Print this page
Tuesday, 02 January 2018 10:05

በ“አደፍርስ” - መደብና ኪነ ጥበብ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

“ቅዱስ ያሬድ ጨርሶታል፤ የሙዚቃን ነገር ከግዕዝ፣ ከዕዝል፣ ከአራራይ በላይ የሙዚቃው ህይወት ይኖራል ማለት ዘበት ነው፡፡ በግዕዝ ጀምሮና አነሳስቶ በዕዝል ደርቦና ጨምሮ፤ በአራራይ አሳዝኖ ልብን መሥጦና አስደስቶ፣ አራርቆ፤ አሳምሮ፤ ያቀረበ ከሱ ሌላ የለም፡፡”

   የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” መጽሐፍ በዋናነት ብዙ ያከራክር የነበረው፣ ሴራው፣ ማለትም የታሪክ አወቃቀሩ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በአብዛኛው ተደራሲ ዘንድ ባዕድ የሆኑ፣ የማይታወቁ ወይም ያልተለመዱ ቃላትን በድርሰቱ ውስጥ ደንጉሯል የሚል ሀሳብም ነበረ፤ እስካሁንም አለ፡፡ አንድ ፀሐፊ እንዳስቀመጡት፤ “አደፍርስ” መጽሐፍ ውስጥ ስድስት መቶ ያህል ቃላት ለአንባቢ እንግዳ ናቸው። ደራሲ ብርሃኑ ዘርይሁን በዘመኑ በጻፈው አቃቂር እንደጠቆመው፤ የብዙዎቹ ቃላት ፍቺ በከሳቴ ብርሃን መዝገበ ቃላት እንኳ ሊገኝ አልቻለም  ነበር። በዚህና ተመሳሳይ ችግሮች ምክንያት ባለፈው ዘመን፣ የዳኛቸው ወርቁ ይሄ ረዥም ልብወለድ፣ የማይረባ ተደርጎም ታይቷል፡፡
በርካታ ምሁራን በመጽሐፉ ላይ የተለያየ አስተያየት ሰጥተዋል - አዎንታዊና አሉታዊ፡፡ በርግጥ ብዙዎች እንደሚሉት፤ ታሪኩ ልብ አንጠልጣይ አይደለም፡፡ የትረካ አንጻሩም ተውኔታዊ በመሆኑ ደራሲው ለአንባቢያን የሚጎዘጉዘው ብዙ ውበት የለም፡፡ ሜዳውን ለአንባቢው ነው የሚተወው፡፡ በዚህ የተነሳም በታሪኩ ውስጥ ድንገት ያልተገመቱ ርዕሰ ጉዳዮች እየተነሱ ክርክር ሲደረግባቸው እናያለን፡፡ ያ ደግሞ ያሰለቻል፡፡ ምናልባትም በተነሱት ፍልስፍናዎችና ሃሳቦች ላይ ቀልቡን ያልጣለ ሰው፣ መጽሐፉን ወዲያው ሊወረውረው ይችላል፡፡
ይሁን እንጂ የአጻጻፍ ስልቱ ፈሰስ አቅል ነው ብለን ከተስማማን (እንደኔ)፣ ይህንን የታሪኩን በተለያየ አቅጣጫ መፍሰስ ወይም በየአቅጣጫው መበታተን ቀድመን መቀበል ይኖርብናል፡፡ እንደ ሌሎቹ የሀገራችን ደራሲያን፣ ታሪኮች አንድ መስመር ይዞ፣ ልብ እያንጠለጠለ፣ ግጭት እያፋፋመ ይቀጥላል ብለን መጠበቅ የለብንም፡፡
በአጠቃላይ መጽሐፉንና ዓላማውን ስንመለከተው፣ ለውበት ብቻ የተጻፈ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ በዘመኑ ሀገሪቱ ከነበረችበት ኋላቀርነትና ድንቁርና ለመታደግ በሙዚቃም ሆነ በሌሎች የስነ ጽሑፍ ስራዎች ይታይ የነበረው የማስተማር አዝማሚያ እዚህም እንዳለ እናያለን፡፡
አደፍርስ የተባለው ገፀ ባህሪይም በየምዕራፎቹ በዋናነት የሚያደርጋቸው ነገሮች ቢኖሩ፣የሀገሪቱን ወቅታዊ ዋና ዋና ችግሮች አደባባይ ላይ እያሰጡ ሃሳቦችን ማንሸራሸር ነው፡፡ ለምሳሌ ኋላ ቀር እምነትን፣ ባዕድ አምልኮን፣ ማይምነትን፣ ወንጀለኛን የመቅጫ መንገዶችን ወዘተ-- በሚመለከት መጽሐፉ ይሰብካል ማለት ይቻላል፡፡
