Tuesday, 02 January 2018 09:58

“ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም ጉዳይ በወሰደችው አቋም አዝነናል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

(በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በተለይ ለአዲስ አድማስ)

     • የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ ምንም የሚቀይረው ነገር አይኖርም
     • አሜሪካ የሰጠችው ዕውቅና ሰላም ለማምጣት አንድ እርምጃ ነው
     • ንግስተ ሳባና ንጉስ ሰለሞን የተገናኙት በኢየሩሳሌም ነበር

    ከአንድ ሳምንት በፊት የአምባሳደርነት ሹመታቸውን ለፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ያቀረቡት በኢትዮጵያ በብሩንዲና በሩዋንዳ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ራፋኤል ሞራቭ፤ ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም ጉዳይ በወሰደችው አቋም አዝነናል ብለዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ አሜሪካ ለኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲናነት የሰጠችው ዕውቅና፣ በአብዛኞቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት በገጠመው ተቃውሞ፣ በፕሬዚዳንት ትራምፕ አወዛጋቢ ውሳኔ እንዲሁም በኢትዮጵያና በእስራኤል ታሪካዊ ግንኙነት ዙሪያ ከእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ጋር በኤምባሲው ጽ/ቤት ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

    አምባሳደር፤ እንኳን ወደ ኢትዮጵያ በደህና መጡ፡፡ ኢትዮጵያን እንዴት አገኟት?
ገና ከመጣሁ ጥቂት ቀናቴ ነው፡፡ ብዙም አልተንቀሳቀስኩም፤ ደብረ ዘይት ከመሄዴ በቀር፡፡ ነገር ግን እዚህ በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያ ለእስራኤል በጣም ጠቃሚ ሃገር ነች፡፡ እንግዲህ በቆይታዬ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ለማጠናከር እሞክራለሁ፡፡
በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት ምን ይመስላል?
እንግዲህ የእስራኤላውያንና የኢትዮጵያውያን ግንኙነት መነሻው፣ ከንጉስ ሰለሞንና ከንግስተ ሳባ ግንኙነት ጀምሮ ነው፡፡ ይህንን ታሪክም አብዛኛው ኢትዮጵያዊና እስራኤላዊ ያውቀዋል። በመፅሐፍ ቅዱስም ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያም ይህ ታሪክ በሰፊው እንደሚነገር አረጋግጫለሁ። በመጀመሪያው የእስራኤላውያን ፍልሰትም፣ ኢትዮጵያን መጠለያና መጠጊያ አድርገው የኖሩ አይሁዳውያን ነበሩ። ይህ የሆነው እንግዲህ ከሺህ ዓመታት በፊት ነው። እነዚህ የታሪክ ማስረጃዎች የቆየውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታችንን የሚያስረዱ ህያው ምስክሮች ናቸው። ወደ እናት ሃገራቸው የተመለሱ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያንም፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያሉ የግንኙነት ድልድይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያና የእስራኤል መንግስታት ግንኙነት  በደንብ ተጠናክሮ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ መንግስታት የተለያዩ ውጣ ውረዶችን በማሳለፍ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በንጉሱ ዘመን የነበረው ጠንካራ ግንኙነት፣ በ17 ዓመቱ የደርግ ስርአት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም የመንግስት ለውጡን ተከትሎ በድጋሚ ግንኙነታችንን አድሰናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገራት ህዝቦችና መንግስታት መካከል ያለው ግንኙነት፣ እጅግ በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ማለት እንችላለን፡፡
የኢትዮጵያና የእስራኤል መንግስታት ግንኙነት ምን ያህል የተጠናከረ ነው ይላሉ?
