፡፡ ጊዜያችን ከደረሰ የተፃፈልንን ሞት ማግኘታችን አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም ወይ በመጣደፋችን፣ ወይ ሳንደራጅ ዘራፍ በማለታችን ለጥፋት እንዳረጋለን፡፡ እኛም ጠፍተን ጦሳችን ለሌላ ይተርፋል! “ጊዜዋ የደረሰ ቀበሮ አዳኝን ታስመሰግናለች” ማለት ይሄና ይሄ ብቻ ነው! ከዚህ ይሰውረን!!

Read 5017 times