ታዲያ በዚሁ ሀዲድ ላይ ሆኖ ታሪኩ ይዟቸው የሚፈስስ ሁለት ጎራዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጎራዎች ከታሪኩ ጅማሬ አንስቶ እስከ ፍፃሜው የለውጥ አራማጆችና ወግ አጥባቂዎች፣ የተማሩና ያልተማሩ፣ ዘመናዊና ኋላ ቀሩን አስተሳሰቦችና ቅራኔዎች በትይዩ ይዘው ይጓዛሉ፡፡ … ግን ደግሞ የየቱም ወገን ውጥን ሳይነካካ አልቀረም፤ ደግሞም ከግብ አልደረሰም። አደፍርስና መሰሎቹ፣ ክብረትና የመሳሰሉት አሮጌውን ስርዐት በትችት ቆስቁሰውታል፤ ግን ለውጥ አልታየም፤ አልነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ታሪኩ ፍፃሜ ላይ የሚታየው የተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ፣ ስርዓቱ እየተገፋና እየተቧጨረ እንደሆነ ያሳያል፡፡ አደፍርስን የመቱትና ለህልፈት የዳረጉት በተማሪዎች የተወረወሩት ድንጋዮችም፣ በተማሪዎቹ ውስጥ ያለውን የመረረ ቁጣና ኃይል የሚያሳይ ነው፡፡ የጥንካሬና ብርታቱ ተምሳሌትም ነው፡፡
መጽሐፉ ሲጀምር የቁንዲን አየር፣ አሮጌ መልክ፣ የአየር ፀባይ፣ የህይወትን አዙሪት፣ የለውጥን ናፍቆት አሳይቶን፣ ወዲያው ሁለተኛው ገፅ ላይ የምናገኘው የባላባት ልጅ የሆኑት ወይዘሮ አሰጋሽ፣ በድህነትና እጦት ምክንያት ቤታቸው ዘንጋዳ ሊበደራቸው የመጣ ጭሰኛቸው ላይ የሚያሳዩትን የተለሳለሰ እብሪት ነው፡፡ በአንድ በኩል የፈጣሪን ትልቅነትና ዳኝነት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸውን ትልቅነት እያወሩ፣ በሀብታሟ አሰጋሽና በምስኪኑ ጭሰኛ መካከል ያለውን የህይወት ዕጣ፣ የገሀነምና የመንግሥተ ሰማይን ያህል ያጋንኑታል፡፡ ይህንን የሚናገሩት ራሳቸው ሳይሆኑ፣ አንባቢው ራሱ ከተፈጠረው ምልልስ የሚያገኘው ነው፡፡
ታዲያ ይህንን ጭቆና የበዛበትና በሰው ልጆች መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ የሚቃወመው አደፍርስ፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪና የሃያ አራት ዓመት ወጣት በመሆኑ የአሮጌውን ሥርዓት ሁለንተናዊ ድክመት ለማስተማር ሳይንሳዊ መንገዶችን ቢጠቀምም የሚያወራው ነገር ሁሉ ድንጋይ ላይ ውሃ ከማፍሰስ ያልተሻለ እንደነበር፣ በላይ ለተባለው ጓደኛው ሲያወራ፣ ገና ጥቂት ገፆች እንደገለጥን እናገኛለን፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“አንዳንዶቹ ጭራሽ የምለውን ፈፅሞ አይሰሙኝም፤ ደንቆሮዎች ናቸው፤ ወይም አይገባቸውም፡- እኔ ስለ ግብርና ሳወራ፣ እነሱ የሚያወሩት ስለ ብሩክታይት ነው …”