ከዓመት በፊት የእስራኤል ጠ/ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። በተመሳሳይ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝም በእስራኤል ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በቅርቡም የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በአለ ሲመት ላይ የሁለቱ አገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ በዓመት አንድ ጊዜም እየተገናኙ የሚወያዩበት ፕሮግራም አላቸው፡፡ በከፍተኛ የመንግስት አመራሮች መካከልም መደበኛ ግንኙነት አለ፡፡ ማረጋገጫ ባይገኝም በመጪው ዓመት የእስራኤል ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን የመጎብኘት እቅድ እንዳላቸውም እናውቃለን፡፡ በእነዚህ መንገዶች መንግስታቱ ከሚታሰበውም በላይ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው፡፡
አሜሪካ በቅርቡ የኢየሩሳሌምን የእስራኤል መዲናነት ማፅደቋን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጉዳዩ እያወዛገበ ይገኛል፡፡ የእስራኤል ህዝብና ኢየሩሳሌም ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያውያን ስለ ኢየሩሳሌም ያላቸውን አመለካከት ከመዳሰስ ጀምሬ ጥያቄህን ብመልስ ይሻለኛል፡፡ በፕሬዚዳንታችሁ ቤተ መንግስት ግድግዳ ላይ በንግስተ ሳባና በንጉሥ ሰለሞን መካከል የነበረውን ግንኙነት የሚተርከው ስዕላዊ መግለጫ ላይ፣ ሁለቱ ነገስታት ያንን ግንኙነት ያደረጉት በኢየሩሳሌም እንደነበር ይጠቅሳል። ለምን በኢየሩሳሌም ተገናኙ? ለሚለው መልሱ ቀላል ነው፡፡ ኢየሩሳሌም በወቅቱ የእስራኤል ህዝብ ንጉሥ የነበረው የንጉሥ ሰለሞን ዋና መቀመጫ ስለነበረች ነው፡፡ ለአይሁዳውያን፣ ኢየሩሳሌም፣ ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ ዋና ከተማቸው ነበረች። አይሁዳውያን ከአካባቢው ሲሰደዱ ፀሎታቸው ወደ ኢየሩሳሌም መልሰን የሚል ነበር፡፡ ኢየሩሳሌም በሁሉም እስራኤላዊ ልብ ውስጥ ነበረች፡፡ ወደ አካባቢው ሲመለሱም እስራኤልን ብቻ አስበው ሳይሆን ኢየሩሳሌምን አስበው ነው፡፡ እስራኤል የምትባለው ሃገር የተመሰረተችውም በኢየሩሳሌም ላይ ነው፡፡ ለኛ ኢየሩሳሌም፣ የእስራኤላውያን መዲና ናት፡፡ የመንግስታቸውም መቀመጫ ነች። የእስራኤል መንግስት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 70 ዓመታት ኢየሩሳሌም የመንግስቱ መቀመጫ ነች፡፡ ዋና ከተማችን ናት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት፣ ፓርላማው፣ የፍትህ አካላቱ፣ የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍ/ቤት--- በሙሉ የሚገኙት በኢየሩሳሌም ነው፡፡ አሁን የበርካታ ሀገራት አምባሳደሮች መቀመጫቸውን ቴልአቪቭ ስላደረጉ፣ የሀገሪቱን የመንግስት ባለስልጣናት ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ ብዙ መንገድ ተጉዘው ነው የእስራኤል ባለስልጣናትን ማግኘት የሚችሉት፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ኤምባሲያቸውን ከቴልአቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም ለማዘዋወር መወሰናቸው ለእስራኤል ያለው ፋይዳና ፖለቲካዊ አንድምታው ምንድን ነው?
እኛ በፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በጣም ደስተኞች ነን። ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና የመሆኗን እውነታ መቀበላቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲናነቷ ሲረጋገጥ ብቻ በመሆኑ፣ የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ሰላም ለማምጣት አንድ እርምጃ ነው፡፡ በእስራኤላውያንና በኢየሩሳሌም መካከል ያለውን እውነታ ወደ ጎን በመግፋት የሚደረጉ ፖለቲካዊ ማታለሎች ሰላም ለማምጣት አይጠቅሙም፡፡ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረግ መግባባትን ለመጀመር በቀዳሚነት የኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲናነትን መቀበል ያስፈልጋል። ፍልስጤም ራሷን የቻለች ሀገር ለመሆን ያላትን ፍላጎት እኛም እውቅና እንሰጠዋለን፡፡ በዚያው ልክ እስራኤል የአይሁዳውያን ሃገር እንዲሁም ኢየሩሳሌም የአይሁዳውያን የባህልና የእምነት መሰረት መሆኗን መቀበል ያስፈልጋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት አብዛኞቹ አባል አገራት የአሜሪካንን ውሳኔ ተቃውመዋል …  
