Tuesday, 02 January 2018 09:57

“ብትሮጥ ቀድመኸው የሚቀጥለው ፌርማታ ትደርሳለህ”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

“-ነገሮች ለምን ጊዜያቸውን ጠብቀው እንደማይሠሩ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ከሦስትና ከአራት ዓመት በፊት የተደፋ አሸዋ ምናምን -- እስከ 2010 ድረስ ተከምሮ ሲቆይ እንዴት ነው፣ አንድ እንኳን ‘የሚመለከተው አካል’ ሳያየው የሚቀረው! ከስንት ዓመት በፊት አፉን ከፈተ ጉድጓድ፣ እንዴት ነው ለእኛ ቀን በቀን ፈጦ ሲታየን፣ ‘ለሚመለከታቸው’ ይህን ያህል የሚሰወርባቸው!--”
   
   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በነገራችን ላይ…በፊት ቴሌቪዥን ላይ ሰዉ ትከሻ ለትከሻ እየተጋጨ የሚርመሰመስባቸውን እንደ ሜክሲኮ ሲቲ አይነት ከተሞች እያየን… “እንዴት ነው በዚህ አይነት ከተማው ውስጥ የሚንቀሳቀሱት?” እንል ነበር፡፡ አንዲት ከተማ ውስጥ ይሄ ሁሉ መንገድ ላይ! ለመገመት እንኳን ያስቸገርን ነበር፡፡ ልክ ነዋ…ለእኛ ሰው እንደዚህ የሚበዛው ግፋ ቢል መርካቶ፣ ግፋ ቢል ካምቦሎጆ ነዋ! አልሰሜን ግባ በሉት እንደሚሉት፣ ባለወር ተራ መሆናችንን አላወቅን፡፡
እናማ አዲስ አበባ እዛ ደረጃ ላይ አልደረሰች ይሆናል፡፡ ግን እንደ አያያዛችን ከሆነ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከተማ ውስጥ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላው በእግራችን እንዴት መንቀሳቀስ እንደምንችል አንድዬ ይወቀው፡፡
የምር እኮ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ‘ረሽ አወር’ የሚባለው የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት፣ ምን እንደሆነ ለማጥናት የመጣ የውጪ ሰው አገሩ ሲመለስ፣ አእምሮ ሆስፒታል ባይገባ ነው! ቀኑን ሙሉ ‘ረሽ አወር’ የሆነባት ከተማ ነው የምትመስለው!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “ሰዉ ከጠዋቱ አራት፣ አምስት ሰዓት ከተማ ውስጥ ምን ያደርጋል? ሥራ የለውም እንዴ!” ብንል ‘ፌይር’ አይሆንም…ስንትና ስንት ሥራ አጥ ያለባት ከተማ ነቻ! እንደዛም ሆኖ ግን የሰዉ ብዛት የሚገርም ነው፡፡ የምር ግን የፍልሰቱ ጉዳይ ‘ኤክሶደስ’ ነገር ሊመስል የቀረበ አይመስላችሁም!
የሆነ ማእድን ማውጫ ስፍራ ነው፡፡ አንድ አጭርና አንድ ረጅም ሰው ጎን፣ ለጎን ሆነው ይቆፍራሉ፡፡ አጭሩ ሰው የረጅሙን እጥፍ ያህል ነበር የሚቆፍረው፡፡ ይሄን የተመለከተው ሀላፊያቸው ረጅሙን ሰውዬ…
“ያሳፍራል፣ አንተ በቁመት ከእሱ በጣም ትበልጣለህ፡፡ እሱ ግን የአንተን እጥፍ እየቆፈረ ነው” ይለዋል፡፡ ይሄን ጊዜ ረጅሙ ሰውዬ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ምን ይገርማል፡፡ እሱ እኮ ከእኔ ይልቅ ለመሬት ቅርብ ነው” ብሎት አረፈ፡፡
ስሙኝማ…የምር ግን፣ ትልቁ ችግር ስህተትን፣ ጉድለትን አምኖ አለመቀበል ነው፡፡ አዲስ አበባ እንዲህ አስቸጋሪ ከተማ እየሆነች ያለችው በየደረጃው ባሉ ድከመቶች ነው፡፡ ምናልባትም ሥራቸውን ችላ ያሉ ግለሰቦች፣ ግዴለሽ የሆኑ ተቋማት የበዙ ነው የሚያስመስለው፡፡