ይህ የአመለካከትና የፍልስፍና ርቀት በአደፍርስና ለፍርድ ቤት ጉዳይ በመጡ ሰዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በርካታ ገፀ ባህርያት ህይወት የሚታይ ነው፡፡ ለምሳሌ በወይዘሮ አሰጋሽ ዝራውና በአደፍርስ፣ በጎርፉና በአደፍርስ፣ በጴጥሮስና በአደፍርስ፣ በፍሬዋና በጴጥሮስ/አሰጋሽ፣ በሮማንና በአደፍርስ ወዘተ--፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ጉልተው የሚታዩት የጥበብ ቤተሰቦች፣ በተለይ ሥዕልና ሙዚቃ መኖራቸው ታሪኩን የበለጠ ደማቅና ጥልቅ ያደርጉታል፡፡ በእውኑ ዓለም ለለውጥና ለማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ማሳደጊያ፤ ለለውጥ መሳሪያነት የሚያገለግሉት ሙዚቃና ሥዕል፣ በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ዘርፈ ሰፊ መልዕክት ያላቸው ይመስላሉ፡፡ ማህበረሰቡን በመሳሪያ ሳይሆን በጥበብ ለመለወጥ መሞከር የተሻለም እንደሆነ የሚጠቁም ይመስለኛል፡፡
ሰዐሊው ክብረት የሚሰራቸው ምስሎች ማህበረሰቡ ውስጥ ቀደም ሲል ከነበሩት ያፈነገጡና የተለዩ፣ ምናልባትም ከአካል ይልቅ የማህበረሰቡን ሥነ ልቦናዊ ቃናና መልክ የሚያሳዩ በመሆናቸው የተፈጠረው አለመግባባት ቀላል አልነበረም፡፡ በተለይ ክብረት የሚካኤልን ምስል ሲሰራ፣ ምስሉን በሌላና በሚታወቁ አዛውንት ምስል፣ መተካቱ፣ ሃይሉን የሚቃወምና የሚገዳደር ወይም አቅሙን ከሰውየው አቅም ጋር የሚያተያይ ስለሚመስልና ሚዛኑ ላይ ደግሞ ባንድ ወገን ጺወኔ፣ በሌላ ወገን ሮማን መቀመጣቸው፣ ወይዘሮ አሰጋሽን በእጅጉ አስቆጥቷቸዋል፡፡ በታሪኩ ውስጥ እንዳየነው ደግሞ ወይዘሮ አሰጋሽ ወካይነታቸው ግለሰብን አይመስልም፤ ይልቁኑ የሥርዓቱ ቁንጮ ላይ የተፈናጠጡትን ፊውዳሎች የሚያሳይ ነው፡፡
ዳኛቸው ወርቁ፤ በገፀ ባህርይው አማካይነት ሙዚቃን በተመለከተ አንዳንዴ ህይወትንና ተፈጥሮን ራሷን በሙዚቃ ሲመሥላት እናያለን። ሀዘንና ደስታ፣ ሣቅና ለቅሶ፣ ሞትና ህይወት፣ ተስፋና ትዝታ ሁሉ በዚህ ጀርባ እንደተንጠለጠሉ የሚጠቁሙ ሀሳቦች አሉ፡፡ እንዲያውም ሙዚቃ ራሷን እንደዚህ ያስቀምጣታል አደፍርስ በተባለው ገፀ-ባህሪ አንደበት፡-
“በዚህ አካባቢያችን ከሚያምመው የድምፅ ዑደት የበለጠ የምን ሙዚቃ አለ?... ልንገርሽ እንዲያው፣ እውነቱን የተሰማኝን፡፡ ከዱር እንደገባሁ አጥሩ አጠገብ ቆመሽ ባየሁሽ ጊዜ አንቺ መሥለሽኝ ነበር በልዩ ጥበብ ዙሪያውን የምታቃኚው፤ ጉራንጉሩን፣ ሸጥ ሸለቆውን የምታዘፍኚው፤ ከወጣት ጎሮሮ እንደሚፈስስ ዜማ፣ እንደ ጎልማሳ ጩኸትና ድንፋታ፣ እንደ ቤተክርስቲያን ማህሌት፣ እንደ ነጎደጓድ የማዕበል አመጣጥ፣ እንደ ሚያስረገርግ የድል ድምፅ፤ እንደ መከራ- ጭንቅ- ብስጭት- ምንልሁነው ዋይታ፣ ነፋስ እንዳጠኸየው የዝናብ ደመና ስግምግምታ ዙሪያውን ሲምሹከሸክ ሲደረደር፣ ሲድረቀረቅ አንቺ መስለሽኝ ነበር የምትቃኚው፡፡”
ለአደፍርስ ህይወት ሙዚቃ ናት፡፡ ሳቅና ለቅሶ፣ ጣፋጭና መራር! የገበሬዎች መከራ…. የሰዐሊው ምጥ…. የአደፍርስ መባተት…. የወይዘሮ አሰጋሽ መጀነን…. የተማሪዎች ሰልፍ…የጠንቋዮች ዝና…ወዘተ… የህይወት ሙዚቃ ናቸው- በመጽሐፉ፡፡ ሕይወትም እንደ ሙዚቃ ናታ!...