አዎ! መቃወማቸውን ግን ኢየሩሳሌምን የእስራኤል መዲና ከመሆን አያግዳትም፡፡ ውሣኔያቸው በመሬት ላይ ያለውን ሃቅ በምንም መንገድ አይቀይረውም፡፡ ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ሆና ትቀጥላለች፡፡ የመንግስት የአገልግሎት ተቋማትንም በኢየሩሳሌም መገንባታችንን እንቀጥላለን፡፡ የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ በህግ የሚያመጣው ተፅዕኖም ሆነ በተግባር የሚቀይረው ነገር አይኖርም፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት በሶርያ፣ በየመንና በመሣሠሉ ሃገራት ያሉ እውነተኛ ችግሮችን ወደ ጎን ትቶ፣ ሁልጊዜ የእስራኤል ፍልስጤም ግጭቶችን ማጋጋል ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ የእስራኤል መንግስት ዛሬም ቢሆን ለሠላም ድርድር ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለፀ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም በተደጋጋሚ ከፍልስጤማውያን ፕሬዚዳንት ጋር ወይ በኢየሩሳሌም አሊያም በራማላህ ተገናኝቶ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከእነዚህ አማራጮች ውጪ የተባበሩት መንግስታት ውሣኔ ምንም የሚቀይረው ነገር አይኖርም፡፡ ለአካባቢው መፍትሄ የሚያመጣው ቁጭ ብሎ መነጋገርና መደራደር እንጂ ከአንድ አካል የሚመጣ ውሳኔ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ የአሜሪካን ውሳኔ ከተቃወሙ የዓለም አገራት አንዷ ነች፡፡ እስራኤል ውሳኔውን እንዴት ተቀበለችው?
ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም ጉዳይ በወሰደችው አቋም አዝነናል፡፡ ይህን ቅሬታችንንና ሃዘናችንንም ለኢትዮጵያ መንግስት አስታውቀናል፡፡ 16 የአፍሪካ ሃገራት፣ ይሄን የመንግስታቱ ድርጅት ውሳኔን ተቃውመዋል፡፡ ነገር ግን በኛ እና በኢትዮጵያ መካከል ካለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና መደጋገፍ አንጻር አቋሙን አልጠበቅነውም። ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ም/ቤት እጩ በሆነችበት ወቅት እስራኤል ለኢትዮጵያ ሙሉ ድጋፏን ሰጥታ ነበር፡፡ ለአለም ጤና ድርጅት መሪነት በተደረገው ውድድርም እስራኤል ሙሉ ድጋፏን ለኢትዮጵያዊው እጩ ነበር የሰጠችው፡፡ እኛ እነዚህን በጎ እርምጃዎችና አቋሞች በምናንፀባርቅበት ወቅት ተመሳሳይ አጋርነት ከኢትዮጵያ መንግስት እንፈልግ ነበር። ድጋፍ እንኳ ባትሰጠን ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት እንዳደረጉት ድምፀ ተአቅቦ ማድረግ ትችል ነበር። ኬንያና ሩዋንዳ ድምፀ ተአቅቦ ነው ያደረጉት፡፡ ያንን ማድረግም ይቻል ነበር፡፡ በኢትዮጵያ አቋም በጣም አዝነናል። ለወደፊቱ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን ላይ የሚያመጣውን ለውጥ አሁን ማወቅ ባልችልም፣ ውሳኔው በጎ ምልክት እንዳልሆነ ግን መናገር ይቻላል፡፡
ቅሬታችሁን ለኢትዮጵያ መንግስት በግልፅ አሳውቃችኋል?
አዎ! ውሳኔዋን ባሳወቀች ማግስት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝቼ፣ በወሰደችው አቋም ላይ ያለንን ቅሬታ ገልጫለሁ፡፡ በጉዳዩ ላይም ተወያይተንበታል፡፡ ነገር ግን ምላሽ አላገኘንም፡፡
በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችንና ወቅታዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት በተመለከተ ምን ይላሉ?
በእውነት በግጭቶች የሰው ህይወት መጥፋቱ ያሳዝናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለደረሱ የሰው ህይወት መጥፋቶች ሃዘናችንን እንገልፃለን፡፡ ሰላምና ፖለቲካዊ መረጋጋት ለኢትዮጵያ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት በሃገሪቱ እንዲሰፍን እንመኛለን፡፡ ነገር ግን መንግስት ምን ማድረግ እንዳለበት መምከር ድርሻችን ስላልሆነ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አስተያየት ባልሰጥ እመርጣለሁ፡፡

Read 5030 times