ሀሳብ አለን… በየደረጃው ያሉ አለቆች የግልም ይሁን የተቋም መኪናቸውን በየግቢያቸው ይቆልፉባቸውና ለአንድ ሳምንት ከእኛ ጋር በእግራቸው ይኳትኑ፡፡ በሦስተኛው ቀን…“ሳናውቅ በስህተት፣ እያወቅን በቸልተኝነት ለፈጠርነው ችግር ይቅር በሉን” ብለው የጂብራልታርን አለት የሚያክል ቋጥኝ እየተሸከሙ ይቅርታ  እንደሚጠይቁን ትከሻዬ ነግሮኛል፡፡  
ነገሮች ለምን ጊዜያቸውን ጠብቀው እንደማይሠሩ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ከሦስትና ከአራት ዓመት በፊት የተደፋ አሸዋ ምናምን እስከ 2010 ድረስ ተከምሮ ሲቆይ እንዴት ነው፣ አንድ እንኳን  ‘የሚመለከተው አካል’ ሳያየው የሚቀረው! ከስንት ዓመት በፊት አፉን የከፈተ ጉድጓድ እንዴት ነው ለእኛ ቀን በቀን ፈጦ ሲታየን፣ ‘ለሚመለከታቸው’ ይህን ያህል የሚሰወርባቸው! እናላችሁ…ይቺ ከተማ በየቀኑ ችግሮቿ እየበዙ ነው፡፡
ስሙኝማ… የፍጥነት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው በሩጫ ፌርማታ ሲደርስ አውቶብሱ ሄዷል፡፡ አውቶብሱ ደግሞ በጣም ቀርፋፋ ነው፡፡ እናም… ይሄኔ እዛ ለነበረ አንድ ተቆጣጣሪ…
“ብሮጥ የሚቀጥለው ፌርማታ ላይ የምደርስበት ይመስልሀል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየውም ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው…
“ብትሮጥ ቀድመኸው የሚቀጥለው ፌርማታ ትደርሳለህ፡፡”
እናማ… አሠራራችን ሁሉ ብንሮጥ የሚቀጥለው ፌርማታ ቀድመነው የምንደርስ አውቶብስ ሲሆን ችግሩም ያን ያህል እየተባዛ ነው የሚሄደው፡፡ በነገራችን ላይ… አሁን፣ አሁን የአዲስ አበባ ውስጥ የመንቀሳቀስ ነገር በሩጫ የሚቀደም ቀርፋፋ አውቶብስ አይነት ነገር እየሆነ ነው፡፡  መንቀርፈፉ እንዳለ ሆኖ በተለይ እግረኞች በየስፍራው የሚገጥሟቸው መሰናከሎች፣ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ መሄድን ከባድ አድርገውታል፡፡
በነገራችን ላይ… በቃ የእኛ ጊዜ ሁሉም ነገር “ከሌለህ፣ የለህም ነው!” አሀ..  እግረኛ ያደረገን የአርባ ቀን እድላችንም ሆነ ምንም መብታችን ይጠበቅልና! “ተዉአቸው፣ አየተሹለከለኩ መሄድ ይችላሉ!” ነገር አታስመስሉብና! የምር ግን፣ እስቲ ከተማችን ውስጥ ያሉ የእግረኛ መንገዶችን ልብ በሉልኝማ! እንዴ በተወደደ ጫማ ሶሉ ተፈርፍሮ፣ ተፈርፍሮ…የአፍራሽ ግብረ ሃይል ዲጂኖ ሲጫወትበተ የከረመ ነው የሚመስለው፡፡  
የከተማዋን ጽዳት ልብ ብላችሁልኛል! ከዓለም ታላላቅ የዲፕሎማሲ ከተሞች አንዷ፣ የአፍሪካ ዋና መዲና ምናምን እያልን  የምናሞካሻት አዲስ አበባን ንጽህና ልብ ብላችሁልኛል! እኛም ብንሆን ምንም እንኳን የለመድነው ነገር ቢሆንም አሁን፣ አሁን የችግሩ ስፋት እያሸማቀቀን ነው… ለማንም ቱሪስት፣ ‘ኤክስፓትርዬት ምናምን ብለን ሳይሆን ለራሳችን ብለን፡፡ እኛም ንጹህ የመኖሪያ አካባቢዎችን እንፈልጋለና፡፡
በነገራችን ላይ… እነኚህ በየመንገዱ ያሉ የተሰባበሩ ቆሻሻ መጣያዎች ነገር ግርም የሚል ነው። ምናልባትም የሰው ድርቅ የመታው የሚመስለው ‘የድሮው ቦሌ’ አካባቢ የመሳሰሉ ቦታዎች ካልሆኑ በስተቀር ሌሎች ቦታዎች ያሉት ተነቃቅለው፣ ተሰባብረው፣ ተጨረማምተው…እንዴት ነው ነገሩ! ቀጥሎ ሲለወጡ ለስንተኛ ጊዜ ሊሆን ነው? ደግሞስ እንዲህ በተደጋጋሚ በቀላሉ የሚነቀሉ፣ የሚሰበሩ ከሆነ በጥንካሬያቸው የተሻሉ መተካት ያልተቻለው ለምንድነው!  የአዲስ አበባ መዘመን ማለት ከተጀመሩ በኋላ በስለት የሚያልቁ የሚመስሉ ረጃጅም ህንጻዎችና ሲፈለግ የሚፈቀዱ፣ ሲፈለግ የሚከለከሉ ኮንሰርቶች ብቻ ናቸው እንዴ!