የዳኛቸው መጽሐፍ፤ ሙዚቃና ኪነትን በዚህ ብቻ የተወ አይመሥለኝም፡፡ ሦስቱ ገፀ ባህሪያት የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ይህ ኪህሎት ደግሞ ሙዚቃዊ ህይወታቸውን እንደ ጥላ ተከትሎ ሌላ ገፅታቸውን ያሣያል፡፡ ገና ምዕራፍ አራት ላይ ደራሲው ፂወኔን ሲያስተዋውቅ፣ የወይዘሮ አሰጋሽ ልጅ፣ ስድስተኛ ክፍልን አርማኒያ አጠናቅቃ፣ ደብረሲና ያሉት አጎቷ አቶ ወልዱ ዘንድ ስትማር፣ ሀርሞኒካና ክራር መጫወት መቻሏን እንረዳለን። አቶ ወልዱ ውጭ ሀገር የሚኖሩ ሥልጡን ስለሆኑ ለሳቸው ብዙም የሚደነቅ ነገር ስላልሆነ ተቀብለውታል፡፡ ባይሆን ይህ አልዋጥ ያላቸው የወይዘሮ አሰጋሽ የነፍስ አባት አባ አዲሴ ናቸው፡፡ አባ አዲሴ ከክፉ መንፈስ ጋር አያይዘው ጠበልም ረጭተዋታል፡፡ በድጋሚ ሲያደምጧት ግን ዋነኛው “ሌጌዎን” የተባለ ሰይጣን ነው በማለት፣ ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ቤት እንድትመለስ አድርገዋል፡፡ ይህም አዲሱንና ዘመናዊውን ዓለም ያለመቀበልና የመጠራጠር ማሣያ ነበር፡፡
ስለ ሙዚቃና ሙዚቃ መሣሪያዎች ካነሳን አይቀር፣ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ፣ ለገፁ ባህርያቱ የሙዚቃ መሳሪያ የመረጠላቸው በምን መመዘኛ ይሆን? ብለን መጠየቅና የጀርባውን ጥላም መመርመር ያለብን ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ብናየውስ?
ፂወኔ ዘመናዊ ትምህርት የቀመሰች፤ በቀጣዩ ዘመንም በዚሁ ዘመናዊ ስርዓት ቀጥላ፣ አዲስ አበባና ውጭ ሀገር ሄዳ ለመማር ህልም ያላት ወጣት ናት። ይህን ደግሞ በገዛ አንደበትዋ ለአደፍርስ እንዲህ በማለት ነግራዋለች፡-
“እኔም እንዳንተ’ኮ ብዙ ውጥን አለኝ - የተጀመረ ያልተጨረሰ ብዙ ምኞት አለኝ… ብዙ ማድረግ የምፈልገው ነገር-- አዲስ አበባ ለመሄድ፣ ፈረንጅ ሀገር ለመሄድ… ሙዚቃ ለመማር ምን ብቻ ልንገርህ---”
ይህ የፂወኔ ሥልጡንና ዘመናዊ ማንነት ማሣያ ነው፡፡ ይህቺው ፂወኔ ደግሞ ከቤተሰቧ፣ ከአካባቢዋ ማህበረሰብ፤ ከእምነቷ የወረሰቻቸው ባህላዊ አስተሳሰቦችና እምነቶች፣ ፍልስፍናዎች አሏት። እነዚህ በፂወኔ ልብ በደባልነት ይኖራሉ፡፡ እናም ሀርሞኒካው የዘመናዊውን ዐለም ውስጥዋን ቅኝት የሚወክልና ምዕራባዊ ዕውቀት መሻቷን የሚያጠቅስ ሊያደርጋት የፈለገ ይመሥላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከቤተሰብ፣ ከማህበረሰብና ከአካባቢ ያገኘችውን እውቀትና ማንነት ማዜሚያ ይሆናት ዘንድ ክራሩን የመረጠላት ይመሥላል፡፡ ፂወኔ፤ ክራርና ሀርሞኒካ - የዘመናዊውና የነባሩ ልማድና ፍልስፍና ሠገነት!