ሌላ ደግሞላችሁ… ከዚህ በፊት እንዳወራነው አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ ጠዋት ላይ ብዙ ሱቆች ሲከፍቱ ወለላቸውን ያጸዳሉ፡፡ አሪፍ ነገር ነው። አንዳንዶቹ በስነስርአት የሌላውን መብት ሳይነኩ የራሳቸውን ያጸዳሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አይታችሁልኝ እንደሁ ውሀውን እያወጡ እግርኛ መተላለፊያ ላይ ይደፉታል፡፡ ምን አይነት ከተሜነት ነው! ምን አይነት ንጽህና አጠባበቅ ነው! እናላችሁ… የፈረደበት እግረኛ ደግሞ እንባ፣ እንባ እያለው አምስት ብር ከፍሎ ያስጠረጋት ጫማ እንዳትቆሽሽ፣ መሄጃውን ለቆ መኪና መንገድ ይገባል፡፡
የእግረኛ ጣጣ አያልቅም፡፡ ደግሞላችሁ… እንደ አራት ኪሎ አይነት በርካታ ህዝብ የሚመላለስባቸው ስፍራዎች መአት መኪና፣ የእግረኞች መንገዶች ላይ ይርመሰመስላችኋል፡፡ ጭራሹኑ፣ በገዛ መንገዳችሁ “መንገድ ልቀቅ!” አይነት ጡሩምባ የሚነፉባችሁ አሉ፡፡ መቼም የእግረኛና የአዲስ አበባ ጣጣ፣ ማለቂያ ያጣ ነው የሚመስለው፡፡ የሰሞኑ መንገድ ጥገና እነኚህን አይነት ችግሮች የሚያስወግድ ከሆነ እሰየው ነው፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ሌላም ከሥራ ጋር የተያያዘ ስላቅ ነገር ነው፡፡ የግሪክ ኤኮኖሚ ቀውስ ጫፍ በደረሰበት ጊዜ ነው አሉ፡፡ ሁለት ነጋዴዎች እየተመካከሩ ነው፡፡
“ለሠራተኞችህ ገንዘብ ትከፍላለሀ እንዴ?”
“አልከፍልም፡፡ ለወራት ቤሳ ቤስቲኒ አልከፈልኳቸውም፡፡”
“ግን አሁንም ሥራ ይመጣሉ፣ አይደል እንዴ?“
“አዎ፣ ይመጣሉ፡፡”
“የእኔም ይመጣሉ፡፡ ሥራ በሚመጡበት ጊዜ እነሱን ልናስከፍላቸው ይገባል፡፡ ለምን ሠራተኞች አንለዋወጥም?”
ሠራተኞች ይለዋወጣሉ፡፡ ከወር በኋላ ይገናኛሉ፡፡
“ሠራተኞችህን ሥራ በመምጣታቸው ማስከፈል መጀመረህ ምን ለውጥ አመጣ? አሁንም ይመጣሉ?”
“ይመጣሉ፣ ግን እነኚህ ደደቦች ብዙ እንዳይከፍሉ ገንዘብ ለመቆጠብ እየሞከሩ ነው፡፡”
“እንዴት አድርገው?”
“ሰኞ ይመጡና ከሥራ ወጥተው ቤታቸው የሚሄዱት ዓርብ ነው፡፡”
እናማ… ነገራችን ሁሉ “ብትሮጥ ቀድመኸው የሚቀጥለው ፌርማታ ትደርሳለህ፣” ሲሆን ልክ አይመጣም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 921 times