ይህንን ለማዛመድ ደግሞ እናትዋ ወይዘሮ አሰጋሽ የክራር ጨዋታዋን ሲያደንቁ እናያለን። ነብርና አንበሳውን የምታብረከርክበት እንደሆነ ይነግሯታል። በዚህ ወገን ደግሞ የአደፍርስን አኮርዲዮ፤ “የከተማው ጩኸት!” እያሉ ያጣጥሉታል። የከተማ ጩኸትና አስተሳሰብ፤ አኗኗር ጭምር ሊሆን ይችላል፡፡ በቀደመው ላይ መስልጠን፣ ወደ አዲሱ መንፏቀቅ!
 የነፍስ አባታቸው አባ አዲሴም የዚሁ የባህላዊና ሀገራዊው ቅኝት ወገን ናቸው፡፡ የውጭውን ያጣጥሉታል፤… አዲስ ነገር የለውም፤ በኛ ተደምድሟል የሚል አንደምታ አላቸው፡፡
“ቅዱስ ያሬድ ጨርሶታል፤ የሙዚቃን ነገር ከግዕዝ፣ ከዕዝል፣ ከአራራይ በላይ የሙዚቃው ህይወት ይኖራል ማለት ዘበት ነው፡፡ በግዕዝ ጀምሮና አነሳስቶ በዕዝል ደርቦና ጨምሮ፤ በአራራይ አሳዝኖ ልብን መሥጦና አስደስቶ፣ አራርቆ፤ አሳምሮ፤ ያቀረበ ከሱ ሌላ የለም፡፡” ይላሉ፡፡
ወደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው አደፍርስ ስንመጣ ደግሞ በእጅጉ የዘመናዊነት አቀንቃኝ እንደሆነና ከዕድሜው የተነሳ ስሜታዊነቱን በያንዳንዱ ምዕራፍ እናስተውላለን፡፡ ፍልስፍናውና አስተሳሰቡ ዘመናዊ ስለሆነ የተጠቀመው የሙዚቃ መሳሪያም ከውጭ ሀገር የመጣ ነው፡፡ የሚጫወተው አኮርዲዮ ነው። ደራሲው ይህንን ገፀ ባህርይ ዘመናዊ አስተሳሰብ ለማሣየት፣ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያ እንዲጫወት ያደረገው ይመሥለኛል፡፡
ሌላው ሦስተኛው ባለሙዚቃ መሳሪያ የሮማን አባት ወርዶፋ ነው፡፡ ወርዶፋ በታሪኩ ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው አይደለም፤ ብቅ ብሎም የነገረን ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ ፂወኔ በምታዘወትርበት የመኖሪያ ጎጆውና አንጀት በሚንጠው የዋሽንት ጨዋታው እናውቀዋለን፡፡ ተጫውቶ ባያባባንም፣ አውርቶ ባያቆየንም ነግረውናልና! ወርዶፋን ከእነ ዋሽንቱ እናስበዋለን፡፡
ታዲያ ወርዶፋ ማነው ካልን፣ በወይዘሮ አሰጋሽ ሥር የሚተዳደር ምስኪን ሰው ነው፡፡ ወይም በዘመኑ አጠራር ጭቁን! ይህንን ሀሳብ ይዘን ከተነሳን በኋላ ዋሽንቱን ለምን ታጠቀ? ብለን እናስባለን፡፡ ዋሽንት ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ነው፤ ወርዶፋም ባህላዊ አስተሳሰብ ያለውና ከዘመናዊው ዓለም በእጅጉ የራቀ ሰው ነው፡፡ … ሕይወቱም የድህነትና የጥያቄ፣ የጭቆናም ጭምር ነው፡፡ … ዋሽንት ደግሞ ሆድ ለባሳቸው መተንፈሻ ናት፡፡
ዳኛቸው ወርቁ፣ ለገፀ ባህርያቱ ያስታጠቃቸው መሳሪያዎች፣ ፍልስፍናና ሥነ ልቡናቸውን ይወክላሉ ብንል እንሳሳታለን?… በፍፁም! የዳኛቸው “አደፍርስ”፣ ስለ ሀገር አንድነት፣ ስለ ብሔር ብሔረሰብና ቋንቋ ቀድሞ መናገሩም የመጽሐፉ ሌላ መልክ ይመስለኛል፡፡ ለዛሬ ግን ይብቃኝ፡፡     

Read 1530 times